የሕይወት መዓዛ
ቀሲስ ኃይሉ ብርሃኑ
ሚያዝያ ፳፬፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
የሕይወት መዓዛ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት የተሰጠን ልዩ የመዳን መንገድ ነው። መድኃኒዓለም ክርስቶስ ሕይወትን ያጣጣምንበትና ያሸተትንበት መልካም መዓዛ መሥዋዕት ነውና።
አሁን ያለንበት ወቅት የክርስቶስን ትንሣኤ የምናስብበት እንዲሁም የእኛም ለዘለዓለም የመኖር ተስፋ ያረጋገጥንበት በመሆኑ መዓዛ ሕይወት ለመኖር የምንናፍቅበት ወቅት ነው። ይህም በዓለ ኅምሳ የሚባለው ከትንሣኤ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ ድረስ ያለው ኅምሳው ዕለት ነው:: በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ትንሣኤ ታከብራለች፡፡ በክርስቶስም ያገኘችውን ዕረፍተ ነፍስ ዕረፍተ ነፍስ በምልአት ትሰብካለች። በዓለ ኅምሳ በመንግሥተ ሰማያት የምንኖረው ኑሮ መታሰቢያ በመሆኑ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ታዘክራለች፤ በነዚህ ዕለታት ረቡዕና ዓርብ አይጾሙም፤ ቀኖና ለተነሳሕያን አይሰጥም፤ በስግደት፣ በድካም፣ በትምህርት፣ የሚኖሩ ሁሉ በዕረፍት ያሳልፉታል፡፡
በዚህ ወቅት ትንሣኤውን በተመለከተ ድካም የማያስከትሉ የቅዳሴ፣ የመዝሙርና የማሕሌት ሥርዓተ አምልኮ ብቻ ይፈጸማል፤ ይኸውም ጌታችን የትንሣኤያችን በኵር ነውና እኛም እርሱን አብነት አድርገን ከተነሣን በኋላ እግዚአብሔር ረኀብ፣ ጥም፣ ድካም፣ ሕመም፣ ፈተና፣ ሞት፣ ኀዘን፣ መቃብር፣ እርጅና፣ ልደት ልህቀት፣ ኀይለ ዘር፣ ኀይለ ንባብ፣ ኀይለ እንስሳ የሌለበትን፣ ሥርዓተ ምድር አልፎ በአዲስ ሥርዓተ ሕይወት የምትመራውን ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን ለማለት ነው፡፡
ቀኖና የማይሰጠውም ወደፊት ጌታችን ከመበደል ነጻ የምንሆንበትን ሰማያዊ ሕይወት ይሰጠናል፤ በአፋችን ምስጋና በልባችን ደስታ ሞልቶ ሕይወታችን ከበደል ተለይቶ የሚኖርበትን ዘመን ያመጣልናል:: ከተዋርዶ ነፍስ ድነናል፤ ክብረ ነፍስ፣ ክብረ ሥጋ በኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጥቶናል፡፡ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያት የዘለዓለም ሕይወት ተዘጋጅቶልናል ለማለት ነው፡፡ በዓለ ፋሲካ የእግዚአብሔር ክብር የተገለጠበት የዓለምን ሁሉ ደስታ የሚያበሥር ታላቅ በዓል ነው። “በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ የሞት መዓዛ የሚገባቸው ለሞት፤ የሕይወት መዓዛ የሚገባቸውም ለሕይወት ናቸው” እንዲል፡፡ (፪ኛቆሮ ፪፥፲፭)
በዚህ ወቅት ታዲያ የዘለዓለም ሕይወት የምንኖርበት የዘለዓለም የሕይወት መዓዛችን ጌታች መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመልንን የድኅነት ሥራ በማሰብ የምናሳልፍበት ወቅት ነው።
ከላይ እንዳየነው ከሌላው በበዓለ ኅምሳ ሰሞን ስለ ዘለዓለማዊ ሕይወት የምናስብበት ወቅት ስለሆነ እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን።
ዘለዓለማዊ ሕይወት እና ዘለዓለማዊ ሞት ምንድን ነው?
