የቅዱስ ኤፍሬም ቅኔያዊ መዝሙራት /ክፍል ሁለት/

ዳር 14/2004 ዓ.ም

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

“እግዚአብሔር በሰው አምሳል የመታየቱ ምሥጢር”

በዚህ ርእስ ግሩም የሆነውን የቅዱስ ኤፍሬም መጽሐፍ ቅዱስን የመረዳት ጸጋውን እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል ሲናገር  የሰውን የአካል ክፍል እና ጠባይ ለራሱ በመጠቀም ነው፡፡ ይህ መዝሙር እንዴት የሰው ልጅ በእርሱና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ታላቅ የሆነውን ልዩነት አልፎ  ስለእግዚአብሔር ባሕርያት ማወቅ ይችላል? ብሎ ይጠይቃል፡፡ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት ቅዱስ ኤፍሬም ታላቅ ገደል ወይም ቅዱሱ ጸጥታ ብሎ ይጠራዋል፡፡ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም አስተምህሮ ለሰው የሚሰጠውን መጠሪያና ተፈጥሮ ለራሱ በመጠቀም  በእርሱና በሰው መካከል ያለውን ሰፊ የሆነ ልዩነት ያጠበበው እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ እንዲህ ማደርጉ ክብር ይግባውና ለሰው ልጆች ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሣ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለሰው የሚሰጠውን መጠሪያና ጠባይ ለራሱ ተጠቅሞበት እናገኛለን፤ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም ትምህርት ደግሞ እንደ ልብስ ለብሶአቸው እናገኛቸዋለን፡፡

አስተምህሮውን ከዚህ ቅኔያዊ መዝመር ያገኙታል፡፡
1.በእኛ ምሳሌ በመገኘት ራሱን የገለጠልን እግዚአብሔር አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሚሰማን ለማስረዳት ሲል ስለጆሮዎቹ ጻፈልን፤ /መዝ. 33፥15/
እኛን ስለመመልከቱ ሊያስተምረንም ስለ ዐይኖቹ ተረከልን፤ /መዝ. 33፥15/
በዚህ መልክ በምሳሌአችን ተገልጦ ለእኛ ታየን፡፡
እርሱ በባሕርይው ቁጣና ጸጸት የሌለበት አምላክ ሲሆን፤ ዘፍ.6፥6
ስለእኛ ደካማነት እነዚህንም ስሞች ለራሱ በመስጠት ተጠቀመባቸው ፡፡ /1ሳሙ.15፥29/

2.እርሱ በእኛ ምሳሌ ተገኝቶ ባያስተምረን እርሱን ባላወቅነው ነበር፤

በምሳሌአችን ተገልጦ ወደኛ ቀረበ እኛም ወደ እርሱ ቀረብን፡፡  
አባት ከልጁ ጋር ሲነጋገር በልጁ ማስተዋል መጠን እንዲናገር፣
እንዲሁ እግዚአብሔር በእኛ ማስተዋል መጠን ስለፈቃዱ አስተማረን፡፡

3. እንደመረዳታችን መጠን አስተማረን ስንል እርሱ እንደእኛ ነው ማለታችን ግን አይደለም፤

እርሱ በእኛ ምሳሌ ተገለጠ ወይም አልተገለጠ እርሱ እርሱ ነው፤ አይለወጥም፡፡
ሲያስፈልግ እኛን ለማስተማር በአንዱ ጠባያችን  ተገልጦ ይታየናል፤
ሌላ ጊዜ ደግሞ አስቀድሞ የተላበሰውን ምሳሌአችንን እንደልብስ አውልቆ ሌላውን ለብሶ ይገለጥልናል፤
እርሱ በምሳሌአችን ተገኝቶ ለእኛ በመናገሩ እርሱ እንዲህ ነው ማለት ግን አይደለም፤
ነገር ግን ባሕርይው የማይመረመር ነውና በምንረዳው በእኛ ምሳሌ ተገኝቶ ፈቃዱን ገለጠልን፡፡

