የቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ካርታ
ክፍል ሁለት
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ሐምሌ ፲፬፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም.
ውድ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! እንደምን ሰነበታችሁ? የጊዜ ባለቤት አምላካችን ክብር ምስጋና ይድረሰውና ዳግም አገናኝቶናል! በመጀመሪያው ክፍል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የመጭው ዐሥር ዓመታት የመንፈሳዊ እና ዘላቂ ልማት ግቦችን ማስተዋወቅን ዓላማ አድርገን ስለ ዕቅድ በጥቅሉ አቅርበንላችሁ ነበር፡፡
በዚህ ክፍለ ጽሑፍ ደግሞ ስለ መሪ ዕቅዱ ይዘቶች በጥቂቱ ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በርካታ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብት ያላት በርካታ የሰው ሀብት የምታስተዳድር፣ የብዙዎች ልብስና ጉርስ የሆነች፣ ለተራቡ ምግብ ቤት፣ ለታረዙት ልብስ፣ ለታመሙት ሐኪም ቤት፣ ለተሰደዱት መጠጊያ ማረፊያ የሆነች አገልግሎቷ በቃላት በቀላሉ የማይገለጽ ናት፡፡
ምስጋና ለአባቶቻችንና ቀናኢ ለሆኑ ኦርቶዶክሳውያን ልጆቿ፣ ከ ፳፻፲፮ (2016) እስከ ፳፻፳፭ (2025) ዓ.ም ድረስ የሚተገበር የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቶና በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ ይፋ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ዕቅድ በጠባዩ ጥብቅ በሆነ ሥነ ሥርዓት መመራት እንዲሁም ያልተቋረጠ ግምገማና ክትትል ይፈልጋል፤ ያልተጠበቁ ችግሮች ሲያጋጥሙ እና ለመፈጸም አዳጋች ሲሆን በየጊዜው እየተከታተሉ እየከለሱ አማራጭ የማስፈጸሚያ ስልቶችን መከተልን ይሻል፡፡ ከለበለዚያ ዕቅድ በራሱ ውጤት አይደለም፤ የሚፈለገውን ውጤት አያመጣም ከታሰበው ግብም አያደርስም፡፡
ቤተ ክርስቲያን ብዙ ሀገራዊ ሸክምን የተሸከመች፣ ሀገርንና ሕዝብን የሚጠቅሙ ልማቶችን የምትከውን፣ ለሀገር ገጽታና ግንባታ ከፍ ያለ ድርሻ ያላት በመሆኗ የቤተ ክርስቲያን መሪ ዕቅድ መሳካት ለኦርቶዶክሳውያን ብቻ ሳይሆን ለሀገር፣ ሀገረ መንግሥቱና ለሕዝብ የሚሰጠው ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ርእይ ብላ ያስቀመጠችው ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓለም ዐቀፋዊ አገልግሎቷን ለሁሉ በማዳረስ በሁሉም ዘርፍ ጎልበታ፣ አንድነቷ እና ልዕልናዋ ተጠብቆ የሰው ልጆች የእግዚአብሔር መንግሥትን ለመውረስ የተዘጋጁ ሆነው ማየት›› የሚል ሲሆን ይህ ዐምድም የተዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ ማስተዋወቅ ዓላማ አድርገን ያዘጋጀነው ነው፡፡ የዕቅዱን ይዘትና ዋና ዋና ግቦችን ስንመለከት ፲፮ (16) በሚደርሱ ግቦች በአራት ዋና ዋና ዘርፎች ተቀንብቦ ቀርቧል፡፡ ዘርፎቹ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ተቋማዊ የሚሉ ናቸው፡፡
ሀ. በመንፈሳዊ ዘርፍ ከተቀመጡ ግቦች
፩. ግብ- ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት እንድትስፋፋ እና በተግባር የተገለጠ መንፈሳዊ ሕይወት እንዲያብብ ማድረግ የሚለው ወሳኙ ነው፡፡ በዚህም፡-
የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲከፈቱ እና ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣ ከፊል አገልግሎት እየሰጡ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣ የአብያተ ክርስቲያናት እጥረት ያሉባቸው ቦታዎች ላይ አብያተ ክርስቲያናት ማቋቋምና ምእመናን በወርኀዊ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ በንስሐና በቅዱስ የቊርባን ሕይወታቸውን እንዲመሩ ማድረግ
