የሰው ተፈጥሮና ሥርዓተ ጾታ

ክፍል ሁለት
ዲያቆን ዘሚካኤል ቸርነት
ታኅሣሥ ፲፰፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም

የሰው ዘርና መሠረት የሆኑት አዳምና ሔዋን ስያሜያቸው በጾታ ተለይቶ በማይታይበት ሁኔታ (በጋራ ስያሜአቸው) ‹‹ሰው›› የሚሰኙ ሲሆን ‹‹አዳም›› በመባል የሚታወቀው ቀዳሚ ፍጥረትም ከወንድ ጾታ በተጨማሪ የሰው ዘር ሁሉ ምንጭና መጠረያ ሆኖም አገልግሏል፡፡

በአጠቃላይ ‹‹ተባዕታይ/ዊ/››- “ወንዳዊ፣ ወንድ፣ ወንዳማ፣ ወንዳ ወንድ፣ ብርቱም” ማለት ሲሆን ‹‹አንስታይ/ዊ/››- “ሴታም፣ ሴትማ፣ ሴት፣ ባለ ሴትም” የሚለውን ያመለክታል፡፡ አንስትና ብእሲት ለሰው ብቻ ይነገራል፡፡ (ዘፍ.፩፥፳፯)

ጾታቸውና ግብራቸው በአንድነት ሲገለጽ ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ስያሜዎች የሚከተሉትን ትርጉሞች ይይዛሉ፡-

አዳም ማለት “የሚያምር፣ ደስ የሚያሰኝ ሰው፣ ደግ፣ መልከ መልካም፣ የመጀመሪያ ሰው፣ የሰው ሁሉ አባት” የሚል ትርጒም ተሰጥቶታል፡፡

ሔዋን ማለት “ሕይወት” ማለት ነው፡፡ “ሔዋን” ብሎ የሰየማትም አዳም ሲሆን ስያሜው ‹‹የሕያዋን ሁሉ እናት /እመ ሕያዋን/›› መሆኗን ያመለክታል፡፡ (ዘፍ.፪፥፬-፳፬) ከዚህም ሌላ ረዳት ትባላለች፡፡

በሰው ልጅ የውድቀት ታሪክ ውስጥ ሔዋን የመጀመሪያዋ ስሕተተኛ ብትሆንም የድኅነት ተስፋም የተገኘው በእርሷ በኩል ነው፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነው ከአዳምና ከሔዋን ዘር ከሆነችው ከእመቤታችን ነውና፡፡ (ዘፍ.፫፥፲፭) ይሁንና ሃይማኖትን ከልማድ መለየት የተሣነው፣ የአዲሱ ዓለም አስተሳሰብ አራማጅ ትውልድ፣ ለጾታ ልዩነት፣ በተለይም ለሴት የመብት፣ የነጻነትና የእኩልነት መጓደል ተጠያቂ ሃይማኖት እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብ ይሞክራል፤ ሃይማኖት- ሴትን ከሰብአዊነት በታች አድርጎ ይመለከታል፤ የሴትን ሰብአዊ ክብር ይቀንሳል እያለ መክሰሱንና ለሴት ልጅ ብቸኛ አሳቢ፣ ጠበቃና የአዲስ ፍልስፍና ግኝት ባለ ቤት አድርጎ ማወጀና ራሱን መስበክ ከጀመረ ውሎ አድሯል፤ አባባሉ እውነት በጎደለው አመለካከት ላይ የተመሠረተ ባይሆን ኑሮ ወርቃማ አባባል ተብሎ መመዝገብ በቻለ ነበር፡፡ ችግሩ ግን የዚህ ባህል ባለ ቤቶች ዋና ችግር ከሃይማኖት ጽንስ ሐሳብና መሠረታዊ መርሕ ጋር ምንም የማይተዋወቁ የመሆናቸው ጉዳይ ነው:: በሌላም በኩል ለሰው ልጅ መብት ተሟጋቾች መስለው ሲታዩ ራሱን መከላከል በማይችል ሰብአዊ ፍጡር ላይ የሞት ፍርድ ይፈርዳሉ፤ ዓለምን እኛ ብቻ እንኑርባት በሚል ምኞታቸው በማኀፀን ያለውን ፍጡር ከማኅፀን ወጥቶ በምድር ላይ የመኖር መብቱን ያሳጡታል፤ የግላቸውን ዓላማ ለማስፈጸም ብቻ ሃይማኖትን ሲከሱ፣ ሲወቅሱ፣ የግል ስሜታቸውን ከማንጸባረቅ አልፈው ሃይማኖትን ዋቢ አድርገው ለመክሰስ ሲሞክሩ የሚያቀርቡት ተጨባጭ መረጃ ግን ፈጽሞ አይኖራቸውም፤ እውነቱና የእነርሱ ፈሊጥ ፈጽሞ የተለያየ ነው፤ እነዚህ ወገኖች ለምን በሃይማኖት ላይ መዝመትን መረጡ ቢባል ግን የሚከተሉትን ነጥቦችን በምላሌነት ማየት ይችላል፡፡

፩. ሰው፦ በእንስሳዊ ባሕርዩ ልጓም በሌለበት የፍትወት ሜዳ ሽምጥ መጋለብን ይፈልጋል፡፡ ሃይማኖት ግን ልቅነትን ስለማይፈቅድ ሰው እንስሳዊ ልምዱን አስወግዶ ለመንፈሳዊ ሥርዓት መገዛት ያለበት መሆኑን ስለሚያውጅ ሃይማኖት የለሽ ሰው ይህን መንፈሳዊ መርሕ ባለ መቀበል /በልቅነት/ ለሚፈነጭባት ዓለም ምቹ መድረክ ለመፍጠር ይጥራል፡፡

፪. ሃይማኖት- ለሴት ልጅ መብት፣ ነጻነትና እኩልነት ተቃራኒ ነው ብሎ በማስተማርና፥ “የእኩልነት ጠበቃችሁ እኔ ነኝ” እያለ በሚሰብክላቸው ሴቶች ዘንድ እውነት መስሎ ሊታይ በሚችል ፈሊጥና አቀራረብ ተደጋጋሚ ጥረት በማድረግ በሃይማኖት ላይ ጥላቻ እንዲፈጠር ማድረግ የዘመኑ የስንፍና ብሂል ነው፡፡ (መዝ.፲፫፥፩)

፫. ይህን መሰል ፈሊጥ የሚከተሉ ግለሰቦች ከሚኖራቸው አናሳ የሃይማኖት ዕውቀት ሌላ የመጻሕፍትን ጥሬ ቃል እንዳሻቸው በመተርጐም፥ ፈጽሞ የተዛባ አመለካከታቸውን ይዘው ወደ ማኅበረሰቡ በመቅረብ ዓላማቸውን በቀላሉ በሚማረክ አእምሮ ላይ ማሥረጽ እንደ አማራጭ መንገድ ይከተላሉ፡፡ (፪ኛጴጥ.፮፥፳-፳፩)

፬. የሃይማኖትን ቀኖናዊ ሥርዓት፣ ከሕዝባዊ ልማድ ለይቶ የማየት ፍላጐት ስለሌላቸው ሩጫቸው ሁሉ የክፋት ነው፡፡

የእውነትን መንፈሳዊ መሥመር የሳተ ይህ የዘመኑ ሰው አመለካከት እየተደጋገመ ሲነገር እውነትን የሚፈታተን፥ ብዙዎቹንም የሚያደናግር የአስተሳሰብ ክፍተት ማስከተሉ አልቀረም፤ ይሁን እንጂ እውነት ሃይማኖት የጾታ አድልዎ ወይም በወንድና በሴት መካከል የጌትነትና የባርነት ዐዋጅ ያውጃልን? ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛና አጭሩ መልስ አይደለም የሚል ቢሆንም እውነቱን በትክክል ለማረጋገጥ ከምንም በላይ ቃሉ ያረጋግጣልና እውነትን ለመከተል፣ አስተዋይ ልቡና ተመራማሪ ሕሊና፣ ጽኑ ሃይማኖት፣ መልካም ሕይወት ያለው ሁሉ፣ እውነቱን መረዳት ይችል ዘንድ የሚከተሉት ጥቅሶች በአስረጅነት ቀርበውለታል፡፡

፩. “እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር፤ . . . እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረው፤ ወንድና ሴትም አድርጎ ፈጠራቸው፤ እግአብሔርም ባረካቸው፡፡” (ዘፍ.፩፥፳፮-፳፰)

፪.. “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን /አዳምን/ ከምድር አፈር አበጀው፣ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፡፡ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ፡፡” (ዘፍ.፪፥፯)

፫. . . “ነገር ግን ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር፤ እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍ ጣለበት፤ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንት ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት..፡፡” (ዘፍ.፪፥፳-፳፫)

፬. “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ /አንድ አካል/ ይሆናሉ::” (ዘፍ.፪፥፪፳፬)

፭. “ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ /ወደ ጌታ/ ቀረቡና ሊፈትኑት ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? አሉት፤ እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ፤ ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው! … ስለዚህ አንድ ሥጋ /አካል/ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም፤ እግዚአብሔር ያጣመረውን አንድ ያደረገውን እንግዲህ ሰው አይለየው፡፡” (ማቴ.፲፱፥፫-፮)

፮. “ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት እንደዚሁም ደግሞ ሚስት ለባልዋ፡ ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፡፡ ሥልጣን ለባልዋ ነው አንጂ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ፡፡” (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፱)

፯. “እያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ ሚስቶች ሆይ ለጌታ አንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፡፡ ባሎች ሆይ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን አንደወደዳት፣ ሚስቶቻችሁን ውደዱ . . አንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደገዛ ሥጋቸው አድገርው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል፤ የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፡፡ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና … ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት ሚስትም ባልዋን ትፍራ:፡ (ኤፌ.፭፥፳፩-፴፫)

፰. ”በዚህ አይሁዳዊ የለም፤ አረማዊ የለም፤ ገዢ የለም ተገዢም የለም፤ ወንድ የለም፤ ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ናችሁ እንጂ፡፡” (ገላ.፫፥፳፰)

የሰው ልጅ የእኩልነት ሁኔታ ይህን እንደሚመስል ከላይ በተጠቀሰው የእግዚአብሔር ቃል እውነቱን ካያችሁ ሌሎች በምክንያትነትና በተቃራኒ አባባል ሊጠቀሙባቸው ሲሞክሩ የምትመለከቷቸው ጥቅሶችን ደግሞ ንባባቸውንና ትክክለኛ ትርጉማቸውን አስተውላችሁ ልትመለከቱ ይገባል፡ ተቃዋሚዎች ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው አንደኛ መልእክቱ ምዕራፍ. ፪ ቁጥር ፲፩ ላይ “ሴት በጸጥታ ትማር፤ በፍጹም ቅንነትም ትታዘዝ፤ ሴት እንድታስተምር አንፈቅድም፤ በወንድ ላይም አትሠልጥን፤ በጸጥታ ትኑር እንጂ” ብሏልና፡፡ “ሴትን መጨቆን ነው” ሲሉ ይሰማል፤ ዳሩ ግን አባባሉን በትክክል ለሚያስተውልና ምሥጢሩን መርምሮ ለሚረዳ ምሥጢሩ ሌላ ነው፤ በመሠረቱ ከፍ ብሎ እንደተገለጸው ሚስት በገዛ ሥጋዋ ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ለባልዋ ነው፡፡ ባልም በገዛ ሥጋው ሥልጣን የለውም ሥልጣን ለሚስቱ ነው፤ ባሎች ደግሞ እንደገዛ ሥጋቸው አድርገው ሚስቶቻቸውን ሊወዱዋቸው ይገባል፡፡ “ሴት የለም፤ ወንድ የለም፤ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ናችሁ እንጂ” በማለት የሰውን ክቡርነትና የተፈጥሮ እኩልነት አረጋግጦ የጻፈ በባልና ሚስት መካከል ሊኖር የሚገባው የፍቅርና የመተሳሰብ ሰንሰለት ጽኑ መሆኑን አስረግጦ የጻፈ ሐዋርያ እዚህ ላይ ደግሞ የሴት ልጅን የባርነት አንቀጽ ይጽፋል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የተሳሳተ ነው፡፡

ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ጥሬ ቃል እየቀነጨበ እንደ መሰለው የሚተረጉም ቢሆን ኖሮ ቅዱስ ጳውሎስ በሌላ መልእክቱ “ባል ሚስቱን እንደ ራሱ ይውደድ፤ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ ባልም እንዲሁ ለሚስቱ ራሱን አሳልፎ ይስጥ?” ብሉ ማዘዙ ሕይወትን አሳልፎ ከመስጠት የበለጠ ታዛዥነት ስለሌለ ሴት የወንድ ታዛዥ ሆነች ከማለት ይልቅ ወንድ የሴት ታዛዥ ሆነ ማለቱ ይቀል ነበር፡፡ ዳሩ ግን “ሚስት ለባልዋ ትታዘዝ” የመባሉ ምሥጢር እና “ባል ሕይወቱን አሳልፎ እስከ መስጠት ሚስቱን ይውደዳት” የመባሉ ምሥጢር የፍቅርን ፍጹምነት የሚያጐላ ነው፡፡ ምክንያቱም ፍጹም ፍቅር ካለ አንዱ ለሌላው የማይሆነው ነገር የለምና ነው፡፡ በመሆኑም ባልና ሚስት በዚህ በማይፈለቀቅ የፍቅር ሙጫ ተጣብቀው መላው ሕይወታቸውን እንዲመሩ የሚያስተምር ትእዛዝ እንጂ የቤተሰብን የባርነት ሥርዓት የሚያውጅ አይደለም።

