የሰው ተፈጥሮና ሥርዓተ ጾታ

ክፍል አንድ
ዲያቆን ዘሚካኤል ቸርነት
ታኅሣሥ ፲፩፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም

የሰው   ልጅ ተፈጥሮአዊ  ባሕርይ   በስሙ  ተገልጧል፡፡ የተለየ የሚያደርገውም በአምሳለ እግዚአብሔር  የተፈጠረ መሆኑ ነው፤ ነገር ግን አሁን ባለው ዓለም ውስጥ ክብሩን  ለማዋረድ  የሚሞክር  ነገረ  ህልውናም  ፍጹም  በተሳሳተ  እይታ  የሚተነትን  የሐሰት  “ሳይንስ” ይስተዋላል፡፡ መላእክት  ዕውቀት  አላቸው፤  ነገር  ግን  በኃይለ  ዘር አይራቡም:: ከዚህ በተቃራኒው  ደግሞ እንስሳት  ዕውቀት  የላቸውም፤ በኃይለ  ዘር ግን ይራባሉ፤  ሰው ግን እንደ መላእክት ዕውቀት  እንደ  እንስሳት ደግሞ በኃይለ  ዘር ስለሚራባ ከሁለቱም የተለየ ያደርገዋል፤  ዳግመኛም መላእክት  ሕያዋን  ናቸው፤  እንስሳት  ደግሞ  መዋትያን ናቸው፤  የሰው  ልጅ ግን  ሕያውም  መዋቲም  በመሆኑ የተለየ ነው፤ እግዚአብሔር  እንዲህ  ውብና ቅዱስ አድርጎ  የፈጠረው ስላለው ክብር ባለ መረዳትና ባለ ማወቁ ወደ ኃጢአት  ሲወድቅ  ይስተዋላል፡፡

ሰው በዓለም ለመኖር ብቻ የተፈጠረ ፍጥረት አይደለም፤ ይልቁንም ዓለምን ለመጠቀም ጭምር የተፈጠረ እንጂ፣ ከዚህ በተጨማሪ ሰው ዓለምን ወይም እንደገና መገንባትና መለወጥ የሚችል ፍጥረት መሆኑም ልዩ ያደርገዋል፡፡ ሰው መረዳቱንና ዕውቀቱን በፍጥረታት ላይ ይጠቀማል። ምድር በውስጣ ያሉትን ጨምሮ ለሰው ልጅ እንደ ስጦታ ብቻ ተደርጋ የተሰጠች ሳትኾን እንዲሠራባትም ጭምር የተሰጠችው ናት፡፡ እግዚአብሔር የሰጠውን ፍጥረት ተጠቅሞም ከእግዚአብሔር ጋር ይገናኝበታል። ከሁሉ በበለጠ የሰውን ልጅ እጅግ ታላቅ የሚያደርገው ደግሞ እግዚአብሔር ሥጋና ነፍስን ነሥቶ በፍጹም ተዋሕዶ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ የሆነለት ብቸኛ ፍጥረት በመሆኑ ነው። ከሰማይ በታች ያለውን ሁሉ እንዲመራ እንዲያስተዳድርም የምድር ንጉሥም ነው፡፡ በእግዚአብሔር መልክ ስለ ተፈጠረው ሰው ነግሮ የሚጨርስ ማን ነው? ለዚህም ነው ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “ምንት ውእቱ ሰብእ ከመትዘክሮ፤ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጎበኘው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?” እያለ ይጠይቅና ሲመልስም “ከመላእክት እጅግ በጥቂት አሳነስኸው፤ በክብር እና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው፤ በእጆችህም ሥራ ላይ ሾምከው፤ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት” በማለት ይመልሳል፡፡ (መዝ.፰፥፬)

