የመጻሕትና የድምጽ ወምስል የምረቃ መርሐ ግብር ተካሔደ
ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
በማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት አስተዳደር ያሳተማቸውን መጻሕፍትና የድምጽ ወምስል የምረቃ መርሐ ግብር ሚያዚያ 27 ቀን 2004 ዓ.ም. በብሔራዊ ሙዚየም ትልቁ አዳራሽ አስመረቀ፡፡ ከተመረቁት መጻሕፍትና የድምጽ ወምስል ሥራዎች መካከል ዐስሩ የትርጉምና ወጥ መጻሕፍት ሲሆኑ በቪሲዲ እና በሲዲ የተዘጋጁ የአማርኛና የሞሮምኛ ስብከቶች ዘጋቢ ፊልሞች፣ ትርጉም ፊልሞችና መዝሙራት ይገኙበታል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያም መርሐ ግብሩን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር በምረቃው ላይ የተገኙትን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችን በማመስገን ማኅበረ ቅዱሳን ከተሠረተ 20 ዓመታት አንስቶ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ከተጠቀመባቸው መንገዶች ዋነኛው መንፈሳዊ ጋዜጣ መጽሔትና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የተጻፉ መጻሕፍትንና የድምጽ ወምስል ውጤቶችን እያሳተመ ይገኛል፡፡ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ የልማት ተቋማት አስተዳደርን በሥሩ በመመሥሪት ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ ለማድረግ የኅትመት ውጤቶችን በማሳተምና በማሰራጨት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
ከኅትመት ከበቁት የድምጽ ወመስል ሥራወች መካከል ከእያንዳንዱ የተቀነጨቡ ክፍሎች የቀረቡ ሲሆን የመጻሕፍት ደራሲያንና ተርጓሚያን ከመጻሕፍቱ አንድ አንድ አንቀጽ አንብበዋል፡፡ በዲ/ን ታደለ ፈንታው በኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል የመጻሕፍት ዝግጅት ክፍል አስተባባሪና በአቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ የልማት ተቋማት አስትዳደር ዳይሬክተር የመጻሕፍት ዝግጅት ክፍል እንቅስቃሴና የልማት ተቋማት አስተዳደር ልዩ ልዩ ክፍሎች ያከናወኗቸውን ተግባራት አጠር ያለ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
“የንስሓ ሸንጎ” የተሰኘ ወጥ መንፈሳዊ ልቦለድ የድርሰት ሥራቸውን ያቀረቡት ደራሲት ፀሐየ መላኩ ስለ ጥረታቸውና ሥራዎቻቸው ሲገልጹ አለማዊ ሕይወት መሠረቱና ማቃኛው መንፈሳዊ ሕይወት ነው ሁለቱንም ለማገናዘብ አጋጣሚው ነበረኝ ይላሉ፡፡ በተለይም አባታቸው ካህን ስለ ነበሩ ከለጅነት ጀምሮ መንፈሳዊ እውቀትን ለመቅሰም እድሉን አግኝተዋል፡፡ የኅብረተሰቡን ሕይወትና ፍላጎት፣ እምነት፣ ትዝብትና ገመና ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትን ወደ ኅብረተሰቡ አድርሰዋል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ አለማዊውን ሕይወት ማስተካከልና የተሟላ ስብእና ማግኘት እንደሚቻል ማስተማር ስለፈለግሁ “የንስሓ ሸንጎ” የተሰኘውን ወጥ መንፈሳዊ ድርሰት አቅርቤያለሁ ብለዋል፡፡ ሙሉ ጊዜያቸውን ለሥነ ጽሑፍ እንደሚሰጡና የኢትዮጵያዊው ታላቁ የሃይማኖት አርበኛ የሆኑት የቅዱስ ጴጥሮስን ታሪክ ለመጻፍ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ሕልውና እንዳይቋረጥ አጋዥነቱን እያሳየ ስለሆነ ይህንን የጀመረውን ጉዞ ሌሎችንም ጸሐፍት የሚያበረታታ ስለሆነ ቢቀጥልበት በማለት አሳስበዋል፡፡ ደራሲት፣ ገጣሚት፣ ሰዓሊት ፀሐይ መላኩ “እመምኔት” የተሰኘ መንፈሳዊ ልቦለድ መጽሐፍ ከዚህ በፊት ከጻፏቸው መጻሕፍት መካከል አንዱ ሲሆን አሁን ደግሞ “የንስሓ ሸንጎ”ን ይዘው ቀርበዋል፡፡ በመጽሐፉ ዙሪያ በዲ/ን ታደለ ፈንታው መጽሐፍ ያተኮረባቸው መሠረታዊ ነጥቦት ላይ ትንታኔ ተሰጥቷል፡፡
ለምረቃ ከበቁት መጻሕፍት 3ቱን የጻፉት ዲ/ን ታደለ ፈንኀታው ስለ መጻሕፍቱ እንደገለጹት መጻሕፍቱ ነገረ ቅዱሳንን የሚያወሱ ናቸው፡፡ አስቀድሞ የነበሩ አባቶቻችን አሁን ያለው ትውልድ እየተፈተነበት ያለውን ሕይወት እግዚአብሔርን በመያዝ በመንፈሳዊ ሕይወት እንዴት እንደተመላለሱ ስለሚያሳይ ትውልዱ ራሱን እንዲጠብቅ ታላቅ መልእክት ያስተላልፋሉ ብዬ ስለማስብ ትኩረቴ ነገረ ቅዱሳን ላይ አድርጌአለሁ” ብለዋል፡፡
በመጻሕፍቱና በድምጽ ወምስል ሥራዎቹ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን በተለይም ማኅበረ ቅዱሳን ማተማያ ቤት ቢኖረው በኅትመትና ሥርጭት ረገድ አገልግሎቱን ማስፋፋት ይችል እንደነበር ተገልጿል፡፡ በተሰጡ አስተያየቶች ዙሪያ በማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋመት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ደራሲያን የማተሚያ ቤት ሓላፊዎች ከተለያዩ ደራሲያን ማኅበራትና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራንም ያሬዳዊ ዝማሬን አቅርበዋል፡፡