የማይስማሙትን እንዲስማሙ አድርጎ ፈጠራቸው
ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ
እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ከሰባት እርስ በርሳቸው ከማይስማሙ ነገሮች ፈጥሮታል:: አራቱ ባሕርያት እግዚአብሔር በጥበቡ ካላስማማቸው በቀር መቼም የማይስማሙ ባላንጣዎች ናቸው፡፡ ምን አልባት ተስማምተው ከተገኙም በጽርሐ አርያም ባለው የእግዚአብሔር ማደሪያ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚያ ግን ባለጠጋው እግዚአብሔር የውኃ ጣራ፤ የእሳት ግድግዳ ያለው አዳራሽ ሠርቷል፤ ዓለም ከተፈጠረ እስከ ዛሬ ተስማምተው ይኖራሉ እንጂ አንዱ ባንዱ ላይ በክፋት ተነሳስቶ ውኃው እሳቱን አሙቆት፤ እሳቱም ውኃውን አጥፍቶት አያውቅም፡፡ ይህ ትዕግስታቸው በፍጥረት ሁሉ አንደበት ሠሪያቸውን እንዲመሰገን አድርጎታል::
በታች ባለው ምድራዊ ዓለምም ያለው ብቸኛው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሰው ልጅ ነውና እነዚህ እርስ በእርስ የማይስማሙ መስተጻርራን ነገሮች ተስማምተው የሚኖሩበት ዓለም ሆኗል፡፡ እሳት ከውኃ፤ ነፋስ ከመሬት ጋር የሚያጣብቃቸውን የፍቅር ሰንሰለት የሰው አዕምሮ ተመራምሮ ሊደርስበት የማይችል ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ ግን እንዴት ይሆናል? ነፋስ መሬትን ሳይጠርገው፤ መሬትም ነፋስን ገድቦ ይዞ መላወሻ መንቀሳቀሻ ሳያሳጣው፤ ተስማምተው እንዲኖሩ ያደረገ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፡፡ ውኃና እሳት ተቻችለው አንድ ቤት ውስጥ መኖር ችለዋል፤ የጥንት ጠላትነታቸውን በጥበበ እግዚአብሔር አስታራቂነት እርግፍ አድርገው ትተው ከሞት በቀር ማንም ላይለያቸው በቃል ኪዳን ተሳስረዋል፡፡
አሁን እሳት ውኃን በቁጣ ቃል አይናገረውም ውኃም በእሳት ፊት ሲደነግጥ አይታይም እንዲያው ሰው በሚባለው ዓለም ውስጥ በሰላም ይኖራሉ እንጂ፡፡ የነቢዩ ዳዊት ቃል ለነርሱ ያለፈ ታሪክ ማስታወሻ ቃል ነው፡፡ “ከመጸበል ዘይግህፎ ነፋስ እምገጸ ምድር፤ ከምድር ገጽ ላይ ነፋስ እንደሚበትነው አፈር…..” ይባል ነበር አባቶቻችንም ስለ ወንጌላዊው ማቴዎስ ሲተርኩልን “ሶቤሃኬ ተንሥአ ማቴዎስ ወንጌላዊ ከመ ተንሥኦተ ማይ ላዕለ እሳት፤ ውኃ በእሳት ላይ በጠላትነት እንዲነሣ ወንጌላዊው ማቴዎስም ተናዶ ተነሣ” በማለት ወንጌልን ለመጻፍ የተነሣበትን ምሥጢር አጫውተውናል፡፡ ማንኛውም ነገር አጥፊና ጠፊ ሆኖ ከተነሣ በእሳትና በውኃ መመሰል የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልዩ ሥነ ተፈጥሮ ባረፈበት የሰው ሕይወት ግን እንዲህ አይደለም፡፡ እሳትና ውኃ እስከ መቃብር የሚዘልቅ የፍቅር መንገድ ጀምረዋል ነፋስና መሬትም እስከ ፀኣተ ነፍስ ላይለያዩ ወስነዋል፡፡ ይህ የፍቅር ኑሯቸው ደግሞ ሌላ አዲስ ነገር ፈጠረላቸው ለመላእክት እንኳን ያልተደረገ አዲስ ነገር እግዚአብሔር በሰው ሕይወት ላይ እንዲያደርግ አስገድዶታል፤ የማትሞትና የማትበሰብስ ነፍስን በሥጋ ውስጥ አኖራት፡፡ ሌላ አስደናቂ ነገር ነው፡፡ የአራቱ መስተጻርራን መዋሐድ የፈጠረው ሌላ አስደናቂ መዋሐድ፡፡
በጥቂቱም ቢሆን ከመላእክት ጋር ዝምድና ያላት ነፍስ በእጅጉ ከማይስማማት የሥጋ ባህርይ ጋር ተስማምታ መኖሯ አስደናቂ ነገር ነው፡፡ አራቱ ባህርያት ልዩነታቸውን አጥፍተው በፍቅር ተስማምተው ብታይ እሷም ሁሉን ረስታ ከሥጋ ጋር ተስማምታ ለመኖር ወሰነች እናም ሥጋ ብዙ ድካሞች እንዳሉበት ብታውቅም ከነድካሙ ታግሳው አብራው ትኖራለች፡፡ ሥጋ ይተኛል ያንቀለፋል፤ እሷ ግን በድካሙ ሳትነቅፈው እንዲያውም ተኝቶም በሕልም ሌሎችን የሕልም ዓለማት እንዲጎበኝ በተሰጣት ጸጋ ይዛው ትዞራለች፡፡ በሕልም ሠረገላ ተጭኖ በነፍስ መነጽርነት አነጣጥሮ የተመለከተውን አንዳንዱን ሲደርስበት ሌላውንም በሩቅ አይቶ ተሳልሞ ሲተወው ይኖራል፡፡
ያዕቆብ እንዳየው የተጻፈው ሕልም አስገራሚ ከሚባሉት ሕልሞች ዋናው ነው፡፡ ምክንያቱም በምድር ያለ ሰው የእግዚአብሔርን ዙፋን በሕልም ያየበትና የሰማይ መላእክትን የአገልግሎት ሕይወት የተካፈለበት ሕልም ስለሆነ ነው ዘፍ28÷10፡፡ ያዕቆብ በነፍሱ ያየው ይህ አስደናቂ ሕልም ከሦስት ሺህ የሚበዙ ዓመታትን አሳልፎ ፍጻሜውን በክርስቶስ ልደት አይተናል ዮሐ1÷50፡፡ ታዲያ ነፍሳችን በዘመን መጋረጃ የተጋረዱ ምሥጢራትን ሳይቀር አሾልካ መመልከት የምትችል ኃይል ናት ማለት ነው፤ እሷም የፍቅር ውጤት ናት፡፡ ተፈጥሮአችን ከምታስተምረን ነገሮች አንዱ ትዕግስት ነው፡፡ ሁልጊዜ ትዕግስት ፍቅርን፤ ፍቅር ደግሞ ሁሉን ሲገዛ ይኖራል ሰማያዊም ሆነ መሬታዊ ኃይል ለነዚህ ነገሮች ይሸነፋል ምን አልባት ሰው ሁሉን አሸንፎ የመኖሩ ምሥጢር ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ ተፈጥሮው ትዕግስትን፤ ትግስት ደግሞ ፍቅርን ወልዳለታለች ከዚህ የተነሣ ተፈጥሮን መቆጣጠር የቻለ እንደሰው ያለ ማንም የለም፡፡ እስኪ ልብ በሉት ሞትን በቃሉ የሚገስጽ፣ ደመናትን በእጆቹ የሚጠቅስ፣ የሰማይን መስኮቶች የሚመልስ፤ እስከ ሰባተኛው ሰማይ ወጥቶ የሚቀድስ የሰው ልጅ አይደል? ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሁሉም ነገር ለሰው አገልግሎት ሲባል የተፈጠረ ነው፡፡ የማይስማሙትን አስማምቶ ባንድ ላይ ማኖር መቻል ትልቅ ጥበብ ከመሆኑም በላይ ትዕግስት ካለ ሁሉም ፍጥረት ተቻችሎ ባንድነት መኖር እንደሚችልም አመላካች ነው፡፡
ተቻችለው የመኖራቸው ምሥጢር፡-
እያንዳንዳቸውን ብንመለከት አራቱም ባህርያት ለያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ባሕርያት አሏቸው፡- የእሳት ባህርይ ውእየትና /ማቃጠል/ ይብሰት /ደረቅነት/ ሲሆን፤ የውኃ ደግሞ ቆሪርነትና /ቀዝቃዛ/ ርጡብነት /ርጥብነት/ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱም ባህርያት በምንም ይሁን በምን መስማማት አይቻላቸውም እግዚአብሔር ግን በሌላ በኩል የእርቅ መንገድ ፈልጎ ሲያስታርቃቸው እንመለከታለን፡፡ ይሄውም በነፋስና በመሬት በኩል ነው፤ የነፋስ ባህርያት ውእየትና ቆሪርነት ሲሆን የመሬት ባህርያት ደግሞ ይቡስነትና ርጡብነት ናቸው፡፡ አሁን ዝምድናውንና ማንን በማን እንዳስታረቀ ስንመለከት እሳትና ውኃን በነፋስ አስታርቋቸዋል፡፡ ነፋስ በውዕየቱ ከእሳት፤ በቆሪርነቱ ከውኃ ጋር ተዘምዶ አለው፤ በመካከል ለሁለቱም ዘመድ ሆኖ በመገኘቱ እሳትን ከውኃ ጋር አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ የመሐል ዳኛ ባይኖራቸው ኖሮ እሳቱ ውኃውን እንደ ክረምት ነጎድጓድ አስጩሆት ውኃውም እሳቱን እንደ መብረቅ ሳይታሰብ በላዩ ላይ ወርዶበት ተያይዘው በተላለቁ ነበር፡፡
ነፋስና መሬትን ደግሞ ውኃን ሽማግሌ አድርጎ ሲገላግላቸው እናያለን ውኃ በቀዝቃዛነቱ፤ ነፋስን በርጥበቱ መሬትን ይዘመዳቸዋል ይህን ዝምድናውን ተጠቅሞ ሁለቱን መስተጻርራን በትዕግስት አቻችሏቸው ይኖራል፡፡ አብረው በመኖራቸው ደግሞ ነፋስ ከመሬት ትእግስትን ተምሯል አብሮ መኖር ከሰይጣን ጋር ካልሆነ ከማንኛውም ፍጥረት ጋር ካወቁበት ጠቃሚ ነው፤ አብሮነት የለወጣቸው ህይወቶች ብዙ ናቸው፡፡ ዐስራ ሦስቱን ሽፍቶች ያስመነነው አንድ ቀን ከናፍርና ከሚስቱ ጋር የተደረገ ውሎ ነው፤ ያውም ገንዘብ ሊዘርፉና አስካፍን ሊማርኩ ሄደው ህይወታቸውን አስማረኩ፤ የጦር መሣሪያ ታጥቀው ሄደው ላልታጠቀው ተንበረከኩ፡፡ ክርስትና እንዲህ ሲሆን የእውነተኛነቱ ማረጋገጫ ነው ምክንያቱም ክርስትና ማለት አንዱ ብዙዎችን የሚያሸንፍበት፤ ወታደሩ ንጉሡን የሚማርክበት፤ ገረድ እመቤቷን የምታንበረክክበት ያሸናፊዎች ሕይወት ነውና፡፡ ሳይታኮሱ ደም ሳያፈሱ አብሮ በመዋል ብቻ ከህይወታቸው በሚወጣው የሕይወት መዓዛ ብቻ የሰውን አካሉን ብቻ ሳይሆን ልቡን ጭምር መማረክ ያስችላል፡፡ ዐስራ ሦስት ሰው ባንድ ጊዜ እጅ የሰጠውም ከዚህ የተነሣ ነው እናም አብሮነት የሚጎዳው ከሰይጣን ጋር ብቻ ከሆነ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን የአትናስያን ሕይወት የለወጠ፤ ኃጢአቷን ከልቧ እንደ ሰም ያቀለጠ፤ ላንዲት ሰዓት ከዮሐንስ ሐጺር ጋር የነበራት ቆይታ ነው፡፡ እነ ማርያም ግብፃዊትን ከዘማዊነት ወደ ድንግልና ሕይወት የለወጠስ ላንድ ቀን ብቻ ወደ ኢየሩሳሌም ከሚሄዱ ሰዎች ጋር የተደረገ ውሎም አይደል? ያን የመሰለ የቅድስና ሕይወት ባንድ ጀንበር የገነባ አብሮነት በመሆኑ የሕይወት ትምህርት ቤት ነው፡፡