4.በአንድ ቦታ እርሱ በዘመን ርዝማኔ የሸመገለ አረጋዊ መስሎ ሲታየን፤ /ዳን.7፥9/

በሌላ ስፍራ ደግሞ እጅግ ብርቱ የሆነ ተዋጊ ሆኖ ይገለጥልናል፡፡ /ዘፀ.15፥3/
በሽማግሌ አምሳል መታየቱ ፍትሐዊ መሆኑን ለማስተማር ነው፤
ብርቱ ጦረኛ ሆኖ መታየቱ የእርሱን ኃያልነት ለማስረዳት ነው፤
በአንድ ቦታ እንደሚዘገይ በሌላ ቦታ የሚቀድመው የሌለ ፈጣን እንደሆነ መጻፉ፤
በአንድ ቦታ እንዳዘነ በሌላ ቦታ ደግሞ እንዳንቀላፋ ሰፍሮ መገኘቱ፤ኢሳ./7፥13፣ መዝ.43፥23፣ 78፥66/
በአንድ ቦታም  ሁሉን እንዳጣ ምስኪን ሆኖ ስለእርሱ መተረኩ፤
ስለእኛ ጥቅም እንጂ እርሱ ሁሉ የእርሱ የሆነ ባለጠጋ ነው፤
በእውኑ በእኛ ላይ የሚታዩት ጠባያት በእርሱ ላይ አሉን? የሉም፡፡

5.ቸር የሆነው ፈጣሪ አንዳች ሳይቸገር፣ ያለፈቃዳችን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ሥራን እንድንፈጽም ማስገደድ ይቻለዋል፤

ከዚህ ይልቅ ግን በፈቃዳችን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ሥራን እንድንሠራ ይሻል፤
ስለዚህ እርሱ የሚወደውን የጽድቅ ሥራ እንድንሠራና በጽድቅ ተውበን እንድንገኝ በእኛ አምሳል ተገለጠልን፡፡
አንድ ሠዓሊ የሣለውን ሥዕል በቀለማት እንዲያስውበው፤
አምላካችንም በአምሳላችን ለእኛ በመገለጥ በጽድቅ ሕይወት አስጌጠን፡፡

6.አንድ ሰው በቀቀንን ንግግር ለማስተማር ቢፈልግ ራሱን በመስታወት ጀርባ ይሰውራል፤

በቀቀኑዋን ግን ከመስታወቱ ፊት በማድረግ የሰውን ቋንቋ ያሰማታል፤
በቀቀኑዋም ድምፁን ወደሰማችበት አቅጣጫ ስትዞር የራሱዋን ምስል በመስታወት ውስጥ ታገኛለች፤
ምስሏን ስትመለከት ሌላ በቀቀን እርሱዋን እያነጋገረቻት ይመስላታል፤ስለዚህም አጸፌታውን ትመልሳለች፤
በዚህ መልክ ሰውየው በበቀቀን አምሳል በመገኘት ለበቀቀኑዋ ንግግርን ያስተምራታል፡፡

7.ይቺ በቀቀን ከሰው ጋር ተግባብታ የምትኖር ፍጥረት ነች፤

ነገር ግን እንዲህ እንድትግባባ ከእርሱዋ ተፈጥሮ ውጪ የሆነው ሰው ሊያስተምራት ተገባ፤
እንዲሁ ከሁሉ በላይ እጅግ ከፍ ከፍ ያለው መለኮት፤
ስለፍቅር ከላይ ከከፍታው ራሱን ዝቅ በማድረግ በእኛ ምሳሌና ልማድ ተገኝቶ ፈቃዱን ያስተማረን፤
ሁላችንን  ወደ ጽድቅ ሕይወት ለመምራት በደካማው በሰው አምሳል ለእኛ ተገለጠልን፡፡


