የምእመናን ድርሻ በቤተ ክርስቲያ

ክፍል አራት

ዲያቆን ዳዊት አየለ

ታኅሣሥ ፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

የጾም ሥርዓትና ማድረግ ያለብን ነገሮች፦ ጾም ‹‹ጾመ›› ‹‹ለተወሰነ ጊዜ እህል ውኃ ተወ፤ ጦመ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ‹‹መተው፣ መጠበቅ፣ መከልከል›› ማለት ነው፡፡ ጾም ከምግብ መከልከል ብቻ ሳይሆን ከክፉ ተግባር ሁሉ መቆጠብ ጭምር ነው፡፡ (ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ ፲፻፲፱) ሠለስቱ ምዕትም፡‹‹ጾምስ በታወቀው ሰዓት፣ በታወቀው ዕለት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው›› በማለት የጾምን ትርጕም በፍትሐ ነገሥት ያስረዳሉ። (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭)

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ እንዳለው በጾም ጊዜ የስሜት ሕዋሳት ሁሉ ከክፉ ድርጊት ሊታቀቡ ይገባል፤ አፍን ክፉ ከመናገር፣ ዓይንን ክፉ ከማየት፣ ጆሮን ክፉ ከመስማት፣ እጅን ክፉ ከማሠራት፣ ከመቀማት፣ እግርን ከክፉ መንገድ ልብን ክፉ ከማሰብ ከልክሎ ነው እንጂ ከዚህ ሁሉ ሳይከለከሉ ቢጾሙ ዋጋ አይገኝበትም፤ በረከትም አይኖረውም፤ እንዲሁም አእምሮን ጎድተው ሰውን አስክረው የማይገባ ሥራ ከሚያሠሩና ከሚያሳስቡ የአልኮል መጠጦችም መጠበቅ ይገባል። (መጽሐፈ ምዕዳን በአባ ገብረ ኪዳን)

ጾም ልጓመ ሥጋ፣ የሥጋን (የኃጢአትን) ምኞት የምታጠፋ፣ የነፍስን ቁስል የምትፈውስ (የምታደርቅ) ጸጥታንና ርጋታን የምትሰጥ፣ ኃይለ ፍትወትን የምታደክም፣ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ ከእግዚአብሔር ኃይልን የምታሰጥ፣ የጸሎት እናት፣ የዕንባ መገኛ መፍለቂያዋ፣ አስቀድሞም ለአዳም የተሰጠች የፍቅር ሕግ፣ በብሉይም የነበረች በሐዲስም ዳግም በጌታ የተሠራች (ሠራዔ ሕግ ነውና) ሲሆን ሰውና እግዚአብሔር የሚገናኙባት ቀጭን መንፈሳዊ መንገድ ናት፤ ከእንስሳዊ ጠባይ የምትከለክልና ሰው መላእክትን መስሎ የሚኖርባት ደገኛ ሥርዓት ናት። በክርስትና ሕይወታችን ውስጥ ጾም ለአምላካችን እግዚአብሔር ፍቅር ስንል ለተወሰነ ሰዓት ሥጋችንን ለርኀብና ለጥማት አሳልፈን በመስጠትና በመትጋት የምንኖረው በመሆኑ የአምልኮት መገለጫም ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ›› በማለት እንደተናገረው ለአምላካችን እግዚአብሔር መገዛታችንን አምልኮታችንን ከምንገልጽባቸው ክርስቲያናዊ ተግባራት መካከል አንዱ ጾም ነው። (መዝ.፪፥፲፩-፲፪)

