የቅዱሳን አማላጅነት
ክፍል አራት
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ኅዳር ፳፮፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? እንኳን ለጾመ ነቢያት (ለገና ጾም) አደረሳችሁ! ጾመ ነቢያት አባቶቻችን ነቢያት አምላካችን ተወልዶ ያድነን ዘንድ የጾሙት ጾም ነው፤ እኛ ደግሞ ከሰማያት ወርዶ፣ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ አድኖናል ስንል ውለታውንና ፍቅሩን እያሰብን እንጾማለን!
በዘመናዊ ትምህርታችሁ የዓመቱን አንድ አራተኛ (ሩቡን የትምህርት ዘመን) ጨረሳችሁ አይደል! መቼም ከነበራችሁ ዕውቀት እንደጨመራችሁ ተስፋ እናደርጋለን! በርትታችሁ ተማሩ እሺ! መልካም!
ባለፈው ተከታታይ ትምህርታችን ስለ አማላጅነት ምንነት፣ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ስለ ቅዱሳን መላእክት አማላጅነት በተወሰነ መልኩ ተምረን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ስለ ቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችንን አማላጅነት እንማራለን! ተከታተሉን!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የቅዱሳን አማላጅነት ያስፈለገበት ምክንያት እግዚአብሔር ከኃጥአን-ጸሎት ይልቅ የወዳጆቹ የቅዱሳንን ጸሎት ስለሚቀበል፣ ጸሎታችን በፍጥነት ወደ እግዚአብሔር እንዲደርስልንና ፈጣሪያችንም ስለ እነርሱ ሲል ቸርነቱን ስለሚያደርግልን ነው፡፡
መጽሐፈ ሄኖክ በተባለ መጽሐፍ ላይ ‹‹በሰማይ የሚኖሩ ጻድቃን በአንድ ቃል ሆነው ተባብረው ያመሰግናሉ፡፡ ለሰውም ፈጽመው ይለምናሉ›› ተብሎ እንደተጻፈ ቅዱሳን በተሰጣቸው ቃል ኪዳን እኛን ያማልዳሉ፤ (ሄኖክ ፲፪፥፴፬) ስለ እኛ ይጸልያሉ፤ በቅዱስ መጽሐፍ ሰዎችን ከእግዚአብሔር አማልደው ያስታረቁ፣ ምሕረትን ያሰጡ ብዙ ናቸው፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር የቅዱሳንን ጸሎት እንደሚሰማና ምልጃቸውም ግዳጅ ፈጻሚ መሆኑ በሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ ተገልጿል፡፡ አባታችን አብርሃም ከሚስቱ ከሣራ ጋር ጌራራ ወደሚባል አገር በሄደ ጊዜ አቤሜሌክ የተባለ ንጉሥ ሣራን ለራሱ ሚስት ሊያደርጋት ወሰዳት፤ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር በሕልሙ እንዲህ አለው፤ ‹‹…የሰውየውን ሚስት መልስ፣ ነቢይ ነውና ስለ አንተም ይጸልያል ትድናለህም…፤›› (ኦሪት ዘፍጥረት ፳፥፯)
አያችሁ ልጆች! አባታችን አብርሃም ስለ አቤሜለክ እንዲጸልይለት እግዚአብሔር ነገረው፤ ምክንያቱም አብርሃም ጻድቅና ነቢይ ነው፤ አብርሃም አቤሜሌክ ላይ ከሚመጣበት ቅጣት እንዲድን፣ እንዲጸልይለትና እንዲያማልደው ተነገረው፡፡
ቅዱሳን በጸሎታቸው እኛን ከእግዚአብሔር አማልደው ከሚመጣብን መከራ እንድንድን ይረዱናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹…የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮችም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና…›› በማለት ገልጾልናል፡፡ (መዝ.፴፫፥፲፭)
ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ስለ ቅዱሳን አማላጅነት ሌላ ታሪክ ደግሞ እንመልከት፤ በአንድ ወቅት ሕዝበ እስራኤል የፈጠራቸው እግዚአብሔር እየመገባቸውና ድንቅ ተአምራት እያደረገላቸው እነርሱ ግን ጣኦትን አመለኩ፤ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ተነሣሣ፤ ‹‹… እግዚአብሔርም ሙሴን እኔ ይህን ሕዝብ አየሁት፤ እነሆም አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው፡፡ አሁንም ቁጣዬ እንዲቃጠልባቸውና እንዳጠፋቸውም ተወኝ፤ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ›› አለው፡፡
ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፤ ‹‹…ዘራችሁን እንደ ሰማይ ክዋክብት አበዛለሁ፤ ይህችንም የተናገርኳትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለው፤ ለዘለዓምም ይወርሷታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን፣ እስራኤልንም አስብ፤ እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ…›› (ኦሪት ዘጸአት ፴፪፥፯-፲፬) ስለ ባለ ሟሉ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ስላማለደላቸው ሕዝቡ ከጥፋት ዳኑ፡፡
የጻድቁ ኢዮብ ባልንጀሮች በበደሉ ጊዜ ከሚመጣባቸው ቁጣ እንዲድኑ፣ ጻድቁ ኢዮብም ስለ እነርሱ እንዲጸልይ፣ ከእነርሱ ጸሎት ይልቅ የጻዲቁ ኢዮብ ጸሎት በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው እንዲህ ተነገራቸው፤ ‹‹…ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፤ እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለው …›› (መጽሐፈ ኢዮብ ፵፪፥፰)፤ የቅዱሳን ልመና እንደ እርሱ ፈቃድ ስለሆነ የሚለምኑትን ሁሉ ይሰማቸዋል፡፡ ‹‹በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል፡፡›› (፩ኛ ዮሐ.፭፥፲፬-፲፭) የጻድቃን ምኞት በጎ ብቻ ነውና፡፡ (ምሳ.፲፩፥፳፫)
የቅዱሳን አማላጅነትን በሁለት ከፍለን እናየዋለን፡-
በዐጸደሥጋ፡- ቅዱሳን በሕይወተ ሥጋ ሳሉ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ሲል ምሕረትና ይቅርታን ያደርጋል፡፡ ከላይ ካየናቸው ታሪኮች በተጨማሪ እንመልከት፤ ቅድስት ሥላሴ በአብርሃም ቤት ከተስተናገዱ በኋላ ሰዶም በኃጢአቷ ምክንያት ልትጠፋ እንደሆነ ለአብርሃም ሲነግሩት ለከተማይቱ ምሕረትን ለመነ፤ ቅድስት ሥላሴም ምልጃውን ተቀብሉት፡፡ ነገር ግን በከተማይቱ ዐሥር ጻድቃን እንኳን በመጥፋታቸው ምክንያት ልትጠፋ ቻለች፡፡ (ዘፍ.፲፰፥፲፮-፴፫)
ቅዱስ እስጢፋኖስ ለወገሩት ሰዎች ምሕረት ለመነላቸው፡፡ ‹‹…ተንበርክኮም ጌታ ሆይ ይህንን ኃጢአት አትቁጠርባቸው›› ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ይህንንም ብሎ አንቀላፋ፤ ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር፡፡ (የሐዋ.ሥራ ፯፥፷)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቅዱስ እስጢፋኖስ መወገር ተስማምተው ከነበሩት አንዱ ሳውል የተባለው በንስሐ ተመልሶ ክርስቲያን ሆኖ፣ ስለ ክርስቶስ መስክሮ .ብዙ ምእመናንን በማስተማር ወደ ክርስትና የመለሰ. ብርሃነ ዓለም የተባለው ቅዱስ ጳውሎስ ነው፤ አያችሁ ልጆች! የቅዱስ እስጢፋኖስን የይቅርታ ጸሎትና ምልጃ እግዚአብሔር ተቀብሎ ሳውልን ወደ ሕይወት (ወደ ክርስትና ) አመጣው፤ አገልጋዩም አደረገው፡፡
በዐጸደ ነፍስ፡- እግዚአብሔር በዐጸደ ሥጋ ሳሉ ለቅዱሳን የሰጣቸውን የማማለድ ጸጋና ሥልጣን ከዕረፍታቸው በኋላ በዐጸደ ነፍስ አይነሣቸውም፡፡ (ሉቃ.፲፮፥፲፱) በዚህ ዓለም ባለ ጸጋ የነበረው ነዌ በደጁ ወድቆ ሳይንከባከበው የነበረውን አልዓዛርን ሁለቱም በሞቱ ጊዜ በአብርሃም ዕቅፍ ነዌ የተባለው ሰው ዓልአዛርን አየው፡፡ ይህ ባለጸጋ የውኃ ጥም ጸንቶበት ስለ ነበር አልዓዛርን ‹‹እባክህ ውኃ›› ብሎ እንዳይለምነው በምድር ሳለ የፈጸመውን ግፍ ያውቃልና ስላሳፈረው አብርሃምን ለመነ፡፡ አብርሃምም እርሱ በሕይወተ ሥጋ ሳለ በሠራው ክፋት ምክንያት ይህ ቅጣት እንዳገኘው፣ አልዓዛርም በምድር ስለ ሠራው መልካም ሥራ ከቅጣት መትረፉን አስረዳው፡፡ ይህ ባለጸጋም አብርሃምን ‹‹እባክህ በምድር አምስት ወንድሞች አሉኝ›› ብሎ ማለደላቸው፡፡ ከዚህ ታሪክ እንደምንረዳው ኃጥአን በዐጸደ ነፍስ ሳሉ በምድር ላሉ ወገኖቻቸው የሚጸልዩ ከሆነ ወዳጆቹ ቅዱሳንማ ምንኛ ይጸልዩልን ይሆን?
ቅዱሳን ከዕረፍታቸው በኋላ በዐጸደ ነፍስ በዚህ ዓለም ያደርጉት እንደ ነበረው በጾምና በስግደት እንዲሁም ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራ መቀበል የለባቸውም፡፡ ነገር ግን በዚህ ዓለም ሳሉ የሠሩትን ትሩፋትና የተቀበሉትን ቃል ኪዳን እያሳሰቡ በጸሎታቸው የሚታመኑትንና ስማቸውን የሚጠሩትን ሰዎች ሲረዱና ለክብር ሲያበቁ ይኖራሉ፡፡ ይህ ግን የሚደረግላቸው አስቀድሞ በዚህ ምድር ሳሉ በሠሩት ሥራ ነው፡፡ ሥራቸው ይከተላቸዋልና፡፡ (ራእይ ፲፬፥፲፫)
‹‹ከዚያም ቦታ ዓይኖቼ ከመላእክት ጋር የሚኖሩበት ማደሪያቸውን ከቅዱሳንም ጋር የሚኖሩበት ቦታቸውን አየሁ፡፡ ስለ ሰው ልጆችም ፈጽመው ይለምናሉ፡፡›› (ሄኖክ ፱፥፳፪-፳፫)
‹‹በሰማይ የሚኖሩ ጻድቃን በአንድ ቃል ሆነው ተባብረው (በዚህ በምድር ሳሉ) ያመሰግናሉ፡፡ ለሰውም ፈጽመው ይለምናሉ፡፡›› (ሄኖክ ፲፪፥፴፬) ቅዱሳን በአካለ ሥጋ ሆነው ምሥጢራዊ የሆኑ ነገሮችን ማንም ሳይነግራቸው የሚያውቁ ከሆነ በአካለ ነፍስ ሲሆኑ የበለጠ እንደሚያውቁ ሐዋርያት መስክረዋል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጥልቅና ሰፊ ከሆነው የአማላጅነትን ትምህርት ለግንዛቤ እንዲሆናችሁ በጥቂቱ ተመለከትን፤ አስተማሪዎቻችንን በመጠየቅ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ የበለጠውን ግንዛቤ እንድትይዙ ልናሳስባችሁ እንወዳለን፤ ቅዱሳን በተሰጣቸው ጸጋ፣ ቃል ኪዳናቸውን አምኖ በስማቸው ለሚማጸን፣ በስማቸው ለሚዘክር፣ መታሰቢያቸውን ለሚያከብር ከእግዚአብሔር ያማልዱታል!
ኃጢአት ሠርቶ ከእግዚአብሔር በተጣላ ጊዜ ተጸጽቶ፣ ይቅርታን ፈልጎ ሲመጣ፣ በቅዱሳን ቃል ኪዳን ሲማጸን፣ ስለ ቅዱሳን ሲል እግዚአብሔር ምሕረት አድርጎለት ይታረቀዋል፡፡ ‹‹…በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን፣ እስራኤልንም አስብ …›› (ኦሪ. ዘጸ. ፴፪፥፲፫)
ልጆች! ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በርትታችሁ ተማሩ! ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡
ይቆየን! ቸር ይግጠመን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!