የቤተክርስቲያን ፈተና እና ምዕመናን

በዲ/ን ቀለመወርቅ ሚደቅሳ

መግቢያ

የቤተክርስቲያን ታሪክ የሚጀምረው ከዓለመ መላእክት ነው፡፡ ታዲያ ፈተና ሁሌ አብሯት የሚኖር ቤተክርስቲያን መፈተን የጀመረችው በዚሁ በዓለመ መላእክት ነበር፡፡ ዲያብሎስ ትዕቢትንና ሐሰት ከራሱ አንቅቶ መላእክትን «እኔ ፈጠርኋችሁ» በማለት ባሰማው የሐሰት አዋጅ ከሰው ልጅ ወደዚህ ምድር መምጣት ጀምሮ በብሉይ ኪዳንም በርካታ ፈተናዎች ተፈራርቀዋል፡፡

በብሉይ ኪዳን በብዙ ኅብረ ምሳሌ ከአቤል እስከ ክርስቶስ ምጽዓት ስትታሰብ የመጣች ቤተክርስቲያን በሐዲስ ኪዳን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን በመጣ ጊዜ በአማናዊ ደሙ አጽንቶ አካለ ክርስቶስ አድርጓታል፡፡ /ኤፌ 1፥23/ ቤተክርስቲያን ለሰው ዘር ሁሉ በሰማይ ያለውን የእግዚአብሔርን መንግሥት የምታስተምር ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበትና ወደ ሰማያዊው ርስትም የምትመራ የጽድቅ መንገድ ናት፡፡ መቼም ቢሆን ደግ ነገር ሁሉ የሚገጥመው ፈተና አይጠፋምና ቤተክርስቲያን ጉዞዋ ሁሉ በፈተና የታጠረ ነው፡፡

በዚህች አጭር ጽሑፍ ቤተክርስቲያን ፈተና በሚያጋጥማት ወቅት ምእመናን ምን ዓይነት ኑሮ መኖር፤ ምን ዓይነት አቋም መያዝ እንዳለባቸው ለማየት እንሞክራለን፡፡ ካሰብነው ለመድረስም ዋና ዋና የቤተክርስቲያን የፈተና ምንጮችንና ያስከተሏቸውን ጉዳቶች ለማንሳት እንጀምራለን፡፡
1.    ዋና ዋና የቤተክርስቲያን የፈተና ምንጮች
የቤተክርስቲያንን ታሪክ ስናጠና ለቤተክርስቲያን የመፈተን ምክንያት የሚሆኑ አካላትንና ድርጊቶችን ቆጥሮና ወስኖ ማስቀመጥ ወይም መገደብ ባይቻልም ጐልተው የሚታዩትን መዘርዘር ግን ይቻላል፡፡ ከእነዚህ የፈተና ምንጮች ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1.1 መናፍቃን
«የቤተክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች በጌታ አነጋገር «ጸራዊ» በሐዋርያት አነጋገር «ቢጽ ሐሳውያን» በሊቃውንት አነጋገር «መናፍቃን» ይባላሉ፡፡ የቤተክርስቲያን ልጆች ሳይሆኑ የቤተክርስቲያን ልጆች መስለው ወይም ከቤተክርስቲያን እምነትና ትምህርት የተወሰነውን የተማሩ ፤የተወሰነውንም ተምረው ያልያዙ ጐደሎዎች ናቸው፡፡ እነርሱም እንክርዳድ ስንዴ መስሎ እንደሚያድግ በክርስቶስ ዐጸደ ወይን በቤተክርስቲያን ውስጥ የበቀሉ አሳሳቾች ናቸው፡፡ » /የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ 48/
