የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት

ክፍል ሦስት
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ኅዳር ፲፫፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለከበረው ጤንነታችሁ እንዴት አላችሁልን?! በፈቃደ እግዚአብሔር አዲሱን ዓመት ከተቀበልን ሁለት ወራትን አሳልፈን ሦስተኛውን ጀምረናል! ለዚህ ያደረሰን አምላክ ይመስገን! ለመሆኑ ትናንት ከነበረው ማንነታችሁ ላይ ምን ለውጥ አመጣችሁ? በዘመናዊ ትምህርትስ ምን ያህል ዕውቀትን ሸመታችሁ? በመንፈሳዊ ሕይወታችሁስ በሥነ ምግባር ምን ያህል ለውጥ አመጠችሁ?

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በርትታችሁ መማር ይገባል፤ ባለፈው ተከታታይ ትምህርታችን ስለ አማላጅነት ትርጉም እንዲሁም ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ተምረን ነበር፡፡ በዚህ የትምህርት ክፍለ ጊዜያችን ደግሞ ስለ ቅዱሳን መላእክት አማላጅነት እንማራለን! መልካም!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ስለ ቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ለአብነት እንመልከት! ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔር በዕለተ እሑድ የፈጠራቸው ናቸው፤ ዘወትር እግዚአብሔርን ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ ያመሰግናሉ፡፡ ከእግዚአብሔር ተልከው የሰው ልጆችን ይራዳሉ፤ ከክፉ ነገር ይጠብቃሉ፡፡ እግዚአብሔር በሰጣቸው የማማለድ ጸጋ እኛ በስማቸው ስንማጸን ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቁናል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ከተጻፉልን የተወሰነውን ለማስረጃት እንመልከት፤ ኢየሩሳሌምና የይሁዳ ከተሞች በጠላት ተማርከው በነበሩበት ጊዜ ከነበረባቸው መከራ እግዚአብሔር ይታደጋቸው ዘንድ የእግዚአብሔር መልአክ ስለ ሰዎች መዳን ምሕረትንና ይቅርታን ለማሰጠት የእግዚአብሔር መልአክ እንዲህ ሲማጸን እንመለከታልን፤ ‹‹…የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ “አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቆጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? …›› (ዘካ. ፩፥፲፪)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! መልአኩ ‹‹አቤቱ …›› እያለ ሲማጸን (ሲለምን) እግዚአብሔር ደግሞ የመልአኩን አማላጅነት (አሳታራቂነት) ተቀብሎ እንዲህ በማለት መለሰለት፤ ‹‹…ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ፡፡ …›› (ዘካ. ፩፥፲፮) ቅዱሳን መላእክት የሰዎችን ልመና ወደ እግዚአብሔር ያቀርባሉ፤ የእግዚአብሔርን ምሕረት ለሰዎች ያሰጣሉ፤ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን፣ የሚፈሩትን፣ ሕጉን ጠብቀው በሥርዓት የሚኖሩትን በመከራቸው ጊዜ ይጠብቋቸዋል፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ በማለት ይመሰክርልናል፤ ‹‹…በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና እግርህም በድንጋይ እንዳይሰናከል በእጃቸው ያነሣሃል…፡፡›› (መዝ.፺፥፲፩)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ስለ ቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ከሚያስረዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መካከል አንዱ የነቢዩ ዳንኤል የትንቢት መጽሐፍ ነው። እንዲህ የሚልም ኃይለ ቃል በመጽሐፉ ውስጥ ተጽፎ እናገኛለን፤ ስለ ዓለም ፍጻሜ መቃረቢያ በተናገረበት ትንቢቱ በእግዚአብሔር የሚያምኑ እንዳይሰናሉ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በአማላጅነቱ እንደሚጠብቃቸው እንዲህ ገልጾናል፤ ‹‹በዚያን ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል…፡፡›› (ዳን.፲፪፥፩)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ምሳሌ መስሎ እንዲህ አስተምሮናል፤ ‹‹…ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፤ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም፤ የወይን አትክልት ሠራተኛውንም እነሆ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቁረጣት፤ ስለምን ደግሞ መሬቱን ታጎሳቁላለች?” አለው፡፡ እርሱ ግን መልሶ “ጌታ ሆይ ዙሪያዋን እስክኮተኩትላትና ፋንድያ (ማዳበሪያ) እስካፈስላት ድረስ በዚህች ዓመት ደግሞ ተዋት፡፡ ወደ ፊትም ብታፈራ ደኅና ነው፤ ያለበለዚያ ግን ትቆርጣታለህ” አለው፡፡›› (ሉቃ.፲፫፥፮-፱)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን በምሳሌ ያስተማረውን ትምህርት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምሥጢሩን የገለጠላቸው አበው መተርጉማን ይህን ኃይለ ቃል እንዲህ አመስጥረው ያብራራሉ፤ የወይኑ ጌታ የተባለ እግዚአብሔር ነው፤ ፍሬ የታጣባቸው የወይን አትክልት የተባሉ እስራኤላውያን ናቸው፤ የወይን አትክልት ሠራተኛ የተባለ መጋቤ ብሉይ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነው፤ ሦስት ዓመት የተባለ ደግሞ በብሉይ ኪዳን የነበረው ዘመነ መሳፍንት፣ ዘመነ ነገሥት፣ ዘመነ ካህናት ተብለው የሚታወቁ ዘመናት ናቸው፡፡ በእነዚህ ዘመናት መምህራንን ልኮ ቢያስተምራቸውም እነርሱ ግን (ቤተ እስራኤል) ምንም በጎ ፍሬ ታጣባቸው፤ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር ሊቀጣቸው ባለ ጊዜ በወይን አትክልተኛ ሠራተኛ የተመሰለው መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤል ስለ ሕዝቡ ምሕረትን ከእግዚአብሔር ጠይቆ አማልዶ ምሕረትን አሰጣቸው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላው ምሥጢር ደግሞ ሦስት ዓመት የተባለ በአዲስ ኪዳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ተመላልሶ ያስተማረበት ነው፤ የወይን አትክልት እስራኤላውያን (በወቅቱ የነበሩ) አላመኑበትም፤ ምግባር አልነበራቸውም፤ የሃይማኖትና የምግባር ፍሬ ፈልጎ አጣባቸው፤ በዚህን ጊዜ እንዲቆረጡ ትእዛዝ ሲተላለፍ በወይን አትክልት ሠራተኛ የተመሰለው መጋቤ ሐዲስ ቅዱስ ገብርኤል ምሕረትን ለመነ፤ ‹‹የዘንድሮን ተዋቸው›› ብሎ ተማጽኖ ለንስሐ ጊዜን ለመነላቸው፤ ጌታችንም የቅዱስ ገብርኤልን ልመና (አማላጅነት) ተቀብሎ ሕዝቡን ማረ፤ ለንስሐ ዕድሜ ሰጣቸው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እግዚአብሔር ስለ ቅዱሳን መላእክት ልመናና ጸሎት ብሎ አማላጅነታቸውን ተቀብሎ ምሕረትን ይሰጣል፡፡ ‹‹…ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሠዊያ ላይ ለቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው፤ የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ…፡፡›› (ራእ ፰፥፫)

በቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ታምነን፣ ስማቸውን ጠርተን በረከታቸውን እንቀበል፡፡ ከቅዱሳን መላእክት ረድኤት በረከታቸውን ይክፈለን! ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ! ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ! በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ቸር ይግጠመን!

ይቆየን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!