የቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት የተደረገው ሙከራ ከሸፈ!
በሕይወት ሳልለው
በቦሌ ደብረ ምሕረት የቅዱስ ሚካኤልና አቡነ ጎርጎርዮስ ቤተ ክርስቲያን በኅዳር ፲፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. በቄሮ ስም የተደራጁ ወጣቶች ባደረጉት የማጥቃት ሙከራ በሰንበት ተማሪዎች ርብርብ ሊከሽፍ እንደቻለ የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋይ ሽመልስ መላክ ጠቅሷል፤ ቤተ ክርስቲያኑ ከ፳፻፰ ዓ.ም. ጀምሮ አደጋ ላይ እንደነበርም አያይዞ ገልጿል፡፡
የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንደነበር የገለጹት ምንጮቹ በአቅራቢያ ይኖሩ የነበሩ ምእመናን ቤታቸውን በመሸጥ የመኖሪያ ስፍራ መቀየራቸው ተጽዕኖ ማሳደሩን አስታውቀዋል፡፡
በተጓዳኝም በቄሮ ስም የተደራጁ ወጣቶች ከዚህ በፊት ቤተ ክርስቲያኑን እናቃጥላለን በሚል መዛታቸውን ምንጮቹ አስታውቀዋል፡፡ ኅዳር ፲፪ የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል ከተከበረ በኋላ ኅዳር ፲፭ በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ተሰቅለው የነበሩትን ሰንደቅ-ዓላማዎችን እያወረዱ ወደነበሩት የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች፤ (አቶ መስፍን በዳዳ፣ መለሰ ፈይሳ፣ ቶማስ መኮንንና ዳዊት ደጀኔ አበበ) ሁለት ወጣቶች በመቅረብ የያዙት ሰንደቅ ዓላማ ትክክል አለመሆኑን ክርክር ይጀምራሉ፡፡ በዚያም ሳቢያ ሰንደቅ ዓላማቸውን መጠቀም እንደማይችሉና አሻፈረኝ ካሉም ወደ ጥል እንደሚያመሩ ያስጠነቅቋቸዋል፡፡ ሆኖም ማስፈራሪያቸውን እንዳልተቀበሉት በመረዳት እነ መስፍንን እስከ ቤተ ክርስቲያኑ በር በመከተል ሌሎች ፳ የሚሆኑ አባሎችንም በማሰባሰብ በአራቱም አገልጋዮች ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ታውቋል፡፡
እነ መስፍንም የእነርሱን መሰባሰብና መብዛት በማጤን በአካባቢው ወደነበሩት ሰዎች የእርዳታ ጥሪ በማቅረባቸው ከፍተኛ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ተገልጿል፡፡ በአቅራቢያ የነበሩ ፖሊሶች ወደ ቦታው በመድረስ ሁኔታውን ለማጥናት በሚሞክሩበት ሰዓት ሁለት ቄሮ ነን የሚሉ ወጣቶችን እነ መስፍን ይዘው ስለነበር ለፖሊሶቹ ለማስረከብ ጥረት ቢያደርጉም አንድ የፖሊስ አባል እንዳስመለጣቸው አስታውቀዋል፡፡ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይም የፌዴራል ፖሊስ ወደ እነርሱ በመምጣትና በጥይትም በማስፈራራት ወጣቶቹ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ቢያስገድዷቸውም ‹‹ደብራችንን እናስከብራለን፤ ከዚህም አንሄድም›› በማለት እንደተቃወሙና በዚያም ግርግር ተኩስ በመከፈቱ የጥበቃ ሠራተኛ የሆነ አንድ ግለሰብ ወዲያውኑ በፌዴራል ፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ሲሞት ሲራክና ዳግም ዮሐንስ የተባሉ ወንድማማቾች ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ለማወቅ ተችሏል፤ ሌላ ስሙ ያልተጠቀሰ ግለሰብም እግሩ ላይ በተተኮሰበት ጥይት ጉዳት ደርሶበታል፤ ወጣቶቹም ወደ ሆስፒታል ለሕክምና ተልከው በመረዳት ላይ ይገኛሉ፡፡
ይህ ድርጊት ከተፈጸመ በኋላ የሰንበት ተማሪዎች ቤተ ክርስቲያኑን ከጥቃት ለመጠበቅ እዚያው ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ማደር እንደጀመሩ ሲያስታውቁ ፖሊሶች ደግሞ የአካባቢውን ወጣት እንደሚያፍሱ መግለጻቸውንም ጠቁመዋል፡፡