የቤተ ክርስቲያን በዓላት አከባባር

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ  

መስከረም ፲፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ አሸጋግሮ በሰላም ለዚህ ዕለት አደረሳችሁ! ዕንቁጣጣሽ እንዴት አለፈ? መቼም ደስ ብሏችሁ እንዳሳለፋችሁ ተስፋችን ነው! ትምህርት ለመጀመር እንዴት እየተዘጋጃችሁ ነው? ባለፈው ዓመት በትምህርታችን ደከም ያለ ውጤት አስመዝግበን የነበርን ዘንድሮ በርትተን በመማር በጥሩ ውጤት ከክፍል ክፍል ለመሻገር ከአሁኑ ማቀድና መበርታት እንዳለብን እንዳትዘነጉ!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ባለፈው ዓመት ለእናንተ ያስተምራሉ በማለት በጻፍንላችሁ በርካታ ቁም ነገሮችን ስንማማር እንደ ነበር ታስታውሳላችሁ አይደል? አሁን ደግሞ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በዓላት እንዴት እንደሚከበሩ እኛም ደግሞ በምን ዓይነት መልኩ በበዓላት ላይ መሳተፍ አንዳለብን ልንነግራችሁ ወደድን፤ መልካም ቆይታ!

በቅደስት ቤተ ክርስቲያን በዓላት የሚከበሩት አምላካችን እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገልንን፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ቅዱሳን መላእክት ቅዱሳን አባቶች እናቶቸ ከፈጠሪ አማልደው ለእኛ ያደረጉልንን ድንቅ ውለታ ለማስታወስ ነው፡፡ በዓላት በተለያየ መልኩ ይከበራሉ፤ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅጽረ ግቢ እንዲሁም ደግሞ ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውጪ በአደባባይ ይከበራሉ፤ በእነዚህ በዓላት ወቅት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይቀርባል፤ እመቤታችን ትወደሳለች፤ ቅዱሳን ይታወሳሉ፤ ይዘከራሉ፤ ተጋድሏቸው ይነገራል፤ በረከታቸውን አንቀበላለን፡፡ ታዲያ ልጆች! ይህ ሁሉ የሚደረግልን በዓሉን በሥርዓት ስናከብረው ነው፤ የበዓሉን መከበር ምክንያት ተረድተን (ለምን እንደሚከበር ገብቶን) መሆን አለበት፤ ስለ በዓላቱ አከባበር ምክንያት ከተረዳን (ከተገነዘብን) በዓሉን በተመለከተ ብቻ መልካም ተግባራትን እንፈጽማለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በበዓላት ወቅት ክርስቲያኖች ሁሉ በዓሉን በተመለከተ የራሳቸው የአገልግሎት ድረሻ አላቸው፤ አባቶቻችን ጳጳሳት መነኮሳት ካህናትና ዲያቆናት የበዓሉን አከባበር እየመሩ ምእመናን ደግሞ እነርሱን በመከተል ሥርዓት ባለው መልኩ የአምልኮ ሥርዓት እንፈጽማን፤ ታዲያ በዓላትን ስናከብር እያንዳንዱን ሥርዓት ለምን እንደሚከበሩ ልንጠይቅና ልንረዳ ያስፈልጋል፤ በተለይ የአደባባይ በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ ረጅም የሆነ የእግር ጉዞ ሊኖረው ስለሚችል ከወላጅ አልያም ከታላላቅ ወንድም እኅቶቻችን ጋር ካልሆነ በቀር ለብቻችንን መሆን የለብንም፡፡

ዕድሜአችን ከፍ ያልን በሰንበት ትምህርት ቤት የምናገለግል ለዝማሬ አገልግሎት የተመረጥን ብንሆንም ታላላቆቻችን ከአጠገባችን ሊሆኑ ያስፈልጋል፤ አልያም እኛ ከእነርሱ ልንለይ አይገባም፡፡ ምክንያቱም በዓሉን ለማክበር በርካታ ምእመናን ስለሚገኙ ከሰው ብዛት የተነሣ የመጣንበት እንዳይጠፋን፣ አልያም ልጆች ስለሆንን ረጅም ጎዳና በእግራችን ስለምንጓዝ ሊደክመን ስለሚችል እንዲሁም በግርግሩ ጉዳት እንዳይደርስብን ለመጠንቀቅ ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የቅዱስ መስቀል በዓል ነው፤ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን የተሰቀለበትና በክቡር ደሙ የቀደሰው ለክርስቲያኖች ዓርማችን፣ ከጠላት ሰይጣን የሚሰነዘርብንን ፍላጻ የምንመክትበት ቅዱስ መስቀሉን የተሳሳተ አመለካከት በነበራቸውና እምነት በሌላቸው ሰዎች በቆሻሻ መጣያ ሥፍራ ተጥሎ ለብዙ ዘመናት ጠፍቶ የነበረውን ቅዱስ መስቀል ንግሥት ዕሌኒ ከተቀበረበት ለማውጣት ምልክት ይሆናት ዘንድ ደመራን አስደምራ በውስጡም ዕጣን ጨምራ በማንደድ የዕጣኑ ጢስ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አመልክቷት እርሷም ሥፍራውን በማስቆፈር ቅዱስ መስቀሉን አገኘች፡፡ እኛም ክርስቲያኖች ይህን በዓል አደባባይ በመውጣት እናከብረዋለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የእኛም ከቤታችን አቅርቢያ ከሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት በመሄድ በበዓላት ወቅት ማድረግ ባለብን ተሳትፎ በጸሎት፣ በዝማሬ፣ አባቶቸ የሚሰጡንን ምክር በመስማት፣ በዓላትን ልናከብር ያስፈልጋል፤ አሁን ያለንበት ወቅት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ የሠራልንን ውለታ እያሰብን እኛም ለሰዎች መልካም በማድረግ፣ አብዝተን ለአገራችን ሰላም ለሕዝባችን ፍቅር እየጸለይን እናሳልፍ!

አምላካችን እግዚአብሔር በረከቱን ያድለን! ቸር ይግጠመን!

ይቆየን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!