የማኅበሩ መልእክት
የካቲት 14 ቀን 2008 ዓ.ም
በሚመስለን ከተጨባጩ፤ በመላምትም ከእውነታው አንጣላ
በአሁኑ ወቅት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ባሉ አማኞችም ሆነ በሀገራችን ውስጥ ባሉ ዜጎች መካከል ልዩነቶችን አጉልቶ በማሳየት የመጠቃቃትን ስሜት ለመፍጠር የሚጣጣሩ መኖራቸውን ለመታዘብ የተለየ ጥናት የሚጠይቅ ነገር አይደለም፡፡ በተለያየ መንገድ የምንሰማቸው ዜናዎችና ወሬዎችም ከዚህ የራቁ አይደሉም፡፡ ምንም እንኳ ልዩነት ተፈጥሮአዊ እስከሚመስል ድረስ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ውጤቱ ግን እንደየዘመኑ የማኅበረሰብና የተቋማት መሪዎች አቅም እንደ ማኅበረሰቡም ግንዛቤ ይለያያል፡፡
የማኅበረሰብና የተቋማት መሪዎች ለሚመሩት ማኅበረሰብ እንደ አንድ ጤነኛ ሰው ጭንቅላት የሚታዩ ሲሆን የተለያዩት የማኅበረሰብ አካላትን በአንድ አካል ውስጥ እንዳሉ ብልቶች በማዋሐድና ጤንነታቸውንም በመጠበቅ ልክ እንደ አንድ ጤናማ ሰው ሙሉ ጤነኛ አካል አድርገው ይመሯቸዋል፡፡ ውሕደታቸው፣ መናበባቸው፣ መረዳዳታቸውና መተባበራቸውም ልክ በአንድ ጤነኛ ሰው እንዳሉ የተለያዩ ብልቶች ይሆንና ከልዩነታቸው የሚጎዱ ሳይሆን በልዩነታቸው የሚያጌጡና የሚጠቀሙ ይሆናሉ፡፡ የማኅበረሰቡ አካላትም እንደዚያው ጤነኛ ብልቶች ከሆኑ ለራሳቸውም ሆነ ብልት ለሆኑለት አካል ጠቃሚዎች ይሆናሉ፡፡ በሽተኞች ሲሆኑም ፈጥነው ሕክምና ካላገኙና ካልዳኑ ጉዳታቸው በእነርሱ ሳይወሰን መላው አካልን ይጎዳሉ፤ ሕመሙ ሲከፋም የጋራ ሞትን ያስከትላሉ፡፡ ስለዚህም በሰውነታችን እንደምናየው፣ ëአፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳልô ከሚሉት ዓይነት አባባሎችም እንደምንረዳው እያንዳንዱ ብልት ለሌላው ጤንነት የድርሻውን ይወጣል፡፡ ይህ መሆን ካልቻለ ለሁሉም የሚደርስባቸው ጉዳት ታላቅ ይሆናል፡፡ ብልቶች ከተለያዩ ውጤቱ የአካል መለያየትና የሁሉም የሰውነት አካል የጋራ ሞት እንደሆነ የታወቀ ነውና፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስለ ሰው ልጆች ማኅበራዊ ሕይወት ጤንነትም ሆነ በውስጧ ስላለው መንፈሳዊ አገልግሎት ልጆቿን ከምታስተምርበትም ሆነ ዓለምን ከምትመክርበት፤ ተቋማዊ ሂደቷንም ከምትመራባቸው መንፈሳዊ አስተምህሮዎችና መርሆዎች አንዱና ዋናው ይህንኑ የሚከተል እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆርንቶስ ምእመናን በላካት የመጀመሪያይቱ መልእክት ላይ የሚከተለውን ብሏል፡-
አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል። አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና። እግር፦ እኔ እጅ ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም ብትል፥ ይህን በማለትዋ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? ጆሮም፦ እኔ ዓይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ቢል፥ ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል። ሁሉም አንድ ብልት ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ? ዳሩ ግን አሁን ብልቶች ብዙዎች ናቸው አካል ግን አንድ ነው። ዓይን እጅን፦ አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን፦ አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም። /1ኛ ቆሮ 12 ፥ 12 – 21/
