የተቀማ ማንነት
ኀዳር ፲፯፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
የማንነት ጥያቄ በሁላችንም አእምሮ ውስጥ የሚታሰብ ነው፤ ምላሽ አግኝተን የተሻለ መረዳት ያለን ስንቶቻችን እንደሆንን ማወቅ አዳጋች ቢሆንም በዘመናት ሂደት በሰዎች ታሪክ ውስጥ ካካበትነው ዕውቀት አልያም ደግሞ ባሳለፍነው ተሞክሮ የተወሰነ መረዳት ሊኖረን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ በተለይም የአምላክን ቅዱስ ቃል ተምረን የምናውቅበት የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በመጠኑ እንኳን ካለን የመፈጠራችን ምክንያት ወይም የመኖራችን ትርጒም ይገባናል፡፡
ዓለምን ከእነጓዟ የፈጠረ ኤልሻዳይ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ ሰዎችን ከሌሎች ፍጥረታት ለይቶ ሲፈጥረን ስሙን እንድንቀድስና ክብሩን እንድንወርስ እንደሆነ ቅዱሱ መጽሐፍ አስቀድሞ ይነግረናል፡፡ (ዘፍ.፩፥፳፮) በዕፀ በለስ ምክንያት የሰው ዘር ያጣውን ልጅነት ሊመልስለት አንዱ እግዚአብሔር ወልድ ባሕርይውን ዝቅ አድርጎ፣ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከንጽሕት ድንግል ተወልዶ፣ መከራን ተቀብሎ፣ በመስቀል ተሰቅሎ የሞተልን፣ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ ብሉ ጠጡ ያለን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ የድኅነትን መንገድ የመሠረተልን መከራ መስቀሉን ተቀብለን በክርስቶስ ክርስቲያን እንድንሆን ነው፡፡
ቅዱስ ቃሉን አስተምሮ፣ በፈቃዱና በቸርነቱ የሰጠን እውነተኛዋ ሕይወት ክርስትና የማንነታችን መገለጫ መሆኗን ግን ተረድተን ይሆን? ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› ያለን ጌታ እርሱ ክርስቶስ ተብሎ ክርስቲያን እንድንባል እንዳደረግን፣ በእውነተኛውም መንገድ መጓዝ እንዳለብን የተረዳን ስንቶቻችን እንሆን? (ዮሐ.፲፬፥፮)
የምድራዊ ሕይወት ባመጣብን ጣጣ፣ በድመክመታችን ሳቢያና በኃጢአታችን ብዛት ለጥፋት ተዳርገን፣ ቀና በሚመስለው ጎዳና አሳችና ጠማማ መንገድ እየተጓዝን ያለን፣ ማንነታችንን የተቀማን ሰዎች ጥቂት አይደለንምና ቆም ብለን ልናስብ ይገባል፡፡ አስቀድሞ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ከፈጣሪያችን አጣልቶ ለ፶፻፭፻ (አምስት ሺህ አምስት መቶ) ዘመን ፍዳ አጽንቶ በኃጢአት ባርነት ገዝቶ እንዳሠቃየን ሁሉ ዛሬም አሳሳች በሆነችው ዓለም ጠፍተን እንድንቀር በተለያየ መንገድ ያጠምደናል፡፡ በጥቅም፣ በሀብት፣ በዝና የተደለሉት ወንድሞቻችን ዛሬ የት ናቸው? የዓለም ብልጭልጭ እያዋዛች ስባ፣ ጎትታ ጥላቸው፣ በርኩስ መንፈስ ተይዘው፣ በስካር ለዝሙት የተዳረጉ የዳንኪራ ቤት ደንበኞች የሆኑ ከእኛ የወጡ ኦርቶዶክሳውያንም ናቸው፡፡
“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በኃጢአታችን ሳቢያ የአምላክ ቁጣ በላያችን በበረታበት በዚህ ጊዜ ምድራዊ ሕይወትን እንኳን ለመኖር አዳጋችና አሳሳቢ ደረጃ በደረሰበት ወቅት፣ ዛሬ እንሙት መቼ በማናውቅበት በአሁኑ ሰዓት ተስፋ አጥተን፣ ማንነታችን ተቀምተናልና እናስተውል! እንመለስ! የተቀማ ማንነታችን እናስመልስ!
ክርስትና ሕይወት ነው፤ እርሱ ክርስቶስ በሞቱ ሞትን አጥፍቶ እውነተኛ ሕይወትን ሰጥቶናልና፡፡ ተስፋ ነው፤ የመሠረታት አምላክ ነውና፡፡ ብርታትና ጽናት ነው፤ መከራ መስቀሉ ኃይልን ያደርጋልና፡፡ ‹‹መስቀል ኃይልነ›› እንዲል፡፡ (የዘወትር ጸሎት) ሥቃይና መከራ ችለን ፈተናችንን ማለፍ የሚቻለን፣ ዓለም የምታመጣብንን ሥቃይ መቋቋም፣ እስከ መጨረሻውም ልንጸና የምንችለው ክርስቶስ በተቀበለልን ጽኑ ሥቃይ በመስቀሉ ቤዛነት አምነን እርሱን ስንከተል እንጂ “ጦር መዛዥ ስለመጣ እኛም መሣሪያ ይዘን ጦርነት እንግጠም” ማለት ለማንም አይበጅም፤ ማንነታችንም አይደለም፡፡ ይህ ፍራቻ የፈጠረው የተሳሳተ አስተሳሰብና አካሄድ በመሆኑ “ጠላት ሲመጣ ዝም ብለን መሞት ሞኝነት ነው፤ ተዋግተን ማሸነፍ አምላክ የፈቀደው ነው” ብለን ለባሰ ጥፋት እንዳንዳረግ እንጠንቀቅ!
ይልቁንም ጠላትን ለማሸነፍ የሚያስችለንን ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ የወሰድብንን የተቀማ ማንነታችንን “ክርስቲያናዊነታችንን” እናስመልስ፤ በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ጦርነት ሲኖር ፍራቻ እንዲፈጠርብን ያደረገብን ያጣነው ማንነታችን ነው፤ ለሃይማኖት መሞት ክብር እንጂ ውርደት አይደለምና፡፡ የሰማዕትነትን ክብር ከታደሉ ቅዱሳን ጋር እንድቆጠር የሚያደርገን ክርስትናችንን ማጣት እጅጉን ያሳስባልና በጊዜ መመለስ ያስፈልጋል፡፡
ከምንም በላይ የንስሓ ልብ ይኑረን! ርኅራኄ አጥተን ለወገኖቻችን ምሕረትን ማድረግ ያልቻልን አካላት በሙሉ ትክክል የሆንን ሊመስለን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ በመልክም፣ በገጽም፣ በባሕርይም የሚመስለንን ፍጡር በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፍ ወይም ለማጥፋት መፈለግ ማንንም አይጠቅምምና፡፡ የራስን ወንድም ወይም ወገን መግደል ምኑ ላይ ይሆን ጥቅሙ? ይህ ክርስቲያን ከሆንን ሰዎች አይጠበቅምና ልብ እናድርግ! ማንነታችን ስለተቀማን ደግሞ እንዘን!
በቁጭትና በመንፈሳዊ ቅንዓት ተነሣሥተንም እውነተኛ ማንነታችን እንፈልግ፤ እናስመልስ፤ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ለወገኑ ለጠላቱም ጭምር የሚጸልይ እንጂ ስለ ጎዳኝ ልጉዳው፣ ስለ መታኝ ልምታው፣ ስለ ተጠቀመብኝ ልጠቀምበት፣ ስለ ረገመኝ ልርገመው፣ ቤተሰቤን ስለ ገደለብኝ ልግደልበት አይልም፡፡ የሚያሣቃዩንንና በዳዮቻችንን መታገሥ፣ የሚረግሙንን መመረቅ፣ ለሚያሳዱዱን መጸለይ ለፍቅር የሞተልን፣ በቀራንዮ እንደ በግ እየተጎተተ፣ ጥፊንና ሕማማን እንዲሁም ግርፋትን ችሎ፣ እንዲያውም ለጠላቶቹ “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ የለመንንና የተሠዋልን ጌታ አስተምሮናል፡፡
በክፋት፣ በምቀኝነት፣ በክፉ ቅንዓት ምድር ላይ መርዝ ረጭቶ የበረዘን ጠላት ማንነታችን ቀምቶ ከፈጣሪ እንዳጣለን በማስተዋል የደኅነታችን መገኛ ወደ ሆነው፣ ክርስቶስ ተብሎ ክርስቲያን እንድባል ያደለን፣ የእውነተኛ ማንነታችን መገለጫ የሆነውን ክርስትናችን ወደ ሰጠን አምላካችን እንመለስ፡፡ ኃይላችን እርሱ ነውና፤ ማሸነፊያችን እርሱ ነውና፤ ተስፋችን እርሱ ነውና፤ ዘለዓለማዊ ሕይወትና ተድላ ደስታን የሚሰጠን እርሱ ነውና የተቀማ ማንነታችን እናስመልስ!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!
