የቅዱስ ሚካኤል ታቦት “ካህኑን” አቃጠለ
ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ
- የአብያተ ክርስቲያናት ዝርፊያ ተባብሷል
የሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ታቦት ግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ሌሊት በሌቦች ተዘርፎ ሲወሰድ መንገድ ላይ የዘራፊውን “ካህን” አእምሮውን አስቶ፤ መንገዱን አስትቶ፤ በሰው ማሳ ውስጥ እንዳስገባውና ታቦቱም ወደ ሰማይ እየዘለለ ዘራፊውን እንዳቃጠለ የሀባቦ ጉዱሩ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉኀን ብዙዓለም ግንባር ተናገሩ፡፡
“እንዲሁም ተጠርጣሪው ‘ወየው ለእኔ፤ ወየው ለእኔ’ እያለ ሲጮህ በአካባቢው አትክልት ሲጠብቁ ያደሩ ሰዎች እንደሰሙ እና ተጠርጣሪው እስር ቤት ከገባ በኋላም ‘እባቦች እየመጡብኝ ነው’ እያለ ለፖሊስ እንደሚያመለክት፤ ፖሊሶችም ወደ ታሰረበት ክፍል ሲገቡ ምንም እባብ እንዳላገኙ” ሊቀ ትጉኀን ብዙዓለም የቅዱስ ሚካኤልን ድንቅ ተአምር መስክረዋል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ታቦት ድንቅ የሆነ ገቢረ ተአምራትን እንደሚያደርግ የተጠቀሰ ነው፤ ያሉት ደግሞ በጉዱሩና በሀባቦ ጉዱሩ ወረዳዎች በሰባኬ ወንጌልነት የሚያገለግሉት ቆሞስ አባ ወልደ ገብርኤል አበበ ሲሆኑ፤ የሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ታቦትም ገቢረ ተአምሩን ሊሰርቅ በሞከረው “ካህን” ላይ አሳይቷል ብለዋል፡፡
የሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ቄስ ዋለ ዓለሙ ስለ ሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የዘረፋ ሙከራ እንዳመለከቱት “በዕድሜ ዘመኔ እንዲህ ያለ ነገር ተመልክቼ አላውቅም፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ የሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሁለት ጊዜ (ኅዳር 10 እና ግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም) ተዘርፏል፡፡ የግንቦት ሁለት ቀን ግን ለየት ያለ ነበር፡፡ በዕለቱ ታቦት፣ ሙዳየ ምጽዋት፣ መስቀልና መጽሐፍ ባልታወቁ “ካህናት” ተዘርፈው ታቦቱ ከአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ተወሰዶ በአንድ ሕፃን ልጅና በሦስት ሴቶች ተገኝቷል” በማለት አስረድተዋል፡፡
የተዘረፈውን ታቦት የእርሻ ማሳ ውስጥ ተቀምጦ ከተመለከቱት ልጆች መካከል ብዙነሽ ዓለማየሁ ስለሁኔታው ስትናገር “አራት ሆነን በአህያዎቻችን ዕቃ ጭነን ወደ ገበያ ስንሄድ ከሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ካሉ የእርሻ ማሳ ደረስን፡፡ በዚህን ጊዜ አብሮን የነበረው ሕፃን የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ የሚመስል ነገር አየና ለእኛም አሳየን፡፡ እኛም ወንጌል መስሎን ለመሳለም አንሥተን ለመሳለም ስንሞከር አቃተን፤ አንቀጠቀጠን፡፡ ፈርተን አህዮችን ነድተን ልንሄድ ስንል አህዮች ቀድመው ስለወደቁ መነሣት አልቻሉም፡፡ አህዩችን ለማስነሣት ብንሞክርም አልተቻለም፡፡ በመጨረሻ ነገሩ ተአምር መሆኑን ስለተረዳን ለዲያቆናት ስልክ ደወልን” በማለት ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡
ወንጌል መስሏት ለመሣለም የፈለገችው እንሰኔ ዓለማየሁ ስለተመለከተችው ተአምር ስትገልጽ “ጠጋ ብዬ ላነሣው ስሞክር ቀኝ እጄን አሸማቀቀኝ፣ ለዲያቆን ታደለ ደወልን፤ እርሱ መጥቶ ታቦቱ ላይ ፎጣውን አልብሶ ካህናት ሊጠራ ሔደ፤ ከፎጣው ብርሃን ሲወጣ ስንመለከት፤ ታቦቱ የተቃጠለ መሰሎን አለቀስን፤ ታቦቱ ግን ምንም አልሆነም” ብላለች፡፡ አያይዛም ታቦቱን አስቀድሞ የተመለከተው ሕፃን ሌሊቱን ሙሉ ሲባንን ማደሩን አውስታለች፡፡
የሬፍ ቶኮ ታኔ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ሊቀ መንበር ኮንስታብል ደረጀ ጉቱ ስለሁኔታው ሲያስረዱ “የቤተ ክርስቲያኑን መሰበር የሰማነው ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ ሲሆን፤ ታቦቱንም ሚግሮ ዳሞት አካባቢ ወድቆ፤ በአካባቢውም መዝሙረ ዳዊትና የተሰበሩ ሦስት ባንኮኒዎችን አገኘን፡፡ በመዝሙረ ዳዊቱ ላይ ባገኘነው ማስታወሻ መሠረት ተጠርጣሪውን ልንይዝ ችለናል” ብለዋል፡፡
“ታቦቱን ካለበት ቦታ ማን ያነሰዋል እያልን ስንመካከር ከመካከላችን የነበረ አንድ የሌላ እምነት ተከታይ ‘እኔ አነሣለሁ’ ብሎ ቀረበ፤ ነገር ግን ታቦቱን ሲቀርብ ፈራ፤ ‘ሰውነቴን አቃጠለኝ ራሴን አቃጠለኝ እንደ አንድ ነገር አደረገኝ’ ብሎ በመደንግጥ ሄደ” በማለት ኮንስታብል ደረጀ ተናግሯል፡፡
ታቦታቱን ለማክበር ከመጡት አባቶች መካከል ቆሞስ አባ ወልደ ገብርኤል ስለሁኔታው ሲናገሩ “ታቦቱን ዘራፊው አስቀምጦት የሄደበት ቦታ ዙሪያ ገባው ጭቃ ነበር፡፡ ይህ ጭቃ ታቦቱን ሳይነካ በታቦቱ ዙሪያ መሆኑ የሚያመለክተው ታቦቱ ሌባውን አስሮት ማቆየቱና ሌባው ታቦቱን በዙሪያው ሲዞር ማደሩን የሚያመለክት ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ታቦቱ የተገኘው በእኛ የእርሻ ማሳ ላይ ነው፤ የሚሉት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆኑት ግለሰቦች በበኩላቸው “ታቦቱ እኛ ማሳ ጋር ሲደርስ አልሄድም ማለቱ እግዚአብሔር ስለወደደን ነው፡፡ ይህ ታቦቱ ያረፈበት መሬት የበረከት መሬት ነው” ሲሉ ታቦቱ የተገኘበትን ቦታ ከልለው ለቤተ ክርስቲያን መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ታቦተ ሚካኤል ድንቅ የሆነ ሥራውን በዐደባባይ ሠርቶ በሆታና በዝማሬ ግንቦት 3 ቀን 2005 ዓ.ም ወደ መንበረ ክብሩ መመለሱን ቄስ ጋሸነው እንዳላማው አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘም ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ብዙዓለም በወረዳቸው ስለተፈጸሙ የአብያተ ክርስቲያናት ዘረፋ እንዳስታወቁት “ከሰኔ 2004 ዓ.ም እስከ ግንቦት 2005 ዓ.ም በወረዳው ካሉ ዐሥራ አንድ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በፎቃ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ በእንባቦ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን፣ ሎያ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እና በሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ላይ ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ ዘረፋና የዘረፋ ሙከራ ተካሂዶባቸዋል፡፡ እንዲሁም ብራና መጽሐፍት፤ መስቀሎች፤ መጋረጃዎችና መጎናጸፍያ እንዲሁም ሙዳየ ምጽዋቶች መወሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የፎቃ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት ቄስ ዘላለም ጌትነት በበኩላቸው በፎቃ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ የሆነ የዘረፋ ሙከራ እየተደረገ በመሆኑ ለአገልግሎት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
የፎቃ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ዘበኛ አቶ አሰፋ ትእዛዙ ከዘራፊዎቹ ስለገጠማቸው ጥቃት ሲናገሩ “ዓምና በግንቦት ወር ላይ ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ ሦስት ሌቦች መጥተው የቤተ ክርስቲያኑን በር ነኩ፡፡ በራፉ ላይ ያስቀመጥኩት ቆርቆሮ መሳይ ነገር ወደ መሬት በመውደቅ ድምፅ አሰማኝ፡፡ እኔም በፍጥነት በመነሣት ባትሪ ሳበራ ሌቦቹ ጨለማውን ተገን አድርገው ወደ እኔ መጡ፡፡ በገጀራ ሊመቱኝም ሞከሩ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጥበቃ በትራቸውን ዛፉ ከለከለው፡፡ በመጨረሻም እግሬን በአንካሴ ወጉኝ፡፡” ብለው ዘራፊዎቹ የተደራጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይም በወረዳው ካሉ አብያተ ክርስቲያናት የዘረፋ ጥቃት ከደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ የእንባቦ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አንዱ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ዘላለም ኩምሳ ናቸው፡፡
አቶ ዘላለም የእንባቦ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የታነጸና ረዥም ዕድሜ ያለው በመሆኑ ዘራፊዎችም ከፍተኛ ትኩረት ያደርጉበታል፡፡ ለዚህም ለሦስት ጊዜያት ያህል ሌቦች የዘረፋ ሙከራ እንዳካሄዱበትና የቤተ ክርስቲያኑን ቁልፍና ካዝና በመስበር መጋረጃዎች እንደተወሰዱ ተናግረዋል፡፡
በጥርጣሬ የተያዙ አካላትና መዝረፋቸውን ያመኑ ሰዎች አሉ የሚሉት ደግሞ የወረዳው የፖሊስ ናቸው፡፡ ቢሮው ማንኛውንም ችግሮች ለማስወገድ ቀን ከሌሊት እንደሚሠራና በየቀበሌው ፖሊስ በማስቀመጥ፣ ለሕዝቡ ስለ ሌብነት በማስተማር፣ ለጥበቃ አካላት ሥልጠና በመሥጠት እንደ ሀገር ይሠራል፡፡” ብለዋል፡፡
አያይዘውም “በጥርጣሬ የተያዙ ሌቦችንም ማስረጃ አቅርበን ተገቢውን ፍርድ እንደሚያገኙ እናምናለን ሕዝቡም ሊተባበር ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የሀባቦ ጉዱሩ ወረዳ ቤተ ክህነት የሚገኘው ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ በቀድሞው ወለጋ ሀገረ ስብከት በአሁኑ ደግሞ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት ተብሎ በሚጠራው ሥር ሲሆን በወረዳ ቤተ ክህነቱ ሥር አሥራ አንድ አብያተ ክርስቲያናት መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