የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያንን ዳግም ለማነጽ የገቢ ማሰባሰቢያ ተካሔደ

መጋቢት 28/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በቅርቡ በአክራሪ ሙስሊሞች ሙሉ ለሙሉ ወደተቃጠለው በስልጤና ሃዲያ፣ ጉራጌ ከንባታ ሀገረ ስብከት ጋራሬ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን መጋቢት 23/2004 ዓ.ም. መንፈሳዊ ጉዞ ተካሔደ፡፡ የጉዞው ዓላማ በቃጠሎው ምክንያት የተጎዱትንና ተስፋ በመቁረጥ ላይ የሚገኙትን የአካባቢውን ምእመናንን በቃለ እግዚአብሔር ለማጽናናት ቤተ ክርስቲያኑን ዳግም ለማነጽ እንዲረዳ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ለማካሔድ ታስቦ የተዘጋጀ ነበር፡፡

አዲስ አበባ በሚገኘው በማኅበረ ነህምያ የስልጤ ዞን አብያተ ክርስቲያናት መርጃ ማኅበር ከሥልጤ አካባቢ ተወላጆች ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ጉዞ ሲሆን በተጨማሪም በአዋሳና ሻሸመኔ የሚገኙ ምእመናን ቤተ ክርስቲያኗ ያለችበት ሁኔታ ለማየትና የአቅማቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ በቦታው ተገኝተዋል፡፡

 

በሥፍራው ከተገኘው ማኅበረ ምእመናን በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በጥሬ ገንዘብ ከ200,000 /ሁለት መቶ ሺህ ብር/ በላይ ሊሰበሰብ ችሏል፡፡ በተጨማሪም ገንዘብና ጥሬ እቃ ለማቅረብ ከምእመናን ቃል የተገባ ሲሆን በዕለቱ በተጋበዙ መምህራነ ወንጌል የማጽናኛ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን ያሬዳዊ ዝማሬም ቀርቧል፡፡

 

ከሥፍራው ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ከመንግሥት በተሰጠው ውሳኔ መሠረት ቤተ ክርስቲያኑን ለመሥራት ተለዋጭ ቦታ የተሰጠ ሲሆን የይዞታ ማረጋገጫም ለማግኘት ተችሏል፡፡ የቀድሞው ቤተ ክርስቲያን ይዞታ አሁን ከተሰጠው ቦታ ድንበር ላይ የሚገኝ ሲሆን ለጥምቀተ ባህር ቤተ ክርስቲያን  እንድትጠቀምበት ውሳኔ አግኝቷል፡፡

 

የአካባቢው ምእመናን ከጎናቸው መሆናቸውን ለመግለጽና ለማጽናናት የመጡትን ምእመናን አመስግነው በተካሔደው መርሐ ግብር እንደተደሰቱ በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በዕለቱ ከ1500 በላይ ምእመናን በመርሐ ግብሩ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

 

የጋራሬ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያንን ዳግም ለማነጽ ግንቦት 5/2004 ዓ.ም. የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቀሌምንጦስ  የመሠረት ድንጋይ ያኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