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሰፊው ግልጽ አድርጎ እንዳስቀመጠው፡- በሀገራችን በኢትዮጵያ የምንገኝ ሁላችን ራሳችን ለራሳችን የሰጠነው የተለያየ ማንነት ቢኖርም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ልዩነታችን እንደ ዓይን እና ጆሮ፣ እጅ እና እግር ወይም እንደ ልብና ኩላሊት ከመሆን ያለፈ አይደለም፡፡ አንዳንዶቻችን የተስማማንን ማኅበረሰባዊ የማንነት መለያዎች ለራሳችን ብንሰጥና በዚያም መለያ ብንመደብ እንኳ ካወቅንበት ይህ ልዩነታችን በአንድ አካል ውስጥ እንዳሉ ብልቶች በየተሰጠን ጸጋ፣ ሙያና ችሎታ የምንጠቃቀምበት የምንከባበርበት እንጂ የሚጎዳን ሊሆን አይችልም፡፡ በመጀመሪያ በተፈጥሮ ሰው ሆነን በመፈጠራችን ልዩነት የሌለን መሆኑን ማስታወስ ነው፡፡ ያም ባይሆን ደግሞ ልዩነትን እንደተፈጥሮ ጸጋ ብንወስደው እንኳ ይህ የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይደለም፡፡
ቅዱሱ ሐዋርያ በደንብ እንደገለጸው ዓይን እጅን አታስፈልገኝም ልትለው የማትችለውን ያህል በሀገራችንም አንዱ ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍል አታስፈልገኝም ቢለው ተፈጥሮአዊ አይደለምና ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ምንም እንኳ ጥርስ ምላስን እንደሚነክሰው፣ እግርም እግርን እንደሚረግጠው ወይም እጅ እጅን እንደሚያቆስለው ካለበለዚያም ጣትም ዓይንን እንደሚያስለቅሰው ሁሉ በቀደመው ታሪካችን አልፎ አልፎ የእርስ በርስ ወይም የብልት ከብልት መጎዳዳት ተከስቶ የነበረ መሆኑ ቢታወቅም ይህም ከልዩነት የተነሣ ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮም ጠፍቶ የማያውቅ በመሆኑ በብልቶቻችን ዘንድ በእንደዚህ ዓይነት ምክንያት እስከመጨረሻው መለያየት ሆኖ እንደማያውቀው ሁሉ ራሳችን ሆን ብለን ካልፈቀድንለት በስተቀር እኛንም እንዲህ ዓይነት ታሪካዊ ምክንያቶች ሊለያዩን አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እጅ ዓይንን ብቻ ሳይሆን እጅንም የሚጎዳ መሆኑ እንዲህ ያለ ጉዳት የእርስ በርስ መሆኑንም እንድንረዳ ፈጣሪ የሰጠን የማስተዋል ወይም የመመርመሪያ መንገድ ይመስለናልና፡፡
ስለዚህም ታሪካዊ ክስተቶችን እያነሣንና እየጣልን በቁስል ላይ ቁስል ከምንጨምር ይልቁንም በአንድ አካል እንዳሉ ብልቶች የቆሰለውን የማዳን እንጂ ያልቆሰለውን የማቁሰልን ተግባር ልንጸየፈው ይገባናል፡፡ ምንአልባት በሰዎች ዘንድ ቅዱሱ ሐዋርያ እጅን ወይም እግርን አታስፈልጉኝም የሚል ዓይን ወይም ጆሮ ሊኖር አይችልምÂ እንዳለው በእኛም ዘንድ ይህ ሊሆን አይገባውም፡፡ መስሎን የምንል ሰዎች ካለንም መናገር በመቻላችንና ይህንኑንም አብዝተን በማለታችን ምክንያት ግን የአካል ክፍል አድርገን ያልቆጠርነው ክፍል አካል አለመሆን አይችልም፡፡ እንኳን በሌሎቹ በራሳችንም ላይ ቢሆን እንዲህ ያለው ነገር የምንናገረውን ያህል ቀላል፣ ጉዳቱም ለሌሎቹ ብቻ ሊሆን አይችልምና ደጋግሞ መመርመሩ ነገሮችንም በእውነት ማጤኑ በእጅጉ አስፈላጊ ይመስለናል፡፡
ስለዚህም ነገሮችን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገለጸውና የሕይወታችን መመሪያ በሆነው መንገድ እንድንመረምራቸውና በሌሎች አካላትም ይሁን በራሳችን ስሜት ተገፋፍተን ለእኛ ምንአልባትም ጠቃሚ ከመሰለን፣ ነገር ግን ደግሞ በእውነት ጠቃሚ ካልሆነው ነገር እንድንድንና አንዳችን ለሌላችን ጠቃሚዎች እንድንሆን የሚከተሉትን ነገሮች እንድናጤናቸው ያስፈልጋል፡፡
1.የሚመስለንን አንመነው፤ ይልቁንም እንመርምረው፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ ተደጋግመው ከተገለጹልን ነገሮች አንዱ የሚመስለንን ነገር ይዘን እንዳንቀመጥ ነው፡፡ እንኳን እንዳሁኑ አስመሳይ በበዛበት ዓለም ውስጥ እየኖርን ቀርቶ በንጽሕና በቅድስና በሚኖሩትም ዘንድ ይህ ፈተና የሚሆን መሆኑን ዐውቀን እንድንጠነቀቅ ብዙ ጊዜ ተጽፎልናልና፡፡ ለምሳሌ ያህል በሃይማኖት ዐዋቂዎች መምህራን ነን ብለው ከሚኖሩት ብዙዎቹ የራሳቸው መንገድ ብቻ ትክክል መስሏቸው ከኖሩ በኋላ ጌታ አላውቃችሁም ሲላቸው እነርሱ እንደሚያውቁትና ራሱንም ሳይቀር በአንተ ስም አይደለም ወይ ይህን ተአምር ያደረግን እያሉ እንደሚከራከሩትም ራሱ ጌታችንም አስቀድሞ አሳስቧል /ሉቃ 13 ፥ 25/፡፡ ከዐሥሩ ደናግልም አምስቱ ማሰሮ በመያዛቸው ብቻ የሚጠቀሙ ይመስላቸው እንደነበር ነገር ግን በማሰሮው ውስጥ የሚያስፈልገውን ዘይት ይዘው ባለመገኘታቸው የሠርጉ ታዳሚ ሳይሆኑ እንደቀሩ ተጽፎልናል /ማቴ 25 ፥ 1-10/፡፡ እንዲሁም መክሊቱን የቀበረውም ሰው የተሻለ ያደረገና በጌታው ዘንድ የበለጠ የሚመሰገን ይመስለው ነበር፤ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀረ፡፡ /ማቴ 25 ፥ 14-30/፡፡ እኒህ ሁሉ የገጠማቸው ከመሰላቸው በተቃራኒው ነው፡፡ ምክንያቱም በመሰላቸው እንጂ በሚሆነውና በእውነታው አልኖሩምና፡፡
ከላይ በጠቀስነው መልእክትም ላይ ቅዱስ ጳውሎስ ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋልÂ /1ኛ ቆሮ 12 ፥ 22 – 23/ ሲል እንደገለጸው የሚመስለን ከእውነታው ብዙ ጊዜ ሊራራቅ እንደሚችል ማሰብና መመርመር ከነባራዊ እውነትም ጋር መታረቅና መስማማት ለሁላችንም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ነገሮችን በአግባቡ ሳይመረምሩና በአግባቡ ሳያጠኑ ወይም በስሜታቸው ተገፋፍተው የሚቀሰቅሱንን እየሰማን ለራሳችን ባለንና በሰጠነው ማንነት ላይ ተመሥርተን ሌሎች የማያስፈልጉ ከመሰለን በእጅጉ እንሳሳታለን፡፡ እንደ እውነታው ከሆነ ሁላችንም ብንሆን አንዳችን ለሌሎቻን የምናስፈልግና የምንጠቅም መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ነገሩን በጽድቅና በኩነኔ ብቻ ሰፍረን