የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያስተላለፉት መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

* ብፁዕ አቡነ አብርሃም
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
* ብፁዕ አቡነ ሄኖክ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
*ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!!
እንደዚሁም በዚህ ቀኖናዊና ዓመታዊ የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ የተገኛችሁ በሙሉ፤ ጸጋንና ሐዋርያነትን ያጐናጸፈን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ትንሣኤውን በሰላም አክብረን ይህንን ዓመታዊውን የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ለማካሄድ ስለ ሰበሰበን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን፤ የጉባኤው አባላት የሆናችሁ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም እንኳን ለርክበ ካህናት ጉባኤ አደረሳችሁ! እንኳንም በሰላም መጣችሁ!

“ረከብነ ጸጋ ወተሰየምነ ሐዋርያተ ከመ ናስምዖሙ ለኣሕዛብ ወይእመኑ በስሙ፡- ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን” (ሮሜ.፩÷፭)፤ይህ ሐዋርያዊ አስተምህሮ የኛን ተልእኮና ተልእኮው ያስፈለገበትን ምክንያት አጉልቶ ያሳያል፤ የተቀበልነው ስጦታም ምን ያህል ታላቅ እንደ ሆነ ምንባቡ ያስረዳል፤ ሐዋርያው በዚህ መልእክት የቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ ዋና ግብ ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ማድረግ ነው በማለት ያስተምረናል፤ እውነት ነው ድሮውኑም ቢሆን ለእግዚአብሔር መታዘዝ አቅቶን ነው የወደቅነው፤ ዛሬም የምንነሣው ከእምነት የተነሣ መታዘዝን ገንዘብ ስናደርግ ነው፤ ከሁሉ በፊት እምነት ይቀድማል፤ ከሱ በኋላ ደግሞ ለእምነቱ በሙሉ ልብ መታዘዝ ይከተላል፤ ይህ ሲሆን መዳንና ትንሣኤ ይገኛል፤

ዓለም በእግዚአብሔር እየተደረገላት ያለ ጥሪ ይኸው የመታዘዝ ጥሪ ነው፤

ይህንን መለኮታዊ ጥሪ ለዓለም የማድረስ ኃላፊነትም ለኛ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የተሰጠ እንደሆነ ሐዋርያው አስገንዝቧል፤ ኃላፊነቱ ሲሰጠን ከነ መሳርያው ነው፤ እሱም ጸጋና ሐዋርያነት ነው፤ እኛም እሱን ተቀብለናል፤ እንግዲያውስ የተቀበልነውን ጸጋና ሐዋርያነት በዓለም ውስጥ ላለው ሕዝበ እግዚአብሔር አገልግሎት ማዋል ከኛ ይጠበቃል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በአሁኑ ጊዜ የሌለበት ክፍለ ዓለም የለም፤ ምክንያቱም የዚህ ሲኖዶስ ወኪሎች ሊቃነ ጳጳሳት በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በካናዳና በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በእስያና በአውስትራሊያ ወዘተ የሚገኙ ሕዝበ እግዚአብሔር ምእመናንን በማገልገል ላይ ይገኛሉና ነው፤ ይህ ዕድል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መለኮታዊ ተልዕኮውን በአጽናፈ ዓለም ሁሉ ለማድረስ ምቹ መደላድል ፈጥሮለታል፡፡ከዚህም በመነሣት በየክፍለ ዓለሙ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃነ ጳጳሳት ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ባሻገር የየአካባቢውን ሕዝብ በማስተማርና በማቀፍ የተጣለባችሁን ሐዋርያዊ ተልእኮ በትጋትና በንቃት መወጣት ይኖርባችኋል፡፡

በማእከል ሆኖ እየመራ የሚገኝ ቅዱስ ሲኖዶስም ለዚህ ተልእኮ ምቹ መደላድል የመፍጠር ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይገባዋል፡፡ በተለይም ትምህርተ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የተማሩና በጥልቀት የተገነዘቡ፣ ብስለትም ያላቸው፤ እንዲሁም በቋንቋና በሥነ ልቦና ዕውቀት የላቀ ሀብተ ጸጋ ያላቸውን በሐዋርያነት እያሠለጠነ በአጽናፈ ዓለም ሁሉ ሊያሰማራ ይገባል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

በብሂለ አበው (ፀሐይ ለመስኮቷ ሳታበራ…) እንደሚባለው ለሌላው በብቃት መድረስ እንችል ዘንድ እኛ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሲኖዶሱ መንበር በሚገኝባት ምድረ ኢትዮጵያ ከመቸውም የተሻለ ሥራ በመሥራት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ሕዝቡንም ማገልገል ይገባናል፤ ሁላችንም እንደ የምንገነዘበው በሲኖዶሳችን ያልታቀፉ ብዙ ወገኖች በሀገር ውስጥ አሉን፤ እነዚህ ወገኖች አንዳንዶቹ በተለያየ ምክንያት ከኛ የወጡ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የሄዱት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ፣ ሌሎችም ወደ መንጋው እንዲቀላቀሉ በርትቶ መሥራት የዚህ ጉባኤ ተቀዳሚ ተልእኮ ነው፤ ምክንያቱም ጸጋንና ሐዋርያነትን የተቀበልንበት ዋናው ምክንያት ይህንን ለማድረግ ነውና፡፡ ከዚህ አኳያ የቤተ ክርስቲያናችን ተደራሽነት በሳሳበት ኣካባቢ ሁሉ የተለየ ትኵረት ሰጥተን መሥራትና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውሉደ ክህነትና ምእመናን የሆን ሁላችን፣ ከሁሉ በፊት ያለንን ዓቅምና ብቃት በአግባቡ መገንዘብ ይኖርብናል፤ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይሁንና ለፈጣሪው በቈራጥነት የሚታዘዝ ምእመን፣ ወጣት፣ ካህን አለን፤ ይህ ትልቅ ጸጋ ነው፤ ይህንን ጸጋ እግዚአብሔር፡ ለእግዚአብሔር መንግሥት በሚመች ሁናቴ ዝቅ ብሎ ማገልገል የክብር ክብር ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሐቅ፣ በቅንነት፣ በትጋትና በታማኝነት ቆመን ካገለገልነውና አባትነታችንንና መሪነታችንን በመልካም አሠራር በትክክል በኅሊናው እንዲቀረጽ ካደረግን፣ ይህ ኃይል ከጐናችን እንደማይለይ እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ይህንን ካሳካን ለኛ የተሰጠ ኃይልና ብቃት በየትም አይገኝም፡፡

በዚህም በዚያም ሃይማኖቱ የሚጠይቀውን ስብእና እና ቁመና ይዘን ከተገኘን፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ ያለውን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን ሳይቀር ለመስጠት ወደ ኋላ የማይል የእግዚአብሔር ሕዝብ አለን፤ ስለዚህ ይህንን ማሳካት እንችል ዘንድ ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንድናስገኝ የተቀበልነውን ጸጋና ሐዋርያነት በክብር እንያዝ፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!!

ለሕዝበ እግዚአብሔር የምናበረክተው አገልግሎት በመንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚውና በማኅበራዊው አገልግሎትም ጭምር ነው፤ ከዚህ አንጻር ሕዝባችን የተሻለ ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያገኝ፣ በኢኮኖሚውም ከድህነት የተላቀቀ እንዲሆን፤ እንደዚሁም ሰላሙና አንድነቱ የተጠበቀ እንዲሆን፣ በማስተማርም በተግባር በመሳተፍም የሕዝቡ መሪዎችና አርአያ ሆነን መሥራት ይገባናል፤

በተለይም ከሰላም እጦት የተነሣ በእጅጉ እየተጎዳ ያለውን ሕዝባችን ሰላምና ፍትሕ እንዲያገኝ በጸሎትም በትምህርትም፣ በምክርም ተግተን መሥራት አለብን፤እንዳጋጣሚ ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእንግልት የተላቀቀበት ጊዜ ብዙ እንዳልሆነ ይታወቃል፤ ለእንግልት እየተዳረገ ያለውም የሌሎች እጅ ባይለየውም በዋናነት በገዛ ልጆቹ ነው፤ እናት በገዛ ልጆቿ ስትንገላታ ማየት እጅግ አሳዛኝ ነገር ነው፤ እንደዚህ ያለው ነገር በደንብ ያልታሰበበት አካሄድ በብስለትና በንስሓ ማስተካከል አሸናፊነትን እንጂ ተሸናፊነትን አያሳይምና እንዲታሰብበት እንመክራለን፤ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ልማትና ዕድገት እናሻግራለን ብላችሁ እየደከማችሁ ያላችሁ ወገኖቻችን እባካችሁ መለስ ብላችሁ እናታችሁ የተንገላታችበትን እዩና በቃ በሉ፤ሁሉን የሚያግባባ ነገር ፈልጉና ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት ፍቱ፤ በዚህ አማራጭ እናት ሀገር እፎይታ እንድታገኝ አድርጉ፤ ይህንም ለውድ እናት የሚደረግ ካሣ አድርጋችሁ ውሰዱት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ መልእክትና ጥሪም ይህ ነው፤

በመጨረሻም

የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ አፈጻጸማችን በመገምገም ለቀጣዩ ጊዜ የሥራ አቅጣጫን የሚያስቀምጠው የርክበ ካህናቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተጀመረ መሆኑን ለኦርቶዶክሳውያን ሕዝበ ክርስቲያን እናበስራለን፤

እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣
ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