የቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክት ቤተ ክርስቲያኒቱ በአንገብጋቢነት የምትሻውን ወቅታዊ ጥያቄ የሚመልስ አሳብ የያዘ ነው

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

 
ከአራት ዓመት በፊት 2001 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ተሻለ የአገልግሎት ደረጃ ለማድረስ በመከረበት ጉባኤው ቤተ ክርስቲያኒቱ ያሉባትን ለአገልግሎቱ እንቅፋት የሆኑ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን ለማስወገድ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች፣ የተያዙ አቋሞች ነበሩ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጊዜው በቤተ ክርስቲያኒቱ “የአስተዳደር ችግሮች፣ የሙስናና የቤተሰብ አስተዳደር” በቤተ ክርስቲያኒቱ የአገልግሎት መስመሮች ውስጥ ሁሉ መንሰራፋቱን አምኖ ያንን ለማጥራት፣ ዘመኑን የዋጀ በተጠና ዕቅድና አፈጻጸም የሚከናወን፣ ሓላፊነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ውሳኔ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው፡፡ 

ይሁን እንጂ ወደ ተግባር ለመግባት የተደረገው እንቅስቃሴ ግን ወዲያውኑ ፈተና ገጥሞት ነበር፡፡ ውዥንብር ለመፍጠር፣ አለመግባባትን ለማስፈን የአባቶችን ስም በማጥፋት ለማሸማቀቅ በተለያዩ መንገዶች ጥረት የሚያደርጉ፣ በተናጠልና በቡድን የሚን ቀሳቀሱ የተለያዩ አካላት ስለነበሩ ርምጃው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በመሠረተ አሳቡ ግን የቤተ ክርስቲያኒቱን የአገልግሎት አካሄድ የማሳደግና የሚያስወቅሱ ነገሮችን የማስወገድ ብርቱ ፍላጎት እንደነበረው ቅዱስ ሲኖዶስ በአቋሙ አሳይቶ አልፏል፡፡

ይህ የነበረ የቅዱስ ሲኖዶስ ሐሳብ ዛሬ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በግልጽ የተግባራቸው መጀመሪያ፣ የትኩረት አቅጣጫዎቻቸው ሁሉ ራስ እንደሆነ በቅርቡ ለበዓለ ትንሣኤ ባስተላለፉት ይፋዊ መልእክትና ለእንኳን አደረሰዎ በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ  ባንጸባረቁት አቋም ከላይ አስቀድመን ያነሣናቸውን የቅዱስ ሲኖዶስ አቋሞች አስተጋብተዋል፡፡ ሃይማኖት በምግባር መገለጽ እንዳለበትና ከሃይማኖቱ አሳብ ጋር ስምሙ የሆነ አካሄድ እንዲኖረን የመከሩት ቅዱስነታቸው “ያረጀው ነገር ሁሉ በክርስቶስ ደም ተቀድሶና ነጽቶ ሐዲስ ሆኗል፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሠርቶ የሚያሠራ የመልካም ነገር ሁሉ አርአያ መሪ እንደመሆኑ መጠን አዲሱን መንገድ ከፍቶ እንድንጓዝበት ሲያደርግ እኛም በአዲስ መንፈስ በአዲስ ሕይወት ልንመላለስበት እንጂ እንደገና ወደ አረጀውና ወደ አፈጀው ሕይወት ተመልሰን ልንዘፈቅ አይደለም” ብለዋል፡፡

መልእክታቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆችና አገልጋዮች ሁሉ በየደረጃው ያሉ ፍጹም ክርስቲያናዊ ምግባር እንዲላበሱ ያላቸውን አባታዊ ፍላጎት አንጸባርቀዋል፡፡ ይህ የቅዱስነታቸው ምክር በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አካላትም ዘንድ ሊተኮርበት የሚገባ ነው፡፡ ለመልካም ምግባር እንድንሰለፍ በሥራችንም ሁሉ እንድንበረታ ባስተላለፉት በዚሁ ምክራቸው መሠረት የትኞቹም አገልጋዮች መመላለስ ቢችሉ ቤተ ክርስቲያን አሉባት ከሚባሉ ችግሮች ሁሉ መላቀቅ የሚያስችላት አቅም ይሆናል፡፡

