የማቴዎስ ወንጌል

 ነሐሴ 9 ቀን 2006 ዓ.ም.

ምዕራፍ ስድስት

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሚከተሉት አሳቦች ተጠቃልለው ይገኛሉ፡፡

  1. የምጽዋት ሥርዓት

  2. ጠቅላላ የጸሎት ሥርዓት

  3. የአባታችን ሆይ ጸሎት

  4. ስለ ይቅርታ

  5. የጾም ሥርዓት

  6. ስለ ሰማያዊ መዝገብ

  7. የሰውነት መብራት

  8. ስለ ሁለት ጌቶች

  9. የዕለት ጉርስና የዓመት ልብስ

1. የምጽዋት ሥርዓት፡- ጌታችን በዚህ ትምህርቱ እንደ ግብዞች መመጽወት እንደማይገባ ተናግሯል፡፡ ግብዞች የሚመጸውቱት ሰው ሰብስበው፣ ቀን ቀጥረው በተመሳቀለ ጉዳና በአደባባይ ነው፡፡ የሚመጸዉቱትም ለመጽደቅ ሳይሆን ለውዳሴ ከንቱ ስለሆነ፤ ስለዚህም አንተ በምትመጸውትበት ጊዜ ቀኝ እጅህ የምትሠራውን ግራ እጅህ አትወቀው ብሏል፡፡ እንዲህም ያለበት ምክንያት፡-

ሀ. በቀኝ አጅህ የያዝኸውን በግራ እጅህ አትያዘው ማለቱ ነው፡፡ ምክንያቱም ግራ ደካማ ስለሆነ ጥቂቱን ብዙ አስመስሎ ልቀንስለት ይሆን ያሰኛል፡፡ ቀኝ ግን ኃያል ስለሆነ ብዙውን ጥቂት አስመስሎ አንሷል ልጨምርበት ያሰኛል፡፡

 

ለ. ግራ እጅ የተባለች ሚስት ናት፤ ሚስት በክርስትና ሕይወት ካልበሰለች ሀብቱ እኮ የጋራችን ነው፣ ለምን እንዲህ ታበዛዋለህ? እያለች ታደክማለች፡፡ ከሰጠ በኋላ ግን ከሚስት የሚሰወር ነገር ስለሌለ ይነግራት ዘንድ ይገባል፡፡ ብትስማማ እሰየው፤ ባትስማማ ግን መለየት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ጥንቱን የተጋቡት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ሰጥተው መጽውተው ለመጽደቅ ነውና፡፡ 

 

ሐ. ግራ እጅ የተባሉት ልጆች ናቸው፤ የአባታችን “የቁም ወራሽ የሙት አልቃሽ” እያሉ ያደክማሉና፡፡

 

መ. ግራ እጅ የተባሉት ቤተሰቦች ናቸው፤ የጌታችን ወርቁ ለዝና፣ ልብሱ ለእርዝና እህሉ ለቀጠና እያሉ ያዳክማሉና፡፡

 

ይህን ሁሉ አውቀን ተጠንቅቀን የምንመጸውት ከሆነ በስውር ስንመጸውት የሚያየን ሰማያዊ አባታችን በጻድቃን፣ በሰማዕታትና በመላአክት ፊት ዋጋችንን በግልጥ ይሰጠናል፡፡

 

2. የጸሎት ሥርዓት፡- ግብዞች የሚጸልዩት ለታይታ ነው፤ አንተ ግን ከቤትህ ገብተህ ደጅህን ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፡፡ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ያስረክብሃል፡፡ ብሏል፡፡ ይህም ማለት የምትጸልይበት ጊዜ ሕዋሳትህን ሰብስበህ፣ በሰቂለ ልቡና ሆነህ ወደ ሰማያዊ ወደ እግዚአብሔር አመልክት፤ ተሰውረህም ስትጸልይ የሚያይ አባትህ ዋጋህን ይሰጥሃል ማለት ነው፡፡ ይህ የግል ጸሎትን የተመለከተ ነው እንጂ በቤተ ክርስቲያን የሚደረግ የማኅበር ጸሎትን አይመለከትም፡፡

