የመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም የሐዲስ ኪዳን ደቀ መዛሙርት ተመረቁ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በማእከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት በመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም የመጻሕፍተ ሐዲሳት እና ሊቃውንት ጉባኤ ቤት 18 የሐዲስ ኪዳን ደቀ መዛሙርት ኅዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና ሕዝበ ክርስቲያን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተመረቁ፡፡
ጉባኤ ቤቱ የተጀመረው በ1860 ዓ.ም በመምህር ወልደ ሚካኤል ነው፡፡ መምህር ወልደ ሚካኤል በጎንደር ከተማ ደብረ መድኃኒት ዐቢየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት ወመርቆሬዎስ የመጻሕፍት ጉባኤ ቤት ከመምህር ወልደ አብ የተማሩ ናቸው፡፡ መምህር ወልደ አብ ደግሞ ሐዲስ ኪዳኑን ተማሩት ከአለቃ ከብቴ ነው፡፡ በ1882 ዓ.ም የመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በድርቡሽ ተቃጥሎ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ለ19 ዓመታት ተዘግቶ ቆይቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ሲቃጠል ደቀ መዛሙርቱም ‹‹እኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ነን›› በማለት ራሳቸው መምህር ወልደ ሚካኤል እና ስምንት ደቀ መዛሙርት በድርቡሽ ሰማዕት ሆነዋል፡፡ በዚህም የሰንበት ትምህርት ቤቱ አዳራሽ በጉባኤ ቤቱ ታላላቅ መምህራን ተሰይሟል፤ ይኸውም ‹‹ወልደ አብ ወልደ ሚካኤል›› ይባላል፡፡
መምህር ወልደ ሚካኤል ከዐረፉ በኋላ በጉባኤ ቤቱ የተተኩት መምህር ተክለ ማርያም ናቸው፡፡ መምህር ተክለ ማርያም ብዙ መምህራንን አፍርተዋል፡፡ ለአብነትም፡- ዶክተር አለቃ አየለ፣ መምህር ወልደ ሰንበት፣ መምህር ወልደ ጊዮርጊስ፣ መምህር ክፍሌ ይመር፣ መምህር ምሕረቱ፣ መምህር ታየ እና መምህር ገብረ ማርያም ይገኙበታል፡፡ በመቀጠልም መምህር ተክለ ማርያም ካረፉ በኋላ በእሳቸው እግር ተተክተው ያስተማሩ መምህር ክፍሌ ይመር ሲሆኑ ለ 47 ዓመታት ያህልም በጉባኤ ቤቱ አስተምረዋል፡፡ ከዚያም እስከ ቅርብ ጊዜ የነበሩት እና የሚታወቁት መምህር ወልደ ሰንበት ከ38 ዓመት በላይ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ አስተምረዋል፡፡
ከየኔታ ወልደ ሰንበት ዕረፍት በኋላ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በምክትል መምህርነት ሲያገለግሉ የነበሩት መጋቤ ሐዲስ ቃለ ሕይወት በዛ በአባቶች ወንበር ተተክተው በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡
በዕለቱ 18 የሐዲስ ኪዳን ደቀ መዛሙርት የተመረቁ ሲሆን ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ከውዳሴ ማርያም ትርጓሜ እስከ ራዕየ ዮሐንስ ትርጓሜ ተምረው አጠናቀዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በጉባኤ ቤቱ 50 ደቀ መዛሙርት በመማር ላይ ናቸው፡፡
የጉባኤ ቤቱ የትምህርት አሰጣጥም ዘወትር ከሰኞ እስከ ዐርብ ጠዋት ከ3፡00 እስከ 6፡30 ሲሆን እንዲሁም ዘወትር ሰኞ፣ረቡዕ እና ዐርብ የስብከት ዘዴ ከ2፡00 እስከ 3፡00 እርስ በእርሳቸው ይማማራሉ፡፡ ይኸውም 30 ደቂቃ የስብከት፣10 ደቂቃ የአስተያየት መቀበያ፣10 ደቂቃ የጥያቄ መጠያየቂያ፣10 ደቂቃ የእርማት ማስተካከያ በማድረግ የመማር ማስተማሩ ሂደት በዚህ መልክ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዘመናዊ ትምህርት መማር ለሚፈልጉ ደቀ መዛሙርት አራቱ ወንጌላትን ከጨረሱ በኋላ ማታ ማታ ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ ጉባኤ ቤቱ ይፈቅዳል፡፡
