የቱን ታስታውሳላችሁ?

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
መስከረም ፲፬፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋገራችሁ! አዲሱን ዓመት ከተቀበልን ሳምንታትን አስቆጥረን ወር ሊሞላን ጥቂት ቀናት ብቻ ቀሩን! አዲሱ የትምህርት ዘመን እንዴት ነው? ትምህርት ጀመራችሁ አይደል? በርቱ! እንግዲህ ጥሩ ውጤትን እንድታስመዘግቡ ልትበረቱ ይገባል! ትናንት ከነበራችሁ ዕውቀት አዲስ የማታውቁትን ልትጨምሩ ትምህርት ጀምራችኋልና መምህራን የሚያስምሯችሁን በአግባቡ ተከታተሉ! ከዚያም ያልገባችሁን ጠይቁ! ከትምህርታችሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን መጻሕፍት አንብቡ! ከዚያ ስትጠየቁ መልሱ እሺ? መልካም!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ስለ አዲስ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ መልእክት መካከል ከተላኩትና አስተማሪ ከሆኑት አንዱ ምን ይላል መሰላችሁ? ‹‹አዲስ ዓመት እንደ ንጹሕ ወረቀት ነው፤ በዚህ ንጹሕ ወረቀት ላይ መልካም የሆነ ታሪክን የመጻፉ ዕድል በእያንዳንዱ ሰው እጅ ነው!›› አይገርምም ልጆች! እንግዲህ በተሰጠን አዲስ ዓመት መልካም የሆነ ታሪክን መጻፍ እንጀምር፤ ጎበዝና አስተዋይ፣ ታታሪ፣ ታዛዥ ልጅ በመሆን ወላጆቻችንን እናስደስት፤ የእኛንም አዲስ ታሪክ እንጻፍ፡፡

ታዲያ ልጆች! ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መማርንም እንዳንዘነጋ! በሰንበት ሄደን በመማር በሥነ ምግባር ያጌጠ፣ በሃይማኖቱ የጸና ጎበዝ ሆነን ማደግ አለብን፤ መልካም! ለዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው “የቱን ታስታውሳላችሁ” በሚል ርእስ እስከ ዛሬ ትማሩት ከነበረው የተወሰነ ጥያቄዎችን አዘጋጅተን ነው፤ ምላሽችሁን ደግሞ በድረ ገጽ አድራሻችን “website.amharic@eotcmk.org” ትልኩልናላችሁ!

፩ኛ. የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል አይሁድ በክፋት ከቀበሩት ከ፫፻ (ከሦስት መቶ) ዓመታት በኋላ በጌታ ፈቃድ ከተቀበረበት ያወጣችው ማን ናት?——————————ለክርስቲያኖች ነጻነትን ዐውጆ እምነታቸውን በነጻነት እንዲያመልኩ ያደረገው ልጇስ ማን ይባላል?———————፡፡

፪ኛ. ቅዱስ ላሊበላ ከዓለት (ከድንጋይ) ቤተ መቅደስ ሲሠራ እርሷም አብራ ነበረች፤ ወላጆቿ በሃይማኖትና በሥነ ምግባር አሳድገዋታል፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ ከቅዱስ ላሊበላ ጋር ትዳር መሠርታ በላስታ ላሊበላ ከሚገኙ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ቤተ አባ ሊባኖስ የተባለውን ቤተ መቅደስ የሠራችው ውድ የእግዚአብሔር ልጅ ማን ናት?————

፫ኛ. ቅዱሳን ሐዋርያት ምእመናንን እንዲያገለግሉ ከመረጧቸው ሰባቱ ዲያቆናት አንዱ ነው፤ ስለ ጌታችን ሲያስተምር “ለምን ታስተምራለህ” በማለት በድንጋይ ወገሩት፤ እርሱ ግን ‹‹ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው…›› በማለት ይጸልይላቸው ነበር፤ በሰማዕትነትም አለፈ፤ ይህ ቅዱስ አባት ማን ይባላል?————–