በእርግጥ እግዚአብሔር ያልባረካት ሕይወት ከማንም ጋር ብትውል ለውጥ እንደሌላት በይሁዳ፣ በዴማስ፣ በግያዝ ሕይወት ማወቅ ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን የተሰበረ መንፈስ ለሌላቸው ቅንነት ለጎደለባቸው ማለት እንጅ አብሮ በመኖር የሚገኘውን ጥቅም የሚተካ ሌላ ነገር አለ ማለት አይደለም፡፡ ነፋስን በቅጽበት ዓለማትን መዞሩን ትቶ ባህሩን የብሱን መቆጣቱን ረስቶ ተረጋግቶ እንዲኖር ያደረገው ከመሬት ጋር አብሮ መኖሩ እኮ ነው ፡፡
መሬትም በአንጻሩ ከነፋስ ጋር በመኖሩ ፈጣን ደቀ መዝሙር ሆኗል፡፡ መሬትን የምናውቀው የማይንቀሳቀስ ፅኑ ፍጥረት መሆኑን እንጂ መሬት ሲንቀሳቀስ የምናውቀው አይደለምን? በሰው ባህርይ ውስጥ የመሬትን ባህርይ ተንቀሳቃሽ ያደረገው ከነፋስ ጋር አብሮ መሠራቱ ነው እንጂ ሌላ ምን አለው መጽሐፍ ስለ መሬት ሲናገር የተናገረው እንዲህ ነበር፡፡ ”ዘአጽንኣ ለምድር ዲበ ማይ፤ ምድርን በውኃ ላይ ያጸናት” መዝ 135÷6 በማለት የምድርን ፅናት ይመሰክራል፡፡ ሰውን ስንመለከተው ሌላ አዲስ ፍጥረት ይመስለን ይሆናል እንጂ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ሁለት ፍጡራን አንዷ ከሆነቸው ምድር የተገኘ ምድራዊ ፍጥረት ነው፡፡ ነገር ግን የሚንቀሳቀስ ምድር መሆኑ አስገራሚ ፍጥረት ያደርገዋል የዚህ ምሥጢር ደግሞ የተሠራበትን ምድር በነፋስ ሠረገላ ላይ ጭኖ የፈጠረው መሆኑ ነው የተጫነበት ሠረገላ ፈጣን ከመሆኑ የተነሣ የማይንቀሳቀሰውን እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል፡፡
መሬትም ለፈጣኑ የነፋስ እግሮች ጭምትነትን ያስተምርለታል፡፡ ባጭር ጊዜ አድማሳትን ማካለል የሚቻለው ነፋስ ጭምትነትን ገንዘብ ሲያደርግ ትዕግስትን ለብሶ ሲመላለስ ማየት ምንኛ ድንቅ ነው፡፡ ከዚያም በላይ አራቱንም በሌላ ሁለት ነገር እንከፍለዋለን፡- ቀሊልና ክቡድ ብለን፡፡ ቀሊላኑ እሳትና ነፋስ ሲሆኑ ክቡዳኑ መሬትና ውኃ ናቸው፡፡ እንደ ውኃና ነፋስ ምን ቀላል ነገር ይኖራል? እንደ መሬትና ውኃስ ማን ይከብዳል? ቢሆንም ግን አብረው ይኖራሉ እንዲያውም ክቡዳኑ መሬትና ውኃ ከላይ የተቀመጡ ሲሆን ቀሊላኑ እሳትና ነፋስ ግን ከስር ሆነው ክቡዳኑን ሊሸከሙ ከእግዚአብሔር ተወስኖባቸዋል፤ ሁለቱም እርስ በእርስ ተጠባብቀው ይኖራሉ፡፡ ነፋስና እሳት ቀላል ከመሆናቸው የተነሣ ወደ ላይ እንዳይወጡ መሬትና ውኃ ከላይ ሆነው ይጠብቃሉ፤ መሬትና ውኃ ደግሞ ከባዶቹ ናቸውና ወደታች እንውረድ ሲሉ ነፋስና እሳት ሓላፊነቱን ወስደው ከመውደቅ ይታደጓቸዋል፡፡ ይህ የተፈጥሮ ስጦታ ሰውን ወደታች ወርዶ እንጦርጦስ እንዳይገባ፤ ወደ ላይም ወጥቶ እንዳይታበይ ማእከላዊ ፍጡር አድርጎ ሲጠብቀው ይኖራል፡፡ ፈጡራንን ሲፈጥር በመካከላቸው መረዳዳትን የግድ ባያደርገው ኖሮ ማንኛውም ፍጡር አብሮ ለመኖር ባልተስማማ ነበር፡፡ ምንም ላንጠቅመው የሚወደንና የሚጠብቀን የሰማዩ አምላክ ብቻ ይሆናል፡፡ ፍጥረታት ግን እርስ በእርስ ተጠባብቀው የሚኖሩት አንዱ ያለ አንዱ መኖር ስለማይችል ብቻ ነው፡፡
እንደዚያማ ባይሆን ኖሮ ነፋስ እሳቱን አግለብልቦ አንድዶት እሳቱም በፋንታው ውኃውን አንተክትኮት ውኃም መሬትን ሰነጣጥቆ ጥሎት አልነበረምን? ግን ይህ ሁሉ ከመሆኑ አስቀድሞ ከእግዚአብሔር የተሰወረ አልነበረምና አራቱንም ኑሯቸውን እርስ በእርስ የተሳሰረ አድርጎታል፡፡ መሬትና በውስጧ የሚኖሩ አራቱ ባህርያት ተስማምተው መኖራቸው ከመሬት በላይ የሚኖሩ ፍጥረታት ተስማምተው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል፡፡ አንዱ ሌላውን በመታገሱ የተከሰተ ነውና ለሁሉም ነገር መሠረቱ ትዕግስት መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡
ከዕለታት አንዳንድ ቀናት አሉ አራቱ ባህርያት የማይስማሙባቸው፡፡ ታዲያ በነዚህ ቀናት ሰው ተኝቶም እንኳን አይተኛም፤ የነፋስ ባህርይ የበረታ እንደሆነ ሲያስሮጠው ከቦታ ቦታ ሲያንከራትተው ያድራል፤ የመሬት ባህርይ ቢጸና ደግሞ ከገደል ሲጥለው፤ ተራራ ተንዶ ሲጫነው ያያል፤ እሳታዊ ባህርይም በእሳት ተከበን፤ እሳት ቤታችንን በልቶ ሲያስለቅሰን ያሳያል፤ ውኃም እንደሌሎቹ ሁሉ ሰውን በባህሩ ሲያጠልቀው ውኃ ለውኃ ሲያመላልሰው ያድራል፡፡ እያንዳንዳቸው ተስማምተው እንዲኖሩ ባያደርጋቸው ሰው በመኝታው እንኳን እረፍት ማግኘት እማይችል ፍጡር ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትዕግስት ለማንኛውም ነገር መሠረት ነው፡፡
ሁሉም በጎ ነገሮች በሰማይም በምድርም የሚገኙት የትዕግስት ውጤቶች መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ሰው በራሱ የትዕግስት ውጤት መሆኑን ካየን የምንጠብቀው አዲሱ ዓለም መንግሥተ ሰማይ የትዕግስት ስጦታ ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ የሚለው “እስከ መጨረሻው የታገሰ ይድናል” ነውና፡፡ ሞታችንን የገደለው፤ ጨለማን የሳቀየው ማነው? ክርስቶስ በዕለተ አርብ በህማሙ ወቅት ያሳየው ትእግስትም አይደል! ይሄ ትዕግስት ፍጥረቱን ሁሉ ያስደነቀ ትዕግስት ነበር፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አንዱ “ኦ! ትዕግስት ዘኢከሠተ አፉሁ በሕማሙ በቅድመ እለ ይረግዝዎ፤ በመከራው ወቅት በሚወጉት ሰዎች ፊት የማይናገር ትዕግስት” ሲል በቅዳሴው ያደንቃል፡፡ በዚህ አስደናቂ ትዕግስቱ እኮ ነው ኃይለኛውን እስከ ወዲያው ጠርቆ ያሰረው ማቴ12÷29፡፡ ኃይለኛውን አስሮ ቤቱ ሲዖልን በርብሮ አወጣን፡፡ እንግዲያውስ ትዕግስት ጉልበት ነው፤ ትዕግስት ውበት ነው፡፡ በዓለም ላይ በጦርነት ከተሸነፉት በትዕግስት የተሸነፉት ይበዛሉ፤ ባለ መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ጦር የነበረው ሰናክሬም በሕዝቅያስ ትዕግስት መሸነፉን አንዘነጋውም፡፡