የምእመናን ድርሻ በቤተ ክርስቲያን

ክፍል ሁለት
ዲያቆን ዳዊት አየለ
ጥቅምት ፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

በጸሎት ጊዜ ልናደርጋቸው የሚገቡ ሥርዓቶች፦

ጸሎት ሰው ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገራት ናት፤ የተበደለ ደኃ ከንጉሥ እንዲጮኽ ሰው ወደ ልዑል እግዚአብሔር የሚጮሃት ጩኸት ነች። ባለፈው እያመሰገነ፣ ለሚመጣው እየለመነ፣ የእግዚአብሔርን ጌትነቱን እየመሰከረ፣ በደሉን እያመነ እግዚአብሔርንም እራሱንም ደስ የሚያሰኝባት ጩኸት ናት። “ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነው” እንዳሉ ፫፻ ምዕት በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የበደለውን ይቅር በለኝ እያለ ለሚጸልይ ሰው ብዙ ሥርዓት አለው። አንድ ክርስቲያን ለጸሎት በቅድመ እግዚአብሔር ሲቆም መርሳት የሌለበት መሠረታዊ ነገሮች በተደረገለት ማመስገን፣ የፈጣሪውን ጌትነቱን መመስከር፣ በእርሱነቱ ውስጥ የጎደሉበትን ነገሮች እያሰበ እንዲመላለት መጠየቅ ናቸው። (መጽሐፈ ምዕዳን በርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን፣ ፍትሐ ነገሥት ምን አለ? በመምህረ መምህራን በጽሐ ዓለሙ)

ጸሎት ለሚጸልይ ሰው ሊያውቃቸውና ሊጠነቀቃቸው የሚገቡ ፮ ሥርዓቶች አሉ፤ የመጀመሪያው ከሁሉ አስቀድሞ ጥግ፣ መቋሚያ ሳይፈልግ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “…ማለዳ በፊትህ ቆሜ በባለሟልነት እገለጣለሁ…” እንዳለው በእግር ቀጥ ብሎ መቆም ነው፡፡ (መዝ.፭፥፫) በሁለተኛም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ “ወገባችሁ የታጠቀ ይሁን” ብሎ እንዳስተማረን የሥጋ ወገባችንን እንደታጠቅን ወገብ የተባለ ልቦናችንን በንጽሕና መታጠቅ ያስፈልጋል፤ (ሉቃ.፲፪፥፴፭) በሦስተኛም “መብረቅ ከምሥራቅ ብልጭ ሲል እስከ ምዕራብ እንዲታይ የወልደ እግዚአብሔር አመጣጡ እንደዚያ ነው” እንዲል በቅዱስ ወንጌሉ በልብ ሌላ ነገር እያሰብን ወዲህና ወዲያ ሳንል በክት ልቡና ፊታችንን ወደ ምሥራቅ ማዞር ይኖርብናል፤ (ማቴ.፳፬፥፳፯) በዐራተኛም ነገረ ሥጋዌውን፣ ከሲኦል ወደ ገነት እንደመለሰን እንዲሁም ለስቅለት ያበቃውን ቸርነቱን እያሰብን ጸሎት ስንጀምርና ስንፈጽም እንዲሁም መስቀልን በሚያነሡ አንቀጾች ሁሉ ጣቶቻችንን በመስቀል አምሳያ አመሳቅለን ገጻችንን ከላይ ወደ ታች ማማተብ ይጠበቅብናል፤ በአምስተኛም የምንጸልየውን ጸሎት በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ሆነን ምሥጢሩን እያስተዋልን ቀለሙ እንዳይነጥብ አድርገን “በምትጸልይበት ጊዜ አትቸኩል” እንደተባልን በቀስታ ሳንጮህ መድገም ነው፤ (ሲራ.፯፥፲) በስድስተኛም አስተብርኮና ስግደት የአምልኮና የተገዥነት ምልክት ነውና ጌታ አብነት ሊሆነን ሐሙስ ማታ ሲጸልይ እንደሰገደ፣ ስግደታችንን በአብራከ ነፍስ በእውነተኛ እምነት አድርገን፣ ለአንድነቱ ለሦስትነቱ በመገዛት ልንሰግድ ይገባል።