ብፁዕ አባታችን ከላይ እንደገለጹት እነዚህ ወገኖች ስልታቸውን በየስፍራውና በየዘመኑ እየለዋወጡ ሐመረ ኖኅ ቤተክርስቲያንን በምንፍቅና ማዕበላቸው እያንገላቷትና እያማቷት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ወዳልተሰበኩት ሕዝብ ደርሳ ትምህርቷን እንዳታስተምር ልዩ  ልዩ የክህደት ትምህርት በመፍጠር አባቶችን ሥራ ያስፈቱ ናቸው፡፡ይልቁንም በአሁኑ ዘመን በክህደት ትምህርታቸው ብቻ ሳይቆጠቡ ቤተክርስቲያን ላይ ሁሉን አቀፍ ዘመቻ የከፈቱበት ወቅት ነው፡፡ የተቸገሩ ምእመናንን የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ እንሰጣለን በማለት፣ የቤተክርስቲያኒቱን የመንፈሳዊ ትምህርት ተቋማት እንረዳለን በማለት፣ እንዲሁም ለሆዳቸው ያደሩ ሰዎችን በመጠቀም የቤተክርስቲያን ዋነኛ የፈተና ምንጭ ሆነው ቀጥለዋል፡፡
1.2 አላውያን ነገሥታት
በቤተክርስቲያን ታሪክ ከጌታ ትንሣኤ እስከ 70 ዓ.ም ድረስ ያለው ዘመን ዘመነ ሐዋርያት ከ70 ዓ.ም እስከ 160 ዓ.ም ያለው ደግሞ ዘመነ ሐዋርያነ አበው እንዲሁም ከ16ዐ ዓ.ም እስከ 312 ዓ.ም ያለው ዘመነ ሰማዕታት  በመባል ይታወቃል፡፡
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ክፍላተ ዘመናት የነበረው የቤተክርስቲያን አገልግሎት ከአይሁድ ጋር የተደረገ ተጋድሎ ነው፡፡ ይኸውም ምንም እንኳን የአይሁድ ማኅበረሰብ ቃል ኪዳን የተገባለት፣ ትንቢት የተነገረለት፣ በአንድ አምላክ አማኝ ቢሆንም የክርስቶስን አዳኝነትና አምላክነት ላለመቀበል በአመጽ በመግፋቱ፣ እነርሱን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስና ለማቅረብ የተደረገ ጥረት ነበር፡፡
ሦስተኛው ክፍል ግን ቅዱሳን አበው ከአላውያን ነገሥታት ጋር ባደረጉት ተጋድሎ የሚዘከር ዘመነ ሰማዕታት ነው፡፡ በክርስትና ሃይማኖት ትምህርትና በመምህራኑ አማናዊ ምሳሌነት በመላው ሮም የክርስትና ሃይማኖት ተስፋፍቶ ነበር፡፡ በመሆኑም ለባሮች የነጻነት ትምህርት የተሰበከላቸው ሲሆን ባለጸጋዎችም ቢያምኑ የክርስቶስ አገልጋዮች ለመሆን እንደሚበቁ ተነገራቸው፡፡ /1ቆሮ 7፥22/  የአሕዛብን የቀደመ ትዕቢትና ኩራት የእግዚአብሔር ቃል  ሲያፈራርሰው፤ የአሕዛብን የአመንዝራነት ሕይወት የክርስቲያኖች ቅድሰና አሸነፈው፡፡ በአሕዛብ ልማድ በወንዶች መካከል ሴቶች የክብር ቦታ ያልነበራቸው ሲሆን በክርስትና እኩልነትና መከባበር ታወጀ፡፡
ከዚህ በኋላ ግን ክፉዎች በክርስቲያኖች ላይ የሰውን ሥጋ ይበላሉ፤ ለቄሳር አይታዘዙም፤ ግብር አይከፍሉም፤ የሚሉ ተራና ክፉ ወሬዎችን አወሩ ፡፡ በዚህ የተነሳ እንደነ ዲዮቅልጥያኖስ ያሉ ኢአማኒያን/ከሃድያን/ ነገሥታት ስልጣናቸውን መከታ አድርገው ብዙ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት እንዲያልፉ ያደረጉበት እኩይ ተግባር ፈጸሙ፡፡ ይህም ደጉ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ መንበረ ሥልጣኑን ይዞ ለክርስቲያኖች ሠላም እስኪያወርድላቸው ድረስ የቀጠለ ጉዳይ ነበር፡፡
ቤተክርስቲያን ለምድራዊ ኑሮ ሲባል በተለያየ ሥርዓተ መንግሥት ሥር የሚኖሩ ሰዎችን ነው በሥርዓቷና እና በትውፊቷ እንዲኖሩ የምትጥረው፤ የእርሷ ድርጊት ሁሉ ከአመራራቸው ጋር የማይሄድ የሚመስላቸው ሁሉ እንደየዘመናቸው ሁኔታ መከራን አጽንተውባቸዋል፡፡ ይህም የሁል ጊዜ የቤተክርስቲያን የፈተና ምንጭ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው፡፡

1.3 የአባቶች አለመግባባት /በአባቶች መካከል አለመግባባት መከሰት/
«የክርስቶስ ፍቅር ገብቷቸው ክርስትናንና ከዚያ የሚከተሉትን ኃላፊነቶችን፣ ክህነትን እስከ ጵጵስና ድረስ «አውቃለሁ፤ እበቃለሁ» ብለው ወይም « ይገባኛል» ብለው ሹመት ፈልገውና ተካሰው ሳይሆን «እኛ አንበቃም ተውን» እያሉ፣ ነገር ግን ለመንጋው የግድ መሪ ስለሚያስፈልገው «እናንተ ለዚህ ሓላፊነት ትበቃላችሁ መንጋውን ጠብቁ» እየተባሉ አደራ ሲጣልባቸው የተሰጣቸውን ከባድ ሓላፊነት የሚጠይቀውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል የተወጡ ብዙ ቅዱሳን አባቶች ቤተክርስቲያናችን አሏት፡፡

«በተቃራኒው ደግሞ እነዚህን ሓላፊነቶች ለራሳቸው ግላዊ ክብርና ዝና መጠቀሚያ በማድረግ የክርስቶስን ክብርና በደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያንን ደኅንነትና ዕድገት ሳይሆን የራሳቸውን ምድራዊና ጊዜያዊ ፍላጐት ማስፈጸሚያ መሣሪያ ያደረጉትም ብዙዎች እንደነበሩ የቤተክርስቲያን ታሪክ መስታወት ሆኖ ያሳየናል» /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱና ትምህርቱ ገጽ 7/
ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ በአሠራርና በአመራር ምክንያት በአባቶች መካከል አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ የአባቶች አንድነት የቤተክርስቲያን የአንድነቷ መገለጫ ነው፡፡ ይህ አንድነት በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ችግር ከገጠመው የቤተክርስቲያን የፈተና ምንጭ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም፤ ይህም በተለይ ለውጭ ጠላቶች በራችንን ወለል አድርጐ የሚከፍትላቸው ነው፡፡
1.4 የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት መዳከም
የክርስትና ሕይወት በየጊዜው በመጠን እየተለካ የሚያድግ ሕንጻ እግዚአብሔር ነው፡፡ ክርስትና በቤተክርስቲያን መሠረተ እምነት /ዶግማ/ በማመን በክርስቶስ ሕግና ሥርዓት መመራትና መኖር ነው፡፡