ዘለዓለማዊ ሕይወት
ክርስትና የሕይወት መንገድ ነው፡፡ መንገዱም ደግሞ ወደ ዘለዓለማዊ ክብር የሚያደርስ የሕይወት የድኅነትና የቅድስና መንገድ ነው፡፡ ዘለዓለማዊ ሕይወት እግዚአብሔር ለሰው ከሰጠው ስጦታዎች ታላቁ ነው። “አንተ የዘለዓለም ሕይወት ቃል አለህ” (ዮሐ. ፮፥፷፰) እና “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘለዓለም ሕይወት ናት”(ዮሐ. ፲፯፥፫)
“መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፣ የዘለዓለምን ሕይወት ያዝ” (፩ኛ ጢሞ.፮፥፲፪)
የክርስቲያኖች ዘለዓለማዊ መድረሻችን
ሰዎች ስለ ሰማይ እናስባለን፤ እርሱ የእኛ ዘለዓለማዊ መኖሪያ ነውና፡፡ ለዚያም ነው ጌታችን ደጋግሞ ስለመንግሥተ ሰማያት የተናገረው፤ በብዙ ምሳሌም መንግሥተ ሰማያትን በተለያዩ መስሎ ያስተማረው። (ማቴ.፲፫፣ ማቴ. ፳፭) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለን» አለ፡፡ (፪ኛ ቆሮ. ፭፥፩)
እግዚአብሔር የሚገልጠውን መንግሥተ ሰማይን እንጠባበቃለንና፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም በሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም እንደምንኖር «እነሆ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው» (ራእ.፳፩፥፫) እያለ ይነግረናል፡፡ በዚያች አዲሲቱ ሰማይ «ሌሊት አይሆንም፤ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም ለዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ» (ራእ. ፳፪፥፭) እንዲሁም «ፊቱንም ያያሉ ስሙም በግምባሮቻቸው ይሆናል፡፡» (ራእ. ፳፪፥፬) እንዳለ እኛም ሁላችን ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ፤ በእውነት ፀዋትወ መከራ የለባትምና መንግሥተ ሰማያት ዕረፍት ናት። ልቅሶ፤ ኀዘን፣ የልብ መቆርቆር፣ መዋረድ፣ ነፍስን የሚያሳዝናት፤የሚያስደነግጣት፣ ፍርሃት የለባትምና በእውነት መንግሥተ ሰማያት ዕረፍት ናት፡፡ (ኢሳ.፴፭፥፲) በፊትህ ወዝ መብላት መጠጣት እሾኽም አሜከላም የለባትምና በእውነት መንግሥተ ሰማያት ዕረፍት ናት፡፡ (ዘፍ.፫፥፲፰-፲፱)
በመንግሥተ ሰማያት ዕረፍተ ሥጋ ዕረፍተ ነፍስ፣ ተድላ ሥጋ ተድላ ነፍስ፣ በጎነት፣ የዋህነት፣ ቅንነት፤ ፍቅር አለ፡፡ በመንግሥተ ሰማያት ምቀኝነትና መፎካከር የለም፡፡ በመንግሥተ ሰማይ ሕማመ ሥጋ ሕማመ ነፍስ፣ ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ የለም፡፡ በመንግሥተ ሰማይ ብርሃን እንጂ ጨለማ፣ መዓልት እንጂ ሌሊት የለም:: በመንግሥተ ሰማይ ደም ግባት ማሸብረቅ አለ፡፡ በመንግሥተ ሰማይ ለዘለዓለም የማያልፈውን በጎውን ክብር ማግኘት ነው እንጂ መሻት፤ መሰልቸት፣ መራብ፣ ቁንጣን የለም። ነገር ግን ሰማይ ከምድር እንደሚበልጥ ሁሉ መንግሥተ ሰማይም ከዚህ (ከገነት ደስታ) ትበልጣለች፡፡
