የቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ካርታ

ክፍል አንድ

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ሐምሌ ፱፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም.

ውድ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! እንደምንከረማችሁ? እንደምን ሰነበታችሁ? የዛሬ የዚህ ክፍለ ጽሑፍ ዓላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የመጭው ዐሥር ዓመታት የመንፈሳዊ እና ዘላቂ ልማት ግቦችን ማስተዋወቅ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያንን የዐሥር ዓመት መሪ ዕቅድ በዝርዝር ከመዳሰሳችን በፊት ዕቅድ ምን እንደሆነና የዕቅድን አስፈላጊነት በትንሹ መዳሰስ አስፈላጊ ነው፡፡

ዕቅድ ምንድን ነው?

አንድ ድርጅት ርእዩን እና ተልእኮውን ለማሳካት ግብዓቶችን፣ ጥረቶችን እና ተግባራትን እንዲያዘጋጅ እና እንዲመድብ፣ ሀብቱን በብቃት ለመጠቀም፣ አካባቢው ውስጥ ያለውን ትርፍ እና እድገት ለማሳደግ፣ የተቋሙን ዓላማ ለማሳካት፣ የድርጅትና የግለሰቦችን ምርታማነት ለማሳደግ የሚጠቅም ወይም የሚረዳው ፍኖተ ካርታ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ዕቅድ ውሱን የሆነውን የሀገር ሀብት ከፍተኛ ጥቅም በሚያስገኝ መንገድ በማደራጀትና በማቀነባበር የተወሰነ ዓላማዎችን በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ የሚነደፍ የወደፊት የድርጊት መርሐ ግብር ማለትም ነው፡፡
ሲጠቃለል ዕቅድ ማለት በተወሰነ ሀብት፣ የተወሰነ የልማት ሥራን፣ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማን፣ ለምን፣ እንዴት፣ በማንና መቼ መከናወን እንዳለበት አስቀድሞ የሚቀየስ የዓላማ ማስፈጸሚያ መሣሪያ ነው፡፡

ዕቅድ የወደፊቱን የልማት እንቅስቃሴ የሚያመላክት፣ ድርጊትን የሚያስከትልና ለተፈጻሚነቱም በተለያዩ ደረጃዎች ባለቤት የሚኖረው አሠራር መሆኑንም እንረዳለን፡፡

የፍኖተ ካርታ (የዕቅድ) አስፈላጊነት፡-

የአንድ አገር ወይም ተቋም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ብሎም መንፈሳዊ ዕድገት የሚወሰነው ባለው ወይም በሚገኝው የዕቅድ ሀብቶች መሠረት ሆኖ የአንድ ዕቅድ አስፈላጊነት በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኘውን የተወሰነ ሀብት፣ ገንዘብና የሰው ኃይል ወዘተ …. በሚገባ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻል ነው፡፡

ዕቅድ ምን ተግባር መቼ መሠራት እንዳለበት እንድናውቅ ያስችላል፤ ለወደፊት ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ወይም ያልተጠበቀ ችግር ለመቀነስ ይረዳል፤ ወደ ስኬት ለማምራት ይረዳናል፤ ለቁጥጥር አመች በመሆኑ ፣ የታዕቀዱ ተግባራት ትክክለኛ ወደ ታለመለት ግብ እያመሩ ለመሆናቸው እና የታለመለትን ግብ መምታቱን ለመቆጣጠር ይረዳል፡፡

ዕቅድ አስቸጋሪ ውሳኔዎችን ለማስወገድ በዕቅድ አፈጻጸም ሂደት ችግሮ ሲያገጥሙ ዕቅዱን መሠረት በማድረግ እንዲወሰኑ መርዳቱ፣ የአንድን ድርጅት ዓላማ ለማሳካት ተመራጭ መንገድ በመሆኑ፣ ኃላፊነትን ተጠያቂነትን ግልጽ ማድረግ ማስቻሉ፣ የጋራ አመለካከት በመፍጠር የልማት ቅደም ተከተሎችንና አቅጣጫ ጠቋሚዎችን በግልጽ ለማመልከት የሚያስችል መሆኑ እንዲሁም የአገልግሎት ሥራዎች ሥርጭት ተደጋጋፊና የተቀናጀ እንዲሆን የተቀነባበረ ጥረት ማስተባበር አስፈላጊ በመሆኑ ወዘተ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ካርታ፡-

ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት የሆነች መሆኗ ጥያቄ አያስነሣም፡፡ ከሃይማኖታዊ ተልዕኮዋ ባሻገር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ብሎም በቀደመው ዘመን ድርሻዋ ከፍ ያለች ተቋም ነበረች፡፡

በዚህም ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቷን ለሀገርና ለሕዝብ ያልተገደበ አገልግሎት ስታውል የኖረች፣ ተደማጭነቷ ከፍ ያለ፣ የምእመናን ኩራት፣ የሀገር ክብር የነበረች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ዛሬም እስከ በርካታ ተግዳሮቶቿ ሚናዋ ትልቅ ነው፡፡ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተልእኮዋን ትወጣ ዘንድ፣ እንደጥንቱ የታፈረች፣ የተከበረች ለወዳጅ ክብር፣ ለጠላት ኃሳር ሆና ሰማያዊና ምድራዊ ተልእኮዋን ትወጣ ዘንድ ግን ዘመኑን መዋጀት ያስፈልጋታል፡፡

እንደ ተቋም ዘመኑን መዋጀት አለባት ሲባል አንዱ ማሳያ በጠራ ፍኖተ ካርታ (ዕቅድ) መመራት ጊዜንና ሀብትን ማቀናጀት፣ ዛሬንና ነገን ማገናኘት፣ ጥነካሬዋን ማጉላት፣ ተግዳሮቷን መፍታት የሚያስችል ትልም ማበጀት ማለት ነው፡፡ ‹‹አለማቀድ ለመውደቅ ማቀድ ነው›› እንዲሉ ዓላማና ዕቅድ ሳይኖር ይህንን የፈተና ዘመን መሻገር፣ ሰማያዊ ተልእኮን መወጣት፣ ሕዝቡን መርቶ መንግሥተ እግዚአብሔር ድረስ ማድረስ፣ ተቋማዊ አንድነትን ጠብቆ ከውስጥና ከውጭ ፈተናዎች ተላቆ ካሰቡት ለመድረስ ይከብዳል፡፡

በመሠረቱ ዕቅድ ከቤተ ክርስቲያን የተገኘ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህ ዓለም የተፈጠረው፣ ተፈጥሮም የሚመራው በእግዚአብሔር ዕቅድ መሆኑን እንኳን ብንተወው ለዛሬው ዘመናዊው ሊቃውንት ለሚያነሡና ዓለም ለሚገለገልበት የዕቅድ ፅንሰ ሐሳብ ዮሴፍን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ዮሴፍ በግብጽ በፈርዖን ቤት ሳለ ንጉሡም እጅግ የሚያስጨንቅ ሕልም ባየ ጊዜ ሕልሙንም ዮሴፍ በፈታለት ጊዜ በግብጽና በአካባቢው ላይ ስለሚከሠተው ረኀብና ጥጋብ በነገረው ጊዜ ዮሴፍም በግብጽ ላይ ሁሉ ሲሾም በሰባት የጥጋብ ዓመታትና በሰባት የረኀብ ዓመታት ስለሚደረገው ነገር ዐቅዶ ግብጽንና አካባቢውን እንዴት ከክፉ ቀን እንዳዳነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡

ዮሴፍ የ፲፬ (14) ዓመታትን (የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ) ዕቅድ ዐቅዶ ነበር፡፡ በዚህም ግብጽን ብቻ ሳይሆን በቅናት ተነሣስተው በክፋት አሳልፈው ለሸጡት ወንድሞቹና ቤተሰቦቹም ጭምር የክፉ ቀን ማለፊያ መሆን እንደቻል እንረዳለን፡፡ (ዘፍ ፵፩፥፵፮) ስለዚህ ብትዘገይም ቤተ ክርስቲያናችን የዐሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ማዘጋጀቷ ይበል የሚያሰኝ ድንቅ ጅማሮ ነው፡፡

ተወዳጆች! ስለ ፍኖተ ካርታ (ዕቅድ) እንደ መግቢያ ይህንን ያህል ካየን በቀጣይ ክፍል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጭው ዐሥር ዓመታት የመንፈሳዊ እና ዘላቂ ልማት ግቦችን በጥቂቱ እናስተዋውቃችኋለን፡፡

መልካም ሳምንት!