የሰው ልጅ ምንነት በምስጋና ያጌጠ፣ በጥንተ ተፈጥሮ ከመላእክት ያነሰ ቢሆንም መላእክትን የመምሰል ምሉዕ ጸጋ ተችሮታል፤ መላእክት ግን ያገለግሉትና ይራዱት ዘንድ ለእርሱ የተዘጋጁለት፣ የእግዚአብሔር የእጁ ሥራም የሆነ በምድራውያን ፍጥረታት ላይ የጸጋ ገዥነት ሥልጣን ተሰጥቶት የተሾመ ክቡር ፍጥረት ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ምንነትና ክብር የሚጀምረው ከጥንተ ተፈጥሮውና ከተሰጠው የገዥነት ሥልጣን ነው፡፡ ይህን ክብሩን ጠብቆ ባለ መኖሩ ምክንያት የደረሰበትን ፍዳ ሲናገር ደግሞ “ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ፤ ሰውስ ክቡር ሆኖ ተፈጥሮ ነበር፤ አላወቀም እንጂ፤ ልብ እንደሌላቸው እንስሳትን መሰለ” በማለት ይገልጣል፡፡ (መዝ.፵፱፥፲፭) የሰው ልጅ እግዚብሔርን መመስል መነሻው/መሠረቱ/ ደግሞ የሰው ጥንተ ተፈጥሮ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሰው ጥንተ ተፈጥሮ ስንልም በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል መፈጠሩ “ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ” የሚለው አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ (ዘፍ.፩፥፳፮) ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ስለሆነ መነሻውም መድረሻውም እግዚአብሔርን መምሰል ነው፡፡ (፩ኛ ጴጥ.፩፥፭-፯)

“የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ፡፡” (ዘፍ.፩፥፳፮) እንዴት የሚደንቅ ቃል ነው! የሚያስፈልገውን ቀድሞ ፈጥሮ የፍጥረቱ ማጠናቀቂያ አደረገው፤ ምንም እንዳይጎድልበት በእግዚአብሔር ሙላት ተፈጠረ፤ ቀድመውት በተፈጠሩት ላይ ንጉሥ አድርጎ ሾመው፡፡

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ የሰው ልጅ በመጨረሻ በመፈጠሩ ምክንያት ክብሩ ከሌሎች ፍጥረታት ያነሰ ነው እንዳይባል ዩኖሚየስ ለተባለ ለአርዮስ ተከታይ ሲመልስ እንዲህ ነበር ያለው፤ “ዩኖሚየስ የተባለው የአርዮስ ተከታይ ቀድሞ በመወለዱ ምክንያት ቃየል ከአቤል ይበልጣል” ይላል፡፡ ይህ ማለት ከምድር ላይ በቅለው የተገኙ ዕፀዋት በሦስተኛ ቀን ስለተገኙ በአራተኛው ቀን ከተገኙት ከዋክብት ይበልጣሉ ማለት ነው፡፡ ማንም ሰው የምድርን ሣር ድንቅ ከሆኑት ከዋክብት ይበልጣሉ ብሎ አይጃጃልም፡፡ ዕውቀት የሌላቸው ግዑዛን የሆኑት በጊዜ ከሰው ቀድመው በመገኘታቸው ከሰው ሊበልጡ አይችሉም፡፡ ቃየልም አቤልን በጊዜ ስለቀ ደመው ሊሸለም አይችልም፤ አቤል ይሸለማል እንጂ በማለት የሰውን ልጅ ታላቅነት አስተምሯል። ይህን ታላቅነቱንና ክብሩን ጠብቆ ባለ መኖሩ ምክንያት የደረሰበትን ፍዳ ሲናገር ደግሞ “ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ፤ “ሰውስ ክቡር ሁኖ ተፈጥሮ ነበር፤አላወቀም እንጂ፤ ልብ እንደ ሌላቸው እንስሳትን መሰለ” በማለት ይገልጣል፡፡ (መዝ.፵፱፥፲፭)

የሰው እግዚብሔርን መመስል መነሻው /መሠረቱ/ ጥንተ ተፈጥሮ ነው፡፡ የሰው ጥንተ ተፈጥሮ ስንልም በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል መፈጠሩ “ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ” የሚለው አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ (ዘፍ.፩፥፳፮) ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ስለሆነ መነሻውም መድረሻውም እግዚአብሔርን መምሰል ነው፡፡ (፩ኛ ጴጥ.፩፥፭-፯)

በክርስትና የነገረ ሰብእ ትምህርት መሠረት አርአያ እግዚአብሔርና አምሳለ እግዚአብሔር ዋና ማዕከል ናቸው። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አርአያ እግዚአብሔርን ነጻ ፈቃድ፣ በራስ መወሰን ኢመዋቲነት፣ በፍጥረታት ላይ ያለውን ገዥነትና መልካም ሥራ ለመሥራት የሚያደርገው ጥረት አድርገው ይገልጹታል፡፡ … ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ስለተፈጠረ ዐውቆና ተረድቶ የሚሠራቸው ነገሮች አሉ፡፡

እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር “ንግበር ሰብአ በአርአያነ ፈጠረ ወበአምሳሊነ፤ ሰውን እንደ መልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር” ካለ በኋላ “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረው” ይላል፡፡ (ዘፍ.፩፥፳፮) ይህም ማለት ሰው አርአያ እግዚአብሔር እና አምሳለ እግዚአብሔር ተሰጥቶታል ማለት ነው፡፡ እነዚህንም በፍጥረት ጊዜ ሲፈጠር ሰጥቶታል፤ “በእግዚአብሔርም መልክ ፈጠረው” ይላልና፡፡ ሁለተኛውን ማለትም የእግዚአብሔር ምሳሌን ግን ከተሰጠው ከእግዚአብሔር መልክ ተነሥቶ የተሰጠውን ጸጋ በማሳደግ ወደ ፊት ይደርስበት ዘንድ የተሰጠው፣ ሆኖም ገና ያልደረሰበት ጸጋ ነው፡፡ አርአያ እግዚአብሔር /የእግዚአብሔር መልክ/ የተባሉት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት በእግዚአብሔር ዘንድ በምልዓት ያሉት፣ ለሰው ደግሞ እንደ ዓቅሙ መጠን በጸጋ የተሰጡት ሲሆኑ እነዚህም ብዙ ኀብረ መልክና ገጽታ ያላቸው ናቸው፡፡ ይህም ቅድስና፣ ፍቅር፣ ነጻነትና ኃላፊነት፣ ጥበብ ገዢነት፣ ሰብእና፣ ርቱዕነትና፣ ንጽሕና፣ ክብር፣ ፍትሐዊነት፣ ርኅራኄ፣ ምክንያታዊነት አሳቢነትና ዐዋቂነት እና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡ እነዚህ ለሰው በተፈጠረ ጊዜ የተሰጡት በዘርነት /በመነሻነት/ ደረጃ ነው፡፡

የእግዚአብሔር መልክ የተባሉት የቅድስና መገለጫዎች ለሰው የተሰጡት ያሳድጋቸውና ይንከባከባቸው ዘንድ ነው፡፡ መንፈሳዊ ሕይወትና መንፈሳዊነት የሚባለው እነዚህን የማሳደጉና ወደ ፍጹምነት ደረጃ የመውሰድ ሂደት ነው፤ በዚህም ሰው ከተሰጠው የእግዚአብሔር መልክ በመነሣት ወደ እግዚአብሔር ምሳሌ ያድጋል ማለት ነው፡፡

እነዚህም ተዘክሮተ አምላክና ከእርሱ /ከእግዚአብሔር ጋር/ በኅብረት መኖር፣ የቅድስና ሕይወት የመጨረሻውም ፍጹምና ዘለዓለማዊ ሕይወት ናቸው፡፡ ሐዋርያው “የሥጋችን አባቶች መልካም ሆኖ እንዲታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፤ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል” በማለት እንደ ገለጸው እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረበት ዋና ዓላማና በየጊዜው በእኛ ላይ የሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ግባቸው እኛን ከቅድስናው እንድንካፈል ማድረግ ነው፡፡ (ዕብ.፲፪፥፲) “ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ” ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና ያለውም ለዚህ ነው፡፡ (ዕብ.፲፪፥፲፬)

ጥንት ግኖስቲኮች ከሚያስተምሩት የክሕደት ትምህርት መካከል አንዱ ሥጋን ርኩስ ብሎ ማመን ነበር፡፡ ሰው ሥጋና ነፍስ እንዳለው ያምናሉ፡፡ የሰው ነፍስ ግን እንደ እሳት ክፋይ ከልዑሉ አምላክ መለኮታዊ ባሕርይ ተከፍላ የምትመጣ ነች፡፡ ሥጋ ግን ምድራዊና ክፉ ስለሆነ የመለኮት አካል የሆነች ነፍስ በመለኮት ሥልጣን በሥጋ ውስጥ ታስራ ትገኛለች፡፡ ከእዚህ እስራት ልትፈታ የምትችለው ሰው ዕውቀትን /ግኖሲስ/ ገንዘብ ማድረግ የቻለ እንደሆነ ነው በማለት እጅግ በጣም ከባድ የሆነ ክሕደትን ያስተምራሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ የእምነት ምልከታ ውስጥ ገብቶ መነዋወጽ ወደ ከባድ ክሕደት የሚያደርስ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ “የሰው ሥጋ ርኩስ ነው” የሚሉትን ሰዎች አፍ ይዘጋ ዘንድ እንዲህ ይላል፡- “የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፡፡ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና፡፡” (ዘፍ.፱፥፮)

