የቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ካርታ

ክፍል ሦስት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ሐምሌ ፳፪፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም.

ውድ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! እንደምን ሰነበታችሁ? የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም የተመሰገን ይሁን! ባለፈው ክፍለ ጽሑፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የመጪው ዐሥር ዓመታት የመንፈሳዊ እና ዘላቂ ልማት ግቦችን ማስተዋወቅን ዓላማ አድርገን፣ በክፍል አንድ ስለ ፍኖተ ካርታ (ዕቅድ)፣  በክፍል ሁለት ደግሞ ከዋና ዋና ዘርፎች በመንፈሳዊ ዘርፍ የተዘረዘሩ ግቦችን አቅርበንላችሁ ነበር፡፡ በክፍል ሦስት ደግሞ ቀጣዩን ክፍል ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

ለ. በማኅበራዊ ልማት ዘርፍ፡-

ከአራቱ ዋና ዋና ዘርፎች ሁለተኛው ዘርፍ የማኅበራዊ ልማት ዘርፍ ነው፡፡ ማኅበራዊነት በሚንጸባረቅባት ማኅበራዊ ኃላፊነቷ ከፍ ባለች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማኅበራዊ ልማትን አጠናክሮ ለመቀጠል ታሳቢ አድርጎ በዚህ ዘርፍ ማቀድ የሚመሰገን ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም ትኩረት ከተሰጠባቸው ማኅበራዊ ኩነቶች መካከል፡-

አንደኛ፡- ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ የሆነ፣ በሥነ ምግባር እና በእምነት የተገነባ ምእመን መፍጠር፤

ሁለተኛ፡- የቤተ ክርስቲያን የማኅበራዊ እና የማኅበረሰብ ዋስትናን ማጎልበትና ማዘመን፤

ሦስተኛ፡- አንድ አጥቢያ፣ አንድ ቤተ መቅደስ፣ አንድ የትምህርት ተቋም፣ አንድ የጤና ተቋም የሚሉ ሥነ ምግባርን፣ ትምህርትን፣ የማኅበራዊ ዋስትናን ለምሳሌ ጤናና ትምህርትን ታሳቢ ያደረገ ዘርፍ ነው፡፡

ቀደም ሲል በሀገራችን ብዕር ቀርጻ ብራና ዳምጣ ቀለም በጥብጣ ሃይማኖትና ቋንቋ ሳይገድባት ድንቁርናን የተዋጋች ሥልጣኔን ያስፋፋች፣ ዕውቀትን መገለጫዋ አድርጋ ትምህርት ሚኒስቴር ሳይኖር፣ የትምህርት ተቋማት ሳይከፈቱ፣ ትምህርትን በማስፋፋት ትምህርት ሚኒሰቴር ሆና የኖረች፣ አሳዳጊና ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ሰብስባ ማዕከል አቋቁማ እያስተማረች ለቁም ነገር ያበቃች፣
የፍትሕ ተቋማት ሳይኖሩ ፍትሕ ሥጋዊ ፍትሕ መንፈሳዊ አስፍና ሕዝቡን በመምራት የመንግሥታትን ሚና የተወጣች፣ አረጋውያንን በመጦር፣ ማኅበራዊ ተቋማትን በማስፋፋት፣ ጤና ተቋማት ሳይኖሩ በጠበል አጥምቃ፣ በመስቀሏ ዳስሳ፣ በእምነቷ ቀብታ ከምትፈውሳቸው ባሻገር የጤና ተቋማትን በመገንባት ሁሉ አይተኬ ማኅበራዊ ኃላፊነቷን በመወጣት ታሪክ በደማቁ መዝግቧታል፡፡

ይሁን እንጂ በመካከል ተዳክሞና ትኩረት አጥቶ የነበረውን ማኅበራዊ ዘርፍ ወደ ቀደመውና ከፍ ወዳለው ደረጃ ለመመለስ ያስችላል ተብሎ ከታቀደው ዕቅድ አንዱ ዘርፍ ማኅበራዊ ዘርፍ መሆኑ ጥሩ እይታ ነው፡፡

ሐ. ኢኮኖሚያዊ ልማት ዘርፍ፡-

ሦስተኛው ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ልማትን የሚመለከተው ዘርፍ ነው፡፡ ኢኮኖሚ አቅም ነው፡፡ ወንጌል ቢሰበክ፣ ካህናት ቢሠለጥኑ፣ አብያተ ክርስቲያናት ቢሠሩ፣ የትምህርትና ጤና መሠረተ ልማት ማሟላት ቢታሰብ፣ የገዳማትንና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ችግር ለመፍታትና ማጠናከር ቢታሰብ ወዘተ ኢኮኖሚ መሠረት ነው፡፡

