የማይቀበሩ መክሊቶች

   በዲ/ን ምትኩ አበራ

 

«ወደ ሌላ አገር የሚሔድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንዲሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፣ ለእያንዳንዱ እንደአቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያው ሔደ…» ማቴ 25÷14  ይህንን ታሪክ ማንሣታችን በወርኃ ዐቢይ ጾም በዕለተ ገብርሔር አንድም እየተባለ የሚተነተነውን ቃለ እግዚአብሔር ለማውረድ ተፈልጎ አይደለም፡፡

ጌታችን የተናገራቸው ሁለቱ ኃይለ ቃላት የሚያስደምሙ ስለሆኑ ነው «… እንዲሁ ይሆናልና” የሚለውና «ለእያንዳንዱ እንደአቅሙ» የሚሉት፡፡ ጌታችን እንዳለው እንዲሁ እንዳይሆንብን ዳሩ ግን እንዲሁ እንዲሆንልን ቅዱስ ፈቃዱን እየተማፀን ለእያንዳንዳችን እንደአቅማችን የተሰጡንን የማይቀበሩ መክሊቶች በአጭሩ እንመልከት፡፡

እንደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሥርዓትና እምነታችን እኛ በአርባና በሰማንያ ቀናችን በጥምቀት ከቅድስት ቤተክርስቲያናችን የተወለድን ሁላችን፤ ባለጸጎች/የጸጋ ባለቤቶች፣ ነን « እንደተሰጠን ጸጋ ልዩ ልዩ ሥጦታ አለን» ሮሜ 12÷6 ነገር ግን አንዳንዶች የተሰጠንን ጸጋ ባለማወቅ፣ ሌሎቻችንም የያዝነው ጸጋ ስጦታ ሳይሆን በእኛ ጥበብ ያገኘነው እየመሰለን ወዘተ… እንኳንስ ልናተርፍባቸው ቀርቶ ቀብረናቸው፤ የጸጋውን ባለቤት «አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፡፡ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁና ፈራሁህ፣ ሔጄም መክሊትህን በምድር ቀበርኩት እነሆ መክሊትህ» ለማለት የተዘጋጀን ይመስላል ማቴ 25÷24፡፡

እንድናተርፍባቸው ከተሰጡንና የማይቀበሩ ከሚባሉት መክሊቶቻችን መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

ዕውቀት

ዕውቀት ለፍጡራን ሁሉ የባሕርይ ሳይሆን ተከፍሎ የሚሰጥና የሚነሳ /የሚወሰድ/ ነው፡፡ ይህ ዕውቀት መክሊት/ስጦታ/ ነው፤ 1ቆሮ21÷7 የተሰጠበት ምክንያት ደግሞ እንድንታበይበት ሳይሆን ለሌላው እንድንጠቅምበት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ «ዕውቀት ያስታብያል»  ስለሚል አበው ሲመርቁ ዕውቀት ያለትዕቢት ይስጥህ፤ ይላሉ 1ቆሮ1-3፡፡ ዲያብሎስ አዋቂ ተደርጐ ተፈጥሯልና አዋቂ ነው፡፡ በዚህ ዕውቀቱ ግን እሱ ጠፍቶበት ሌላውን ለማጥፋት ይተጋበታል እንጅ ለሌላው ለመጥቀም አንዳች አይሠራም፡፡ ሰው በተሰጠው ዕውቀቱ በጎ ሥራን እንዲሠራበትና ለሌላው እንዲተርፍበት እግዚአብሔር ይሻል፡፡ እግዚአብሔር የሚጠይቀን በተሰጠን የዕውቀት መክሊት ክፉ ሥራ ስለሠራንበት ብቻ አይደለም በዕውቀታችን መጠን ያላወቀውን ከማሳወቅ ጀምሮ ምን ያህል እንደሠራንበት ይመረምረናል፡፡ ስለዚህ ብዙ ባወቅን ቁጥር ብዙ ማትረፍ እንዳለብን መረዳት ያሻል፡፡ «ብዙ ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል» ተብሏልና፡፡

 ሀብት

በመጀመሪያ ደረጃ ሀብታም/ባለሀብት/ መሆን በክርስትና ሕይወት አይነቀፍም፡፡ ለእግዚአብሔር ፍርድ ምድራዊ ሀብት መመዘኛ አይሆንም፡፡ እሱ ሀብታሙን ፈርቶ ድሃውን ንቆ ሳይሆን ለሁሉም እንደየሥራቸው ነው የሚፈርድባቸው፤ ራዕ 22÷12 ሀብት በምንለው በዚህ ዓለም በንብረትና ገንዘብ በከበርን ጊዜ ሁላችን ልናስታውሰው የሚገባ ቁምነገር አለ፡፡

•  አንደኛ የሰጠን እግዚአብሔር መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ እርግጥ ነው ወጥተን ወርደን ጥረን ግረን ሥራ ሳንመርጥ በላባችን ወዝ ያፈራነው የድካማችን ውጤት ነው፡፡ ግን ይህን ሁሉ ብቻችንን ልናደርገው አንችልም፡፡ በመግባት በመውጣታችን ጊዜ የረዳን፣ ጉልበታችንን ያጠነከረ፣ እጃችንን ያበረታ፣ ጤናውን የሰጠን እግዚአብሔር ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ መጽሐፍ «ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ እንዳትል» የሚለን /ዘዳ 8÷17/፡፡

• ሁለተኛው ደግሞ ታማኝ መጋቢ እንድንሆንለት ማለትም ቀን ከፍቶበት ሆድ ብሶት ሲቸገር ያየነውን ወንድማችንን ችግሩን እንድናስወግድለት ላጣውና ለነጣው ድሃ እንድንደርስለት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ቅዱስ ልጁ ለጢሞቴዎስ «ባለጠጎች ሊረዱና ሊያካፍሉ የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው» ያለው፤ ይህንኑ ለማስታወስ ነው 1ኛ ጢሞ 6÷19 ጠቢቡ ሰሎሞንም ሀብት የማትረፊያ መክሊት መሆኑን ሲያስረዳ «ያለውን የሚበትን ሰው አለ፤ ይጨመርለታልም፤ ያለቅጥ የሚነፍግ ሰውም አለ ይደኸያልም»  ነው ያለው ምሳ 11÷24 ይህ ሰው ለሰዎች ሲሰጥ በምድር ይከፍሉኛል ብሎ አስቦ ባለመሆኑ የሚበትን በማለት በዚህ በሚያልፈው ምድራዊ ሀብት የማያልፈውን ሰማያዊ ሀብት ማትረፍ እንዲቻል የነገረንን ልብ እንበል፡፡ ቀላል ምሳሌ እናስቀምጥ፤ በሰፈራችን አንድ ትልቅ ድግስ ላይ የድግሱ ባለቤት ጐረቤቶቹንና ወዳጆቹን ጠርቶ፤ የድግሱ እድምተኞች ከመምጣታቸው አስቀድሞ፤ አንዱን ወጥቤት፣ ሌላውን ሥጋ ቤት፣ ሌላዋን እንጀራ ቤት ወዘተ እያለ ይመድባል፡፡ እነዚህ ሰዎች የድግስ ቤቱ ሹማምንት ቢሆኑም ድግሱ የእነሱ አይደለም ስለዚህ በሰው ድግስ ለመጠቃቀም አንዱ ባዶ ሳህን ይዞ እያዩ ለሌላው ሁለተኛ እንጀራ ቢደርቡለት፣ አንዱ ደረቅ እንጀራ እየበላ ለሚያውቁት የሰፈራቸው ሰው የወጥ ሳህኑን አቅርበው ወጡን ቢገለብጡለት፣ የሰው ድግስ በማበላሸታቸው ይጠየቁበታል እንጂ አይመሰገኑበትም የዚህ ዓለም ባለጸጐችም እንዲሁ ናቸው የተሰጣቸው ሀብት ሊያጋፍሩበት፣ ሊያስተናብሩበት፣ መክሊት ሊያተርፉበት እንጂ በዚህ ዓለም ሊመራረጡበት በልጠው ሊታዩበት ወዘተ… አይደለም፡፡ « የአመጻ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሏችሁ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ” የተባለውን፤ ባለጸጎች ሁሉ ልብ ሊሉት ይገባል፡፡/ሉቃ 16÷9/

ሥልጣን

ሌላኛው መክሊት ሥልጣን ነው፡፡ ሥልጣን ሲባል ሁሌም ትዝ የሚለን ያየነውም እሱኑ ብቻ ስለሆነ ይመስላል፤ መፍለጥ መቁረጥ፣ ማራድና ማንቀጥቀጥ ነው፡፡ ተረታችንም «ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል» የሚል ነው፡፡ በዚህ መንፈስ ብዙዎች «እኔ እግዚአብሔርን ብሆን ኖሮ…» ብለው የሚፎክሩት አይሆኑም እንጂ ቢሆኑ ኖሮ፤ ከቤተ ክርስቲያን የሚያባርሩት፣ ከሥልጣን የሚሽሩት ወደሞት የሚያወርዱት ባጠቃላይ የሚፈልጡትና የሚቆርጡት ብዙ ነው፡፡ አላወቁትም እንጂ እግዚአብሔርን መሆን እነሱ እንዳሰቡት መቅሰፍ መግደል ብቻ ሳይሆን፤ እግር ማጠብ በጥፊ መመታት፣ በምራቅ መታጠብ፣ የእሾህ አክሊል መድፋት፣ በጦር መወጋት፣ ለሰው ልጆች ድኀነት መሰቀልና መሞትም ነው፡፡  በአንጻሩ በተሰጠው መክሊት ያላተረፈው፤ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል በሚል አሳብ ተተብትቦ፤ ሥልጣን መፍለጥ መቁረጥ የመሠለው ምስኪን የሚያገኘውን ዕድል በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፡፡ «ያባሪያ ግን ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ፣ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ሰዓት ይመጣል ከሁለትም ይሰነጥቀዋል ዕድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርጋል፡፡» /ሉቃ 12÷42-46/፡፡ ጥሩ ክርስቲያን ባለሥልጣን ሲሆን አይኮፈስም፤ «ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው፡፡» ተብሎ እንደተጠቀሰው፤ በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ በመሾሙ እንደጠቢቡ ሰሎሞን ይህንን ሕዝብ የማስተዳድርበት ጥበብ ስጠኝ እያለ ወደ ፊጣሪው በመጸለይ መክሊቱን ለማትረፍ ይተጋል፡፡

አንድ ታሪክ እናስታውሳችሁ፤ የሊቀ ጳጳሱ የዲሜጥሮስን ወደ ጵጵስና መዓርግ መምጣት እናቱ ሰምታ «ሹመት ያዳብር» ትለው ዘንድ አስቦ መልእክተኛ ይልክባታል እሷ ግን አንዳች አለመናገሯን ከመልእክተኛው የተረዳው ሊቀጳጳሱ ዲሜጥሮስ «ይህን የሚያህል መዓርግ አግኝቶ እንዴት በመልእክተኛ ይልክብኛል» ብላ ይሆናል ይልና ራሱ ለመሔድ ይወስናል፡፡ የጵጵስና መዓርግ ልብሱን ለብሶ በአጀብ ወደ እናቱ የደረሰው ሊቀጳጳሱ ዲሜጥሮስ የጠበቀው ግን ሌላ ነው፡፡ እናቱ ደስታዋን አልገለጠችለትም፡፡ ይልቁንም «እንዲህ ሆነህ /በመዓርግ ልብሱ/ ከማይህ ሞተህና ተገንዘህ አስከሬንህ በሳጥን ሆኖ ወደመቃብር ስትወርድ ባይህ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም በፊት በራስህ ኃጢአት ብቻ ነበር የምትጠየቀው፡፡ አሁን ግን በተሾምክላቸው ምእመናን ኃጢአትም ትጠየቃለህ» አለችው፡፡ አባታችን ዲሜጥሮስ ይህ የእናቱ ንግግር ተግሣጽ ሆኖት ዕድሜውን ሙሉ የምእመናንን ነፍሳት ለመታደግ ሲወጣ ሲወርድ ኖሯል፡፡ስለሆነም ሥልጣነ ሥጋም ሆነ ሥልጣነ መንፈስ የተሰጠን ለማትረፊያነት ነው፡፡

 ትዳር

ክብር ምሥጋና ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእውነተኛ ትዳርን አንድነት የባልና የሚስትን ኑሮ ባስተማረበት አንቀጽ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር «… ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው…. ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ. ….ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው አንጂ ወደፊት ሁለት አይደሉም እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው … ያለዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላይቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል አላቸው … » ማቴ 19÷4-9

ይህንን ትምህርት አጠገቡ ሆነው በቀጥታ ሲሰሙ የነበሩት ደቀመዛሙርቱ የባልና የሚስትን ሥርዓት ጥሩ ነው ብለው አላሳለፉትም፡፡ ይልቁንም « የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም» አሉት፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ጌታ «ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም…» ብሎ ሐዋርያትን በትዳር ላይ ያላቸውን አቋም እንዲያስተካክሉ ያደረጋቸው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ጌታችን ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው ሲል ትዳር ከእግዚአብሐር ተፈቅዶ የተሰጠና የሚሰጥ መሆኑንም ጭምር ነግሮናል፡፡ ብዙዎች ወዳጅ የሚሏቸውን ጠጋ ብለው «እባክህን ጥሩ ሚስት ፈልግልኝ እባክሽን ጥሩ ባል ፈልጊልኝ» ይሏቸዋል፡፡ ትዳር « ለምኑ ይሰጣችኋል ፈልጉ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችኋል…» ማቴ 7÷7 ከተባልናቸው ጉዳዮች ውስጥ በመሆኑ፤ ስንፈልግ የምንለምነው እግዚአብሔርን የሚሰጠንም ከእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ሰዎች ምክንያቶች ናቸው፡፡ ለዛውም እንደአብርሃም ሎሌ ታማኝና ቅን ከሆኑ ብቻ /ዘፍ 24÷1-97/፡፡እንግዲህ ልብ እንበል፤ ትዳር የዚህን ዓለም ኃላፊና ጠፊ ተድላ፤ ደስታ ብቻ ፈጽመን የምናልፍበት ሳይሆን፤ በሚታየው የማይታየውን፣ በሚጠፋው የማይጠፋውን ገንዘብ እንድናደርግበት ማለትም እንድናተርፍበት የተሰጠን መገበያያ መክሊት ነው፡፡ በጥሩ ክርስቲያናዊ ሥርዓት የመሠረትነው ትዳራችን መክሊት መሆኑን ከተረዳን ትዳርን እንደጦር በመፍራት ከጋብቻ ለሸሹ ሰዎች አርአያ እንሆንበታለን፡፡ ከሁሉ የበለጠው ደግሞ ለቤተ ክህነቱም ሆነ ለቤተመንግሥቱ የሚሆን ምርጥ ዘር አገርንና ወገንን የሚጠቅም ዜጋ /ልጆች/ እናስገኝበታለን፡፡ በዚህ ትርፋችን ይበዛል መክሊት መባሉም ለዚህ ነው፡፡ ከላይ እንዳየናቸው ሁሉ ሙሉ አካላችን፣  ጤናችን፣ ውበታችን፣ ልጆቻችን ወዘተ…እነዚህ ሁሉ   የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው፡፡ ስጦታዎቹ ማትረፊያ መክሊቶች በመሆናቸው «ከብዙ ዘመንም በኋላ የነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው፡፡» ተብሎ እንደተጻፈ ቁጥጥር አለብንና ልናስብበት ይገባል ማቴ 25÷19/፡፡

ዕድሜ

ዕድሜ መስታወት ብቻ ሳይሆን መክሊትም ነው፡፡ ግን ስንቶቻችን በብድር ዕድሜ ላይ እንዳለን እናውቅ ይሆን? እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጅ ዘመንን በዓመት፣ በወር፣ በሳምንት፣ በቀን፣ በሰዓት፣ በደቂቃ፣ በሰኮንድ… ወዘተ እየለካና እየገደበ አመላልሶ በመቁጠር ይጠቀምበት ዘንድ ዘመንን በቁጥር ሰጥቷል፡፡ «… ዘመንን ቀንን በቁጥር ሰጣቸው…» እንዲል /ሲራ17÷1/ በዚህ በሚለካውና በሚሰፈረው የቁጥር ዘመን ውስጥ የእያንዳንዳችን ዕድሜ ይገኝበታል፡፡ ያም በእግዚአብሔር ዘንድ የተወሰነ ነው፡፡ « የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው የወሩም ቁጥር በአንተ ዘንድ ነው፤ እርሱም ሊተላለፈው የማይችለውን ዳርቻ አደረግህለት…» ኢዮ 14÷5 ይለናል፡፡

