የምሥጢር ቀን
በሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ፣
በምዕ/ጐጃም ሀገረ ስብከት የ፬ቱ ጉባኤያት መምህር
ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
ከስምንተኛ መዓርግ ላይ ደርሶ የተፈጠረው የሰው ልጅ (አዳም) ሕገ እግዚአብሔርን ተላልፎ የተከለከለውን ዕፅ በመብላቱ የተሰጠው ጸጋ ስለ ተወሰደበት ምሥጢረ መለኮትን ማወቅ ተስኖት ነበር፡፡ የአምላክ ሰው መኾን አንዱ ምክንያትም ምሥጢረ መለኮት ለተሰወረበት ዓለም ምሥጢረ መለኮትን መግለጥ ነው፡፡ ጌታችን ወደዚህ ዓለም ሲመጣም ዓለም ምንም ምሥጢር አልነበራትም፡፡ ምሥጢራት ዅሉ በልበ መለኮት ተሰውረው ይኖሩ ነበር እንጂ፡፡ በሌላ አነጋገር የተፀነሰ እንጂ የተወለደ ምሥጢር አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ከሕዝብ ለይቶ ምሥጢራትን ይነግራቸው የነበረው (ማቴ. ፲፫፥፲፩)፡፡ በቀዳማዊው ሰው በአዳም በኩል ለሰው ልጀች ዅሉ የተሰጠው የመንግሥቱ ምሥጢር በሁለተኛው ሰው በክርስቶስ በኩል ዳግመኛ ተገለጠ፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው ለቀደሙት ሰዎች በብዙ መንገድ በብዙ ኅብረ አምሳል ምሥጢራትን ይናገር የነበረ እግዚአብሔር ቅደመ ዓለም በነበረውና ተቀዳሚ ተከታይ በሌለው በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተናገረ (ዕብ. ፩፥፩-፪)፡፡ ማንም ያየው የሌለ እግዚአብሔርነቱን ወደ ዓለም መጥቶ ተረከው፡፡ በአብ ልብነት ተሰውሮ ይኖር የነበረውን የመንግሥቱን ምሥጢርም ከልደቱ ጀምሮ በብዙ መንገድ ገልጦታል፡፡ በልደቱ ቀን ከገለጸልን ምሥጢር የተነሣ ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት›› ብለን ዘመርን፡፡ ‹‹ይህንን ምሥጢር እናይ ዘንድ ኑ! እስከ ቤተልሔም እንሒድ›› (ሉቃ. ፪፥፲፭) ብለው ሲናገሩ ከእረኞች አፍ መስማታችንም ይህንኑ ምሥጢር ያስረዳል፡፡ ሶርያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ይህን ሲያጸናልን ‹‹ንዑ ርዕዩ ዘንተ መንክረ፤ ይህን ድንቅ ምሥጢር ታዩ ዘንድ ኑ!›› በማለት ሕዝቡን በዓዋጅ ይጠራል፡፡
እግዚአብሔር ለሰው የገለጠው ምሥጢር ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በፈጸመው የማዳን ሥራ በቤተ ኢያኢሮስ ምሥጢረ ድኅነትን፤ በቤተ አልዓዛር ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን፤ በጌቴሴማኒ ምሥጢረ ጸሎትን ካሳየ በኋላ በዕለተ ዐርብ መጋረጃው ተቀዶ የሰው ልጅ ባሕረ እሳትን ተራምዶ እስክናይ ድረስ ደገኛውን ምሥጢረ ድኅነት ገለጠልን፡፡ በደብረ ታቦር ደግሞ ምሥጢረ ሥላሴን ገልጦልናል፡፡ እግዚአብሔር ምሥጢራትን ለመግለጥ ሦስት መንገዶችን ይጠቀማል፤ እነዚህም ሰው፣ ጊዜ እና ቦታ ናቸው፡፡ በደብረ ዘይት የገለጠውን በደብረ ታቦር፣ በጌቴሴማኒ የገለጠውን በዮርዳኖስ፤ ለነቢያት የገለጠውን ለሐዋርያት አይገልጠውም፡፡ በተለይ በሐዋርያት ልቡና ያኖረውን፤ ከዅሉም በላይ ደግሞ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልቡና የሰወረውን ምሥጢሩን ማንም ፍጡር ሊያውቀው አይችልም፡፡ አበው እንደ ነገሩን በልበ ሐዋርያት ተሰውሮ የቀረውን የወንጌል ምሥጢር እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚያውቀው የለም፡፡ ምክንያቱም የሐዋርያትን ክብር ካላገኙ ሐዋርያት ያወቁትን ማወቅ ስለማይቻል ነው፡፡ ከሐዋርያት በኋላ ተነሥቶ ወደ ሐዋርያት መዓርግ መድረስ የተቻለው ቅዱስ ጳውሎስ ብቻ ነው፡፡ ክብር ይግባውና መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱ ልብ ሊያስቀምጠው የፈለገው አንድ ምሥጢር አለው፡፡ ይኸውም ጊዜው ሲደርስ የሚነገር፣ ከትንሣኤ በኋላ የሚበሠር እንጂ በማንኛውም ጊዜ የማይገለጥ አዲስ ምሥጢር ነው፡፡ ለዚህ ምሥጢር መገለጫ ይኾን ዘንድ የተመረጠው ቦታ ደግሞ ደብረ ታቦር ነው፡፡
ደብረ ታቦር ለምን ተመረጠ?
፩. ትንቢቱ፣ ምሳሌው ሊፈጸም
በቀደመው ዘመን ነቢያት ትንቢት ከተናገሩላቸው ቅዱሳት መካናት አንዱ ደብረ ታቦር ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ፤ ታቦርና አርሞንኤም በአንተ ስም ደስ ይላቸዋል›› (መዝ. ፻፹፰፥፲፪) በማለት ከደብረ ታቦር እስከ አርሞንኤም በደረሰው የመለኮት ብርሃን የተፈጠረውን ደስታ ሲገልጥ እንሰማዋለን፡፡ ምንድን ነው ይህ ደስታ? ሊባል ይችላል፡፡ ነቢዩ ከአንድ ሺሕ ዓመት በኋላ ስለሚደረገው፣ ተራሮችንና ኮረብቶችን ሳይቀር ስላስፈነደቀው ደስታ ይህን ትንቢት ተናገረ፡፡ ምናልባት ‹‹በአንተ ስም ደስ ይላቸዋል›› ብሎ ግዑዛን ለኾኑ ተራሮች ለሰው በሚናገር መልኩ መናገሩ ሊያስገርም ይችላል፡፡ የሰው የደስታው መገለጫ የገጹ ብሩህነት ነው፡፡ እነዚህ ተራሮችም በዚህ ዕለት በተገለጠው መለኮታዊ ነጸብራቅ የተነሣ ጨለማ ተወግዶላቸው የፀሐይን ብርሃን በሚበዘብዘው አምላካዊ ብርሃን፣ ብርሃን ኾነው የዋሉበት ቀን ነውና ነቢዩ ለሰው በሚናገርበት ግስ ተናግሮላቸዋል፡፡
ሌላም ምሥጢር አለው ይላሉ ሊቃውንቱ፤ ‹‹በአንተ ስም ደስ ይላቸዋል›› የሚለውን ኃይለ ቃል በተራሮች ስም የተጠሩት ልዑላኑ አገልጋዮች ነቢያትና ሐዋርያት በጌታ ስም ደስ ይላቸዋል ማለት ነው ብለው ይተረጕሙታል፡፡ ለምሳሌ በአባቶቻችን ዘመን በዚህ ቅዱስ ተራራ ጽኑ ሰልፍ እንደ ተደረገ በመጽሐፈ መሳፍንት እናነባለን (መሳ. ፬፥፩)፡፡ በእስራኤል ላይ ገዥ ኾኖ የተነሣው፣ በክፉ አገዛዙ ምክንያት እስራኤልን ያስለቀሰው አሕዛባዊው የሠራዊት አለቃ ሲሳራ ድል የተነሣው በዚሁ ሥፍራ ነበር፡፡ ደብረ ታቦር ዘጠኝ የብረት ሠረገሎች የነበሩትን ባለ ሠራዊት ሰው ሲሳራን ድል ለማድረግ ምቹ ቦታ ነበር፡፡ ያውም በጥቂት ኃይል በሴቲቱ ነቢዪት ዲቦራ በሚመራ የጦር ሠራዊት፡፡ ይህም በኋለኛው ዘመን ለሚደረገው የድል ዘመን ጥላ የኾነ ታሪክ ነው፡፡ አባቶቻችንን በብረት በትር ቀጥቅጦ የገዛውን ባለ ብዙ ሠራዊት ዲያብሎስን ከሴቲቱ ነቢዪት የተወለደው የይሁዳ አንበሳ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቅዱስ ሥፍራ ድል እንደሚያደርግላቸው፤ እስራኤል ዘነፍስንም ከዲያሎስ ባርነት ነጻ እንደሚያወጣቸው የሚያሳይ ምሥጢር ነበረው፡፡ ሲሳራን፤ ባራቅ እና ዲቦራ ድል ያደርጉታል ተብሎ ታስቦ ነበርን? ይልቁንም ሲገዛን ሊኖር አስቦ አልነበረምን? የድንግል ልጅ መድኃኒታችን ክርስቶስ ግን የሲኦልን በሮች ሰባብሮ ጠላታችንን በጽኑ ሥልጣን አስሮ ነጻ አወጣን፡፡ ምሳሌው አማናዊ የሚኾንበት ዘመን መድረሱን ሊያበስራቸውም ሐዋርያቱን መርጦ ወደ ደብረ ታቦር ይዟቸው ወጣ፡፡
፪. ደብረ ታቦር ዅሉን የሚያሳይ ቦታ ስለ ነበር
ደብረ ታቦር ላይ ቆሞ ዓለምን ቁልቁል መመልከት ይቻላል፡፡ ከተራራው ጫፍ ላይ ኾኖ ሲመለከቱ ዅሉም በግልጥ ይታያል፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ዼጥሮስ በዚህ ቦታ መኖርን የተመኘው ‹‹ሠናይ ለነ ሀልዎ ዝየ፤ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው›› (ማቴ. ፲፯፥፭) ሲል ነበር በተራራው የመኖር ፍላጎቱን የገለጠው፡፡ ደብረ ታቦር ዅሉንም ከላይ ኾኖ ለማየት የሚያስችል ከፍ ያለ ቦታ ነውና፡፡ ከዘመናት አስቀድሞ የተሰወረውን ምሥጢር ለዅሉ ግልጽ ሊያደርግ አስቦ ዅሉን ወደሚያሳየው ቦታ ወሰዳቸው፡፡ እግዚአብሔር ይህንን በምሥጢር አደረገ፡፡ በክርስቶስ ሰው መኾን ያልታየ ምሥጢር፣ ያልተገለጸ ድብቅ ነገር የለምና፡፡ አፈ በረከት ተብሎ የሚጠራው ቅዱስ ኤፍሬም በረቡዕ ውዳሴ ማርያም ላይ ‹‹የማይታወቅ ተገለጠ፤ የማይታይ ታየ›› ሲል የተናገረውም ስለለዚህ ነው፡፡ አሁን የማይታየውን እግዚአብሔርን የምናይባት ድብቁን የእግዚአብሔርን ነገር በእምነት የምናስተውልባት አማናዊቷ የታቦር ተራራ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በእርሷ ውስጥ የሚኖሩ ዅሉ ዓለምን ቁልቁል እየተመለከቱ ጣዕሟን ሲንቁባት ይኖራሉ፡፡ ከእርሷ ተለይተው ከላይ ከተራራው ጫፍ ኾነው ዓለምን ስለሚመለከቷት ቤታቸውን በተራራው ለማድረግ ይመኛሉ፡፡ ዅልጊዜም ‹‹እግዚአብሔርን አንዲት ልመና ለመንኹት፤ እሷንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ዅሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ›› (መዝ. ፳፮፥፬) እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዓለም ውስጥ ኾኖ የታቦር ተራራን (ቤተ ክርስቲያንን) ማየት አይቻልም፡፡ ከታቦር ተራራ (ቤተ ክርስቲያን) ላይ ኾኖ ግን የዓለምን ምሥጢር ማወቅ ይቻላልና፡፡
፫. በተራራ የተነጠቅነውን ጸጋ በተራራ ለመመለስ
አዳም እንደ አጥቢያ ኮከብ የሚያበራ፣ ግርማው የሚያስፈራ ብርሃናዊ ፍጡር እንደ ነበር፤ ሥነ ተፈጥሮውን የሚናገሩ መጻሕፍት ምስክሮቻችን ናቸው፡፡ ይህንን ብርሃናዊ የጸጋ ልብሱን ተጐናጽፎ የተቀመጠው በእግዚአብሔር ተራራ በገነት ነበር፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ የጠላት ዐይን አርፎበት ኖሮ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ይህን ብርሃናዊ ልብሱን ለብሶ እንደ ማለዳ ኮከብ እያበራ መኖር አልተቻለውም፡፡ እናም በዚያው በእግዚአብሔር ቅዱስ ተራራ ላይ ሳለ ይህን ጸጋዉን ባለማወቅ ተገፈፈ፡፡ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው የተቀማነውን ጸጋ ለማስመለስ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ቅዱስ ተራራ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ በገለጠው ብርሃን ተስፋን አስጨበጠን፡፡ ቅዱስ ወንጌል እንደ ተናገረው በዚህ ዕለት ሐዋርያት፣ ነቢያት በተገኙበት በዚህ ሥፍራ የክርስቶስ አካል ብሩህ፤ ልብሱም ከበረዶ ይልቅ ነጭ ኾነ፡፡
የሰው ልጅ ከቅዱስ ተራራ ከገነት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እንዲህ ኾኖ ታይቶ አያውቅም፡፡ ሰውነቱ በኃጢአት በልዞ በበደል መግነዝ ተገንዞ የሚያስቀይም መልክ ይዞ ይታይ ነበር እንጂ እንደዚህ ዓይነት መልክ አልነበረውም፡፡ ዛሬ ግን እንደዚያ አይደለም፤ የአዳም አካል መልኩ ተለውጧል፡፡ ከጥቁረቱ ነጽቷል፡፡ ወንጌላውያን ይህን ምሥጢር ሲገልጡት ‹‹ወተወለጠ ራዕዩ በቅድሜሆሙ፤ መልኩ በፊታቸዉ ተለወጠ›› (ማቴ. ፲፯፥፪፤ ማር. ፱፥፪)፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ ተብሎ የሚጠራው የአገራችን ሊቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ይኼን