በጸሎት ጊዜ ሲጸለይ በቦታው ሁሉ ጣቶችን ዘርግቶ እጅን ማንሣት (ከፍ ማድረግ) ዓይንን ወደ ሰማይ ማንሣት ይገባል፤ ጌታ አልዓዛርን ባስነሣው ጊዜ እንዳደረገው፤ እንዲሁም ጸሎት ደረትን እየደቁ በፍጹም የንስሓ እንባ በትሕትና ሊሆን ይገባል። ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ሊጸልይባቸው የሚገቡ ሰዓቶች በአንድ ዕለት ውስጥ ሰባት ናቸው፤ እነርሱም፦

የመጀመሪያው ማለዳ ከፀሐይ መውጣት በፊት ጽልመተ ሌሊቱን አሳልፎ መዓልትን ስላሳየን፣ የሁሉ አባት አዳም የተፈጠረበት ሰዓት ስለሆነ፣ እንዲሁም ጌታ በጲላጦስ ፊት ቁሞ የተመረመረበት ነውና መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “…በማለዳ ቃሌን ስማኝ፥ በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ…” እንዳለው እኛም እጃችንን ፊታችንን ንጹሕ አርገን (ታጥበን) ወደ ዕለት ተግባሮቻችን ከመግባት በፊት በፊቱ (በእግዚአብሔር ፊት) ቆመን እንድንጸልይ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሠርታልናለች። (መዝ.፭÷፫)

ሁለተኛው በሦስት ሰዓት የምንጸልየው ጸሎት ነው። በዚህ ሰዓት የሁሉ እናት ሔዋን የተፈጠረችበት ሰዓት ነው፤ እመቤታችን ብሥራተ ገብርኤልን የሰማችበትና ጌታን ያለ ዘርዐ ብእሲ የፀነሰችበት ነው፣ ጌታ በጲላጦስ ፊት የተገረፈበት ነው፤ በጽርሐ ጽዮን መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደበት ነው፤ እንዲሁም “…ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ ከቀኑ ሦስት ስዓት በጉልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም” ተብሎ እንደተጻፈ ነቢዩ ዳንኤል የጸለየበት (ይጸልይ የነበረበት) ሰዓት ነውና በዚህ ሰዓት እግዚአብሔርን እንድናመሰግነው ሥርዓት ነው። (ዳን.፮÷፲)

ሦስተኛው የቀትር ጊዜ (ስድስት ሰዓት) ጸሎት ነው። በቀትር ጊዜ የፀሐይ ሙቀቷ ይጸናል፤ አእምሮ ይዝላል፤ ሰውነት ይደክማል፤ ያን ጊዜ አጋንንት ይሰለጥናሉና (ይበረታሉና)፤ እንዳይሰለጥኑብን “…ከአደጋና ከቀትር ጋኔን…” እንዳለው ቅዱስ ዳዊት (መዝ.፺÷፮)፣ አዳምም የካደበት ነው፤ ሄኖክ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ያጠነበት ነው፤ እንዲሁም ጌታ የተሰቀለበትም ሰዓት በመሆኑ ስለኛ ብሎ መከራ መስቀልን መቀበሉን እያሰብን በዚህች ሰዓት እንድንጸልይ ሥርዓት ነው።

አራተኛው በዘጠኝ ሰዓት የሚደረገው ጸሎት ነው። በዚህ ጊዜ ቀሌምንጦስ “በዘጠኝ ሰዓት መላእክት ለእግዚአብሔር ይገዛሉ፤ የሰው ልጆችም ሁሉ ጸሎት ወደ ልዑል እግዚአብሔር የምትደርሰው በዚሁ ሰዓት ነው ”እንዳለው መላእክት የሰውን ግብር የሚያሳርጉበት ጊዜ ነውና ክፉ ሥራችንን ትተው በጎ ሥራችንን እንዲያቀርቡልን፣ ጌታ መራራ ሐሞትን በመስቀል ላይ ስለኛ ብሎ የተቀበለበትን ክብርት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው የለየበት ነው፤ (ቀሌ.፫÷፰) እንዲሁም ሐዋርያት ለጸሎት ይወጡበት የነበረ ሰዓት በመሆኑ በዚህ ሰዓት የጌታችንን ሞቱን እያሰብን ልንጸልይ ሥርዓት ተሠርቶልናል።