ከምንኖርባት ከተማ ወጣ ባልን ጊዜ የነገሥታትና የመኳንንትን ድንኳናቸውን ብናይ፣ ልዩ ልዩ የሚኾን የጦር ዕቃቸውን ብንመለከት፣ ጋሻ ጦራቸው ሲያሸበርቅ ብንመለከት ፈጽመን እናደንቃለን፣ ደስም ይለናል፡፡ አይቻለንም እንጂ ቢቻለንና ንጉሡ በወርቅ የተሠራ የጦር ዕቃውን ይዞ በፈረስ ሆኖ በመካከላቸው ሲሔድ ብናየው የነገሥን ያህል ይሰማናል፡፡ የማታላፍ በልዕልናም ያለች የቅዱሳን ማኅደር መንግሥተ ሰማያትን ባየን ጊዜ’ማ እንደ ምን እንሆን ይሆን? “በዘለዓለም ማደሪያቸው ይቀበልዋችኋል ተብሎ እንደተነገረ፡፡ (ሉቃ.፲፮፥፱) “ዓይን ያላየው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው” ተብሎ እንደተነገረ፡፡ (፩ኛ ቆሮ.፪፥፱) ስለ መንግሥተ ሰማያት መናገር የሚቻለው’ማ ማን ነው? በእውነቱ ይህችን መንግሥተ ሰማያት ከመውረስ ውጭ ከሆኑ በላይ ጎስቋሎች የሉም፤ ይህችን መንግሥተ ሰማያት ከሚወርሱ ሰዎች በላይም ንዑዳን ክቡራን የሉም፡፡ እንግዲያውስ ወንድሞች ሆይ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ንዑዳን ክቡራን ከሚኾኑ ሰዎች የምንቈጠር እንሁን፡፡ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባትም እንትጋ፡፡ (ዕብ.፬፥፲፩)
ኑ ስለ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንነጋገር፡፡ ለነፍሳችንም መድኃኒት እንግዛ:: እንግዲህ ዓይኖቻችሁን በዕንባ ሙሉአቸው:: ያን ጊዜ የልቡናችሁ ዓይኖች ይከፈታሉና። ከዘለዓለማዊ መከራ አምልጣችሁ ሰማያዊውን መንግሥት ለመውረስ የምትፈልጉ ሁላችሁ ሀብታምና ድኻ፣ ጌታ እና አገልጋይ፣ ወጣትና ጎልማሳ፣ አዛውንትና ሕፃናት ሳትሉ፤ በሁሉም ዕድሜ ውስጥ ያላችሁና በሁሉም ፆታ ያላችሁ ተያይዛችሁ ኑ! ከቅዱስ ዳዊት ጋር “አቤቱ ዓይኖቼን ክፈትልኝ፣ እኔም የሕግህን መልካምነት ልይ፤ ዓይኖቼንም አብራልኝ› እያልን ወደ ይቅርባዩ ጌታ ጸሎታችንን እናቅርብ፡፡
ኑ መንገድ ዳር የተቀመጠው ዓይነ ስውር »የዳዊት ልጅ ሆይ ማረኝ› እንዳለ እኛም ማረን ብለን እናልቅስ፤ ድምጻችንን እናሰማ። የሚገሥፀን ቢኖር ወይም ሰላማችንን ነሳችሁ ብሎ የሚከሰን ቢኖር እንኳ ከቀደመው ለቅሶአችን የበለጠ ድምጻችንን ከፍ አድርገን እናልቅስ። ክርስቶስ የልቡናችንን ዓይኖች እስኪ ከፍትልን ድረስ አብዝተን እናልቅስ እንጂ ማንባታችንን አንተው።
ስለዚህ ወደ እርሱ ቅረቡና ብርሃንን ተጎናጸፉ።
በፊታችን ዓለምና የዓለም የሆነው ሁሉ የተናቀ ይሁን፡፡ ቀኑ ሳይመሽ አሁን ራሳችሁን አዘጋጁ፤ በሩ እንዳይዘጋባችሁም ፍጠኑ። እነሆ ምሽቱ ቀርቧል፡፡ ለሁሉም እንደ ሥራው ደሞዙን የሚከፍል እርሱ በክብርና በታላቅ ግርማ ሊመጣ ነው፡፡ ለእያንዳንዱም እንደየ ሥራው ይከፍለዋል፡፡ ወንድሞቼ ሆይ አሁን ሰዓት እያለን ንስሓ እንግባና የንስሓ ፍሬ እናፍራ፡፡ እንግዲያውስ የተወደዳችሁ ወገኖቼ ሆይ ኑ የሚያስጨንቅና የሚያስፈራ ቀን ሳይደርስባችሁ ተዘጋጁ:: ኑ ራሳችንን በአምላካችን የይቅርታ ባሕር ላይ እንጣል፡፡ እግዚአብሔር ራሱ ‹‹ሸክማችሁ የከበዳችሁ ወደኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ›› ብሎ ወደ እርሱ እንሔድ ዘንድ እያበረታታን ነው:: (ማቴ. ፲፩÷፳፰) ሰዎች ሁሉ የሚድኑበት ንስሓ ጸጸት፣ ነፍስ የምትወደው ራስን መግዛት ዕንባና፥ ጸሎት የሚያስፈልጉን ናቸው። እርሱ የተወሰኑትን ሰዎች ብቻ ለይቶ የጠራ አይደለም፡፡ ሁሉም ይድኑ ዘንድ እንጂ። እርሱ ሀብታምም ድኻም ብትሆኑ ወደኔ ኑ አለ፡፡ ‹‹ወደኔ የመጣውን ወደ ውጭ አላወጣውም›› አለ፡፡
ዘለዓማዊ ሞት
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በሚል መጽሐፋቸው ሞት ማለት ‹‹መሞት፣ መለየት፣ የነፍስ ከሥጋ፣ የሥጋ ከነፍስ መራቅ፣ እየብቻ መሆን፣ መድረቅ፣ መፍረስ፣ መበስበስ፣ መነቀል፣ መፍለስ፣ መጥፋት፣ መታጣት›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ (ኪዳነ ወልድ፣ገጽ፣፭፻፹፩)
የሥጋ ሞት የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው፡፡ ዕረፍት ነው፡፡ በእርሱ ሰው ከዚህ ዓለም ብዙ ጭንቀትና ድካም አርነት ይወጣል፡፡ ነፍስም ከሥጋ በተለየች ጊዜ ወደ ወዲያኛው ዓለም ትሸጋገራለች፡፡ ሥጋ ወደ መቃብር ሲወርድ ይፈርሳል፤ ይበሰብሳል፡፡ እንደ ገናም ተሰብስቦ እንደ አዲስ ሆኖ ይገጣጠማል፡፡ ወደ አለ መበስበስ ይለወጣል፡፡ ከነፍስ ጋርም ይዋሐዳል፡፡ በሞተ ሥጋ የምናየው እንዲህ ነው፡፡
በሞተ ነፍስ ግን አሰቃቂና አስፈሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ሞት ሲከናወን መበስበስ ያለ ቢኾንም እንኳን፥ በሥጋ ላይ እንደሚሆነው ዓይነት ነፍስ ወደ አለ መኖር አትሄድም፡፡ እንደ ገና መፍረስ መበስበስ የማይስማማውን ሥጋ ተዋሕዳ ትኖራለች፤ ወደ ማይጠፋው እሳትም ትጣላለች እንጂ፡፡ የነፍስ ሞት እንግዲህ ይህ ነው፡፡
የዘለዓለም ሞት ያለባት የእሳተ ገሃነም ከባድነት ለማየት ደግሞ ሰዎች በዚህ ዓለም በእሳት ሲቃጠሉ ማየት ይህን ለመግለጽ ቃላት ጉልበት የሌላቸው ከሆኑ፥ በወዲያኛው ዓለም በምረረ ገሃነም ያለው ቃጠሎ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ለመግለጽ ጭንቅ ነው፡፡ በዚህ ዓለም የሚያጋጥሙ መከራዎች ቢያንስ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ፍጻሜ አላቸው፡፡ ወደ እሳተ ገሃነም የሚጣል ኃጥእ ግን ለዘለዓለም ሲቃጠል ነው የሚኖረው፤ ሥጋው ወይም ነፍሱ ተቃጥለው ወደ አመድነት አይለወጡም፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር በእሳተ ገሃነም የሚያነቃን ለምንድን ነው? ካልን ዲያብሎስ ወደዚያ ይጥላቸው ዘንድ አስቦ ሰዎች እሳተ ገሃነም እንዳለ አድርገው እንዳያስቡ ያሳምናቸዋል፡፡ በተቃራኒ እግዚአብሔር ደግሞ “እሳተ ገሃነም አለ” እያለ ያስገነዝበናል፡፡ ለምን? ስለ እሳተ ገሃነም ካወቅን ወደ እርሱ እንዳንጣል ብለን እንድንጠነቀቅ ብሎ አስቦ!
ይህ ማለት የነፍስ ዘለዓለም መኖር እንዳለ ሁሉ የነፍስ መሞት አለ ማለት ነው።የሥጋ ሞት እንዳለ ኹሉ እንደዚሁም የነፍስ ሞት አለ፡፡ ነቢዩ፡-“ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” ብሎአልና፡፡ (ሕዝ.፲፰፥፬) የነፍስ ሞት ግን እንደ ሥጋ ሞት ሳይኾን እጅግ የሚያሰቅቅ ነው፡፡
በዚህ የተነሣ በተሰጣቸው ዘመን ከእግዚአብሔር ተለይተው በኃጢአት ሜዳ ተሰማርተው የኖሩ ሰዎች ከዚህ ዓለም ኑሯቸው መለየትንና በሞት መወሰድን እጅግ በጣም አድርገው ይፈራሉ። ዕለተ ሞታቸውን ለማስቀረት ባይችሉም ለማዘግየት የሚቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ነገር ግን የሆነው ቢሆን ከሞት ሊቀር የሚችል ማንም የለም። ስለዚህ ኃጥአን ዕለተ ልደታቸውን የሚያከብሩ ሲሆን ዕለተ ሞታቸውን ግን ሲፈሩ ይኖራሉ። ቅዱሳን ግን ሲወለዱ ከፍትወታት እኩያትና ከአጋንንት ጋር ለመዋጋት ስለሆነ መወለዳቸው መስቀሉን ለመሸከም ነው። “ዓለም የራሱ የሆነውን ይወዳልና ቅዱሳን ከዓለም ስላልሆኑ የዚህ ዓለም ገዢ ዲያብሎስ አጽንቶ ይዋጋቸዋል” እንዲል፡፡ (ዮሐ.፲፭፥፲፱)
ታዲያ ለምን እንሞታለን?
ምንም እንኳን እግዚአብሔር ሞትን ባይፈጥረውም በዘመነ ሐዲስ ለእኛ ጥቅም አድርጎታል፡፡ ሞትን ስናስብ በጎ ማድረግን እንለማመዳለን፡፡ ክፉ ማድረግን እንጠላለን፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ሞት የብዙ ቡራኬዎች ምንጭ ነው፡፡ እንዴት? እንደምትሉኝ አልጠራጠርም፡፡
♦ አቤል ጻድቅ የሆነው በመሞቱ ነው፡፡
♦ አብርሃም ጽድቅ ሆኖ የተቈጠረለት በእምነት አንድያ ልጁን ለመሥዕዋት ለማቅረብ በመወሰኑ ነው፡፡
♦መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ የሆነው ስለ ክርስቶስ አንገቱን በመስጠቱ ነው፡፡
♦ እነ ሠለስቱ ደቂቅ፣ እነ ነቢዩ ዳንኤልም እንደዚሁ፡፡ (የክርስቲያን መከራ እና ሌሎች በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)
ሞትን የምንፈራው ለምንድን ነው?