በጾም ወቅት የሥጋ አለቃ ነፍስ ናት፤ ነፍስ ፈላጭ፣ ቆራጭ፣ አዛዥ ናት፡፡ ሰው መልካም ሥራ ከሠራ በነፍስ በሥጋው ይቀደሳል፤ ርስት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳል፡፡ ክፉ ከሠራ ደግሞ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ያጣል፤ ወደ ሲኦልም ይወርዳል፡፡ ሰው ኀጢአት ሠራ ሲባል ፈቃደ ሥጋው ሠልጥኖበታል ማለት ነው፡፡ ገቢረ ጽድቅ ፈጸመ ሲባል ደግሞ ፈቃደ ሥጋውን አሸንፏል (ለፈቃደ ነፍሱ እንዲገዛ አድርጓል) ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ሲቀደስም ሲረክስም የሚኖረው በፈቃደ ሥጋ እና ፈቃደ ነፍስ መካከል ባለው የአሸናፊነትና ተሸናፊነት ትግል ነው፡፡

አማናዊት እናታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ክርስቲያን በዓዋጅ የሠራቻቸው አጽዋማት ሰባት ሲሆኑ እነርሱም፦ ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)፣ የጋድ ጾም፣ ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ድኅነት (ረቡዕ እና ዓርብ)፣ የሐዋርያት ጾም እና የፍልሰታ ጾም ናቸው፤ እነዚህን አጽዋማት በሥርዓትና በትሕትና መጾም ከአንድ ምእመን የሚጠበቅ ክርስቲያናዊና መንፈሳዊ ግዴታው ነው። በዚህም ጾም ዲያብሎስን ድል ከምንነሣባቸው መንፈሳዊ ትጥቆች አንዱ ነውና ጠላት ዲያብሎስን ድል እንነሳዋለን።

ዐቢይ ጾም፦ ጌታችን የጾመው ጾም ነውና ‹‹የጌታ ጾም›› ተብሎ ይታወቃል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እከብር አይል ክቡር፣ እነግሥ አይል ንጉሥ፣ እጸድቅ አይል ጽድቅ የባሕርዩ የሆነ አምላክ ነው፡፡ ለእኛ አርአያ ቤዛ ሊሆነን፣ እናንተም ብትጾሙና ብትጸልዩ አጋንንትን ድል ትነሣላችሁ ሲለን፣ ጾምን ለመባረክና ለመቀደስ፣ በመብል ምክንያት ስተን ስለ ነበር ስለ እኛ ኀጢአት እና በደል ሲል ዐርባ ቀንና ሌሊት የጾመው ጾም ነው፤ እኛም እርሱን አብነት አድርገን እንጾማለን። ዐቢይ ጾም በውስጡ ስምንት ሳምንታት (፶፭ ቀናት) ያሉት ሲሆን ስምንት ቅዳሜዎችና ሰባት እሑዶች ይገኛሉ በድምር ፲፭ ቀናት ማለት ነው፤ እነዚህ ቀናት (ቅዳሜና እሑድ) ከጥሉላት ብቻ እንጂ ከእህል ውኃ ስለማይጾምባቸው የጾሙ ቀናት በአጠቃላይ ፵ ቀናት ይሆናሉ።

ጾመ ድኅነት (ረቡዕ እና ዓርብ)፦ ጾመ ድኅነት ከስሙ እንደምንረዳው የድኅነት(የመዳን) ጾም ማለት ሲሆን በብሉይ ኪዳኑ አጽዋማት በጾመ አስቴርና በጾመ ዮዲት የተተካ የሐዲስ ኪዳን ጾም ነው። በብሉይ ኪዳን በሐማ ምክንያት በእስራኤል ላይ ታውጆ የነበረው ሞት በጾመ አስቴር እንደተሻረ ሁሉ በሐዲስ ኪዳንም በዕለተ ረቡዕ በጌታችን ላይ በተፈጸመው ምክር የዲያብሎስ ሴራ ፈርሷል፤ እንዲሁም በብሉይ ኪዳን በጾመ ዮዲት ምክንያት ሆሎሆርኒስ ድል እንደተደረገ ሁሉ በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ በተቀበለው መከራ ዲያብሎስ ድል ተነሥቷል፤ እኛም በጾመ አስቴር ፈንታ ምክረ አይሁድን አስበን ረቡዕን በጾመ ዮዲት ምትክ የጌታችንን መከራውን አስበን ዓርብን እንጾማለን።