አምስተኛው በሠርክ (፲፩ ሰዓት) የሚጸለይ ጸሎት ነው። በዚህች ሰዓት ጌታችን ወደ መቃብር የወረደበት፣ ነፍሳትን ገነት ያስገባበት ሰዓት ነው፤ ዳግመኛም ሠርክ የምጽአት ምሳሌ ነው፤ ሰው ሲሠራ ውሎ የሠራውን ዋጋ የሚቀበለው በሠርክ እንደሆነ ሁሉ ምእመናንም ሲጋደሉ ኑረው ዋጋ የሚያገኙት በምጽአት ነውና ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “…እጆቼ የሠርክ መሥዋዕትን አነሡ…” እንዳለ በሠርክ ጊዜ እንድንጸልይ ሥርዓት ነው። (መዝ.፩፻፵÷፪)

ስድስተኛው በንዋም ጊዜ የምንጸልየው ጸሎት ነው። የዕለቱን የሥራ ጊዜ አሳልፈህ የሌሊቱን የዕረፍት ጊዜ ስላመጣህልን እናመሰግንሃለን በማለት እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተያዘበትና “…አባት ሆይ የሚቻልስ ከሆነ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ…” እያለ በጌቴሴማኒ የጸለየበት ነውና በንዋም (መኝታ) ሰዓት አምላካችንን ልናመሰግነው ይገባል። (ማቴ.፳፮÷፴፱)

ሰባተኛው ጸሎተ መንፈቀ ሌሊት ነው። ጌታ የተወለደበት፣ የተጠመቀበትና የተነሣበት ዳግመኛም የሚመጣበት እንዲሁም ጳውሎስና ሲላስ የጸለዩቡት ሰዓት ስለሆነ ልክ እንደማለዳው የጸሎት ሰዓት ተናጽተን ልንጸልይ ይገባል።

እነዚህ ሰባቱን የጸሎት ጊዜያቶች ልክ “ስለ እውነት ፍርድህ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለው” እንዳለው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት እኛም ሳናስታጉል ልንጸልይባቸውና ልናመሰግንባቸው እንደሚገባ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያዛል። (መዝ.፻፲፰÷፻፷፬) የነግህ (ማለዳ) እና የሠርክ ጸሎት ቤተ ክርስቲያን ሊደረጉ ከሚገቡ መካከል ሲሆን ይልቁንም በሁለቱም ሰንበታት እና በበዓላት ቀን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን ልንጸልይ ይገባል። ስንጸልይ ጸሎታችን የሠመረ እንዲሆን ከቂም፣ ከበቀል፣ ከተንኮል፣ ከትዕቢት፣ የሥጋ ነገርን ከመውደድ ተለይተን ሊሆን ያስፈልጋል። (መጽሐፈ ምዕዳን በርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን፣ ፍትሐ ነገሥት ምን አለ? በመምህረ መምህራን በጽሐ ዓለሙ)