ኃጢአትን ሳይሆን ሞትን የምንፈራ ከሆነ ፍርሃታችን የሕፃናት ፍርሃት ነው፡፡ ሕፃናት ጭምብል ያስፈራቸዋል፤ እሳትን ግን አይፈሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ድንገት ወደ በራ ሻማ ብንወስዳቸው ምንም ሳይፈሩ እጃቸውን ወደ ሻማውና ወደ እሳቱ ይዘረጋሉ፤ ፈጽሞ የተናቀ ጭምብል ግን ያስፈራቸዋል፡፡ እኛን የሚያስፈራን እሳት እነርሱን ምንም አያስፈራቸውም፡፡ እኛም ልክ እንደ እነርሱ እጅግ ሊናቅ የሚገባውን ጭምብል ይኸውም ሞትን እንፈራለን፤ ሊፈ’ራ የሚገባውንና ልክ እንደ እሳት አእምሮ የሚያሳጣውን ኃጢአትን ግን አንፈራም! እንዲህ እንድንሆን የሚያደርገንም የነገሮቹ ተፈጥሮ አስፈሪ ስለሆነ ሳይሆን የራሳችን ስንፍና ነው፡፡ ሞት ምን እንደ ሆነ ብናስተውል ኖሮ በየትኛውም ጊዜ ባልፈራነው ነበር፡፡ እንግዲህ እስኪ ንገረኝ! ሞት ምንድን ነው? ሞት ማለት ልብስ እንደ ማውለቅ ነው፡፡ ሥጋ የነፍስ ልብሷ ነውና፤ ይህን ልብሳችንን ለጥቂት ጊዜ ካወለቅን በኋላም እጅግ ደስ በሚያሰኝ ውበት መልሰን እንለብሰዋለን፡፡ በሚሞተው ሰው አትዘን፤ በኃጢአት በሚኖረው እንጂ!
ሞትን የምንፈራበት ሌላ ምክንያት እነግርህ ዘንድ ትወዳለህን? በትሕርምትና በተጋድሎ ሕይወት ስለማንኖር ነው፤ ንጹሕ ሕሊና ስለ ሌለን ነው፡፡ እንዲህ ቢሆን ኖሮ ሞትም ቢሆን፣ ረሀብም ቢኾን፣ ሀብትን ንብረትን ማጣትም ቢሆን፣ ወይም ሌላ ምንም የሚያስፈራን ነገር ባልኖረ ነበር፡፡ መልካም ምግባር ያለው ሰው በእነዚህ ነገሮች ምንም አይጎዳምና፤ ውስጣዊ ደስታዉንም አያጣምና፡፡ በጎ ተስፋ ስላለው ወደ ቀቢጸ ተስፋ የሚጥለው ምንም ነገር የለምና፡፡ በጎ ሕሊና ያለውን ሰው ሊያሳዝነው የሚችለው ነገርስ ምንድን ነው? የሀብቱ መወሰድ ነውን? እርሱማ በሰማያት ያጠራቀመው ሀብት አለው! ከአገሩ እንዲሰደድ በመደረጉ ነውን?
ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሰማያት ወዳለችው ከተማ ተጓዥ ነው! በእግረ ሙቅ መታሰሩ ነውን? ነጻና አፍአዊ እስራት ሊያገኘው የማይችል ልብ አለው! የሥጋው መሞት ነውን? ይህም ቢሆን ዳግም ይነሣል! ከጥላ ጋር የሚታገል፣ ነፋስንም የሚጎስም ሰው ማንንም ሊጎዳ አይችልም፡፡ ከጻድቅ ሰው ጋር ትግል የሚገጥም ሰውም ልክ ጥላን እንደሚጎስምና እጎዳዋለሁ የሚለውን መጉዳት ስለማይችል ኃይሉን በከንቱ የሚያጠፋ ሰው ነው፡፡
ቀዳማዊው አዳም ባለመታዘዝ ሞትን አመጣ፥ ዳግማዊው አዳም ክርስቶስ ግን እስከ መስቀል ድረስ በሚጓዝ የመስቀል ሕይወት በትንሣኤ በኩር ሆነ። “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ፥ በኃጢአትም ሞት፥ እንዲሁም ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ … በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ፡፡” (ሮሜ ፭፥፲፪-፳፩)
በክርስቶስ ከተገኘው ሕይወት የተነሣ የሚመጣውን ሕይወትና ትንሣኤን ማመን ተስፋም ማድረግ ተችሏል፡፡ ሁላችንም እንደምንነሣ እናውቃለን። እርሱን ለማየት ወደሚያበቃ መንፈሳዊ አካልም በሚመጣው ትንሣኤና አዲስ ሕይወት በኃጢአት ያጣነው የብርሃን ልብስ ይመለሳል። አሁን ያስቀመጥናቸው ልዩነቶች ኹሉ በጽድቅና በኃጢአት መካከል ባሉ ልዩነቶች ይተካል። ያሁኑ ደረጃ፥ ክብርና መዓርግ፥ ሀብትና ንብረት ሁሉ ያልፋል። ዛሬ ለጥፋት ሥራ አጥፊዎችን የከበቡ ሰዎች ሁሉም የሥራቸውን ዋጋ በሚቀበሉ ጊዜ ማንም ለማንም አይቆምም። “በኃጢአታችን ብዛት የእግዚአብሔርን መንግሥት ስለማንወርስ ስለዚሁ ምክንያት በጣም እናዝናለን” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እኔም እንዲህ እለዋለሁ፡ ወዳጄ ሆይ! እንግዲያውስ ሞትን ፈርተህ ማዘንህን ተወውና ሥርየትን ታገኝ ዘንድ ስለ ኃጢአቶችህ እዘን!
በመጨረሻም ሰው አስቀድሞ ወደነበረበት ኑሮ ሊመለስ አይገባውም አሁን በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ወደ ማይጠፋበት መንግሥት ሰማያት ወደ ዘላለማዊ ሕይወት መግባት ተሰጥቶታልና:: ለዚህ ደግሞ በንሰሐ ታጥቦ ሥጋውን ደሙን በልቶ ጠጥቶ ተዘጋጅት መኖር አለበት።
ክርስቶስም ለደቀመዛሙርቱ «ሥጋዬን ብሉ» የሚለው የሚያጠግበው የተራበ ሥጋን ሳይሆን የተራበች ነፍስን ነው:: ደሜን ጠጡ የሚለው ቃልም የተጠማ ሥጋን ሳይሆን የተጠማች ነፍስን እርካታን የሚሰጥ ነው:: ጌታችን ይህንን ምግብ የሚራቡ የተቀደሱ እንደሆኑ ሲናገር እንዲህ አለ «ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣ ይጠጣም» አለ፡፡ በዚህ በበዓለ ኀምሳ እኛም እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት በጽናት በቤቱ ጸንተን ቆይተን በኅምሳኛው ቀን ከተሰጣቸው መንፈስ ቅዱስ ተሳታፊዎች እንድንሆን እስከ ዐሥረኛው ማዕረግ ቅድስና እንድንበቃ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ይርዳን። አሜን!!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
አሜን!!!
ምንጭ፦
- ኆኀተ ስብከት ዘቅዱስ ያሬድ ቅጽ ፪ በሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ
- ኤልኬራዛ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ
ትርጒም በዲያቆን ማለዳ ዋስይሁን - ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ሕይወቱና ትምህርቱ አዘጋጅ በዲ/ን ታደለ ፈንታው
- የክርስቲያን መካራ እና ሌሎች በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትርጒም ገብረ እግዚአብሔር ኪዱ
- ሰማዕትነት አያምልጣችሁ እና ሌሎች በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትርጒም በገብረ እግዚአብሔር ኪደ
- ፍኖተ ቅዱሳን
በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ - ድርሳነ ኤፍሬም
የቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ የትምህርቶቹ ስብስብ ቅጽ ፩
በዲ/ን መዝገቡ ከፍያለው - የነገረ መለኮት መግቢያ መምህር ግርማ ባቱ