 

3. የአባታችን ሆይ ጸሎት፡- ጌታችን ማንም ቢሆን ሲቆምና ሲቀመጥ፣ ሲተኛና ሲነሣ ሊጸልይ የሚችለውን አጭር የኅሊና ጸሎት አስተማረ፡፡ ይህንንም በዝርዝር እንመለከተዋለን፡-

ሀ. አባታችን ሆይ፡- ጌታችን ከግብርናተ ዲያብሎስ /ከዲያብሎስ ባርነት/ ነጻ እንዳወጣን፣ አጥተነው የነበረውን ልጅነት እንዳገኘን ሲያጠይቅ አቡነ /አባታችን/ በሉኝ አለ፡፡ ጌታ ሎሌውን መምህር ደቀመዝሙሩን ምን ቢወደው ያበላዋል፣ ያጠጣዋል፣ የልቡናውን ምሥጢር ያጫውተዋል እንጂ ርስቱን አያወርሰውም፡፡ ርስቱን የሚያወርሰው ለልጁ ነው፡፡ እርሱ ግን ጌታችን እና አምላካችን ሲሆን የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትን የሚያወርሰን ስለሆነ አቡነ በሉኝ አለ፡፡ አባት ለወለደው ልጁ እንዲራራ የሚራራልን ስለሆነ አቡነ በሉኝ አለ፡፡

ለ. በሰማያት የምትኖር፡- እንዲህ ማለቱ ራሱ ከምድራዊ አባት ሲለይ ነው፡፡ ምድራዊ አባት ሲወልድ በግዘፍ ሲያሳድግ በግዘፍ ነው፡፡ ኋላም ሓላፊ ርስቱን ያወርሳል፡፡ ጌታችን ግን ሲወልደን በረቂቅ፣ ሲያሳድገንም በረቂቅ ነው፡፡ ኋላም የማታልፍ ርስቱን መንግሥተ ሰማይን ያወርሰናል፡፡ በተጨማሪም ጌታ በሁሉ ምሉዕ ሲሆን ስለ ልዕልናው በሰማይ የምትኖር ይባላል፡፡

ሐ. ስምህ ይቀደስ፡- ይህም “ስምየሰ መሐሪ ወመስተሠፀል” ስሜ መሐሪና ይቅር ባይ ነው፡፡” ያልኸው ይድናልና፤ መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለው ስምህን አመስግነው ቅድስናህን ተሳትፈው እንዲኖሩ፣ እኛም ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ብለን አመሰግነንህ ቅድስናህን ተሳትፈን እንድንኖር አድርገን በሉ ሲለን ነው፡፡

መ. መንግሥትህ ትምጣ፡- መንግሥተ ሰማይ ትምጣልን ልጅነት ትሰጠን በሉ ሲል ነው፡፡ እንዲህም ማለቱ መንግሠተ ሰማይ ከወዲያ ወዲህ የምትመጣ፣ ከወዲህም ወዲያ የምትሔድ ሆና ሳይሆን ትገለጽልን በሉ ማለቱ ነው፡፡

ሠ. ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁም በምድር ይሁን፡- መላእክት በሰማይ ሊያመሰግኑህ ፈቃድህ እንደሆነ እኛም በምድር ያለን ደቂቀ አዳም እናመሰግንህ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን፡፡ ኋላ ሙተን ተነሥተን እንድናመሰግንህ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን በሉ ሲል ነው፡፡

 

ረ. የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ፡- በዚህ ዓለም ሳለን ለዕለት የሚሆነን ምግባችንን ስጠን በሉ ሲል ነው፡፡

 