«ሺሕ ዓመት አይኖር» እያልን የምንገልጸውም ይህንኑ ነው፡፡ ዕድሜ ገደብ አለው ለማለት ነው፡፡ በዚህ ንግግር ዘለዓለም አለመኖርን ለመግለጽ እንደታሰበ ልብ ይሏል፡፡ ቅዱስ ዳዊትም ይህንኑ ሺህ ዓመት አይኖር የሚለውን አባባል ሲያጐላው « የሰው ዕድሜ ሰባ ዓመት ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፡፡» ይላል፡፡/መዝ 89÷10/ይህንን ውሱን የሆነውን ዕድሜያችንን የሚሰጠን እግዚአብሔር ሲሆን፤ ጊዜውም ከየዕለት ደቂቃዎች ጀምሮ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርገው ሥራችን ለዚህ አብቅቶን ሳይሆን በቸርነቱ ነው «በቸርነትህ ዓመታትን ታቀናጃለህ፡፡» ተብሏልና /መዝ 65÷11/

እግንዲህ ጊዜ የተሰጠን፣ ዘመን የተሻገርነው፣ ዕድሜም የተጨመረልን፤ እንደትጉህ ነጋዴ በቅንነት ወጥቶና ወርዶ ነግዶና አትርፎ የጽድቅ ሥራ ሠርቶ ለመገኘት እንጂ፤ እንደዛ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ ልንቀብረው አይደለም አበው ሲመርቁ ዕድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ ይስጥህ የሚሉት፤ በዕድሜያችን ንስሐ እንድንገባበት በዘመኑም እንድንደሰትበት ለእኛ መሰጠቱን ተረድተውት ነው፡፡ የሚያጠግብ እንጀራ እምጣዱ ላይ ያስታውቃል እንዲሉ፤ ከዘመን ዘመን በመሸጋገሪያው ዋዜማ ምሽት ጀምረን በዘፈንና በጭፈራ በማንጋት የተቀበልነው ዕድሜና ዘመን፤ ዘመኑም የፍስሐ ዕድሜውም የንስሐ አይሆንም፡፡ ያውም እኮ የእግዚአብሔር ቃል «የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞችም በስካርም በዘፈንም ያለልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣኦት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና፡፡…» እያለን     1 ጴጥ 4÷3፤ ውሻ እንኳን ወደበላበት ሲጮህ እንዴት የሰው ልጅ የሚያኖረውን፣ ከዘመን ወደ ዘመን የሚያሸጋግረውን ያጣዋል፡፡ «በሬ  የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ ፤ እስራኤል ግን አላወቀም ሕዝቤም አላስተዋለም…» ያለው ቃል ትዝ ሊለን ይገባል በእውነት ጋጣችንን እንወቅ፡፡ /ኢሳ 1÷3/ የተሰጠንን የዕድሜ መክሊት አንቅበረው፡፡

ባለፈው ዓመት ያልታረቅን ዘንድሮ እንታረቅ፤ ባለፈው ዓመት ስንሰክር የነበርን ዘንድሮ ልብ እንግዛ፤ ባለፈው ዓመት ንስሐ ያልገባን ዘንድሮ ንስሐ እንግባ እንቁረብ፤ ባለፈው ስናስጨንቅ የነበርን ዘንድሮ እናጽናና፤ ይኼኔ ነው በዕድሜ መክሊታችን በእጥፍ የምናተርፈውና «አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ ወደ ጌታህ ተድላ ደስታ ግባ» የምንባለው፡፡ ዕድሜያችን ልናተርፍበት የተሰጠን መክሊት ያውም በብድር መሆኑን መቼውንም ቢሆን አንዘንጋው፤ ሉቃ 13÷6-9 ዘመኑ ዘመናችን ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ ይፈጥናል፡፡ «… የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡» እንዳንባል ይልቁንም በዚህ አጭርና ፈጣን ዘመናችን ራሳችንንና ሌላውን የእግዚአብሔርን ፍጡር ሁሉ እንጠቀምበት፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤ እንዳለው፤ እንዳይፈ ረድብን ራሳችንን እንመርምር፡፡ አንድም በስንሐ አንድም የተሰጡንን የምናተርፍባቸው እንጂ የማንቀብራቸውን መክሊቶቻችንን ቀብረናቸው እንዳገŸ ለሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም ምልጃ ይርዳን፡፡ 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር