የቤተልሔም እንስሳት(ለህጻናት)
ልጆች ዛሬ ስለቤተልሔም እንስሳት ነው የምንጽፍላችሁ፡፡ ቤተልሔምን ታውቃላችሁ? ቤተልሔም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደባት ከተማ ናት፡፡ እና ልጆች የቤተልሔም እንስሳት የጌታችን መወለዱን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተደስተው «ምን ይዘን እንሒድ? ምንስ እናበርክት?» በማለት በሬዎች፣ በጎች፣ ጥጃዎች፣ አህያዎች ሌሎች እንስሳትም ተሰብስበው «ምን እናድርግ» እያሉ መወያየት ጀመሩ፡፡
ፀሐይ ልጆቿን ጨረቃንና ከዋክብትን ጠራቻቸውና
«ልጆቼ ሆይ ዛሬ ታላቅ ደስታ በኢየሩሳሌም ሀገር በቤተልሔም ከተማ ተፈጽሟል የዓለም ፈጣሪ ጌታችን ተወልዷልና ፍጥረታት ሁሉ በደስታ የምንሆንበት ቀን ነው፡፡ እና ልጆች የጥበብ ሰዎች /ሰብዓ ሰገል/ ጌታችን መወለዱን ሰምተው ከሩቅ ሀገር ተነሥተው መምጣት ፈልገዋልና ከእናንተ መሐከል ማነው ጎብዝ? እነዚያን የክብር እንግዶች ፈጥኖ ይዟቸው የሚመጣው?» ስትል ጠየቀቻቸው፡፡ ሁሉም «እኔ እኔ ካልተላኩ» ብለው ሲያስቸግሯት እናታቸው ፀሐይ ዕጣ አወጣች፡፡ ለአንዷ ኮከብ ወጣላት፣ ከደስታዋ ብዛት በሰፊው ሰማይ ላይ ክብልል ክብልል እያለች እየበረረች እንግዶች ዘንድ ደረሰች፡፡ እንግዶቹም ለታላቁ ጌታችን የምናበረክተው ብለው ዕጣን፣ወርቅ፣ከርቤ ይዘውለት ሲመጡ አገኘቻቸው፡፡ ኮከቧም በጣም ደስ አላትና ቦግ ብላ በራች፡፡ ወደ ቤተልሔም እየመራቻቸውም ሔደች፡፡
ጌታችን በተወለደባት ሌሊት በቤተልሔም ከተማ አካባቢ ከብቶቻቸውን ሲጠብቁ ያደሩ እረኞች ነበሩ፡፡ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፡፡ ወዲያውም ያሉበት ቦታ በብርሃን ተጥለቀለቀ በዚህ ጨለማ ምን ብርሃን ነው የምናየው ብለው ፈርተው ሊሸሹ ሲሉ የእግዚአብሔር መልአክ «አይዞአችሁ ልጆች እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ፤አትፍሩ፡፡ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱ ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል ይህም ምልክት ይሆንላችኋል ሕፃን ተጠቅልሎ ተኝቶ ታገኛላችሁ አላቸው፡፡ ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ፡፡ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ፡፡ /ሉቃ.2፥8-20/፡፡ ልጆች ይገርማችኋል የዚያን ዕለት አበባዎች በደስታ አበቡ፣ ሣር ቅጠሎችም ለመለሙ፣ ንቦች ማራቸውን አበረከቱ፣ ላሞችም ወተታቸውን ሰጡ ሁሉም ያለውን ሰጠ፡፡ የቤተልሔም እንስሳት «እኛስ ምን እንስጥ?» እያሉ ግራ ገባቸው በመጨረሻም አህያ ከሁሉም የበለጠ ሐሳብ አመጣች «ግን ጌታችን በበረት ነው የተወለደው አይደል?» ስትል ጠየቀቻቸው «አዎን» አሏት «ታዲያ እኮ ልብስ የለውም ደግሞም እንደምታዩት ጊዜው ብርድ የበዛበት ነው፡፡» አለች፡፡
«እና አህያ ምናችን ልብስ ይሆነዋል ብለሽ አሰብሽ?» አለች በግ፡፡ «ለምን ትንፋሻችንን አንሰጥም» አለች፡፡ ሁሉም በጣም ደስ አላቸው፡፡ ትንፋሻቸውን ሊያበረክቱለት ጌታችን ወደ ተወለደበት በረት እየሮጡ ሔዱ፡፡
ልጆች እናንተስ ለጌታችን ልደት ወደ ቤተክርስቲያን ምን ይዛችሁ ልትሔዱ አሰባችሁ? ሻማ፣ ጧፍ ልትሰጡ አሰባችሁ? ጎበዞች! ልጆች እናንተም መባ ሰጥቶ መመለስ ብቻ ሳይሆን ቅዱስ ቁርባንን ተቀብላችሁ መምጣት አለባችሁ፡፡ እንደ ቤቴልሔም ልጆች /እረኞች/ እየዘመራችሁ የጌታችንን ልደት አክብሩ እሺ? በሉ፤ ደኅና ሁኑ ልጆች፡፡