ሰ. በደላችንን ይቅር በለን እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል፡- ማረን፣ ይቅር በለን፣ ኃጢአታችንን አስተስርይልን፣ በደላችንን ደምስስልን መተላለፋችንን ሁሉ ይቅር በለን፤ ይቅርታን እናገኝ ዘንድ እኛም የበደሉንን ሁሉ ይቅር እንላለን ሲል ነው፡፡

 

ሸ. አቤቱ ወደ ፈተናም አታግባን፡- ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ ወደ ኃጢአት፣ ወደ ክህደት፣ ወደ መከራ፣ ወደ ገሃነም አታግባን ከዚህ ሁሉ አድነን እንጂ በሉኝ ሲል ነው፡፡

 

ቀ. መንግሥት ያንተ ናትና፡- መንግሥተ ሰማያት ያንተ ገንዘብህ ናትና በሉኝ ሲል ነው፡፡

 

በ. ኃይል ምስጋናም ለዘላለሙ፡- ከሃሊነት፣ ጌትነት፣ ለዘላለሙ ገንዘብህ ናትና፤ አሜን በእውነት በሉኝ ሲል ነው፡፡

 

4. ስለ ይቅርታ የሰውን ኃጢአት ይቅር ባትሉ የሰማይ አባታችሁ እናንተንም ይቅር አይላችሁም፡፡ የሰውን ኃጢአት ይቅር ብትሉ ግን እናንተም የሰማይ አባታችሁ ይቅር ይላችኋል ብሏል፡፡

 

5. የጾም ሥርዓት፡- ግብዞች በሚጾሙበት ጊዜ ሰው እንዲያውቅላቸው ፊታቸውን አጠውልገው፣ ግንባራቸውን ቋጥረው፣ ሰውነታቸውን ለውጠው የታያሉ፡፡ እነዚህም በዚህ ዓለም የሚቀረውን ውዳሴ ከንቱ በማግኘታቸው የወዲያኛውን ዓለም ዋጋ ያጡታል፡፡ እናንተስ በምትጾሙበት ጊዜ ራሳችሁን ተቀቡ፣ ፊታችሁንም ታጠቡ፡፡ የተቀባ የታጠበ እንዳይታወቅበት አይታወቅባችሁ አለ፡፡ ይህስ በአዋጅ ጾም ነው ወይስ በፈቃድ ጾም ነው ቢሉ በፈቃድ ጾም ነው እንጂ በዓዋጅ ጾምስ ምንም ውዳሴ ከንቱ የለበትም ምክንያቱም ሁሉ ይጾመዋልና፡፡ አንድም በገዳም ነው ወይስ በከተማ ቢሉ በከተማ ነው እንጂ በገዳምስ ምንም ውዳሴ ከንቱ የለበትም፡፡ የምሥጢራዊ መልእክቱም ታጠቡ ንጽሕናን ያዙ፣ ተቀቡ ደግሞ ፍቅርን ገንዘብ አድርጉ ማለት ነው፡፡ እንዲህም በማድረጋችሁ ማለት ጾመ ፈቃድን ተሰውራችሁ በመጾማችሁ ተሰውሮ የሚያያችሁ አባታችሁ በቅዱሳን መካከለ ዋጋችሁን ይሰጣችኋል አለ፡፡

 

6. ሰማያዊ መዝገብ፡- ጌታችን ሰማያዊ መዝገብ ያለው አንቀጸ ምጽዋትን ነው፡፡ ኅልፈት፣ ጥፋት ያለበትን፣ ብል የሚበላውን ነቀዝ የሚያበላሸውን ምድራዊ ድልብ፤ ሌቦች ግንቡን አፍርሰው ግድግዳውን ምሰው የሚወስዱትን ቦታ አታደልቡ አለ፡፡ ይህም ስለ ሦስት ነገር ተናግሮታል፡፡

 