8.እርሱ አንድ ጊዜ በእድሜ ርዝማኔ ያረጀ ሽማግሌ መስሎ ሲታይ ሌላ ጊዜ በተዋጊ ተመስሎ ይገለጥልናል፤

በአንድ ቦታ የማያቀላፋ ትጉህ እረኛ ሆኖ ሲታይ፤ በሌላ ስፍራ ደግሞ እንዳንቀላፋ ሆኖ ይገለጥልናል፤/መዝ.12ዐ፥3-4/
በአንድ ቦታ እንደሚጸጸት ሆኖ ሲገለጥልን፤ በሌላ ስፍራ ደግሞ ጸጸት የሌለበት ጌታ እንደሆነ ያስተምረናል፤/ኢሳ.40፥28/
በፈቃዳችን ራሳችንን ለማስተማር እንድንበቃ  እርሱ በሚወሰንና በማይወሰን አምሳል ለእኛ ተገለጠልን፡፡
በአንድ ስፍራ ብሩህ በሆነ የሰንፔር ድንጋይ በሚመስል ወለል ቦታ እንደቆመ ሆኖ ሲታየን፤ /ዘፀ.4፥10/
በሌላ ቦታ ደግሞ ሰማይንና ምድርን የሞላ ፤ ፍጥረት ሁሉ በመሃል እጁ የተያዘች እንደሆነች ይነግረናል፡፡ /ኢሳ.40፥12/

9.ሲፈልግ በተወሰነ ቦታ ለእኛ ሲገለጥ፤

ሲፈልግ ደግሞ በሁሉ ስፍራ ይገልጥልናል፤
በአንድ ስፍራ በአምሳላችን ሲገለጥ በቦታ የተወሰነ ይመስለናል፤  እርሱ ግን በሁሉ ስፍራ ነው፡፡
በሌላ ስፍራ እኛን በቅድስና ሕይወት የበቃን ያደርገን ዘንድ ታናሽ መስሎ ለእኛ ይገለጥልናል፤
በተቃራኒው ደግሞ እኛን እጅግ ባለጠጎች ያደርገን ዘንድ በታላቅነቱ ያታየናል፤
እኛን በክብር ለማላቅ ሲል አንዴ ታናሽ ሌላ ጊዜ ታላቅ ሆኖ ይገለጥልናል፤
እርሱ ታናሽ ሆኖ ብቻ እንጂ ታላቅ ሆኖ ባይገለጥልን፤
ደካማ መስሎን ስለእርሱ ግንዛቤ የተዛባ ይሆን ነበር፡፡
እንዲህ እንዳይሆንም አንዴ ታናሽ ሌላ ጊዜ ታላቅ ሆኖ ይታየናል፡፡


10.ኑ  የእኛን ታናሽ የሆነን ተፈጥሮ ለማላቅ ሲል ታናሽ መስሎ የተገለጠውን አምላክ እናድንቅ፤

ለእኛ ታናሽ መስሎ እንደተገለጠ ሁሉ በታላቅነቱ ለእኛ ባይገልጥልን፤
እርሱን ደካማ አድርገን ስለምንቆጥር ስለእርሱ ያለን ግንዛቤ ያነሰ ይሆን ነበር፡፡
አይደለም በታላቅነቱ በእኛ አምሳል ተገልጦልን እንኳ ስለእርሱ መለኮታዊ ባሕርይ መረዳት አልተቻለንም፤
ስለእርሱ ታላቅነት በተመራመርን ቁጥር እጅግ እየረቀቅን በእውቀትም እየመጠቅን እንሄዳለን፤
እርሱን የመረዳት አቅማችን እየጫጨ ሲመጣ ፣ ለእኛ አምሳል በመታየት ወደ እርሱ ፈቃድ ይመራናል፡፡

11.እግዚአብሔር በእኛ አምሳል መገለጡ ሁለት ዓበይት ቁምነገሮችን ሊያስተምረን በመሻቱ ነው፤ /ዮሐ.1፥11/

አንደኛው አምላክ ሰው መሆኑን ሁለተኛው ሰው መሆኑ አምላክነቱን እንዳላሳጣው ሲያስተምረን ነው፡፡
ለእኛ ለባሮቹ ካለው ፍቅር የተነሣ በሚታይ አካል ለእኛ ተገለጠ፤
ነገር ግን በሰው አምሳል በመገለጡ እርሱን በማሳነስ እንዳንጎዳ፣
አንዴ በአንዱ አምሳል ሌላ ጊዜ በሌላ አምሳል ለእኛ ይገለጥልናል፤
በዚህም እርሱን የሚመስለው እንደሌለ አስተማረን፤
እርሱ በሰው አምሳል መታየቱን ሳይተው ለእኛ መገለጡ፤
እርሱን በተለያየ አምሳል እንዳይገለጥ አይከለከለውም፡፡

ክፍል ሦስት ይቀጥላል…….