የመንፈስ ልዕልና
ልዕልና ከተለመደ ነገር ላቅ ማለትን፣ ሰው ሊሠራው ከሚችለው በላይ መስራትን ያመለክታል፡፡ በአስተሳሰብ ምጥቀት፣ በሚፈጸም ጀብዱ ይገለጻል፡፡ ጥብዓት፣ በመንፈሳዊ ቆራጥነት፣ ወኔ፣ በተፋፋመ አካላዊ ሆነ መንፈሳዊ ጦርነት ለመግባት መጨከን የልዕልና መገለጫዎች ናቸው፡፡ “በሞት ጥላ መካከል እንኳን ባልፍ ክፉን አልፈራም አንተ ከእኔ ጋር ነህና” እንዳለ መዝሙረኛው፡፡
ሥጋዊ ፈቃድ የጠየቀውን ሁሉ አለመተግበር፣ በስሜት የተፈጠረን ሁሉ ለማስተናገድ አለመሞከር በተቃራኒው መንፈስ በሥጋ ላይ ማሰልጠን ወይም ሥጋን ለመንፈስ ማስገዛት የልዕልና ተግባር ነው፡፡ የሰሙትን ምሥጢር መጠበቅ፣ የተቀበሉትን አደራ መወጣትም እንዲሁ ቃልን መጠበቅ፣ ታምኖ መሰማራት፣ አደራን መመለስ ለሁሉ አይቻለውም፡፡ ልዕልና በፈተና መጽናትን፣ እንደወርቅ መቅለጥን፣ ሌላው እየበላ ጦም ማደርን፣ ሌላው እየዘነጠ በድህነት መማቀቅን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የሚያልፈውን በማያልፈው አሸንፈው፣ ጊዜያዊውን በዘለዓለማዊው ተቆጣጥረው የተጋረጠባቸውን ያሸንፉታል ለልዕልና የታጩቱ፡፡
ሰው ለልዕልና የሚታጨው የፈተናን የክብር ምንጭነት አምኖ ሲቀበል ነው፡፡ አደራ ለመቀበል መብቃት፣ አደራም ለመስጠት ሰውን ማመን ልዕልና አይደለም ትላላችሁ? “መተማመን ከሌለ አደራ ሰጪም አደራ ተቀባይም አይኖርም” እንዲሉ አበው፡፡ ይህ ብቻም አይደል “አደራ ጥብቅ ሰማይ ሩቅ” በማለት ታምኖ መገኘትና አደራን መወጣትን ከሰማይ ርቀት ጋር ያነጻጽሩታል፡፡ እኒህ የተጠቀሱት የልዕልናና የአደራ ጥብቅነት ማሳያዎች ምግባርን ከሃይማኖት አዋሕደው፣ ፍቅረ እግዚአብሔርንና አክብሮተ ሰብእን አጣምረው እንዲኖሩ ኅሊናን ገርተው፣ ጊዜያዊ የሥጋ ፍላጎትን ተቆጣጥረው ይኖራሉ፡፡
አደራን ለተወጣ ማኅበረሰቡ የሚያቀርብለት ሙገሳ፣ ውዳሴ፣ ሞራላዊ ሽልማት ለልዕልና ያበቃል፡፡ ሌሎች አደራውን ተወጥቶ ክብር የተቸረው ከደረሰበት ለመድረስ አርአያነቱን ይከተላሉ፡፡ እውነትን ከሐሰት የማያቀላቅል፣ የገባውን ቃል የማይከዳ ይከበራል፡፡ እንዲፈራ የሚያደርገው የመንፈስ ልዕልናው ነው፡፡
አደራ የመተማመን፣ የጽኑ ፍቅር ውጤት በመሆኑ አደራ የሚሰጠው ለሚታመን ሰው ነው፡፡ በመተማመን የሚተገበረው አደራ የማያልፍ ዘለዓለማዊ ክብር ያጎናጽፋል፡፡
ክብሩ ምድራዊም ሰማያዊም ሊሆን ይችላል፡፡ “የምትጸድቅን ነፍስ ጎረቤት ያውቃታል” የሚለው ብሂል ለዚህ ትንታኔ ድጋፍ ይሆናል፡፡ አደራን ሳይወጡ ከመቅረት ይልቅ ሞትን መምረጥና ክብርን ተክሎ ማለፍ መብለጡን ሐዲስ ዓለማየሁ በማይጨው ጦርነት ጊዜ ተመልክተውት በኅሊናቸው ታትሞ የቀረን ክስተት እንዲህ ይተርኩታል፡፡
“ጌትየው በጽኑ ቆስለው በጣዕር ውስጥ እንዳሉ እሷ ስታስታምማቸው እንደማይተርፉ ተረድተውት ኖሮ አንቺና ተስፋው ከሞት ተርፋችሁ ሀገራችሁ ለመግባት የበቃችሁ እንደሆነ መሳሪያዬንና አባቴ ሲሞቱ ለመታሰቢያቸው የሰጡኝን ዳዊቴን ለልጄ ለንጋቱ እንድታደርሱልኝ አደራ፡፡ እንግዲህ ያች ሰው ሁሉ ነፍሷን እንድታተርፍ ያን ያህል ሲማጠናት ዐይኗ ዕያየ በቦንብ ተቃጥላ የሞተች የወዳጇን የአደራ ኑዛዜ ለመፈጸም ኖሯል፤ ምን አይነት እስከ ሞት የሚያደርስ ታማኝነት ነው ምን አይነት ሀያል ፍቅር ቢሆን ነው? ለሃይማኖቷ ብላ፣ እንዲያ ተቃጥላ ሞተች፡፡” አለ ሰውየው፡፡ /ሐዲስ፣ 1985፣86ዓ.ም/