በቅዳሴ ጸሎት ጊዜ ከምእመናን የሚጠበቁ ሥርዓቶች፦

ቅዳሴ “ቀደሰ” “ባረከ፣ ለየ፣ አመሰገነ፣ አከበረ” ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም “ምስጋና፣ በንባብና በዜማ የሚጸለይ የቁርባን ጸሎት” ማለት ነው። (ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ ፲፻፴፫ እና ፲፻፴፬) ይህ ታላቅ ጸሎት በቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምእመናን በጋራ በኅብረት ከሚያከናውኑ ጸሎቶች አንደኛውና ከጸሎቶቹ ሁሉ በላይ የሆነ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ልዩ ምስጋና ነው፤ የእግዚአብሔር አንድነቱ፣ ሦስትነቱ፣ ሕማሙ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱና ዳግም ምጽአቱ የሚነገርበት የሚነሳበት ነው፤ ከሁለቱ ወገን (ከካህናትና ምእመናን) አንዳቸው ቢጎድሉ የጸሎት ሥርዓቱ መከናወን አይችልም። (ፍት.መን.አን.፲፪) በቅዳሴ ጊዜ ሁሉም ክርስቲያን አስቀድሞ ተገኝቶ የሚችል አስቀድሶ ሥጋውን ደሙን ይቀበል፤ ያልቻለ በአንቃዕዶ ልቦና በሰቂለ ኅሊና ሆኖ አስቀድሶ ከአምላኩ ጋር መገናኘትና በረከት ማግኘት መቻል አለበት። ማስቀደሳችንም ሆነ መቁረባችን ለነፍሳችን ድኅነት እንዲያሰጠን

ሥርዓተ ቅዳሴ በሚከናወንበት ቦታና ሰዓት የሚከተሉትን ሕግጋት መጠበቅ አለብን፡፡

ሥርዓተ ቅዳሴን ለመካፈል ከመሄዳችን በፊት የአእምሮምና የኅሊና ዝግጅት ያስፈልጋል፤ በክፍል አንድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ የምናደርጋቸው ጥንቃቄ ብለን ያየናቸውን ሥርዓቶችን ሁሉ ጠብቀን ተዘጋጅተን ልንሄድ ይገባል፤ ከገባንም በኋላ ተጀምሮ እስኪፈጸም በጥንቃቄና በሥርዓት ሆነን ልናስቀድስ ይገባል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተን ለቅዳሴ ስንቆም ወንዶች በወንዶች (በሰሜን) ሴቶችም በሴቶች (በደቡብ) በኩል እንደ ሥርዓቱ ልንቆም ያስፈልጋል። “ሁሉም በየመዓርጉ በመላእክት አምሳል ሊቆም ይገባል።” (ፍት.ነገ.አን.፲፪) የሚበቃ ቦታ ቢኖር ሕፃናት ለብቻ ይቁሙ፤ ካልበቃ ወንዶች ከአባቶቻቸው ጋር ሴቶች ሕፃናት ከእናቶቻቸው ጋር ይቁሙ። የሚያስቀድስ ሰው ሁሉም ቅዳሴው ከመጀመሩ አስቀድሞ ሊገኝ ይገባል፤ ቅዳሴው “አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” ተብሎ ከተጀመረ በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ብቻም ሳይሆን ወደ ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ መግባት አይቻልም።

ቅዳሴ ስናስቀድስ ከሐሳብ መከፋፈል ወጥተን፣ ሌላ ነገር ከማሰላሰል ተቆጥበን፣ በሙሉ ሐሳብችን በአንድ ልብ ሆነን ቅዳሴውን ብቻ እየተከታተልን ተሰጥኦ እየተቀበልንና እየመለስን ከእግዚአብሔር ጋር ልንገናኝ ይገባል፤ ተሰጥኦውን የማናውቅ ደግሞ በአንክሮ፣ በተዘክሮ፣ በአንቃእድዎ፣ በንጹሕ ልቡና፣ በሰቂለ ኅሊና ሆነን ኅሊናችን ወደ ዓለማዊ ነገር እንዳይወስደን መቆጣጠር አለበን። “በቅዳሴ ጊዜ የሚስቅ ሰው ካህን ቢሆን ሥጋውን ደሙን ተቀብሎ ወጥቶ አንድ ሱባኤ ይጹም፤ ሕዝባዊ ቢሆን ያን ጊዜ ወጥቶ ይሂድ ሥጋውን ደሙን አይቀበል።” (ፍት.ነገ.አን.፲፪)