ምእመናን የቤተክርስቲያንን ድምጽ አልሰማ ብለው ሕይወታቸውን በቃለ እግዚአብሔር ከመምራት ይልቅ በሥጋዊ ፈቃድ ስሜት መመራት ከጀመሩ የቤተክርስቲያን ትልቁ አደጋዋ ነው፡፡ ይህ በሆነ ጊዜ በአባቶችና በምእመናን መካከል መደማመጥ አይኖርም፡፡ በዚህ ወቅት እግዚአብሔር ጸጋውን ይነሳል፤ የምእመናን ማኅበርም በክፉ ይታወካል፡፡
1.5 የግል ጥቅም አጋባሽ የሆኑ ግለሰቦች
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወቅት ይከተሉት ለነበሩት ሰዎች አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ጠይቋቸው ነበር፡፡ «ምን ልታዩ መጥታችኋል» /ማቴ 11፥7-1ዐ/ ምንም እንኳን  ጌታ የጠየቀው ስለ ዮሐንስ ቢሆንም እርሱን ስለመከተላቸውም የሚያመለክት ነው፡፡ በመጽሐፍ እንደምናነበው ጌታን ይከተል የነበረው ሕዝብ ሁሉ ትክክለኛና አንድ ዓላማ ብቻ የነበረው አልነበረም፡፡ ይከተሉት የነበሩትን ሰዎች በሦስት ዋና ዋና  ክፍል መመደብ ይቻላል፡፡
ሀ. ሕብስት አበርክቶ ያበላ ስለነበር ጊዜያዊ እንጀራ ለመብላት ለሆዳቸው የሚከተሉት ነበሩ
ለ. የማስተማር ጥበቡን፣ እውቀቱን ለማድነቅ እንዲሁም ዓለምን ሊያድን የመጣ ንጉሥ ምን ዓይነት እነደሚመስል መልኩን ለማየት የሚከተሉት ነበሩ
ሐ. ድውያንን ሲፈውስ ለምጻሞችን ሲያነጻ ሙታንን ሲያነሳ አይተው ከደዌ ሥጋ ብቻ ለመፈወስ የሚከተሉት ነበሩ፡፡
መ.ድውያንን ፈወሰ ለምጻሞችን አነጻ ሙታንን አነሳ እንዲሁም ከተለያዩ ሀጢአትን ከሚሠሩ ጋር ይውላል ያድራል በማለት ለክስ የሚከተሉትም ነበሩ።
እነዚህ ሁሉ ግን የጌታችን የእግር መንገድ ሥራዎች ምድራዊ ሀብት እንጅ ዋነኛ ዓላማዎች አልነበሩም፡፡ የቃሉን ትምህርት ሰምተው ተአምራቱን አይተው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው ለአድኅኖተ ዓለምና ለእኛ አርዓያ ምሳሌ ሊሆን በመሆኑ ከአምስቱ ገበያ ሕዝብ ግን ይህን ተረድተው የተገኙት መቶ ሃያው ቤተሰብ ብቻ ናቸው፡፡
በቤተክርስቲያን ጉዞ ውስጥ እስከ ዛሬም ድረስ ለሥጋዊ ጥቅማቸው ፤ ወይም አድናቂና አጨብጫቢ ሆነው ብቻ ቤተክርስቲያን ላይ እንደ ክፉ ተባይ የተጣበቁ ግለሰቦች ነበሩ፤ አሉ፡፡ እነዚህ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ፍላጐታቸው ሥጋዊ ጥቅማቸው ማጋበስ ብቻ ስለሆነ ከእነርሱ ጋር የማይስማማ አባት፣ ካህን፣ ዲያቆን፣ ምእመን እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ ለዚህም ሲሉ የማያሴሩት የክፋት ሴራ ባለመኖሩ ለቤተክርስቲየን አገልግሎት ነቀርሳዎች ሆነዋል፡፡
2.    ፈተናዎች በቤተክርስቲያን ላይ ምን አደረሱ?