የእኛ ያጸድቃል የሌሎች ያስኮንናል ብለን ብናምን እንኳ በዚች ምድር ላይ ለመኖር ግን አንዱ ለሌላው አስፈላጊ መሆኑ ሊታበል አይችልም፡፡ ምክንያቱም የሃይማኖት ውጤቱ በሰማይ (በፈጣሪ በሚሰጥ ፍርድ) የሚገለጽ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በምድርም ፈጣሪ ለሁሉም ፀሐይ በማውጣቱ ዝናም በማዝነሙና ሁሉንም በመመገቡ የፈቀደለትን እኛ በጉልበትና በግጭት ልናጠፋው እንደማይገባን ብቻ ሳይሆን እንደማንችልም መረዳት አስፈላጊ ነውና፡፡ ስለዚህም ልዩነትን ምክንያት በማድረግ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚፈጸሙ አብያተ እምነቶችን ማቃጠል፤ በአንድ አካባቢ በቁጥር አነስ ያሉና የተለየ ማንነት ያላቸውን ማሳደድ፣ ማፈናቀልና መጉዳት ለጊዜው ማሸነፍ ቢመስልም እውነታው ተቃራኒው ሊሆን እንደሚችል ማሰብና በመከባበርና በመረዳዳት መኖሩ ሊጠቅም እንደሚችል ማስተዋሉ በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህም በሃይማኖትና በብሔር ከመጣላት ራስን ብቻም የተለየ አስፈላጊና ጠቃሚ ሌላውን ደግሞ ጎጂና የማይረባ፣ አንዳቻንን አሳቢ ሌላውን ማሰብ የማይችል፤ አንዱን ተሸካሚና ሌላውንም ሸክም አስመስለው ከሚያቀርቡ የልዩነት ሐሳቦች ራስን ማቀብ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ የሚመስለን ሁሉ እውነታ ላይሆን ይችላልና፡፡
ስለዚህም አሁን በሀገራችን ውስጥ ያለው የብሔር፣ የቋንቋም ሆነ የሃይማኖት ልዩነት እንደ አካል አቅፋ በያዘችን ሀገር ውስጥ በሰላም ለመኖር የሚያስቸግረን አይደለም፡፡ ልዩነቶቻችን የሚጎዱን ወይም ጉዳት ያስከተሉብን ቢመስለን እንኳ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ መመርመርና በመከባበር መኖር ይገባናል፡፡ በመለያየት የምንጠቀም የሚመስለው ካለም ሐሳቡን እንደገና ቢያጤንና ቢመረምር ይሻላል እንላለን፡፡
2.የማኅበረሰብ መሪዎች የጭንቅላትን ሓላፊነት ቢወጡ መልካም ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች በአግባቡ ለመወጣትና በአካል ውስጥ እንዳሉ ብልቶች ተከባብሮ ለመኖር ማኅበረሰቡን የሚመሩ አካላት ሓላፊነትና ድርሻ ትልቅ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግሥታዊ የሆኑም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና የማኅበረሰብ መሪዎች ሁሉ በዚህ ጊዜ እንደ ጭንቅላት ሆኖ ማኅበረሰቡን እንደ ብልት ማዋሐድና የሀገርንም ሆነ የሕዝብን ጤንነት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚወስዱ ግጭቶችን መፍታት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች አማኞቻቸውን ሃይማኖት የታከከ ግጭት እንዳያስነሡና በዚህም ወዳልተፈለገ ሀገራዊ ቀውስ እንዳይገባ የመጠበቅ ሓላፊነት አለባቸው፡፡ ይህን ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ ሁላችንም በተግባር ከመጎዳታችን በላይ በታሪክና በትውልድ ተጠያቂዎች እንሆናለን፤ መውጫውን በማናውቀው ገደልና የችግር አዙሪት (vicious circle) ውስጥም ስንዳንክር ልንኖር እንችላለን፡፡ ስለዚህም ነገሮቹን ሁሉ በአግባቡ የማየት ታሪካዊና ሰብአዊ ሓላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበው በፍጥነት የሚቻላቸውን ሁሉ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ሁላችንም ብንሆን ደግሞ በጠባብ ሐሳቦች፣ በቅርብ ጥቅሞችና ጠንካራና እውነት በሚመስሉ ነገር ግን ደካማና ስሕተት በሆኑ ትንታኔዎች ተይዘን እንዳንታለል ችግሮችንም እንዳናሰፋ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
3.ማኅበረሰባዊ መስተጋብሮችን ሊያናጉ የሚችሉ ልዩነቶችን ከማጉላት ችግሮችንም ከማስፋት መቆጠብ
እያንዳንዳችን እንደግለሰብም ሆነ እንደተቋም የምንኖርበት ዓለም ከሌሎቹ ጋር አንድ ስለሆነ ከግጭት፣ ከልዩነትና ከመሳሰሉት ነጻ የመሆን እድላችን በእጅጉ አነስተኛ ነው፡፡ ሆኖም ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ችግሮችን የሚያዩበት፤ የሚተረጉሙበትና እርሱንም የሚያስረዱበትም ሆነ አቋም የሚይዙበት መንገድ ጉዳዩንና ችግሩን ወይ ይፈታዋል ካለበለዚያም ሊያባብሰው ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ብዙ አካላትን የጥቃት ሰለባ እያደረጋቸውና ማኅበረሰባዊ ቀውሱንም እያባበሰው ያለው የችግሮች በሆነ አካባቢና ዓውድ መከሰታቸው ሳይሆን ከተጨባጭ እውነታው የራቀው መረዳታችን (Perception) እና አንዳንዴም አርቆ አሳቢና ተቆርቋሪነት ያለባቸው የሚመስሉ ትናታኔዎቻችንን መሠረት አድርገን በመጓዛችን ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ታሪክ ቀመስ ጉዳዮችን እየጠቀስን እርስ በርስ ከምንወራከብባቸው ብዙ ጉዳዮች መረዳት ይቻላል፡፡
ትላንት አሁን ያለው ትውልድ ባልነበረበት፣ እንዳሁኑ ዘመንም ሁሉም ነገር በመረጃ በማይታይበትና ባልተሰነደበት፣ አብዛኛዎቹም ነገሮች አሁን ያለው አካል ነቅፎም ሆነ ደግፎ በሚከራከርላቸው አቋሞች መሠረት ሆነ ተብለው የተደረጉ በማይመስሉ በዚያ ባለፈው ዘመን ክስተቶች ይህን ያክል ውርክብና እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተን ከተቸገርን አሁን ራሳችንን አዋቂ አድርገንና ሆነ ብለን እወቁልኝና ስሙልኝ እያልን ብዙ ሚዲያዎችን ተጠቅመን በምናደርጋቸው ነገሮችማ ምን ያህል ችግሮችን ልንፈጥር እንደምንችል መገመት የሚያስቸግር አይመስለንም፡፡ ስለዚህም ምንም እንኳ ሰው ዓላማዬ ብሎ ለያዘው ነገር የሚችለውን ያህል መሥዋዕትነት እስከመክፈል መታገሉ የሚጠበቅ ቢሆንም ለማሸነፍ ወይም ተቆርቋሪና አለኝታ መስሎ ለመታየት በሚደረግ ሩጫ ግን ሳናውቀው ችግሮችን ከእውነታውና ከከባቢያዊ ዓውዳቸው አውጥተን ስሜታችንን በሌሎች ላይ በመጫን ልዩነትን እንዳናሠፋ ችግሮቻችንንም እንዳናውሰበስባቸው ስጋት አለን፡፡ ይህ ማለት አጥፊዎች አይጠየቁ ችግሮችም አይነሱ ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡
አሁን የምናያቸው አብዛኞቹ ግጭቶች ግን ስለትላንት በምናወራው ላይ ሰሚዎቻችን ተናጋሪዎቹን አምነው የሚወስዷቸው አጸፌታዊ እርምጃዎች እንደሆኑ ይደመጣል፡፡ ስለዚህ ስላለፉትም ሆነ አሁን ስላሉት ነገሮች ስንነጋገርና ስንከራከር ዞሮ ዞሮ አንድነታችንን በሚያጠናክር ሓላፊነቱንና ተጠያቂነቱን ባልዘነጋ መልኩ ቢሆን መልካም ይሆናል፡፡ እውነታዎችን ሁሉ እርግጠኞች መሆን እስከምንችል ብናውቅ እንኳ በማወቃችን ብቻ አላስፈላጊ ነገሮችን ላለማድረግ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉን ከመደረጉ በፊት የሚያውቀው ጌታችንም የይሁዳን የማታለልና የማሳመጽ ተግባር ለሚወዱትና ለሚከተሉት ሐዋርያት እንኳ ቶሎ አልገለጸላቸውም፡፡ በዚህም እውነቱን በማወቃችን ብቻ የአንድን ነገር ውጤት ሳናስብና ጉዳቱን ሳንመረምር አፋችን እንዳመጣ ያለጊዜው እንዳንናገር አስተማረን፡፡ ስለዚህም በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሀገር ደረጃ የምናያቸው ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ስሜታዊ መሆን አያስፈልገንም፡፡ ይልቁንም ደጋግመን እንደገለጽነው መኖራቸውን ተቀብለን መፈጠራቸውንም እውቅና ሰጥተን ከስሜትና ከችኮላ ተላቅቀን የራሳችንን ትርጉምና መረዳት ብቻ እንደ እውነት ቆጥረን ከመንቀሳቀስ መቆጠብ፣ ካለፈው የተሻልን ሆነን፣ ችግሮቹን ከማስፋት ወደ ማጥበብ መጓዝ ይኖርብናል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ጉዳዮችን በጥልቀት መመርመርና ማጥናት በመፍትሔዎቹም ላይ በመደማመጥ መወያየት ያስፈልጋል፡፡
4.በራሳችን የሓላፊነት ስፍራ ውስጥ ብቻ ሥራችንን መሥራት
በአሁኑ ወቅት ችግሮቻችንን እያሰፉና በየአቅጣጫው የሴራ ትንታኔዎች ገዝፈው ሰዎችን በመረዳታቸው መጠን የራሳቸውን እርምጃ በመውሰድ ችግር ውስጥ እንዲገቡ ከሚገፉ ነገሮች፣ ዋነኛው ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት የእነርሱ ባልሆነ ቦታ ውስጥ የሚፈጽሙት ደባና ተንኮል ይመስለናል፡፡ ምንም እንኳ በፖለቲካዊ ዓለም ይህ አሠራር ራሱን የቻለ ሳይንሳዊ ዘዴ ያለው ስልት ቢሆንም በተለይ በእምነት ተቋማት ግን አደገኛና ትልቅ ችግር አምጭ መሆኑን ለመረዳት የሚያስቸግር አይመስልም፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ ራሳቸውን “ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ” ብለው የሚጠሩ አካላት እየፈጠሩ ያሉትን ችግር ሁሉም አካል በአግባቡ እንዲገነዘበው መሪዎቻቸውም ይህንኑ ሓላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
ራስን ችሎ በሚያምኑበት ሃይማኖት መመራትና ማምለክ እየተቻለ፤ በነባሯና በጥንታዊዋ ሃይማኖት ውስጥ ሠርጎ በመግባትና እራስን ደብቆ ችግሮችን በማባባስ የፈለጉት ቦታ ለመድረስ የሚቻል ቢመስልም፤ እውነታው ከዚህ ሩቅ መሆኑን ተገንዝቦ መሔድ ወቅቱ የሚፈልገው መፍትሔ ነው፡፡ ለራስ የተለየ ግምት በመስጠት ሁሉን ማድረግ እንደሚቻል በማሰብ የተለያዩ የተንኮልና የማስመሰል ዘዴዎችን ተጠቅሞ ችግር ለመፍጠር መሞከር እውነታውን አይለውጥም፡፡ ለአንዳንድ ሞኞችም ተንኮል ጥበብ፣ እብሪትም አሸናፊነት ቢመስላቸውም እውነታው ሁልጊዜም የተለየ ነው፡፡ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን ታካች ሰው በጥበብ ከሚመልሱ ከሰባት ሰዎች ይልቅ ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል /ምሳ 26፥16/ እንዳለው የተጠበብንና የተራቀቅን ቢመስለንም ሞኝነታችን የተገለጠ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? /1ኛ ቆሮ 1 ፥ 19 – 21/ እንዳለው በከንቱ ከመድከም ያመኑበትን በይፋ ይዞ በራስ ቦታ ተወስኖ በመሔድ በግልጽ የማስተማርም ሆነ የማምለክ ነጻነቱ ስላለ ይህንን ሓላፊነት መወጣት አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሽንገላዎች፣ ጥበብና ቻይነት የሚመስሉ ተንኮሎች፣ ችግሮችን አውሰብስበው ራስን ከመጉዳት በቀር የሚያመጡት ጠቀሜታ አይኖርም፡፡
በቤተ ክርስቲያናችን በሓላፊነት ያሉ አካላትም የታመመውን ብልት እያከሙ እያዳኑ የአካልን ጤንነት መጠበቅ ግዴታቸው መሆኑን እንደማይዘነጉት እሙን ነው፡፡ ሆኖም አንዳንዱ በሽታ የበከለው ብልት በሕክምና የማይድንና ሌላውንም ቀስ በቀስ እያጠቃ አካልን የሚጎዳው፣ መላ ሰውነትንም የሚያጠፋ ከሆነ ደግሞ፣ እርሱን እንደ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በጊዜው ቆርጦ ሌላውን አካል ማዳን አሁንም ጭንቅላት ከተሰኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ የተለያዩ ሓላፊዎች የሚጠበቅ ተግባር መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ ካለበለዚያ ጭንቅላትን ጨምሮ መላውን አካል ማወኩ ማስጨነቁና ብሎም ለሞት መዳረጉ አይቀርምና ሓላፊነትን በአግባቡና በጊዜው መወጣት ይጠይቃል እንላለን፡፡
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ያሉብንን ችግሮች በሰከነ መንገድ በአግባቡ መፍታት ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር ሆኖ ይታየናል፡፡ ልዩ ልዩ መንግሥታዊ አካላት፤ ልዩ ልዩ የማኅብረሰብ መሪዎች ሁሉ በሰከነ መንገድ የጭንቅላትነት ማለትም የማሰብ ሁሉንም ብልት የመጠበቅ የመንከባከብና የአካል መለያየት እንዳይኖር ነቅቶ የመጠበቅ ታሪካዊ ሓላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል የሚል እምነት አለን፡፡ በተለይም ልዩነቶቻችን እንደ ሰውነት ብልቶች ከመጠቃቀሚያነት ወደ መደባደቢያነትና ጎሳን ብሔርን ቋንቋንና ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ ግጭት ውስጥ እንዳይገባ ሓላፊነትን በአግባቡ መወጣት የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል፡፡ ካለበለዚያ አንድ ብልት ያመጣው በሽታ መላው አካልን እንደሚጎዳው ሰውነትንም እንደሚያጠፋው ጥፋቱ ለሚመሩት አካል ጭንቅላት ለሆኑትም እንደማይቀር አስበን ካልሠራን ጉዳቱ አይቀርልንም፤ ከእውነታው ጋርም እንደተጣላን እንቀራለን፡፡ ስለዚህ አስቀድመን ከሚመስለንና ከግምታችን ወጥተን እውነቱን እንያዝ ከሚሆነውም አንቃረን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