የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ቃጠሎ መንሥኤ እየተጣራ ነው
ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በዲያቆን ተመስገን ዘገየ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በስማዳ ወረዳ ቤተ ክህነት ሽሜ አዝማቾ ቀበሌ በምትገኘው በሽሜ ማርያም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ መንሥኤ በወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት እየተጣራ እንደሚገኝ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ሊቀ ካህን ቄስ ሞላ ጌጡ ተናገሩ፡፡
በቃጠሎው በሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ፣ በጥንታውያን የብራና መጻሕፍት፣ በመስቀሎች፣ በአልባሳትና በሌሎችም ንዋያተ ቅድሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የወረዳ ቤተ ክህነቱ ሊቀ ካህን አስታውቀዋል፡፡
የቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ በየነ እንደ ተናገሩት የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን እሳቱን ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም የእሳት ቃጠሎው የደረሰው በሌሊት በመኾኑ አዳጋውን ለመቀነስ የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ሰኔ ፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም መንሥኤው ባልታወቀ ምክንያት በሽሜ ማርያም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ላይ የእሳት ቃጠሎ አደጋ መድረሱ ይታወሳል፡፡ የቃጠሎው መንሥኤም በወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት እየተጣራ ይገኛል፡፡