በቤተክርስቲያናችን በመናፍቃን፣ በአላውያን ነገስታት፣ በጥቅም አጋባሽ ግለሰቦችና በመሳሰሉት የደረሰባት በደል በዚች አጭር ጽሑፍ ዳስሶ መጨረስ ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ ዋና ዋናዎችን ማንሳት ግን ግድ ነው፡፡
2.1 ቤተክርስቲያንን መከፋፈል፦
በሦስቱ ጉባኤያት /ኒቅያ  ቁስጥንጥንያና ኤፌሶን/ ዶግማዋን አጽንታ፣ ክፉዎችን ለይታ፣ ጥርት ያለውን እምነት ይዛ፣ አንድነቷን ጠብቃ የተጓዘችው አንዲት ዓለም አቀፋዊት ኦርቶዶክሳዊ ቤተክርስቲያን ዛሬ ላለችበት ሁኔታ የበቃችው እነ አርዮስ በጫሩት የምንፍቅን የክህደት እሳት ነው፡፡ዛሬ ክርስቲያን በሚለው መጠሪያ የሚታወቁ ቤተ እምነቶች በዓለም እንዲፈጠሩ የሆነው ከላይ በዘረዘርናቸው ምክንያቶች ነው፡፡
የሕንድ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን የአሳዛኝ ታሪክ ምሳሌ ያደረጋት የመናፍቃን ደባ ነው፡፡ የሮም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከኦርቶዶክሳውያኑ ጐራ ተለይታ የኖረችው  እዚህ ግባ በማይባል ፖለቲካዊ / ምድራዊ ሥልጣን/ ምክንያት በተጀመረ ጠብ ነው፡፡
ዛሬ በእኛ ቤተክርስቲያን በአገር ውስጥ አባቶችና በውጭ በሚኖሩት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ፍጹም ክርስቲያናዊ በሆነ አኳኋን በአጭር ጊዜ ውስጥ ካልተፈታና መፍትሔ ካልተገኘ እንደ ሕንድ ቤተክርስቲያን በእኛም በየአጥቢያው ላለመከፋፈልና ጥቁር ነጥብ ስላለመከሰቱ እርግጠኛ መሆን ይከብዳል፡፡
2.2  ምዕመናን ግራ ማጋባት
ቤተክርስቲያን በአባቶች አለመግባባትና በክህደት ትምህርት በምትፈተንበት ወቅት የሚከሰተው ትልቁ ስጋት /ክስተት/ የምዕመናን ግራ መጋባት ነው፡፡ ይህ ደግሞ እነርሱን ለመቀራመት አሰፍስፈው ለሚጠብቁ የቤተክርስቲያን ጠላቶች የመንጋውን በረት ወለል አድርጐ የሚከፍት ነው፡፡ ዛሬ በአሜሪካ ባለችው ቤተክርስቲያን ከሁለቱም ወገን አይደለንም፤ገለልተኛ ነን፤ግን ጳጳስ እንፈልጋን የሚሉ አብያተ ክርስቲያናትና ምዕመናን የዚህ  ምሳሌዎች ናቸው፡፡
2.3 ጽንፈኝነት፦
በክርስትና የሕይወት ጉዞ ውስጥ እጅግ አደገኛ ከሚባሉ በሽታዎች አንዱና ዋነኛው ጽንፈኝነት ነው፡፡ ያውም ደግሞ ተላላፊ በሽታ ነው፡፡ «በዚህ ዓለም ያሉ ነገሮች አፈጣጠራቸውና ሕይወታቸው ከተለያዩ ነገሮች ረቂቅና ድንቅ በሆነው ጥበብ መለኮታዊ ተመጥኖ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ መጠን ሲናወጥ ግን ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡» /ሐመረ ተዋሕዶ 2000 ዓ.ም ገጽ 12/