በዚያ ፍጥረተ ዓለም በፍርሃት በሚናጥበት፣ ሳር ቅጠሉ፣ ሰው አራዊቱ በሚያረግድበት ሰዓት አደራ መስጠትም ሆነ መቀበል አስቸጋሪ ነበር፡፡ ልጄ ሆይ ሰው ሁን ያለው እንዲህ ላለው ሰዓት ይሆን እንዴ? አደራ ሰጭው የሴትየዋን ፍቅርና ታማኝነት መዝነውታል፡፡ አደራ የተሰጣቸው ሁለት ነገሮች ጠመንጃና ዳዊት ናቸው፡፡ ሁለቱም ከጠላት መጠበቂያ ናቸው፡፡ አንዱ አፍአዊ ሌላው መንፈሳዊ ጠላትን ለመውጋት ያገለግላሉ፡፡ አንደኛው ባህር ተሻግሮ የመጣን ጠላት ለመቆጣጠር፣ ሌላኛው ከርስት መንግሥተ ሰማያት ከሚነጥል ጠላት ጋር ለመዋጋት ጋሻ ጦር የሚሆን ነው፡፡
ሴትየዋ በዚያች ቀውጢ ሰዓት የተሰጣትን አደራ ለመፈጸም ተነስታለች፡፡ ታማኝነት፣ አደራና ታላቅ ፍቅር በአንድ በኩል ሞት በሌላ በኩል ትይዩ ሆነው ቀርበዋል፡፡ ሞትን ፈርተው ማፈግፈግ ታማኝነትን ያፈርሳል፣ ታላቅ ፍቅርን ያቀዘቅዛል፣ አደራ በላም ያደርጋል፡፡ ከሁለቱ መምረጥ ስለነበረበት ሞትን ተጋፍጦ ታማኝነትን ማስመስከር ደምቆ ታያት፡፡ ቃልን አጥሮ፣ አደራን በልቶ በቁም ከመሞት ሥጋዊ ዕረፍትን ተቀብሎ ስምን ከመቃብር በላይ ማዋልን መረጠች፡፡ ሞትን ተገዳድረው የወጡት ታማኝነት፣ ሀያል ፍቅርና አደራ የሃይማኖትና የማተብ መገለጫዎች ሆኑ የሴቷ የፍቅር መስዋዕትነት ሀያል ፍቅር እኮ ሞኝም እብድም፣ ሃይማኖተኛም ሁሉንም ያደርጋል ተባለበት፡፡ በምድራዊ አደራ ብላ የፈጸመችው የሃይማኖትና የማኅተብ መገለጫ ሆነ፡፡ ሴትየዋ በዚህ ሰማዕትነቷ ከጊዜያዊ የጭን ገረድነት ወደ ዘለዓለማዊ የፍቅር ተምሳሌትነት ተቀየረች፡፡ ያለውን የሰጠ ይመሰገናል፤ ራሱን የሰጠ ደግሞ ተከብሮ ይኖራልና፡፡ የተሰጣትን አደራ ለመወጣት ያንን መስዋዕትነት ባትከፍል በደራሲው ምናብ ገድሏ ታትሞ ባልቀረ ነበር፡፡
የአደራን ጥብቅነት በተመለከተ ሁለት ነጥቦችን በመጨመር ሀሳቤን ላጠቃልል፡፡ ከዛሬ ዐስራ ዐራት ዓመት በፊት በአንድ ወረዳ ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ መምህር ሆኜ ሥሠራ በአደራ ጠባቂነታቸው ሀገር ስለ መሰከረላቸው የትምህርት ቤት ጥበቃ ባልደረባዬ አጫውቶኛል፡፡ እኒህ ሰው የሰው ገንዘብ እንደማይነኩና አደራ እንደሚጠብቁ የሚያውቅ አንድ መምህር ከቦታው ሲቀየር የተረፈችውን ዐራት ቁና ገብስ የሚያደርስበት ያጣል፡፡ ለሌላ እንዳይሰጠው ከማን ለማን ያደላል፡፡ ይዞት እንዳይሄድ የዐስራ ሁለት ሰዓት የእግር መንገድ ከሌላው ጓዙ በተጨማሪ ዐራት ቁና ገብስ መያዝ ሊጠበቅበት ነው፡፡ አማራጭ ሲያጣ የሰው ገንዘብ እንደማይነኩ ለሚታወቁት የጥበቃ ሠራተኛ አደራ ብሎ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህን ያደረገው ስቀር ይጠቀሙበታል ብሎ በማሰብ ነው፡፡ ታሪኩን የነገረኝ ባልደረባዬ ተመድቦ ይሄዳል፡፡ አንድ ቀን ለዝክር ቤታቸው ሄዶ ጠላ እየጠጡ ሲጫወቱ ተንጠልጥሎ ጠቀርሻ የጠጣ ነገር ይመለከትና ምንነቱን ይጠይቃቸዋል፡፡ ምን እባክህ ያ እገሌ የሚባል ሰው አደራ አስቀምጦብኝ ይኸው ተንጠልጥሎ ቀረ ይሉታል፡፡ ባልንጀራዬም በዚህ ዘመን እንዲህ ያለ ሰው በማየቱ ተገርሞ በዓመቱ እኔ ካለሁበት ትምህርት ቤት ተቀይሮ ሲመጣ አጫውቶኛል፡፡
ቃሌን አጥፌና አደራዬን በልቼ ከችግሬ ላልወጣ ለምን ከፈጣሪዬ እጣላለሁ በማለት ይመስለኛል የሰውየው ጥንቃቄና ታማኝነት ስንቶቻችን ለማይሞላ ሆድ፣ ለማይረካ ፍላጎት ያውም ለነገ ለማይተርፍ ነገር አደራችንን በልተን ከፈጣሪ የተጣላን፤ ሰውም የታዘበን፡፡ 60 ዓመት በፈጣሪያቸው ረድኤት የኖሩ አባት በአንድ እለት ለምሳ ቋጥሯት የነበረችውን አገልግል የዛሬን ይብሉልኝ ብሎ በለመናቸው ጊዜ ዛሬ ያንተን አገኘሁ ብዬ በልቼ 60 ዓመት ከመገበኝ ፈጣሪዬ ልለይ እንዳሉት አባት ማለት ነው፡፡ ላይሞላ፣ ቀዳዳ ላይደፈን፣ ችግር ከልኩ ላያልፍ፣ አምላክ ያለው ላይቀር፣ እኛም ከተፈቀደልን ደረጃ ከፍ ላንል ስንቱን አደራ ኑሮ በላነው?
የጽሑፌ ማጠቃለያ የአለቃ ለማ ኃይሉ እና የአለቃ ተጠምቀ ታሪክ ነው፡፡ በትምህርት የኖሩት ሊቁ አለቃ ለማ ዋድላ ድላንታ ቅኔ ሲማሩ ኖረው ዐባይን ተሻግረው በዘመኑ የቅኔና የመጻሕፍት ማስመስከሪያ ከነበሩት መጀመሪያ ሞጣ ጊዮርጊስ ቀጥሎም ዲማ ጊዮርጊስ ይመጣሉ፡፡ ዲማ ጊዮርጊስም ከአለቃ ተጠምቀ ጋር ይገናኛሉ፡፡ አለቃ ተጠምቀ ዐይነስውር ናቸው፡፡ ብሉይ ኪዳንን ከነ አለቃ ለምለም በ6 ወር የወጡ ተጠምቀና ደቀመዝሙሩ አለቃ ለማ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ይነሳሉ፡፡ ዘመኑ በኢትዮጵያ ታሪክ ክፉ ቀን የተባለው፣ ሰውም ከብቱም ያለቀበት እናት የልጇን ሥጋ ሳይቀር የበላችበት አስቸጋሪ ዘመን ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ከዲማ መምህራቸውን እየመሩ ደብረ ሊባኖስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ከዚያም አንኮበር መጨረሻም አዲስ አበባ መካነ ሥላሴ በማለት አብረዋቸው ኖረዋል፡፡ በወቅቱ ርሃቡ ከመጽናቱ የተነሣ የሚበላ ጠፍቶ በሦስት ቀንም፣ በአራት ቀንም የሚቀመስ ሲገኝ አብረው እየቀመሱ ምግባቸውን ቃለ እግዚአብሔር አድርገው ክፉውን ቀን አሳልፈዋል፡፡ በጊዜው ወጣት የነበሩት አለቃ ለማ በልቼ ወደ ማድርበት ልሂድ ሳይሉ ከመምህራቸው ጋር ተናንቀው ቀኗን አሳለፏት፡፡ በሚያልፍ ቀን፣ በሚያልፍ ችግር የቀለም አባታቸውን አልለወጧቸውም፡፡ እንዲያውም ለዚህ ደረጃ ያደረሰኝ ከእሳቸው ያገኘሁት በረከት ነው ይላሉ፡፡ ይህን የመንፈስ ልዕልና የሚያገኙና ሲያገኙትም የበረከት ምንጭነቱን ተረድተው የሚገጥማቸውን ጊዜያዊ ፈተና የሚወጡ ምንኛ የተባረኩ ናቸው!
- ሐዲስ ዓለማየሁ ትዝታ፣ 1985ዓ.ም፣ ሜጋ አሳታሚ ድርጅት፣
- መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ 1959ዓ.ም፣
- ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ፣ ከበረሃውያን ሕይወትና አንደበት ጥር 2003ዓ.ም፣
- ባሕሩ ዘውዴ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ አ.አ.ዩኒቨርሲቲ 1989ዓ.ም፡፡/