ምእመናን በሰበካ ጉባኤያት አባልነት እና በአገልግሎት እንዲሳተፉ ማድረግ፣ በአጥቢያው በሚደረግ በማንኛውም መንፈሳዊ፣ ማኀበራዊ እና በበጎ አድራጎት አገልግሎት እንዲሳተፉ ማድረግ፣ የምእመናን አንድነት እና ኀብረት እንዲጠናከር በሁሉም አጥቢያዎች እስከ ምእመናን ቤት እና ሰፈር የሚደረስ አደረጃጀት (ማኀበር፣ ዝክር፣ ጽዋ ወዘተ) መዘርጋትና ኦርቶዶክሳዊ አንድነትን ማጠናከር ወዘተ የሚሉ ነጥቦችን ይዟል፡፡
፪. ግብ፡- ገዳማት እና ገዳማዊነትን ማስፋፋት (ምንኩስና፣ ክህነት፣ ቀኖና፣ ሥርዓተ አበው ወዘተ)
ገዳማት የቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት መሠረት እና ምንጭ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ገዳማዊ ሕይወት ላይ ተጸዕኖ የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን መግራት፣ ምንኩስና ከእነ ሙሉ ክብሩ፣ በገዳም ጸንቶ እንዲኖር ማድረግ፤ አርአያነታቸው ሕይወታቸው የሚመሰክር መነኮሳት ማፍራት፣ ሥርዓተ ምንኩስና፣ የሢመተ ክህነት፣ የገዳማዊ ሕይወትና የአርአያ ክህነት መሥፈርቶችን ዘመኑን በዋጀ መልኩ መወሰን ወዘተ የሚል ነው፡፡
፫. ግብ:- የልኀቀት ተቋማትን ማስፋፋት እና በሁለንተናዊ ሰብእና የተገነባ አገልጋይ እንዲያፈሩ ማድረግ፤
በዚህ ግብ ሥር ደግሞ አብነት ትምህርት ቤት እና የሰንበት ትምህርት ቤቶች በሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ማቋቋም እና የወንጌልና የአብነት ትምህርትን በስፋት እንዲማሩ ማድረግ ትኩረት ተደርጎበታል፡፡
፬. ግብ፡-ሁሉን ተደራሽ ያደረገ እና ዘመኑን የዋጀ ስብከተ ወንጌል፣ የትምህርት እና ሐዋርያዊ ተልእኮ ማስፋፋት፤
በዚህ ግብ ሥር ደግሞ ስብከተ ወንጌል ባልተስፋፋባቸው እና አብያተ ክርስቲያናት በሌሉባቸው የገጠር እና ጠረፋማ አካባቢዎች የሐዋርያዊ ተልእኮ ኬላዎችን ማቋቋም፣ የቋንቋ ብዝኀነትን በመጠቀም፣ ተተኪዎችን ማፍራት የሚሉ ወሳኝ ጉዳዮች ተገልጸውበታል፡፡
፭. ግብ:- የቅድስት ቤተክርስቲያን የውጭ አገልግሎት ተደራሽነት ማስፋፋትና ወጥ የሆነ የአስተዳደር ሥርዓት መፍጠር፤
፮. ግብ:- ከሐሰት ታሪክ፣ ከስሑት ርእዮተ ዓለም፣ ከመዋቅራዊ እና ሥርዓታዊ ጥቃት ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ፤
የቤተ ክርስቲያንን ህልውና እና ልዕልና የሚያስጠብቅ ጠንካራ የሕግ አገልግሎት መዘርጋት አስፈላጊነቱ የተጠቀሰበት ግብ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሐሰተኛ ትርክት የተጎዳች በመሆኑ በጣም ወሳኝ ግብ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
፯. ግብ:- ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲን ማጠናከር እና የዓለም አቀፍ ኦርቶዶክሳዊ እንቅስቃሴን ማጠናከር፤
ቤተ ክርስቲያናችን ዓለማቀፋዊት መሆኗን፣ በዓለም ካሉ አብያተ እምነቶች ግምባር ቀደምትና በፍጥነት በውጩ ዓለም እየሰፋች መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህም ዓለማ አቀፍ ግንኙነትንና ትብብርን መሠረት ያደረገ ዕቅድ አስፈላጊ ነው፡፡
፰.ግብ፡-ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እና የሚዲያን ሽፋንን በማሳደግ የቤተ ክርስቲያንን የሚዲያ መሪነት ማረጋገጥ፤
ይህ ዕቅድም ትርጒም ያለው ነው፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ዓለምን የሚመራው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ዘመንን መዋጀት ሲባልም አንዱ ይህንን መሠረት ማድረግ ነው፡፡ አገልግሎቱ በቦታና በሁኔታ ሳይታጠር ተደራሽ እንዲሆን በዘርፉ ዕቅድን ዐቅዶ ዕውቀትንና ልምድን አዳብሮ መገኘት ወሳኝ ነውና፡፡
ይቆየን!
መልካም ሳምንት!