፩. በጥንት ዘመን ማለት ሕገ እግዚአብሔር ከመጣሱ፣ ገነት ከመታጠርዋ በፊት የሰው ልጅ ሕይወት የቅድስና ሕይወት ነበር። ነገር ግን አዳም እንዳይበላ የተከለከለውን ፍሬ በለስ እንዲበላ በማድረግ ሔዋን ምክንያተ ስሕተት በመሆንዋ፣ አሁንም ምክንያተ ስሕተት እንዳትሆን፡ የሴት የሥራ ድርሻ /በመንፈሳዊ ዘርፍ/ ተለይቶ ተቀምጦአል፡፡ ከሴት በፊት የተፈጠረው ወንድ በመሆኑ በአፈጣጠር ቀዳሚነት ስላለው ባል በሚስቱ እንዲከበር የሆነው ነው። (፩ኛጢሞ፪፥፲-፲፣ዘፍ፫፥፮! ፪ኛቆሮ.፲፩ ፥፫)

ወንድና ሴት ማለትም “ሁለቱም ተቃራኒ ጾታዎች የበረከት ምንጮች ናቸው” በሚለው እውነት ሁሉም የሚስማማ ሲሆን ይህ አባባል ግን የበረከት ምንጭነቱ የሁለቱም ጾታዎች የጸጋ ስጦታ እንጂ አንዱ ከሌላው ተለይቶ ያገኘው በረከት ነው አልተባለም። የበረከት ምንጭ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ለአንዱ ወገን ማለትም ለወንዱ ወይም ለሴቷ ብቻ የተሰጠ ጸጋ ነው ተበሎ ሊተረጐም አይችልም: በረከቱ ለሁለቱም ተቃራኒ ጾታዎች የተሰጠ የጋራ ጸጋ ነው፡፡ በመሆኑም በሃይማኖት ረገድ የጾታ እኩልነትን እንጂ ልዩነትን የሚያመለክት ሁኔታ ፈጽሞ አይታይም፡፡ ሌላም ምሳሌ ማየት ይቻላል፤ ይኸውም ቅዱስ ጳውሎስ “ልጆች ሆይ! ለወላጆቻችሁ በእግዚአብሔር ስም ታዘዙ፥ ይህ መልካም ነው፤ መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርሷም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዘ ናት፡፡ እናንተም ወላጆች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በእግዚአብሔር ምክርና ተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው አታሳዝኑአቸው” በማለቱ ሥርዓተ ቤትን ማለትም የቤትን መልካም አስተዳደር ሥርዓት ማስተማሩ እንጂ ልጆች የወላጆቻቸው ባሮች ይሁኑ ማለቱ አይደለም፡፡ (አፌ.፮፥-፩-፮፣ ቆላ.፫፥፳-፳፩)

የጾታ ሲነገር በመንፈሳዊው ዓለም ቀርቶ በሥጋዊው ዓለምም ቢሆን አንዱን ከሌላው ነጥሎ በመመልከት ሊመጣ የሚችል ጤናማ ለውጥ ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፤ የተናጠል ምልከታ ምን ጊዜም ቢሆን ውጤቱ በአንደኛው ጾታ ላይ ነበር የሚባለውን ተጽዕኖ ወደ ሌላኛው ጾታ እንዲዞር ማድረግ ይሆናል፤ በሌላ አገላለጽ አንዱን አግኝቶ ሌላውን ማጣት ይሆናል፤ ለጾታ ልማዳዊ የእኩልነት ችግር ዘላቂና ተመራጭ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ሁለቱን ጾታዎች ያማከለ ሃይማኖታዊ፣ ፍትሐዊና ሚዛናዊ የአመለካከት ሥርዓት በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዲኖር ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው፡፡

ይቆየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!