፬ኛ. አባቷ ቅዱስ ቴዎድሮስ እናቷ ቅድስት አትናሲያ ይባላሉ፤ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ከካህናት ወገን የሆኑ ናቸው፡፡ መልካም ምግባር ነበራቸው፤ በስእለት የወለዷት ሴት ልጅም ነበራቸው፡፡ ሥነ ምግባር፣ ብሉይና አዲስን ኪዳንን በማስተምር፣ ለወላጆቿ ታዘዥ እንድትሆንም በሥርዓት አሳደጓት፡፡ መንኩሳም በገዳም ስታገለግል ነበር፡፡ ሰይጣን ግን በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ አድሮ መከራ አመጣባት፤ አርማንያ ወደ ተባለ አገርም ተሰደደች፡፡ በዚያም ድርጣድስ የተባለውን ንጉሥ መከራ አጸናባቸው፤ በሃይማኖት ጸንታ መስከረም ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀንም በሰይፍም ተሰይፋ ሰማዕትነት ተቀበለች፡፡ ይህች ቅድስት ማን ናት? ———————-

፭ኛ. እግዚአብሔር ድንቅ ነገር ስላደረገላት ዓለምን ንቃ ወደ ምንኩስና ሕይወት ገባች፤ ለሰዎች ልጆች ፈጣሪን ተማጽና ምሕረትን አሰጥታለች፤ በአንድ ወቅት በክፉ ሥራው አጋንንት (ሰይጣን) ያስጨነቀውን፣ ፈጣሪውን ያስከዳውን ሰው ጸልያ እግዚአብሔር ይቅር እንዲለው አደረገች፤ በሰዎች ላይ ክፉ የሚያደርገውን ሰይጣን (ዲያብሎስ) ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ጠይቃ ነበር ፤ ይህች ቅድስት እናታችን ማን ትባላለች? —————

፮ኛ.እግዚአብሔርን የምትፈራ፣ ታማኝ እውነተኛ ሴት ነበረች፤ ሰዎች ግን ምንም ሳታጠፋ በቅናት ተነሣስተው እንድትቀጣ ፈለጉና በሐሰት ያልሠራችውን ጥፋት ሠርታለች አሉ፤ ከዚያም ሦስት ምስክሮች መጡና በሐሰት (በውሸት) መሰከሩ፤ ያለ ጥፋቷ ሊፈረድባት ሲል እውነተኛ የሆነ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነቢዩ ዳንኤል መጥቶ የሐሰት ምስክሮችንና ሐሰተኛነታቸውን ዐውቆ እርሷን ከሞት አዳናት፤ ማን ትባላለች? ————–

፯ኛ.ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት በሥርዓተ ጸሎት ጊዜ ልንዘጋጅባቸው የሚገቡ ውጫዊና ውሳጣዊ ዝግጅቶች የሚባሉት ምን ምን ናቸው?—————————–፣————————————-

፰ኛ.በሥነ ፍጥረት ትምህርታችን እግዚአብሔር በዕለተ እሑድ የፈጠራቸው ሰባቱ የብርሃን ሰማያትን ስም ጻፉ? ————————————————————————–

፱ኛ. ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከክዋክብት መቼ ተፈጠሩ?———————

፲ኛ. አምስቱ አዕማደ ምሥጢረራት የሚባሉት ምን ምን ናቸው?——————————————————————————————————————————-
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከዚህ ቀደም ከተማራችሁት በርካታ ትምህርት “የቱን ታስታውሳላቸሁ” በሚል ጥቂቱን ብቻ ጠየቅናችሁ! ምላሻሁን እንጠብቃለን፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ልዩ ነው፤ ውለታውን ሳንረሳ፣ ትእዛዙን በመጠበቅ እኛ ደግሞ ለእርሱ ያለንን ፍቅር እንግለጽ፡፡ ወላጆቻችን ለእኛ ብዙ ነገር እያደረጉልን በትምህርታችን ጎበዝ ስንሆን፣ በሥነ ምገባር ስንታነጽ ደስ እንደሚላቸው፣ እኛም ፈጣሪ እግዚአብሔር ያዘዘንን ትእዛዝ በመፈጸም ለእርሱ ያለንን ፍቅር እንግለጥ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቀጣይ በሌላ ትምህርት እንገናኛለን! መልሶቻችሁን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ተከታታይ ዐሥር ቀናት ድረስ ከላይ በተጠቀሰው አድራሻ መላካችሁን እንዳትረሱ፤ ቸር ይግጠመን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!