ጾመ ነነዌ፦ ጾመ ነነዌ ማለት የነነዌ ከተማ ሰዎች የጾሙት የንስሓ ጾም ማለት ነው። የነነዌ ኃጢአት ዐመፅ እና በደል በነቢዩ በዮናስ ዘመን ሰማይ ነክቶ ነበር። የነነዌ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ እና ሊመጣ ካለው ቁጣ ይድኑ ዘንድ እንዲያስጠነቅቅ እግዚአብሔር ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ላከው። ነነዌ ነቢዩ ዮናስ ከተወለደበትና ካደገበት ከጋት ሔፌር ፰፻ ኪ.ሜ. ያህል ትርቅ ነበር። መጀመሪያ ከተልእኮው ቢያፈገፍግም «ዮናስም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮኾም፦ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ» እንደተባለው ነቢዩ ዮናስ የኋላኋላ ወደ ነነዌ ሂዶ የእግዚአብሔርን መልእክት አውጇል። (ዮናስ ፬፥፲፩) በዚያን ጊዜ የነበሩት ሰዎችም «የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም ዓዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ» እንዲል (ቁጥ.፭) በንስሓ ጾም ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀው ከጥፋትና መዓት ድነዋልና ጾመ ነነዌ ተባለ።

ጾመ ነነዌ የእግዚአብሔርን ቸርነትና መሐሪነት የምናስታውስበት ጾም ነው፤ ይህም እኛ ፍጡራኑ በበደልን ጊዜ ፈጽሞ ከማጥፋት ይልቅ ምክንያት ፈልጎ እንድንድን ያደርገናል። ዮናስ ለስብከቱ ፈቃደኛ ባይሆን እንኳን እግዚአብሔር በተለየ ጥበቡ ወደ ሀገረ ነነዌ እንዲሄድ አድርጎታል፤ በእርግጥ እግዚአብሔር ሌላ የሚልከው ነቢይ አጥቶም አልነበረም፤ እርሱን ጭምር ሊያስተምረው ስለ ፈለገ እንጂ። የነነዌ ሰዎች የተነሳሕያን ምሳሌ ናቸው፤ ይህም ማለት ሰው ጥፋቱን አምኖ ንስሓ ከገባ እግዚአብሔር ይቅር ማለቱን አይተውም ማለት ነው። አምላክ ለነቢዩ ዮናስ ላልደከመበትና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ሲያዝን በታላቂቱ ነነዌ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጁ ፍጥረቶች በመሆናቸው እርሱ እንደሚያዝን የነገረው ለዚህ ነው። እኛም በዚህ አብነት ስንጾም እግዚአብሔር አምላካችን መዓቱን በምሕረት፣ ቁጣውን በትዕግሥት መልሶ በኃጢአት የወደቅን ይቅርታን እንድናገኝ እንጾማለን፡፡

ጾመ ነቢያት፦ ይህ ጾም የእግዚአብሔርን ሰው መሆን ሲጠባበቁ የኖሩት የነቢያት ትንቢትና ጸሎት በጌታችን መወለድ ፍጻሜ ያገኘበት ወቅት በመሆኑ ‹‹ጾመ ነቢያት (የነቢያት ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ለአዳም የተነገረው የድኅት ተስፋ ስለ ተፈጸመበትም ‹‹ጾመ አዳም(የአዳም ጾም)›› ይባላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆን በስፋት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበት ወቅት በመሆኑም ‹‹ጾመ ስብከት(የስብከት ጾም)››፤ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመሆኑ ደግሞ ‹‹ጾመ ልደት (የልደት ጾም)›› በመባል ይታወቃል፡፡ እንደዚሁም ‹‹ጾመ ሐዋርያት›› ይባላል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹በዓለ ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብረዋለን፤ በዓለ ልደትንስ ምን አድርገን እናከብረዋለን?›› በማለት ነቢያት የጾሙትን ከልደተ ክርስቶስ በፊት ያለውን ጾም ጾመዋልና፡፡

በአጠቃላይ በዚህ በገና ጾም ነቢያትም ሐዋርያትም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም እንደ እነርሱ በረከትን እናገኝ ዘንድ ይህንን ጾም መጾም እንደሚገባን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ በዚህም መሠረት የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን፤ መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ሁላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል፡፡

ጾመ ጋድ፦ የጋድ ጾም የሚጾመው በልደትና በጥምቀት ዋዜማ ነው፤ በመጀመሪያው የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ዋዜማ ቀን የምንጾመው ነው፡፡ ሐዋርያት ‹‹ልደትና ጥምቀት ዓርብ ረቡዕ ቢውል በሌሊት ቀድሰው ሥጋውን ደሙን ይቀበሉ፤ ከሌሊቱ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጹሙ ብለው አይፍረዱ›› ብለዋል (ፍት.ነገ አን ፲፭)፡፡ የልደትና የጥምቀት በዓል በረቡዕ ወይም በዓርብ ቀን ቢሆን በበዓለ ኀምሳ የሚበላውን የጥሉላት ምግብ በጠዋት በመብላት ምእመናን በዓሉን እንዲያከብሩ ታዟል፡፡ ይህም እነዚህ ሁለቱ ታላላቅ የእግዚአብሔር በዓላት በመሆናቸው ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ጾም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት በማሰብ የጥምቀትን ዋዜማ እንጾማለን፡፡ ይህም ማለት በጥምቀት ዋዜማ ከምግብ መከልከል ነው፡፡ የሚቆርብ ሰው አክፍሎ የሚያድር ስለሆነም የጥምቀትን ዋዜማ መጾም ነው፡፡ የጥምቀት በዓል በረቡዕና በዓርብ በሚውልበት ጊዜ በረቡዕና በዓርብ ፈንታ ማክሰኞንና ሐሙስን በመጾማችን ሁለት ሥራ ይፈጸምልናል፡፡ በዚህም የጾምና የበዓል ማክበር ሥራ ይከናወናል፡፡

የልደትንና የጥምቀትን ዋዜማ ጥሉላት መባልዕትን መተው ነው፡፡ይህንንም እንደ ዘይቤው ገሃድ ይለዋል፤መገለጫ፣ግልጥ፣ይፋ መሆን ማለት ነው፡፡እንዲሁም ጋድ ይለዋል፤ ለውጥ፣ልዋጭ ማለት ነው፡፡ጥምቀት ረቡዕ ዓርብ ሲውል በዚያ ለውጥ ማክሰኞ ሐሙስ ስለሚጾም ጋድ ይባላል፡፡ እንዲሁም አንድ ጊዜ ሲጾም አንድ ጊዜ ሲቀር እንዳይረሳ ቅዳሜ ወይም እሑድ በሰንበት ቀን ሲውል ቀን መጾም ዘንድ አይቻልም፤ ነገር ግን እህል ውኃ እንጂ ጥሉላት ከመብላት መጠበቅ ይገባል፡፡

ጾመ ሐዋርያት፦ ጾመ ሐዋርያት በወርኃ ሰኔ ስለሚጾም በምእመናን ዘንድ የሰኔ ጾም በመባል ይታወቃል፤ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለስብከተ ወንጌል ከመሰማራታቸው በፊት የጾሙት ጾም ነው፤ ከበዓለ ኀምሳ በኋላ የሚጾም ጾም ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ካረገ በኋላ ሐዋርያት አዝነው ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ መልአከ እግዚአብሔር ‹‹እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እያያችሁ ለምን ቆማችኋል፡፡ ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል›› አላቸው።(ሐዋ. ፩፥፰-፲፩) ሐዋርያትም የመልአኩን ማረጋጊያ ቃል ከሰሙ በኋላ በኢየሩሳሌም ወደ ምትገኘው ቤተ መቅደስ በመሄድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነገራቸው እስኪፈጸም ድረስ ቀን ከሌሊት በአንድነት ሆነው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከመካከላቸው አድርገው በጸሎት እየተጉ ቆዩ፡፡ አስቀድሞም ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ደቀ መዛሙርቱን ጾሙን እንደሚጾሙት እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር፤ ‹‹የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ አይችሉም፤ ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ ያን ጊዜም ይጾማሉ›› እንዲል፡፡ (ማቴ.፱፥፲፭)

እኔ ሳለሁ አይጾሙም ማለቱ እርሱ ካልሞተና ተነሥቶ ካላረገ፣ መንፈስ ቅዱስም ካልተሰጣቸው በመንፈስ ቅዱስ ባልታደሰ ሰውነት ጾመው ድል መንሣት ስለማይቻላቸው ነው፡፡ ይህን ጾም የምንጾመው ሐዋርያት ጾመው ጸልየው ድል ያደረጉትን ዓለም እኛም የምናሸንፍበት ኃይል እንዲሰጠን ፈጣሪያችንን አምላከ ሐዋርያት ተለመነን እያልን ለመማጸን ነው፡፡ ጾመ ሐዋርያትን እንደ ሌሎቹ አጽዋማት ሁሉ እያንዳንዱ ምእመን ሊጾመው የሚገባ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ግን አብዛኛው ምእመን ‹‹የቄስ ጾም›› ነው በማለት ከጾሙ ሽሽት ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ ይህ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት ያደረገ ባለመሆኑ መስተካከል ይገባዋል፡፡ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ስለሆነ ሁሉም ሊጾሙት ይገባል፡፡

ጾመ ፍልሰታ፦ይህ ጾምም ‹‹ጾመ ማርያም (የማርያም ጾም)›› ወይም ‹‹ጾመ ፍልሰታ ለማርያም (የማርያም የፍልሰቷ ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡‹ፍልሰት› የሚለው ቃልም ‹‹ፈለሰ ሔደ፤ተሰደደ›› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡ ‹ፍልሰታ ለማርያም› ሲልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን የሚያስረዳ መልእክት አለው፡፡

በነገረ ማርያም ተጽፎ እንደምናገኘው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሲሔዱ አይሁድ ‹‹እንደ ልጇ ተነሣች፤ ዐረገች እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት›› ብለው በዓመፃ ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊም አጎበሩን ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጥቶታል፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ።

ሁለት ሱባዔ ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሣ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ በሱባኤው መጨረሻ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም እንደ ልጇ እንደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡ ትንሣኤዋንም ያየ ከሐዋርያት መካከል በጊዜው በደመና ተጭኖ እየተጓዘ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ብቻ ነበር የቀሩት ቅዱሳን ሐዋርያትም በዓመቱ ‹‹ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?›› ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው በየዓመቱ ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ቢይዙ ጌታችን ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፣ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል። (ትርጓሜ ውዳሴ ማርያም) ይህንን ትምህርት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩-፲፭ ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል። (ፍት.ነገ.አን.፲፭)

በጾመ ፍልሰታ ባሕታውያን ብቻ ሳይሆኑ ዓለማውያንም በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተ ሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ እኛም የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ የሚገኘውን ጸጋና በረከት ተስፋ በማድረግ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ፈለግ ተከትለን በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤ የምንችል ደግሞ አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡ በተጨማሪም ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡

ጾምን ሲጾሙ ፊትን ማጠውለግ አይገባም፤ ቁጹረ ገጽ መሆን አይገባም፤ ‹‹በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ እንደጾሙ ለሰው ይታዩ ዘንድ መልካቸውን ይለውጣሉና፥ እውነት እላችኋለው፤ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። እናንተስ በምትጾሙበት ጊዜ ራሳችሁን ቅቡ፤ ፊታችሁንም ታጠቡ። በሥውር ለሚያይ ለአባታችሁ እንጂ፥ ለሰዎች እንደ ጾማችሁ እንዳትታዩ፤ በስውር የሚያያችሁ አባታችሁም ዋጋችሁን በግልጥ ይሰጣችኋል›› ብሎ እንደነገረን ጌታችን ስንጾም ከእግዚአሔር ጋር ተገናኝተን በረከት ለማግኘት እንጂ ለከንቱ ውዳሴ እንዳይሆን ፊትን ማጠውለግ ወይም ጉስቁልቁል ማለት አይገባም፤ ይህም ለፈቃድ አጽዋማት ነው እንጂ በዓዋጅ አጽዋማትስ ከንቱ ውዳሴ የለም፤ ፊታችሁን ቅቡ የተባልነው ፍቅርን ገንዘብ አድርጋችሁ በንስሓ ሆናችሁ ጹሙ ሲለን ነው።

ዐቢይ ጾም የመጀመሪያውን ሳምንት (ጾመ ሕርቃልን) እስከ ፲፪ የቀረውን ሳምንት እስከ ሰሙነ ሕማማት ፱ ሰዓት ድረስ ሥርዓት ነው፤ የቻለ እስከ ፲፪ ሰዓት ድረስ መጾም ይችላል፤ ሰሙነ ሕማማትን ፀሐይ እስክትጠልቅ መጾም ይገባል። የቀሩትን ፮ቱንም አጽዋማት እስከ ፱ እንድንጾም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያስገነዝበናል። በጾም ወቅት ወይን መጠጣት አይገባም፤ ሠርግ ጋብቻም አይደረግም፤ ይልቁንም በዐቢይ ጾም የሰማዕታትን የጻድቃንን ዝክር በዓል እንኳ ቅዳሜ እሑድ እንድናደርግ ፫፻ ሊቃውንት ሥርዓት ሠርተውልናል። ‹‹የወይን ጠጅ ጠጭ አትሁን፤ ለሥጋም አትሳሳ›› እንዲል፤ (ምሳ.፳፫፥፳)

‹‹ጾም የሥጋ ግብር ነው፤ ምጽዋት፣ ዐሥራት በኩራት የገንዘብ ግብር እንደሆነ ሁሉ›› እንዳሉ ፫፻ ሊቃውንት ጾም ማለት የሥጋ ግብር ሥጋን መገበር ማለት ነው፤ ዳግምኛም ጾም እየከፈሉ ለነዳያን እየሰጡ ነው፤ ይህ ካልሆነ እያደለቡ መብላት ነው አይረባም። ድሃ እየቀሙ፣ እያስጨነቁ፣ ከሰው እየተጣሉ ቢጾሙ አይረባም፤ ዋጋም አይኖረውም። በእውነት የሚጾም ጸዋሚ የረኃብን ጾር ያውቃልና ለተራቡት ለሚለምኑትም ይራራ ዘንድ ይችላል ይገባልም። በአጠቃላይ ጾምን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት መጾምና ተገቢውን ድርጊት መፈጸም ከማይገባ ድርጊት መቆጠብ የእኛ የምእመናን አንዱ ድርሻ ነው፤ በመሆኑም የተቀደሰ ጾምን በተቀደሰ ሥርዓት ጹመን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እናገኝ ዘንድ በሥርዓቱ፣ በትሕትና፣ በንስሓና በተሰበረ ልቡና ሆነን ልንጾም ይገባል።

ይቆየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ምንጭ፦ ፍትሐ ነገሥት፣ የወንጌል ትርጓሜ፣ ፍትሐ ነገሥት ምን አለ በመምህር በጽሐ ዓለሙ፣ መጽሐፈ ምዕዳን በአባ ገብረ ኪዳን