ክርስትና በድህነትን መኖርን አያስተምርም፤ በመንፈስ ራሳቸውን ድሃ ያደረጉ ተባለ እንጂ በገንዘብ፣ በሀብት ድሃ የሆኑ ብፁዓን ናቸው አልተባለም፡፡ ገንዘብን ንቀው የሚመንኑ እንጂ ገንዘብ አጥተው የሚመንኑ መናንያን ታሪካቸውም በስንክሳራችንም በገድለ ቅዱሳንም አልተጻፈልንም፡፡

ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንንም ምእመናንንም በኢኮኖሚ አቅም ማጠናከር መሠረታዊ ነገር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ መነሻነት ፍኖተ ካርታው ላይ ሦስተኛው ዋና ዘርፍ የተደረገው ኢኮኖሚያዊ ልማት ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ በጉልህ ከተጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ምርታማና የተወዳዳሪነት አቅም ያለው ለሀገር ግንባታ ጉልህ ሚና የሚኖረው የቤተ ክርስቲያን ኢኮኖሚ መገንባት፣ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ አስተዋጽኦ ማድረግ፣ የዘመናዊ ፋይናንስ ሥርዓትን በመገንባት የቤተ ክርስቲያንን ሀብት መጠቀም፣ የማስተዳደር እና የማስፈጸም አቅምን ማጎልበት የሚሉ ዓላማዎች ተካተውበታል፡፡

ይህንንም ለማሳካት በገዳማት እና በገጠር ቤተ ክርስቲያን የመስኖ ልማት እንዲስፋፋ ማድረግ፣ የእንስሳት እርባታ ማከናወን፣ ዘመናዊ ግብርናን ማስፋፋት፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በንዋየ ቅድሳት ምርት፣ በግንባታ፣ በምርት ማቀነባበር፣ በኅትመትና ተዛማጅ ዘርፎች፣ የቱሪዝም እና የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት፣ ኦርቶዶክሳዊ ባንኮችን፣ ኢንሹራንሶችን በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጠናከር ታቅዷል፡፡

መ. ተቋማዊ ልማት ዘርፍ፡-

አራተኛውና የመጨረሻው ዘርፍ ተቋማዊ ልማት ዘርፍ ነው፡፡ መቼም አንድ ተቋም ምንም ያህል የተዋቡና ወሳኝ እቅዶች ቢኖሩት እቅዱን ተፈጻሚ ለማድረግና ግቡን ለማሳካት ተቋማዊ ቁመናውና ቅርጹ አደረጃጀቱና ቁርጠኝነቱ ጠንካራ ካልሆነ ችግር ነው፡፡ አደረጃጀቱ፣ የሰው ኃይል ስብጥሩ፣ የሚከተለው አስተዳደራዊ ዘይቤ፣ የማስፈጸሚያ ስልቱ፣ የቴክኖሎጅ ዕውቀት፣ አሳታፊነቱ፣ የፈጻሚ አካላቱ የአቅም ግንባታ ሥልጠናና በምርምር የታገዘ መሆን ወዘተ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ መዋቅራዊ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ማስፈን መቻል፣ አሠራርን አሳታፊ ማድረግ፤የሚከተለው የክትትልና ድጋፍ ስልቱ፣ የግምገማና ግብረ መልስ አሰጣጡ ሁሉ ፍኖተ ካርታውን ለማሳካት የማይተካ ሚና አላቸው፡፡
ቤተ ክርስቲያን የሁሉም በመሆኗ ትንሣኤዋም ውድቀቷም፣ ጥንካሬዋም ድክመቷም፣ ደስተዋም ኀዘኗም ለተወሰነ የማኅበረሰብ ክፍል ወይም መዋቅር፣ ለቤተ ክህነት፣ ለካህናት ወይም ለጳጳሳት ለማኅበራት ለማንም ብቻ የሚተው አይደለም፤ ለሁሉም በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ በእኔነት ስሜት በመሳተፍ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በሁለንተናዊ ዘርፍ መሪ ሆና ስትወጣና የመንግሥቱ ወንጌል ለዓለም ሲዳርስ፣ ሁላችንም የሃይማኖት ፍሬ አፍርተን ተያይዘን መንግሥተ እግዚአብሔር ስንገባ ማየት ራእያችን አድርገን እንሠራ ዘንድ ይርዳን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር!