የማኅበሩ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ሰዓት ወደፊት የሚሻሻል መሆኑ ተገለጠ
መስከረም 16 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ
ማኅበረ ቅዱሳን ባሳለፍነው ሳምንት ማጠናቀቂያ የቴሌቪዥን መርሐ ግብርን በኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ሰርቪስ ቴሌቪዥን (EBS TV) ለመጀመር ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቁንና ይህንኑ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የማኅበሩ አባላት፣ ካህናትና ምእመናን፡- ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመጣው የማኅበሩ አገልግሎት ከልብ መደሰታቸውን አስታውቀው፤ ነገር ግን የተመረጠው ጊዜ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከቤተ ክርስቲያን ከሚወጣበት ሰዓት ጋር በጣም መቀራረቡ ፣ በተጨማሪም አጠቃላይ የመርሐ ግብሩ ጊዜ በ30 ደቂቃ መገደቡ እንዳሳሰባቸው ገልጠውልናል፡፡
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው በማኅበሩ ኅትመትና ኤሌክትኒክስ ሚዲያ የሬድዮና ቴሌቪዥን አስተባባሪ ዲያቆን ሄኖክ ኀይሌ “የማኅበሩ የቴሌቪዥን የአየር ሰዓት ልናገኛቸው ከቻልናቸውና ካልተያዙት አማራጭ ጊዜያት ውስጥ የተሻለው ነው፤ ከካህናቱና ከምእመናኑ የተሰጠውን አስተያየት ሙሉ ለሙሉ የምንቀበለው ሲሆን ወደፊት ከጣቢያው ጋር ተነገግረን የሥርጭት ሰዓቱን ለመቀየር ጥረት እናደርጋለን፡፡ ለጊዜው ግን እሑድ ጧት ከ3፡30 እስከ 4፡00 የሚተላለፈውን መርሐ ግብር መከታተል ላልቻሉ በድጋሚ ሐሙስ ጧት 1፡00 እስከ 1፡30 በድጋሚ ስለሚቀርብ ዝግጅቱን መከታተል ይችላሉ ” ብለዋል፡፡