የማኅበረ ቅዱሳን ፲፪ኛው ጠቅላላ ጉባኤ እየተካሔደ ነው

ነሐሴ ፳፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የማኅበረ ቅዱሳን ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ከነሐሴ ፳፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ጀምሮ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽና በማኅበሩ ሕንጻ እየተካሔደ ነው፡፡

DSCN8874

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እና ብፁዕ አቡነ እንጦንስ

በጠቅላላ ጉባኤው መክፈቻ ዕለት ነሐሴ ፳፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ሓላፊዎች፣ ከአገር ውስጥና ከውጪ አገር ማእከላትና ወረዳ ማእከላት የመጡ የማኅበረ ቅዱሳን አመራር አባላት፣ የግቢ ጉባኤያት ተወካዮችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

3

የጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል

5

ጠቅላላ ጉባኤው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎት ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ በቀኑ መርሐ ግብር በጠቅላይ ቤተ ክህነት፤ ማታ ደግሞ በማኅበሩ ሕንጻ በከፍተኛ ተሳትፎ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲኾን በጉባኤውም የማኅበሩ የሁለት ዓመታት አጠቃላይ የአገልግሎት ዕቅድ አፈጻጸምና የኦዲትና ኢንስፔክሽን ሪፖርቶች ቀርበው ጉባኤው ተወያይቶባቸዋል፡፡ እንደዚሁም ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎች በባለሙያዎች ቀርበዋል፡፡

DSCN9433

የሥራ አመራር አባላት ዕጣ በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ሲወጣ

በዛሬው ዕለትም የማኅበሩ ቀጣይ ስልታዊ ዕቅድ በተሳታፊዎች የቡድን ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በመቀጠልም በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ማኅበሩን የሚመሩ የሥራ አመራር አባላት በምልዓተ ጉባኤው በተሰየመው አስመራጭ ኰሚቴ አቅራቢነት በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቡራኬ በጸሎትና በዕጣ ተመርጠዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ፲፪ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ ምሽት የሚጠናቀቅ ሲኾን ሙሉ ዘገባውንም በሌላ ዝግጅት ይዘን እንቀርባለን፡፡