አንድ ሰው ወደ ጉባኤ ቤቱ ገብቶ ለመማር ቢፈልግ የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት አለበት፡፡ አቋቋም፡- አዋቂ ከሆነ ቢያንስ ለራሱ ቅኔ አዋቂ መሆን አለበት፡፡ በተመሳሳይ ቅዳሴ፡- አዋቂም ከሆነ የቅኔ መምህር እንኳን ባይሆን ቢያንስ ለራሱ ቅኔ አዋቂ መሆን አለበት፡፡ ወደ ጉባኤ ቤቱ ገብቶ ለመማር ቢያንስ አንድ ጊዜ ቅኔ መቀኘት አለበት፡፡ ሙያው ቅኔ ብቻ ከሆነ ዘራፊ፣ አስነጋሪ ወይም መምህር የመሆን ግዴታ አለበት፡፡
በአጠቃላይ ወደ ጉባኤ ቤቱ ገብቶ መማር የሚፈልግ ሁሉ ቢያንስ ቅኔ አንድ ጊዜ መቀኘት አለበት፤ ቅኔ ካላወቀ ገብቶ ለመማር አይፈቀድለትም፡፡ ሲገቡም ፈተና ያለው ሲሆን ከ100 ከ50 በታች ያመጣ ገብቶ መማር አይችልም፡፡ ተፈታኙ ቅኔ አዋቂ ከሆነ ፈተናው አገባብ፣ የቅኔ ሙያ እና ከበድ ያለ ንባብ ይሆናል፡፡ ተፈታኙ አቋቋም አዋቂ ወይም የቅዳሴ መምህር ከሆነ ግስ ይጠየቃል፡፡
ጉባኤ ቤቱ በትርጓሜ አተረጓጎም ስልቱም ከሌሎች ጉባኤ ቤቶች ይለያል፡፡ የራሱ የሆነ የአብነት ጥሬ ዘር እና ትርጓሜ ያለው ነው፡፡ የመማር ማስተማር ሂደቱም መምህሩ በመጀመሪያ ለደቀ መዛሙርቱ ከተረጎሙላቸው እና ምሥጢሩን በደንብ ካስረዷቸው በኋላ በበነጋታው ደቀ መዛሙርቱ የተረዱትን በቃል ሸምድደው እና ምሥጢሩን አውቀው ልክ እንደ መምህራቸው ተርጉመው ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ያልፋሉ፤ ደቀ መዛሙርቱ ካልተረጎሙት ግን እዛው ይቆያሉ እንጅ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ማለፍ አይችሉም፡፡ ይህ የአተረጓጎም ስልት ወደር የሌለውና ደቀ መዛሙርቱን በቀላሉ የአብነት መምህራን ሆነው በብቃት እንዲወጡና በሌሎች ቦታዎች ሂደው ጉባኤ ተክለው ወንበር ዘርግተው ለማስተማር ብቁ ያደርጋቸዋል፡፡
ጉባኤ ቤቱ በመላው ዓለም የሚያስተምሩና የሚያገለግሉ ጳጳሳት፣መምህራን እና ሰባክያነ ወንጌልን አፍርቷል፡፡ ለምሳሌ፡- ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ፣ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ እና መምህር ገብረ መድኅን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የብሉይ ኪዳን መምህር እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
ቢሆንም የጉባኤ ቤቱ ክፍተቶች እንዳሉትም መገንዘብ ይገባል፤ ይህም የሰርከ ኅብስት/የዕለት ምግብ/ ችግር ነው፡፡ በቂ መተዳደሪያ ገቢ የሌለው ሲሆን የሚተዳደረውም በበጎ አድራጊ ምእመናን ነው፡፡ ከበጎ አድራጊ ምእመናን መካከል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሰማንያ አምስት ሺህ ብር/85000ብር/ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ወ/ሮ ዘውዴ ገብረ እግዚአብሔር ደግሞ 40 አልጋ፣40 ፍራሽ፣40 ብርድ ልብስ እና 80 አንሶላ በማምጣት ለጉባኤ ቤቱ ድጋፍ አድርጋለች፡፡
በተጨማሪም በቋሚነት ማኅበረ ቅዱሳን ለ10 ደቀ መዛሙርት በየወሩ የ100 ብር ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን ሀገረ ስብከቱ ደግሞ ለ10 ተማሪዎች የ80 ብር ድጋፍ በየወሩ በቋሚነት ያደርጋል፡፡ የደብሩ ሰበካ ጉባኤም የመብራት እና የውኃ አገልግሎት ለደቀ መዛሙርቱ ይሰጣል፡፡ የጉባኤ ቤቱ ምስክር መምህር መጋቤ ሐዲስ ቃለ ሕይወት በዛ በበኩላቸው የሚቻለው ባለተስፋ የሰርከ ኅብስቱን ችግር እንዲቀርፍልን እና ሌሎች የጉባኤ ቤቱን ችግሮች እንዲፈታልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ በተመራቂ ደቀ መዛሙርት ቅኔ እና ወረብ ቀርቧል፤ እንዲሁም በአባ ገብረ ኪዳን ግርማ በመንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባኤያት ምስክር ትምህርት ቤት የሊቃውንት ደቀ መዝሙር በሆኑት ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል፡፡ ተመራቂ ደቀ መዛሙርቱም በመመረቃቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