በእግዚአብሔር መልክስ ብሎ በዚህ ንባብ የገለጸው የሰውን ተፈጥሮአዊ ሥጋ መሆኑን የምንረዳው የሰውን ደም የሚያፈስ በሚለው ንባብ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህንን የተረዳ ማንም ቢሆን ሥጋን ርኩስ ነው ወደ ሚል የእምነት ውድቀት ውስጥ ፈጽሞ ሊገባ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ፍጥረት ፍጹም በመሆኑ፣ ይህ ቀረህ፣ ይህ ይጨመርልህ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት፣ ሰው ለተለያየ ጥቅም በሚል ሰበብ ዝርያቸው የተለያዩ የሆኑትን ፍጥረታት ማዳቀልንና ማደበላለቅን ተያይዞታል፡፡
በተቃራኒውም የሰውን ቁጥር ለመቀነስ የማያደርገው ሩጫ የለም፡፡ ይህ አሠራር አምላክ የሠራውን የፍጥረት ሕግ በማጣጣል ሰው ላሻሽል ወደሚል ያዘነበለ ግብረ ሰዶምን የሚያበረታ በመሆኑ የሰውን ልጅ ቅጥ ያጣ ድፍረት ያሳያል፡፡
በጋብቻ ላይ የሚደረግ ርኩሰትን ስንመለከትም በየትኛውም ዓለም የፍርድ ቤቶች ትልቁ ሥራ ማፋታት ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ተጋቢዎች በአንድ ላይ እንዳይኖሩ የጋብቻ ዓላማና ጥቅም ስላልተረዱ የሥጋን ፍላጎት ልቅ በሆነ መንገድ ለመፈጸም፣ አልፎም ተርፎ ግብረ ሰዶምን እንዲበረታታ በአንዳንድ ሀገሮች እንደሚታየው ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት ጋር እያቆራኘ “በቤተ ክርስቲያኖቻቸው” ጋብቻ እስከ መፈጸም አድርሷቸዋል፡፡

ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፤ ”ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵሰት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ፣ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን። ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ዓመፃ ሁሉ፥ ግፍ፥ መመኘት፥ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፥ ነፍስ መግደልን፥ ክርክርን፥ ተንኰልን፥ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፤ የሚያሾከሹኩ፥ ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚፈላልጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት ያጡ ናቸው፤ እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም።” (ሮሜ ፩፥፳፬-ፍጻሜ)

ኦርቶዶክሳዊ የጾታ ትምህርትን አስመልክቶ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ነገርን ከትርጉሙ“ እንዲል እኛም “ኦርቶዶክሳዊ የጾታ ትምህርት ምን ማለት ነው?” በማለት እንጀምራለን፡፡ ኦርቶዶክስዊ የጾታ ትምህርት ሲባል በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ጾታ የሚሰጠውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት፣ ቤተ ክርስቲያን ስለ ጾታ ያላትን አመለካከት፣ ቀኖናዊ ሥርዓትና ባህላዊ ትውፊት የሚያመለክተውን ትምህርት ማለት ነው፡፡

ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደምንረዳው ጾታ የሚለው ቃል በአርአያ እግዚአብሔር ከተፈጠረው የሰው ዘር ጀምሮ፣ በመውለድ መዋለድ፣ የመብዛትንና የመባዛትን ተፈጥሮአዊ ጸጋ ከእግዚአብሔር አምላክ ያገኘ ፍጡር ሁሉ ተባዕታይ፣ አንስታይ ወይም “ወንዴና ሴቴ” እየተባለ የሚጠራበት በተፈጥሮ አካል የሚለይበት ስያሜ ነው፡፡ በዚህ እውነታ ላይ ሌላ አከራካሪና አነጋጋሪ የትርጉም ልዩነት ስለማይኖር በዚሁ መሠረተ ሐሳብ እንስማማ ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ “ጾታ” የሚለው ቃል፣ በቋንቋነቱ ሲታይ ደግሞ ከላይ በተሰጠው ትርጉም ብቻ ሳይገደብ፣ ተራ፣ ረድፍ፣ ክፍል፣ ማዕረግ፣ ዓይነት ስልት፤ ወገንና ነገድ የሚል ሰፊ ጽንስ አሳብ የሚካተትበት መሆኑን የቃሉ ትርጉም ያስረዳል። ጾታ ቃሉ ግእዝ ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ ሲታይ “ወገን፣ ተራ፣ ረድፍ” ተብሎ መተርጎሙን መረዳት ይቻላል፡፡

ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግም “ጾታን፣ ወገን፣ ነገድ” ብሎ ሲተረጉም “የሚካኤል ሠራዊት በየነገዳቸው፣ የገብርኤልም ሠራዊት በየማኅበራቸው፣ ኪሩቤል በግርማቸው፣ ሱራፌል በቅዳሴያቸው /በምስጋናቸው/ የመላእክትም ሠራዊት ሁሉ በየወገኖቻቸው፣ በቅዱሳን ምስጋና የሚመስገን እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል” ብሏል፡፡ ከዚህም ሌላ ጾታ ክፍለ መጻሕፍትን ስለ ማመልከቱ በመቅድመ ፍትሐ ነገሥት. . . ከቀኖና ለሚገኝ ብዙ ሥራ በልዩ ልዩ “ወገን” የእያንዳንዱን ትርጓሜ የሚያስረዱ ከሆነ ፍጻሜውን የሚያስረዱበት ጊዜ አሉ ተብሎ ተጽፎአል፡፡ (መቅ.ፍ.ነገሥ)

የሰው ዘር ሥርውና መሠረት የሆኑት አዳምና ሔዋን ስያሜያቸው በጾታ ተለይቶ በሚታይበት ጊዜ ቀጥሎ የተገለጸውን ትርጉም ይዞ ይገኛል። በወል ስያሜው ሰው፣ በጾታ ስያሜውም ተባዕት፥ አዳም በመባል የሚታወቀው ቀዳሜ ፍጥረት በስድስተኛው ቀን መጀመሪያ ከምድር የተገኘ የሰው ሁሉ ምንጭ ሆኖ በዘር በሩካቤ የሚበዛ፣ ሞትና መቃብር የሚገዙት፥ ምድራዊ ሰው ሁሉ በእርሱ በምንጩ ስም አዳም እየተባለ የሚጠራ የፍጥረት ሁሉ አባት ነው፡፡ አዳም ማለት “የሚያምር፣ ደስ የሚያሰኝ ውብ፣ ደግ፣ መልካም፣ መልከ መልካም የመጀመሪያ ሰው የሰው ሁሉ አባት፥ ቀይሐ ሥን፥ ብጽሐ አምጣን፣ ሥግው እምድር /ዘተሠገወ እመሬት/” የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡

ጾታዊ ስያሜው ከላይ ባየነው መልኩ የተገጸው ሰው፣ እንስሳዊና መልአካዊ ባሕርያት ስላሉት በሥጋው መዋቲ ድኩም፣ ፈተና የሚፈራረቅበት ሆኖ በነፍሱ ነባቢ፣ ለባዊ፣ ሕያው፣ ባለ አእምሮ አሳቢ ተመራማሪ ይባላል። ይህ አባባል ጾታን ሳይለይ ሰብአዊ ባሕርይ የሚገለጽበት አባባል ሲሆን የእንስትዋን ጾታዊ ስያሜ ደግሞ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡ የእንስት (የሴት) የጾታ ስያሜ- ብእሲት፣ ሔዋ /ሔዋን/፣ ሕያዊት! እመ ሕያዋን የሚል ነው፣ አዳምም የሚስቱን ስም ሔዋን ብሎ ሰየመ፣ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ (ዘፍ.፫፥፮)

ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደምንማረው ‹ጾታ› የሚለውን ቃል በአርአያ እግዚአብሔር ከተፈጠረው የሰው ዘር ጀምሮ በመውለድና መዋለድ የመብዛትንና የመባዛትን ተፈጥሮአዊ ጸጋ ከአምላኩ ያገኘ ‹ፍጡር› ተባዕት፣ እንስት (‹ወንድና ሴት›) እየተባለ የሚጠራበት በተፈጥሮ አካል የሚለይበት ስያሜ ነው፡፡ ይህም የጾታ ትርጒም በሰብአዊ የተፈጥሮ አካል በሚለይበት ጊዜ ወንድን፡- “ተባዕት፣ አውራ፣ ወልድ፣ ብእሲ፣ አዳም” በማለት የሚገለጽ ሲሆን “ሴትንም፡- እንስት፣ ወለት፣ ሔዋንና ሔዋናዊት” በሚባል ስያሜ ይገልጻታል:: ሆኖም ዓለም ቤተ ክርስቲያን ስለ ጾታ በምታስተምረው ትምህርት ላይ የተለያየ አመለካከት፣ ግንዛቤና አባባል ሊኖር ይችል ይሆናል፤ የጾታ ነገር ሲነሣም የነጻነትና የእኩልነት ጥያቄ ቀዳሚ ጉዳይ ሆኖ የሚታይ የዘመኑ ዐቢይ ጉዳይ የመሆኑ ነገር አከራካሪነት የሌለው ነው፡፡

ይቆየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!