የማቴዎስ ወንጌል
ሰኔ 24 ቀን 2006 ዓ.ም.
ምዕራፍ 3
ይህ ምዕራፍ ስለጌታ መጠመቅ ይናገራል፡፡ አጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ የንስሐ ስብከት እየሰበከ ከምድረ በዳ የመጣ ነው፡፡ አስቀድሞ በነብየ ልዑል ኢሳይያስ ስለ ዮሐንስ ተነግሮ ነበር፡፡ ኢሳ.41፡3፡፡ ልብሱ የግመል ጠጉር በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ስለነበር ይህ ሁኔታው ከነብዩ ኢሳይያስ ጋር ያመሳስለው ስለነበር በኤልያስ ስም ተጠርቷል፡፡ ሚል.4፡5፣6፡፡
ኤልያስና መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን የሚያመሳስላቸው ሌላም ነገር አለ፡፡
-
ኤልያስ አክዓብና ኤልዛቤልን ሳይፈራ ሳያፍር በመጥፎ ሥራቸው እንደገሰጻቸው መጥምቁ ዮሐንስም ሄሮድስን የወንድምህን የፊልጶስም ሄሮድስን የወንድምህን የፊልጶስን ሚስት ልታገባ አልተፈቀደልህም በማለት ገስጾታል፡፡
-
ኤልያስ ንጹሕ ድንግላዊ እንደ ነበር ሁሉ መጥምቁ ዮሐንስም ንጹሕ ድንግል ነው፡፡
ዮሐንስ ያጠምቅ የነበረው ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት በመሆኑ በኢየሩሳሌምና በይሁደ የነበሩ ሁሉ ኃጢአታቸው እየተናዘዙ ከእርሱ ዘንድ ይጠመቁ ነበር፡፡
ፈሪሳውያን ሊጠመቁ ወደ እርሱ ዘንድ ሲመጡ አይቶ “እናንተ የእፉኝት ልጆች” በማለት ገሰጻቸው፡፡ ከእፉኝት ልጆች ጋር አይሁድን ያመሳስላቸው ያለምክንያት አልነበረም፡፡ እፉኝት አፈማኅፀንዋ ጠባብ ስለሆነ ከወንዱ እፉኝት አባላዘር ከስሜትዋ የተነሣ ስለምትቆርጠው ወንዱ እፉኝት በፅንስ ጊዜ ይሞታል፡፡ የእፉኝት ልጆች አባታቸውን ገድለው ይፀነሳሉ፡፡ ኋላም የመወለጃቸው ጊዜ ሲደርስ ቀደም ተብሎ እንደተገለጸው አፈማኅፀንዋ ጠባብ ስለሆነ የእናታቸውን ሆድ ቀደው ይወጣሉ፡፡ ያን ጊዜ እናታቸው ትሞታለች፡፡ አይሁድም እንደ አባት የሆኑአቸውን ነብያትን /እነኤርሚያስን/ የጌታን ልደት በመናገራቸው ገድለዋቸዋል፡፡ ኋላም እንደ እናት የሚራራላቸውንና የሚወዳቸውን ጌታ ቀንተው ተመቅኝተው ይገድላሉና በእፉኝት ተመሰሉ፡፡
መንፈስ ቅዱስንም በእሳት መስሎ ተናግሯል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእሳት የተመሰለበትም ምክንያት፡-
እሳት ምሉዕ ነው፡፡ በየትም ቦታ ይገኛል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ምሉዕ ነው፡፡ የማይገኝበት ሥፍራ የለም፡፡
እሳት በምልዓት ሳለ ቡላድ ክብሪት ካልመቱ አይገለጽም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ ሲያናግር፣ ምስጢር ሲያስተረጉም፣ ተአምር ሲያሠራ እንጂ በእኛ ላይ አድሮ ሳለ አይታወቅምና፡፡
እሳት ከመነሻው ማለትም ክብሪት ጭረን ስንለኩሰው በመጠን ነው፡፡ ገለባውን ወረቀቱን እንጨቱን እየጨማመርን ስናቀጣጥለው ግን ኃይሉ እየጨመረ፣ እየሰፋ እየተስፋፋ ይሄዳል፡፡
መንፈስ ቅዱስም መጀመሪያ በ40 ቀን ለወንዶች በ80 ቀን ለሴቶች በጥምቀት ጊዜ ጸጋውን ሲሰጥ በመጠኑ ነው፡፡ ኋላ ግን በገድል በትሩፋት ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን እያደገ ይመጣል፡፡
እሳት የነካው ምግብ ይጣፍጣል፡፡ ማለትም አሳት ጣዕምን መዓዛን ያመጣል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በሕይወታችን ጣዕመ ጸጋንና መዓዛ ጸጋን የምናገኘው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
-
እሳት በአግባቡ ቢጠቀሙበት ለሰው ልጅ ጥቅም ይውላል፡፡ ዳሩ ግን አያያዙን ካላወቁበት ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ መንፈስ ቅዱስም በአግባቡ በወንጌል የተጻፈውን መሠረት አድርገው ለሚመረምሩት ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል፡፡ ጸጋን ያጐናጽፋል፡፡ ነገር ግን ከተጻፈው ውጭ በአጉል ፍልስፍና በትዕቢት ሊመረመሩ የሚነሡ ሁሉ ትልቅ ጥፋት በሕይወታቸው ያመጣሉ፡፡
-