«ማዕከላዊ ደረጃ የሌላቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም እግዚአብሔርና ጣዖታት፤ እውነትና ሐሰት፤ ሕይወትና ሞት ፤መንግሥተ ሰማያትና ገሃነመ እሳት፤ ክርስትናና ከክርስትና ውጭ ያሉ እምነቶችና አስተሳሰቦች.. » /ሐመረ ተዋሕዶ 2000 ዓ.ም ገጽ 13 / እነዚህ በራሳቸው ብቻ ቀዋምያን ከሆኑ ነገሮች ውጪ ያሉትን ግን በመጠን፣ መያዝ መኖር ተገቢ ነው፡፡ «መጠን ማለት» አንተም ተው አንተም ተው» ዓይነት ጉዳይ ሳይሆን ሁሉንም ነገር በራሱ አግባብና በተገቢው መጠን ማድረግና ከዚያ አለማሳለፍ ሲሆን ጽንፈኝነት ደግሞ ከዚህ ከተገቢው ልክና መጠን ማለፍ ነው፡፡» /ሐመረ ተዋሕዶ 2000 ዓ.ም ገጽ 14/
አይሁድን ከክርስትና የለያቸው ክርስቶስ ምድራዊ መንግሥትን አልመሠረተም፤ አንቀበለውም የሚል ጽንፈኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ ወደ ክርስትና የመጡትንም ከአሕዛብ ወገን ወደ ክርስትና ከመጡት ጋር ሲያጣላቸው የነበረው « ጥምቀት ያለ ግዝረት ዋጋ የላትም» የሚለው ጽንፈኛ አስተሳሰብ ነው፡፡
ዛሬ ብዙዎችን ከቤተክርስቲያን እየለየ ያለ ይህ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ነው፡፡ ሰባኪ እገሌ እንዲሰብክ ካለተፈቀደለት ጉባኤ አልመጣም፤ ዲያቆን እገሌ እንዲቀድስ ካልሆነ አላስቀድስም፤ እነ እገሌ ወጥተው’ እነ እገሊት ካልተመረጡ ይህንን ማኅበር አልፍልገውም፤ እዚህ  ሰንበት ት/ቤት አልደርስም፤ ብለው የቀሩ ሰዎች በጽንፈኝነት ቀሳፊ ቀስት የተወጉ ናቸው፡፡
ቤተክርስቲያን በተፈተነች ቁጥር አንዱን ጽንፈ ይዘው በማክረርና በመወጠር ከማኅበረ ምእመናን የተለዩትን ቆጥረን አንጨርስም፡፡
ምንተ ንግበር /ምን እናድርግ/?
«ሰውን ብትታገል ብትዋጋ ታሸንፈዋለህ ወይም ያሸንፍሃል ቤተክርስቲያንን ግን ለማሸነፍ አይቻልም ቤተክርስቱያን ሁል ጊዜ ትዋጋለች ተሸንፋ ግን አታውቅም ዲያብሎስ ዝናሩን አራገፈ ቀስቱን ጨረሰ፡፡ ቤተክርስቲያንን ግን አልጎዳትም» ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን በመጥቀስ የጻፉት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ነው / የቤ.ተ. ገጽ 48/። ፈተና የቤተክርስቲያን የመኖሯ መገለጫ እንደሆነ በጽሑፋችን መግቢያ ላይ ገልጸናል፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን ፈተና በሚገጥማት ወቅት በሚነሳው ማዕበል ተከፍተን ከመርከቧ ወደ ባሕር እንዳንወርድ ምን ማድረግ ይገባናል? ጥቂት ነጥቦችን እናነሳለን፡፡
3.1 መንፈሳዊ ሕይወትን መጠበቅና ማጽናት ነው
የ አበው አባቶቻችን የተጋድሎ ገድል ስናነብ የምንረዳው ምንም እንኳን ወጥ የሆነ መንፈሳዊ ሕይወት ቢኖራቸውም ከባድ ፈተና በገጠማቸው ጊዜያት ግን የበለጠ ይበረታሉ። በርካታ ቃል ኪዳናትን የተቀበሉት በርካታ መንፈሳዊ መጻሕፍትን የጻፉት የብዙ ጸጋ ባለቤት የሆኑት በፈተና ውስጥ ነው፡፡