ሀ. እህሉን፡- ነዳያን ከሚበሉት ብለው ብለው፣ ልብሱንም ነዳያን ከሚለብሱት ብለው አኑረውት ብል ቢበላው ወይም ነቀዝ ቢያበላሸው ምቀኝነት ነውና፡፡

 

ለ.ለክፉ ጊዜ ይሆነኛል ብሎ ሰስቶ ነፍጎ ማኖር በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግበውን ለጋስ አምላክ እግዚአብሔርን ከዳተኛ ማድረግ ነውና፡፡

 

ሐ. ምንም እጅ እግር ባያወጡለት ገንዘብን ማኖር ጣዖትን ማኖር ነውና ስለሆነም ኅልፈት ጥፋት የሌለበትን፣ ሰማያዊ ድልብ ሌቦች ግንቡን አፍርሰው ግድግዳውን ምሰው ከማይወስዱት ቦታ አደልቡ፤ ገንዘባችሁ ካለበት ዘንድ ልባችሁ በዚያ ይኖራልና አለ፡፡ ምሥጢራዊ መልእክቱም ውዳሴ ከንቱ ያለበትን ውዳሴ ከንቱ የሚያስቀርባችሁን፣ ሌቦች /አጋንንት/ በውዳሴ ከንቱ የሚያስቀሩባችሁን ምጽዋት አትመጽውቱ፤ ውዳሴ ከንቱ የማያስቀርባችሁን፣ ውዳሴ ከንቱ የሌለበትን ሌቦች /አጋንንት/ በውዳሴ ከንቱ የማያስቀሩባችሁን ምጽዋት መጽውቱ፤ መጽውታችሁ ባለበት ልባችሁ ከዚያ ይኖራልና ማለት ነው፡፡

7. የሰውነት መብራት፡- የሥጋህ ፋና ዓይንህ ነው፤ ዓይንህ ነው፤ ዓይንህ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ የቀና እንደሆነ ሥራህ ሁሉ የቀና ይሆናል፡፡ ዓይንህ የታመመ ከሆነ ጨለማ እንደምን ይጸናብህ? የታመመው ዓይንህ የታመመ ከሆነ ጨለማ እንደምን ይጸናብህ የታመመው ዓይንህ እንደምን ያይልሃል አለ፡፡ ምሥጢራዊ መልእክቱም እንደሚከተለው ነው፡፡

 

ሀ. ብርሃን የተባለው አእምሮ ጠባይዕ ነው፤ እዕምሮ ጠባይህ ያልቀና እንደሆነ ሥራህ ያለቀና ይሆናል፤ በተፈጥሮ የተሰጠህ አእምሮ ጠባይህ እንደምን መክበሪያ መጽደቂያ ይሆንሃል ማለት ነው፡፡

 

ለ. ብርሃን የተባለው ምጽዋት ነው፤ ምጽዋትህ ውዳሴ ከንቱ የሌለበት እንደሆነ ሥራህ ሁሉ የቀና ይሆናል፡፡ ምጽዋትህ ግን ውዳሴ ከንቱ ያለበት እንደሆነ ሥራህ ሁሉ ያልቀና ይሆናል፤ ከአንተ የሚሰጥ ምጽዋትህ ውዳሴ ከንቱ ያለበት ከሆነ ፍዳ እንደምን ይጸናብህ ይሆን እንዴትስ መክበሪያ መጽደቂያ ይሆንልሃል ማለት ነው፡፡

 

8. ስለ ሁለት ጌቶች፡- ለሁለት ጌታ መገዛት አይቻለውም፤ ይህም ባይሆን ማለት እገዛለሁም ቢል አንዱን ይጠላል ሌላውን ይወዳል፤ ለአንዱ ይታዘዛል ለሌላው አይታዘዝም ምክንያቱም አንዱ ቆላ ውረድ ሲለው ሌላው ደግሞ ደጋ ውጣ ቢለው ከሁለት ለመሆን ስለማይችል ነው፡፡ እንደዚህም ሁሉ ለእናንተም ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አይቻላችሁም አለ፡፡