እሳት ገለባም ይሁን እንጨት፣ እርጥብ ይሁን ደረቅ ያቀረቡለትን ሁሉ ሳይመርጥ ያቃጥላል፡፡ መንፈስ ቅዱስም በንጹሕ ልቡና ሆኖ ለሚለምነው ሁሉ ሕፃን ዐዋቂ ድኻ ሀብታም ሳይል የጸለዩትን ጸሎት ያቀረቡትን መሥዋዕት ይቀበላል፡፡
-
አሳት የበላው መሬት ለእህል ለተክል ተስማሚ ነው፡፡ ጥሩ ምርት ይገኝበታል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰውነት ለገድል ለትሩፋት ያመቻል፡፡
-
እሳት ተከፍሎ አይኖርበትም፡፡ ማለትም ከአንዱ የሻማ መብራት ሌላ ሻማ ብናበራ የሻማው መብራት አይጉድልም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ተከፍሎ ወይም የጸጋ መጉደል መቀነስ ሳይኖርበት እስከ ምጽአት ድረስ ለምእመናን ጸጋውን ሲሰጥ ይኖራል፡፡
-
ሸክላ ሠሪ ሥራዋን ሠርታ ስትጨርስ ስህተት ያገኘችበት እንደሆነ እንደገና መልሳ ከስክሳ በውኃ ለውሳ በእሳት ታድሰዋለች፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ንጹሕ ሆኖ የተፈጠረ ሰው ከእግዚአብሔር ሕግ ቢወጣና በኃጢአት ቢያድፍ በንስሐ ሳሙና ታጥቦ በመንፈስ ቅዱስ ታድሶ አዲስ ሰው ይሆናል፡፡
መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ስለአጠመቀው ሲመሰክር ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ነኝ ብሏል፡፡ በዚህም የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ተናግሯል፡፡ “መንሹም በእጁ ነው” ሲል ገበሬ በመንሽ ፍሬውን ከገለባው እንደሚለይ ጌታችንም ጻድቃንን ከኃጥአን የመለየት ሥልጣኑ የራሱ ነውና፡፡ በጐተራ መንግሥተ ሰማያትን፣ በስንዴ፣ ጻድቃንን፣ በገለባ፣ ኃጥአንን፣ በማይጠፋ እሳት፣ ገሃነመ እሳትን መስሎ ተናግሯል፡፡
ይጠመቅበት ዘንድ ጌታ በኢየሩሳሌም ካሉት ወንዞች ሁሉ ዮርዳኖስን የመረጠበት ምክንያት፡-
-
በተነገረው ትንቢት መሠረት ነው፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ በሚጠመቅበት ጊዜ የሚሆነውን አስቀድሞ ተንብዮ ነበር፡፡ ያን ለመፈጸም ነው መዝ.113/114፡3-5፡፡
-
ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡ ኤልያስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደ ዐረገ ምእመናንም አምነው ተጠምቀው ገነት መንግሥተ ሰማይ ለመግባታቸው ምሳሌ ነው፡፡
-
የእምነት አባት አብርሃም ነገሥተ ኮሎዶጎሞርን ድል ነሥቶ ሲመለስ የጌታን ቀን ሊያይ ወደደ፡፡ ጌታም ምሳሌውን ሊያሳየው ዮርዳኖስን ተሻግሮ እንዲሄድ አዘዘው፡፡ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ሲሄድ መልከ ጸዴቅ ኅብስተ በረከት ጽዋዓ አኰቴት ይዞ ተቀብሎታል፡፡ አብርሃም የምእመናን ምሳሌ ሲሆን ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ፣ መልከ ጸዴቅ ደግሞ የካህናት፣ የቀሳውስት ኅብስተ በረከት፣ ጽዋዓ አኰቴት የሥጋው የደሙ ምሳሌ ነው ዘፍ.14፡10-20፡፡
-
የአዳምና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ ነው፡፡ ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን የባርነት ስማቸውን እንዲጽፉለት አድርጐ የዕዳ ደብዳቤውን አንዱን በሲኦል ሌላውን በዮርዳኖስ ወንዝ አኑሮት ስለነበር ጌታም በዮርዳኖስ ያለውን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ በዚያ ተጠመቀ ቆላ.2፡14፡፡
ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ
ሀ. ሰማይ ተከፈተ፣
ለ. አብ በደመና ሆኖ ስለ ወልድ መሰከረ፣
ሐ. መንፈስ ቅዱስም በጥንተ ተፈጥሮ በውኃ ላይ እንደታየ አሁን በሐዲስ ተፈጥሮ ታየ፡፡
ይህም አስተርእዮ /ኤጲፋንያ/ ይባላል፡፡ የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት የተገለጠበት ወቅት ነውና የመገለጥ ዘመን ተብሏል፡፡
- ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 4ኛ ዓመት ቁጥር 1 መስከረም 1989 ዓ.ም.