‹‹የማይመረመር ብርሃን!›› (ሥርዓተ ቅዳሴ)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሚያዝያ፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
ብርሃን በቁሙ ‹‹መዓልት፣ መብራት፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ኮከብ፣ የእሑድና የረቡዕ ፍጥረት ማለት ነው፡፡›› (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፪፻፹፮) ዛሬ በዚህ ዐቢይ ርእስ ለማለት የፈለግነው ስለነዚህ ተፈጥሮአዊ ብርሃናት ሳይሆን ለሰው ሁሉ ዕውቀትን የሚንሣት፣ ብርሃንነቱ ሕጸጽ የሌለበት፣ ብርሃን የባሕርይ ገንዘቡ ስለሆነው ከብርሃናት መገኘት በፊት ስለነበረው፣ ከብርሃን ስለተገኘው፣ አማናዊው የማይመረመር ብርሃን መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹…የአብ አንድያ ልጅ ብርሃን ይባላል፤ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን …›› እንዲል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎዶጦስ ምዕት ምዕራፍ ፶፫፥፲)
የጨለማ አበጋዝ ዲያብሎስ አዳምን አስቶ፣ ልጅነቱን አሳጥቶ፣ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስን፣ በርዕደተ መቃብር ላይ ርዕደተ ሲኦልን አስፈርዶበት፣ በምድራዊ ሕይወትም መኖሪያው የጨለመበት፣ ከሞትም በኋላ መድረሻው የጨለመበትን፣ ከጽመት ያወጣው ዘንድ ወደ ዓለም ስለመጣው ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ እንዲህ ገልጦልናል፤ ‹‹ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር፡፡›› (ዮሐ.፩፥፱)
የሰው ልጅ ይሀን ብርሃን በተስፋ ይጠብቀው ነበር፤ ነቢያቱ ስለዓለሙ ብርሃን ወደዚህ ምድር መምጣት በትንቢታቸው ገልጠዋል፤ በጸሎታቸው በመማጸናቸውም ..ስሜን ለምተፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች…›› የሚል ተስፋ ተሰጥቷቸዋል፡። (ሚል.፬፥፪) ነቢየ እግዚአብሔር ልበ አምላክ ንጉሥ ዳዊትም ‹‹…ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ…›› በማለት ፍጥረት ከገባበት ጨለማ ይወጣ ዘንድ የዓለም ብርሃን መድኅነዓለም ክርስቶስ እግዚአብሔር ወልድ በእርሱ፣ በባሕርይ አባቱ በአብ፣ በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ይመጣ ዘንድ በትንቢቱ ተማጽኗል፡፡ (መዝ.፵፪፥፫)
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅም እንደመሰከረው መድኅነ ዓለም ክርስቶስ የዓለምን ጨለማ የሚያስወግድ ብርሃን ነው፤ ጌታችንም በአማናዊ ቃሉ እንዲህ ሲልም ገልጧል፤ ‹‹እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ…›› ብሏል፡፡ (ዮሐ.፰፥፲፪) ሠለስቱ ምዕትም እምነታችንን የምንገልጥበትን ዘንድ ባረቀቁልን ( ባዘጋጁንል) ጸሎተ ሃይማኖት ላይ ‹‹ከብርሃን የተገኘ ብርሃን›› በማለት ስለ መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ብርሃንነት አረጋግጠውልናል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምዕት ፲፯፥ ፭) ጨለማ የራቀበት የኃጢአት ቁረት ያቆረፈዳት ነፍሳችን ሕይወት ያገኘችበት የጽድቅ ፀሐይ ክርስቶስ ጽልመት በእርሱ ዘንድ የሌለበት አማናዊ ብርሃን ነው፡፡ አስቀድሞ ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢት እንዲህ መስክሮለት ነበር፤ ‹‹በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃንን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው›› እንዲል፡፡ (ኢሳ.፱፥፪)
አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በመከራ የተጨነቀ ምእመን ከዚህ አስቀድሞ (ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን አስቀድሞ) የሥጋዌ ነገር እስኪደርስ ድረስ ‹‹…በገሃነም በጽኑ መከራ ተይዘው ይኖሩ ለነበሩ የሰው ልጆች ጌታ ተወልዶላቸው ልጅነትን ሰጣቸው፡፡›› (ኢሳ.፱፥፪ አንድምታ) ብርሃን ክርስቶስ ከምሥራቂቱ ድንግል ተወልዶ በደል ያጸለመውን የሰው ልጆች ሕይወትን ወደሚደነቅ ብርሃኑ አወጣቸው፤ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ ‹‹እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ የንጉሥ ካህናት ቅዱስ ሕዝብ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ …›› በማለት የገለጠው ለዚህ ነው፡፡ (፩ኛ ጴጥ.፪፥፱)
ጨለማን ከሰው ልጆች ያስወግድ ዘንድ ከልዑል መንበሩ የወረደው፣ ከድንግል ማርያም የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ የማይመረመር ብርሃን ነው፡፡ የኪስኪስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤራቅሊስ እንዲህ ይነግረናል፤ ‹‹…ከኃጥአን መጸብሐን ጋር ሳለ ሱራፌል ሊመረምሩት አልቻሉም፤ ጲላጦስ ሲጠይቀው፣ የሊቀ ካህናትም አገልጋይ ፊቱን በጥፊ ሲመታው፣ ፍጥረት ሁሉ ከእርሱ የተነሣ ይፈሩ፣ ይንቀጠቀጡ ነበር፤ አክሊለ ሶክ ደፍቶ የሞትን ሥልጣን አጠፋ፤ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ሳለ ከዙፋኑ አልተለየም፤ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አልተለየም፤ በምድር እንደ በደለኛ ሲዘብቱበት በሰማይ የከበረ ጌትነቱ ይነገር ነበር፤ ሰማይን እንደ ድንኳን የዘረጋው ሦስት ቀን በመቃብር አደረ፤ ከሙታንም ጋር ተቆጠረ፤ በሞቱም ሲኦልን በዘበዛት (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤራቅሊስ ፵፰፥፫-፭)
የማይመረመረው ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳኑ ምሥጢር ከፍጥረት ረቂቅ (የማይመረመር) ነው፡፡ በመስቀል ላይ ሁኖ አምላክነቱን በገለጸ ጊዜ ጠላት ዲያብሎስ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹… ያለኃጢአት የሞተ ይህ ማን ነው? በብርሃኑ ብዛት የጨለማውን አበጋዝ ዕውር ያደረገው ይህ ማን ነው?›› (ሃይማኖተ አበው ትምህርት ኅቡዓት ፬፥፲፮)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ መስቀል እስኪሰቀል ድረስ አምላክነቱን ለዲያብሎስ አልገለጠለትም፡፡ በመስቀል ላይ ‹‹አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውከኝ›› ሲል ዲያብሎስ የአዳምና ልጀቹን ነፍስ ከሥጋ ይለይ እንደነበረው ወደማይመረመረው ብርሃን ክርስቶስ ቀረበ፡፡ (ማቴ.፳፯፥፶፬) በዚህን ጊዜ በነፋስ አውታር ወጥሮ ያዘው፤ ቅዱሳን መላእክት ከመስቀሉ ዙሪያ ሆነው ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ ሲያመሰግኑ ተመለከተ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ፣ ወልደ አምላክ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን መሆኑን ገለጠለት፡፡
ለ ፶፻፭፻ (አምስት ሺህ አምስት መቶ) ዘመን ማርኳቸውና የሲኦል ግዞተኞች አድርጓቸው የነበሩትን ነፍሳት ነጻ ሊያወጣ መምጣቱን በዚያን ጊዜ ዐወቀ፤ እንዲህም ሲል መሰከረ፤ ‹‹…ወገኖቹን ይገዛ ዘንድ ያልተወው ይህ ማን ነው? ተሰጥተውኝ የነበሩ ነፍሳትን ሁሉ ወደ ሰማይ ያወጣል እንጂ፤ በሕማም በሞት ከሚለወጥ ባሕርይ ጋር አንድ የሆነ እንዳልቆራኘው የሚከለክለኝ ይህ ሥልጣን ምንድን ነው? ልቆራኘው የማይቻለኝ ይህ ማን ነው? ሕጸጽ የሌለበት ይህ ብርሃን የሚከበው ማን ነው? ወገኖቹን እንዳላጠፋ ከሹመቴ የሻረኝ ይህ ማን ነው? በእርሱ ላይ ግን ሠልጥኜ የምጎዳው የለኝም፤ ይኸውም የተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ በግራ የነበረው ወደ ቀኝ ያፈበት እርሱ ነው፡፡›› (ሃይማኖተ አበው ትምህርት ኅቡዓት ፬፥፲፯-፲፱)
የኑሲስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ደግሞ በሞቱ ሞታችንን ገድሎ፣ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን ስላበሠረን፣ ስለማይመረመረው ብርሃን ክርስቶስ እንዲህ ምስክርነቱን ገልጻል፤ ‹‹ከመስቀል ወደ ሲኦል በመውረድ አዳነን፤ በአባታቸው በአዳም በደል በሲኦል ተግዘው የነበሩ ጻድቃንን ፈታ፤ ከሙታን ተለይቶ አስቀድሞ በተነሣ በእውነተኛ ትንሣኤውም አስነሣን፤ የንስሓንም በር ከፈተልን፡፡›› (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱሰ ጎርጎሬዎስ ፴፮፥፴)
‹‹…በሥጋ ተሰቀለ፤ በመስቀል ላይም ተቸነከረ፤ ሞተ፤ ተገነዘ፤ ተቀበረ፤ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ የሙታን ትንሣኤያቸው፣ ፈርሰው፣ በስብሰው የነበሩትን የሚያድናቸው፣ በጨለማ ላሉ ብርሃናቸው፣ የተማረኩትን የሚመልሳቸው፣ የጠፉትን የሚመራቸው ለተጨነቁት አምባ መጠጊያቸው እርሱ ነው›› እንደተባለውም የማይመረመረው ብርሃን ጌታችን መድኃኒታችን ነው፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱሰ ሄሬኔዎስ ፯፥፲፮)
በትንሣኤው ጨለማን አርቆ ወደ ብርሃን አወጣን፤ ስንፈጠር ቅዱሳን መላእክት የፍጥረታት ጌታን እያመሰገኑ ወደ ኤደን ገነት እንዳስገቡን፣ ሕግ ተላልፈን፣ ትእዛዝ ጥሰን በነበርን ጊዜ ደግሞ ከተድላ ገነት ወደ ምድር ስንባረር ተመልሰን እንዳንገባ፣ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ኪሩቤል የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን ይዘው ይጠብቋት ዘንድ ታዘዙ፡፡ (ዘፍ.፫፥፳፬)
ከብርሃን ወደ ጨለማ ከተደላ ወደ አሣር ገባን፤ ውድቀታችንን የማይሻ፣ መዳናችንን የሚፈልግ አምላካችን እግዚአብሔር እንደሚያድነን የአምስት ቀን ተኩል ቀጠሮን ሰጠን፤ በሞቱ ሞታችንን ገድሎ የትንሣኤውን ብርሃን አበራልን፡፡ ‹‹…ተድላ ደስታ ካለበት ከገነት የተሰደደ አዳምን ዐላውያን አጋንንት ባሉበት በሲኦል ቢያገኘው መልሶ በልዕልና ካሉ ከመላእክትም ጋር አኖረው …፤›› ትንሣኤያችንንም አበሠረን፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤራቅሊስ ፵፱፥፮)
በብርሃኑ ብርሃንን ላሳየን አምላክ ክብር ምስጋና ይድረሰው!!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!