 

9. የዕለት ጉርስና የዓመት ልብስ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን ምግብ ከመስጠትማ ነፍስን እም ኀበ አልቦ አምጥቶ መፍጠር አይበልጥምን ልብስ ከመስጠትማ ሥጋን ከአራቱ ባሕርያት አዋሕዶ መፍጠር አይበልጥምን ነፍስንና ሥጋን አዋሕጄ የፈጠርኳችሁ እኔ ትንሹን ነገር ምግብና ልብስን እንዴት እነሳችኋለሁ አለ ምሥጢራዊ መልእክቱም እንደሚከተለው ነው፡፡

 

ሀ. ምግብ ከመስጠትማ ነፍስን ካለችበት ማምጣት አይበልጥምን ልብስ አይበልጥምን ታዲያ ነፍስን ካለችበት አምጥቼ ሥጋን ከመቃብር አስነሥቼ አዋሕጄ በመንግሥተ ሰማይ በክብር የማኖራችሁ እንዴት ምግብና ልብስ እነሳችኋለሁ ማለት ነው፡፡

 

ለ. ሥጋዬን ደሜን ከመስጠትማ ነፍስንና ሥጋን ማዋሐድ አይበልጥምን ታዲያ ነፍስንና ሥጋን ተዋሕጄ ሰው የሆንኩላቸው እኔ እንዴት ሥጋዬንና ደሜን እነሳችኋለሁ ማለት ነው፡፡

 

ስለሆነም ዘር መከር የሌላቸውን፣ በጎታ በጎተራ በሪቅ የማይሰበስቡትን፣ ሰማያዊ አባታችሁ የሚመግባቸውን አዕዋፉን አብነት አድርጉ፡፡ እናንተ ከእነርሱ አትበልጡምን ከተፈጥሮ አዕዋፍ ተፈጠሮተ ሰብእ አይበልጥምን ለኒያ ምግብ የሰጠ ለእናንተ ይነሣችኋልን አለ፡፡ ምሥጢራዊ መልእክቱም እግዚአብሔር በምድረ በዳ የመገባቸውን እሥራኤል ዘሥጋን አስቡ፤ በዘመነ ብሉይ ከነበሩት ከእነርሱ በዘመነ ሐዲስ ያላችሁት እናንተ እስራኤል ዘነፍስ የተባላችሁት አትበልጡም ለእኒያ የሰጠሁ ለእናንተ እነሳችኋለሁን ማለት ነው፡፡

ስለ ልብስስ ለምን ትጨነቃላችሁ የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤አይደክሙም አይፈትሉም ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገርም ወደ ዕቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ ሃይማኖት የጎደላችሁ ለእናንተማ እንዴት ልብስ ይነሳችኋል ስለሆነም ምን እንበላለን ምን እንጠጣለን ምን እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ፡፡ ይህንንስ ሁሉ ሃይማኖትና ምግባር የሌላቸው አሕዛብ ይፈልጉታል፡፡ እናንተስ አስቀድማችሁ መንግሥቱንና ጽድቁን እሹ፡፡ አስቀድማችሁ ሃይማኖት ምግባርን፣ ልጅነትንና መንግሥተ ሰማያትን ፈለጉ የዚህ ዓለምስ ነገር ሁሉ በራት ላይ ዳራጐት እንዲጨመር ይጨመርላችኋል፡፡ ነገ ለራሱ ይጨነቃልና አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል አለ ይህም ለነገ ያጸናናል ብላችሁ አብዝታችሁ አትመገቡ የነገውን ነገ ትመገቡታላችሁና አንድም ነገ እንናዘዘዋለን ብላችሁ ኃጢአታችሁን አታሳድሩ የነገውን ነገ ትናገራላችሁ ማለት ነው፡፡

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 4ኛ ዓመት ታኅሣሥ 1989 ዓ.ም.