በቅዳሴ ሰዓት መሳቅ፣ አጠገባ ካለው ሰው ጋርም ሆነ በስልክ ዋዛ ፈዛዛ መነጋገር ፈጽሞ የተከለከለ ነው። “አንዱስ እንኳን በቤተ መቅደስ የማይወደድ ሌላ ነገር አይናገር፤ በዙሪያውም ቢሆን አይናገር” የሥርዓት መጽሐፋችን እንዳለውም በቤተ መቅደስ ውስጥ ለምንሆነውና ለምናደርጋቸው ድርጊቶች ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል። (ፍት.ነገ.አን.፲፪) ከተቻለን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለቅዳሴ ስንሄድ ሐሳባችንን ሊሰርቁ የሚችሉ ነገሮችን (ስልኮቻችንንና የመሳሰሉትን) ቤት አስቀምጠን መሄድ ይገባል፤ ካልሆነም በቅዳሴ ሰዓት መጠቀም ከበረከቱ ስለሚያጎድለን ቅዳሴው እስኪያልቅ አለመጠቀም ይገባል።

በጊዜ ቅዳሴ ቀጥ ብለን ቆመን እያንዳንዱን የሚዜመውንና የሚነገረውን ቃል እያስተዋልን ግብረ መልስ ለሚያስፈልጋቸው እየመለስን (ስግዱ ሲባል መስገድ፣ ተንሥኡ ሲባል መነሣት/ልቦናን መነሣሣት)፣ ጸልዩ ሲባል መጸለይ፣ ተአምሁ ሲባል እጅ መንሣት፣ አትሕቱ ሲባል ዝቅ ማለት….ወዘተ) ሊሆን ይገባል፤ በቅዳሴ ጊዜ የግል ጸሎት ማድረስ ሥርዓት አይደለም፤ የግል ጸሎታችንን ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት መጨረስ ወይም “እትው በሰላም” ተብሎ ቅዳሴ ከተፈጸመ በኋላ ማድረስ ይገባል፤ “ከቤተ ክርስቲያን ገብቶ የሚነበቡትን መጻሕፍት የሚሰማ የቅዳሴ ጸሎት እኪፈጸም ድረስ ጸጥ ብሎ የማይቆም ከምእመናን ይለይ” (ፍት.ነገ.፲፪) እንዲል። ቅዳሴ ሳያልቅ አቋርጦ ከቤተ መቅደስም ሆነ ከቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ መውጣትም ሆነ መንቀሳቀስ ተገቢ አይደለም። ለዚህም ምስክር የሚሆነን “ክቡር ወንጌል ከተነበበ በኋላ በጭንቅ በሕመም ካልሆነ በቀር ሥጋውና ደሙ አንድ ሁኖ ተሰጥቶ ዲያቆኑ ሑሩ በሰላም ቄሱ ባርኮ ሳያሰናብት አንዱስ እንኳን ከቤተ ክርስቲያን አይውጣ” የሚለው የፍትሓ ነገሥት መመርያ ነው። (ፍት.ነገ. ፲፪)

ቅዳሴ በቤተ ክርስቲያናችን የሁሉ ነገር ማሠሪያ (መፈጸሚያ) ነውና ሥርዓቱንና ሕጉን ጠብቀን አክብረን የድርሻችንን እየተወጣን የምናስቀድስ ከሆነ በረከቱ ዕጥፍ ድርብ ይሆንልናል፤ ነገር ግን ከሕጉና ከሥርዓቱ ውጭ ሆነን በቅዳሴ ጊዜ ሌሎች ተግባሮችን የምናከናውን ከሆነ በቅዳሴው በኩል የምናገኛቸው ሁሉም ነገሮች ይቀሩብናልና እናስተውል፤ ይበልጥ ደግሞ በዕለተ ሰንበት ምእመን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ተአምሯን ሰምቶ፣ ቅዳሴውን አስቀድሶ፣ ስብከተ ወንጌልን ሰምቶ ከዚያም የታመመ ሲጠይቅ፣ የተጣላ ሲያስታርቅ፣ ያዘነ ሲያረጋጋና የነፍስ ሥራን መሥራት ግዴታው ነውና በዚህ ሥርዓት ልንመላለስ ያስፈልጋል። (ፍትሐ ነገሥት ምን አለ? በመምህረ መምህራን በጽሐ ዓለሙ)

ይቆየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!