የምንማረው ከአባቶቻችን ነውና ቤተክርስቲያን ፈተና ላይ በምትሆን ጊዜ በጋዜጣ በሚጻፈው፣ በድረገጽ በሚለቀቀው «እንዲህ ሆነ እንዲህ ተደረገ» ወሬ ተገፍቶ እርሱን ብቻ በማውራት የራስ ሕይወትን መዘንጋት አይገባም፡፡ የሚሰሙት ዜናዎች፤ የሚፈጸሙት ድርጊቶች የግል መንፈሳዊ ሕይወትን የመሸርሸር አቅማቸው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው የቀደመ መንፈሳዊ ሕይወታችን መጠበቅ ማጽናት እግዚአብሔር አምላክ በፈተና ውስጥ ለቤተክርስቲያን በጐ የሆነውን ሁሉ እንዲያደርግ ጉዳዩን በጸሎት መያዝ መሆን አለበት፡፡
3.2 የቤተክርስቲያንን ድምፅ ብቻ መስማት
ቤተክርስቲያናችን መሠረተ እምነታዊ /ዶግማዊ/ በሆነ ችግር የተፈተነች እንደሆነ የቤተክርስቲያን ቋሚ ምስክር የሆኑ መጻሕፍትን፣ ትውፊተ አበውን፣ የቀድሞ የቤተክርስቲያን ድንጋጌዎችን መጠየቅ፣ ማንበብ በእርሱም ብቻ መመራት ተገቢ ነው፡፡
በአባቶች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ቤተክርስቲያን በተፈተነች ጊዜ ከግጭቱ ተጠቃሚም ተጐጅም ያልሆኑ በአንድም በሌላም ያልወገኑ አባቶችን ድምፅ ብቻ መስማት ተገቢ ነው፡፡ እንዲሁም ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የቀድሞ ሥርዓትና ትውፊት እንዲሁም ትምህርት ምንድን ነው? የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡
የትኛውም ወገን’ትውልድ ቢሆን የኃይል ሚዛኑ ስለመዘነለት ብቻ የሚያራግበውን ተቀብሎ በስሜት መነዳት አያስፈልግም፡፡ የቤተክርስቲያን ድምጽ ከቅዱሳት መጻሕፍት ከትውፊትና ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰማ ነው፡፡ እርሱን ብቻ መስማት ተገቢ ነው፡፡
3.3 ከጽንፍ ራስን መጠበቅ ነው::
በክርስትና ሕይወት የጽንፈኝነትን አደገኛነት ከላይ በጥቂቱ ለመግለጽ ሞክረናል፡፡ የአሁኑ ዘመን ምእመናን የባሕታዊ እገሌ ተከታይ፣ የአቡነ እገሌ ደጋፊ፣ የመምህር እንትና አድናቂ፣ የዘማሪ/ዘማሪት እገሌ ቡድን እየተባባልን መታየታችን የበሽታው ምልክት ነው፡፡ መጨረሻውም መከፋፈል ነው፡፡ አሁን በቅርቡ በተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖደስ ስብሰባ እንኳን ብዙዎቻችን ውሳኔዎችን እንመዝን የነበረው «ማን ምን ተናገረ? የትኛው ጐራ ተሸነፈ? ማን ምን ተደረገ?» በሚሉና በሚመስሉ መስፈርቶች እንጂ ውሳኔው ለቤተክርስቲያን ጠቃሚ ነው ወይስ ሌላ? የሚል አልነበረም፡፡
በእንዲህ አይነቱ ክስተት ማንም አሸናፊ ማንም ተሸናፊ የለም፡፡ ደግ ከተሰራ ቤተክርስቲያን አሸነፈች፤ አበራች፡፡ ሸፍጥ ከተሰራ ቤተክርስቲያን ተጐዳች፤ እውነታው ይሄ ነው፡፡
ከስሜት እንራቅ፤ ከጽንፈኝነት ራሳችንን እንጠብቅ፡፡ ወገንተኝነታችን ለቤተክርስቲያን ብቻ ይሁን፡፡ ያኔ የሰውም የእግዚአብሔርም ፍስሐ ይሆናል ፡፡ አምላከ ቅዱሳን ለዚያ ድል ያብቃን፡፡አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር