የስሜት ሕዋሳቶቻችንና ክርስትና

መምህር ቢትወደድ ወርቁ
ሐምሌ ፲፩፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ሰው በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ውስጥ ሲገኝ የሚሰማውን ስሜት በስሜት ሕዋሳቱ አማካኝነት ይገልጣቸዋል፡፡ ደስታ፣ ቁጣ፣ ፍርሃት፣ ሕመም፣ ፍቅር እና የመሳሰሉት ስሜቶቻችን ናቸው፡፡ ሰው እነዚህን ስሜቶቹን በስሜት ሕዋሳቱ በዐይኑ፣ በእጁ፣ በእግሩ፣ በአንደበቱ፣ በፊት ገጽታውና በሰውነት እንቅስቃሴው ይገልጣል፡፡ እነዚህ ስሜቶች ከሚቀሰቀሱበት ሁነቶች፣ ድርጊቶችና ክስተቶች አንጻር በፍጥነት ምላሽ ሳይሰጥ ነገሮችን በዕርጋታ የሚመረምር ሰው በሳል ወይም ባለ አእምሮ ይባላል፡፡ በተቃራኒው ለጉዳዮች ፈጣን ምላሽ የሚሰጠውን ደግሞ ስሜታዊ እንለዋለን፡፡ ባለ አእምሮ ሰው በመረጋጋቱ ብዙ ሲያተርፍ ስሜታዊ ሰው ግን የሚያጸጽቱና ግላዊ፣ ማኅበራዊ እንዲሁም ሀገራዊ ጥፋቶችን የሚያስከትሉ ዋጋዎችን ይከፍላል፡፡ በመሆኑም መጽሐፍ “እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ” በማለት ያስተምረናል፡፡ (፩ኛጴጥ.፬፥፯-፰)

በስሜት ሕዋሳቶቻችን ለምንገልጣቸው ድርጊቶቻችንና ምላሾቻችን ጥንቃቄ እንድናደርግ ቅዱሳት መጻሕፍት በእጅጉ ያስጠነቅቁናል፡፡ ለምሳሌም ጠቢቡ ሰሎሞን “በዓይኑ የሚጠቅስ መከራን ያመጣል”፤ “ከንፈሩን የሚነክስ ክፋትን ይፈጽማል” በማለት አከታትሎ የተናገራቸው ቃላት ይህንኑ ያስተምሩናል፡፡ (ምሳ.፲፥፲፣ ምሳ.፲፮፥፴) ዓይን የስሜት ሕዋስ ሲሆን ጥቅሻ ደግሞ ለአንድ ድርጊት የምንሰጠው ምላሽ ነው፡፡ ከንፈርን መንከስ የብስጭት፣ የቁጣና በአንድ ጉዳይ የመብገን ምልክት ነው፡፡ ከንፈሩን የነከሰ ሰው ፈጥኖ ወደ ሕሊናው ካልተመለስ ቀጣይ እርምጃው ከንፈሩን የነከሰበትን ሰው መንከስ፣ ማጥቃት ወይም ደግሞ አንዳች ክፉ ነገር ማድረግ ይሆናል፡፡

ስሜት በሚወልደው በአንድ ድርጊት ምክንያት የሚሰጥ ምላሽ ጥንቃቄ ካልታከለበት መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ስለሆነም በደስታ ጊዜ ፈጥኖ ቃል መግባት፣ በቁጣ ጊዜ ፈጥኖ የቃልና የተግባር ምላሽ መስጠት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ከደስታ ስሜት ስንወጣ “እንዲህ ያልኩት ምን ነክቶኝ ነው?” ብለን በማሰብ እንድንሸማቀቅና ቃል ለገባንላትም አካል “አላልኩም” ብለን ልቡን እንሰብራለን፡፡ የስሜት ምላሻችን ማኅበራዊ ኑሯአችንን ከማበላሸቱም ባሻገር ለከኑኔ ያደርሳል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው፡፡ ከልብ ክፉ አሳብ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በውሸት መመስከር፣ ስድብ ነው” ብሎ የተናገረውን ቃለ ትምህርት እናስተውል፡፡ (ማቴ.፲፭፥፲፰)

ከአፍ የምናወጣው ስድብ የስሜታዊነት ምላሽ ነው፤ መግደልም ሰዎች ለፈጸሙብን ድርጊት የምንሰጠው የድርጊት ምላሽ ነው፡፡ ማመንዘርም ለተሰማን የዝሙት ስሜት የምንሰጠው ምላሽ መሆኑን ልብ እንበል፡፡ ለምሳሌም የዳዊት ልጅ አምኖን የገዛ እኅቱ ትእማር ስትገባ ጡቷን፣ ደረቷን ስትወጣ ባቷን ተረከዟን እየተመለከት በሐጸ ዝሙት ተነደፈ፡፡ ከስሜት ሕዋሳቱ በአንዱ በዐይኑ አማካኝነት ወደ ዝሙት ስሜት ገባ፡፡ ከዚያም አልፎ ሰውነቱ ከሳ፤ ጓደኛው ኢዮናዳብ በመከረው ክፉ ምክርም ተመርቶ እኅቱን አስነወራት፡፡ በስሜቱ የጋለበበት የዝሙት ጎዳናም በመጨረሻ ወንድሙ አቤሴሎም በክፋት እንዲነሣበትና ሕይወቱን እንዲነጥቀው ሆኗል፡፡ (፪ኛሳሙ.፲፫፥፩-፴፱)

መስረቅም የስሜት ምላሽ ነው፡፡ አንድ የተራበን ሰው የሻትከውን በእጅህ ለማስገባት ምን ታደርጋለህ? ምግብ ይሰጡህ ዘንድ ትጠይቃለህ? የሻትከውን የራስህ ለማድረግ ጊዜ ትጠብቃለህ? ወይስ ትሰርቃለህ? ብለን ብንጠይቅ፡-
ዛሬ በተግባር እንደሚታየው የብዙ ሰው ምላሽ ማታለል፣ መስረቅ፣ የጥቂት ሰው ምላሽ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ ስርቆት የስሜት ምላሽ መሆኑን እናስተውል፡፡ ክርስትና ለስሜት ፈጥነን ምላሽ ከመስጠት እንድንቆጠብ ያስተምረናል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምእመናን ያስተማረውን ትምህርት ማንሣቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ሐዋርያው “ነገር ግን እላለሁ÷ በመንፈስ ተመላለሱ፤ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ፡፡ ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፤ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ ከቶ አትችሉም” ይልና አያይዞም የሥጋ ፈቃዳትን (ሥጋዊ ስሜቶችን) ገልጦ “አስቀድሜም እንዳልሁ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” ይላል፡፡ (ገላ. ፭፥፲፯-፳፩)

የሥጋ ምኞት የሥጋ ስሜት ነው፡፡ ዝሙት፣ ቅንአት፣ ምቀኝነት ስሜቶች ሲሆኑ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለያየት፣ መግደል ደግሞ የስሜት ምላሾች ናቸው፡፡ ስሜቶቹም ሆኑ ምላሾቻቸው ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጭ እንደሚያደርጉ ተመልከቱ፡፡ ለስሜቶች ፈጥኖ ምላሽ ላለመስጠት መድኃኒቱ ራስን መግዛት ነው፡፡ ራስን መግዛት ማለት ስሜቶችን መቆጣጠር ማለት ነው፡፡ ስሜትን የመቆጣጠር ዓቅማችን የሚለካው ደግሞ ስሜቶቻችንን የሚቀሰቅሱና አሉታዊ ምላሾችን እንድንሰጥ የሚያስገድዱ ነገሮች ሲፈጠሩ ነው፡፡ ጀግና የሚወለደው በጦርነት ሜዳ ላይ እንደሆነ ሁሉ፣ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆነው ራስን መግዛት ገንዘብ ያደረገ ሰውም የሚገለጠው እንደ ጦር የሚወጉ ክፉ ስሜቶች በሚሰሙት ጊዜ በሚያሳየው በጎና መንፈሳዊ ምላሽ ነው፡፡

ሰው ቅድሚያ ራሱን ካልተቆጣጠረና ስሜታዊነትን ካላስወገደ ተቋማትንም፣ ሀገርንም መምራት አይችልም፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል፤ በመንፈሱም ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስድ ይበልጣል” ይላል፡፡ (ምሳ.፲፮፥፴፪) ትዕግሥት ለቁጣና ለችኩልነት ስሜቶች የሚሰጥ በጎ ምላሽ ነው፡፡ በግል ኑሮው ለሚገጥመው ክፉ ስሜት ቀስቃሽ ጉዳዮች ትዕግሥትን የሚያሳይ ሰው በጦር ሜዳ በጀግንነቱ ከሚታወቅ ሰው ይበልጣል፡፡ በመንፈሱ ማለትም በሐሳቡና በስሜቱም ላይ የበላይ ሆኖ ሐሳቡንም ስሜቱንም ምኞቱንም የሚቆጣጠር ሰውም ከተማን ከሚገዛ ሀገረ ገዥ ይበልጣል ይለናል ጠቢቡ ሰሎሞን፡፡

ራስን መግዛት አንድ ስሜታችንን ለሚቀሰቅስ ሁነት ዐራት ዐይና ሆኖ በመገኘት ጉዳዮችን ከራስ፣ ከሌሎች፣ ከመንፈሳዊና ከሞራል ሕግጋት፣ ከማኅበረሰብ ባሕል ወግና ሥርዓት አንጻር መመልከት ነው፡፡ ራስን መግዛት ድርጊቶቻችን ምን አሉታዊና አዎንታዊ ምላሽ ይዘው ይመጣሉ? ብሎ መተንተን መቻል ነው፡፡ ሀገር የሚታወከው፣ ሐመረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በማዕበላት ፈተና የምትናጠው፣ ቤተ ሰብ የሚበተነው፣ ትዳር የሚፈርሰው ስሜታቸውን ብቻ እየተከተሉ በሚጓዙ ሰዎች ነው፡፡ የስሜት መንተክተክ ያበላሸውን ትዳር፣ ፖለቲካ፣ ሥርዓተ ማኅበረሰብ፣ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያነጻ ግላዊና ማኅበረሰባዊ ስክነት ጠፍቷል ብለን መናገር እውነት እንጂ ሐሰት ወይም ግነት አይደለም፡፡
የአምላካችን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም

አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን!!!