ኃይለ ቃል ሲተረጕም ክርስቶስ በዚህ ዕለት የተገለጠው አዳም ከበደል በፊት በነበረው መልኩ እንደ ኾነ መጽሐፈ ምሥጢር በተሰኘው ድርሳኑ ይናገራል፡፡ ‹‹ዘይገሥሦሙ ለአድባር ወይጠይሱ፤ ተራሮችን በእጁ ሲዳስሳቸው የሚጤሱት›› ተብሎ ስለ እግዚአብሔር ኃያልነትና እርሱ ሲዳስሳቸው ተራሮች እንደሚቃጠሉ ሊጦን በተሰኘው የምስጋና ክፍል ተነግሯል፡፡ ታቦር ታዲያ እንደምን አልተናወጠችም? ሊቁ እንደ ተናገረው ባይኾን ኖሮማ ደብረ ታቦር ትፈራርስ ነበር፡፡
እግዚአብሔር ለሙሴ በተገለጠበት ተራራ ሕዝቡ የሚደርሱበትን አጥተው እስኪንቀጠቀጡ ድረስ ከባድ የመብረቅና የነጐድጓድ ድምፅ ይሰማ ነበር (ዘፀ. ፲፱፥፲፰)፡፡ አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ የተገናኘውን የመልከ ጸዴቅን ግርማ በዐይኖቹ መመልከት አልችል ብሎ መልከ ጸዴቅ ቀርቦ እስኪያነሣው ድረስ በፊቱ እንደ በድን ኾኖ ወድቋል፡፡ የእስራኤል ልጆችም ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገር የነበረው የሙሴን ፊት ለማየት ተስኗቸው ፈርተዋል፡፡ የዛሬው ምሥጢር ግን ከዚያ ልዩ ነው፡፡ በደብረ ታቦር ከተገለጠው የእግዚአብሔር ክብር የተነሣ በዙሪያው የነበሩትን ዅሉ እንደ በድን ያደረገ የብርሃን ነጸብራቅ ከክርስቶስ ፊት ወጥቷል፡፡ ምሥጢሩም አዳም ከመርገም በፊት የነበረውን የጸጋ ግርማ ሞገስ የሚያሳይ ነው፡፡ ይኸውም በቅዱሱ የእግዚአብሔር ተራራ በገነት የተነጠቅነው ልጅነታች፤ እንደዚሁም የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ ግርማ ሞገሳችን እንደ ተመለሰልን ያጠይቃል፡፡ በመጀመሪያው ሰው በአዳም ያጣነውን የልጅነት መልካችንን በሁለተኛው ሰው በክርስቶስ አገኘነው፡፡
እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ይህ ጸጋ በቤተ ክርስቲያን ሲታደል ይኖራል፡፡ ወንዶቹ በተወለዱ በዐርባ፤ ሴቶቹ ደግሞ በሰማንያ ቀናቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው በማየ ገቦ ተጠምቀው ዳግመኛ ከብርሃን ተወልደው ሰይጣንን የሚያስደነግጥ መልክ ይዘው ወደየቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ ያስተውሉ! ደብረ ታቦር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በደብረ ታቦር ነቢያትና ሐዋርያት፣ መዓስባንና ደናግል፣ አረጋውያንና ወጣቶች እንደ ተገኙ ዅሉ ቤተ ክርስቲያንም በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነጸች፤ ለመዓስባንና ለደናግል፣ ለአረጋውያንና ለወጣቶች ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን የተዘጋጀች የእግዚአብሔር መገለጫ ተራራ ናት፡፡ ከነቢያት ሁለቱ፤ ከሐዋርያት ሦስቱ መገኘታቸው ዛሬ በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉት አምስት ልዑካን ምሳሌ ነው፡፡ እነዚያ ክርስቶስን እንደ ታቦት በመኻል አድርገው እንደ ተገኙ፣ ዛሬም ልዑካኑ (አገልጋዮች) በቤተ ክርስቲያን በቃል ኪዳኑ ታቦት ዙሪያ የክብሩን ዙፋን ከበው ይቆማሉ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