ቅዱስነታቸው በተለይም በዕለተ ማዕዶት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቤተ ክህነቱ ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት ባስተላለፉት መልእክት በዓሉ ከዲያብሎስ ቁራኛነት ከሞት አገዛዝ ከአሮጌው እርሾ የተላቀቅንበት መሆኑን ካወሱ በኋላ በዚያው አንጻር የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከብልሹ አስተሳሰብ፣ ከብልሹ ምግባር ከሙስና፣ ከብልሹ አሠራር መጽዳት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያላትን ቅድስና ጠብቃ እንድትኖር ልጆቿ በተለይም አርአያ ሊሆኑ የሚገባቸው ካህናት በጎ ካልሆኑና ቤተ ክርስቲያንን ከሚያስተቹ አስተሳሰብና ተግባር እንዲላቀቁ መክረዋል፡፡ ይህም ቀድሞም የነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ቀርጥ አሳብ ተግባራዊ ምላሽ ሊያገኝ የሚችልበት ዕድል እንዳለ ተስፋ ሰጪ ሆኗል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የቅዱስነታቸው መልእክት ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን የሚያምን ሲሆን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ዕድገት በቀና መንፈስ ለሚያስቡ የቅዱስነታቸው የአገልግሎት ጅማሬ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ያስባል፡፡ ይህ የቅዱስነታቸው አቋም በዚሁ ወቅት በሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ብርቱ ድጋፍ እንደሚያገኝና ጠንከር ያሉ መመሪያዎችን በየደረጃው ላሉ የቤተ ክህነቱ አገልጋዮች ያስተላልፋል ተብሎ ይታመናል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን የቅዱስነታቸው መልእክትም ሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ አቋም በየደረጃው ባሉ አካላት ተግባራዊ ምላሽ ይፈልጋሉ፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ተወስነው የማይተገበሩ ውሳኔዎች፣ ሊራመዱ የማይችሉ አቋሞች ሊሆኑ አይገባም፡፡ ለተግባራዊነቱ ደግሞ ከብፁዓን አባቶች ጀምሮ በርካታ የቤተ ክህነቱ አካላት ድጋፍ እንዳላቸው ቅዱስነታቸው አቋማቸውን በንግግራቸው ባንጸባረቁበት ወቅት በሰጡት ሞቅ ያለ የድጋፍ ምላሽ መረዳት ይቻላል፡፡ ከጥቂት ራስ ወዳዶች በስተቀር የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ማሻሻያን በብርቱ የማይፈልግ የለም፡፡ በአስቸኳይና በጥብቅ ይፈልገዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ገጽታ እንዲጎድፍ የሚሻ የለም፡፡ የጎደፈም ነገር ካለ በፍጥነት ማስተካከያ ለማድረግ መረባረብ ይገባል፡፡ የእርምጃው ቁልፍ ያለው ግን በቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ አቋም ላይና በቅዱስ ፓትርያርኩ የአስተውሎት ርምጃ ውስጥ ነው፡፡

ለውጥን ምእመናንን በመላው፣ ማኅበረ ካህናቱ በየደረጃው፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት፣ አድባራትና ገዳማቱ፣ ተማሪዎችና መምህራኑ፣ ደቀመዛሙርቱና መዘምራኑ ሁሉ በብርቱ ይፈልጋሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን የዕረፍት ወደብ መሆን አለባት፡፡ እንደ ቅዱስነታቸው ንግግርም ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም አርአያ መሆን፣ ለዓለሙ ጨው መሆን አለባት፡፡ አሮጌው ነገር ሁሉ ማለፍ አለበት፤ አዲሱ መልካሙ ነገር ሁሉ ሊመጣ ይገባል፡፡ በዚያን ጊዜ ሁሉም አንድ ሆኖ ያስባል፡፡ መንፈሳዊው ሥራ ይሠለጥናል፤ የሥጋው ሥራ ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡

ዛሬ በየአህጉራቱ ያሉ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በብርቱ ተነቃቅተው የዓለምን ብልሹ ነገር ሁሉ እየተዋጉ ነው፡፡ ጠንካራ አደረጃጀትና የአግልግሎት አድማስ ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ የታሪክ፣ የሞራል፣ የዕውቀት፣ የሥነ ምግባርም መሠረት ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይሔንን አቅም ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ የሚያግዳት አንዳችም ነገር የለባትም፡፡ ዋናውና ወሳኙ ነገር የእግዚአብሔርን ቡራኬ ማስገኘት የሚችል በጎ ምግባር፣ ቀና ሐሳብ ቤተ ክህነቱ ይዞ የመገኘቱ ነገር ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ጥቂቱ ብዙ፣ ጥቁሩ ነጭ፣ ክፉው ሁሉ ለመልካም የማይሆንበት ምክንያት እንደማይኖር ማኅበረ ቅዱሳን የጸና አቋም አለው፡፡

በአጠቃላይ ቅዱስነታቸው ያመላከቱንን በጎ መንገድ መከተል ቤተክርስቲያን ያለ አማራጭ ይዛው ልትገኝ የሚገባት አካሄድ ነው፡፡ ለዚህ ጥሪ ምላሽ መስጠት ደግሞ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ ሓላፊነት ነው፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትም ለዚሁ ጥሪ በጎ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

 

ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 21ኛ ዓመት ቁጥር 1 ግንቦት 2005 ዓ.ም.

ወስብሐት ለእግዚአብሔር