የሕንዱ ፓትርያርክ የመስቀል በዓልን በአዲስ አበባ አከበሩ
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
መስከረም ፲፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ካልዕ የመስቀል ደመራ በዓልን በአዲስ አበባ ከተማ በመስቀል ዐደባባይ አከበሩ፡፡
ቅዱስነታቸው በዓለ መስቀልን በአዲስ አበባ ያከበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ያቀረቡላቸውን መንፈሳዊ ግብዣ ተቀብለው ነው፡፡
ፓትርያርኩ በዕለቱ በሰጡት ቃለ ምዕዳን ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በቀረበላቸው መንፈሳዊ ጥሪ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረጋቸውና በዓለ መስቀልን በአዲስ አበባ ከተማ በማክበራቸው መላው የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን እንደተባረኩ፣ በዚህም ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡
መስቀልን ማክበር ማለት ራስን መፈለግና የመስቀሉን ክብር ከፍ ከፍ ማድረግ ማለት እንደኾነ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው ኢትዮጵያውያን ምእመናን በመንፈሳዊ ሥርዓት ብቻ ሳይኾን በሕይወታቸው ጭምር የመስቀሉን ክብር እንደሚገልጹት መስክረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የመስቀል በዓል አከባበር ሥርዓት በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በቅርስነት በመመዝገቡ መደሰታቸውንም ተናግረዋል፡፡
መላው ሕዝበ ክርስቲያን ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን ወደፈጸመበት መስቀል ሊመለከት እንደሚገባው ያስረዱት ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ማጠቃለያም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ለመላው ምእመናን አባታዊ ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡
በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የተመሠረተችው የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአምስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ስትኾን፣ በርካታ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሰባክያነ ወንጌልና ካህናት እንደዚሁም ወደሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ ምእመናን እንዳሏትና ሠላሳ በሚኾኑ አህጉረ ስብከቷ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በመወጣት ላይ እንደምትገኝ ታሪኳ ያስረዳል፡፡
በ፳፻፲ ዓ.ም የሚከበረውን በዓለ መስቀል በማስመልከት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በተዘጋጀው ልዩ ዕትም መጽሔት በገጽ 12 – 13 እንደተጠቀሰው፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ካልዕ በሕንድ ምሥራቅና ማላንካራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ቶማስ መንበረ ፓትርያርክ ሰባተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማርቶማ ዲዲሞስ ቀዳማዊን በመተካት ከስምንት ዓመታት በፊት ስምንተኛው ፓትርያርክ ኾነው ተሹመዋል፡፡
በዘመነ ፓትርያርክነታቸውም ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ በኦሪየንታል አኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ሃይማኖታዊ ግንኙነት እንዲጠናከር ከፍ ያለ መንፈሳዊ ተግባር በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡
ቅዱስነታቸው መስከረም ፲፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ወደኢትዮጵያ በመጡ ጊዜም ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መንፈሳዊ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ፓትርያርኩ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታም በዓለ መስቀልን ከማክበራቸው በተጨማሪ የቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን፣ ደብረ ሊባኖስን፣ ሰበታ ቤተ ደናግል የሴት መነኮሳይያት ገዳምን እና ሌሎችም ቅዱሳት መካናትን እንደሚጎበኙ፤ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ሃይማኖታዊ ግንኙነት በሚመለከትም የመግባቢያ ሰነድ እንደሚፈራረሙ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ከፓትርያርኩ የጉብኝት ዜና ስንወጣ የመስቀል ደመራ በዓል በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በመንፈሳዊ ሥርዓት ተከብሯል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል ዐደባባይ በዓሉ ሲከበርም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የየመምሪያ ሓላፊዎች፤ የገዳማት፣ አድባራት አስተዳዳሪዎች እና አገልጋይ ካህናት፤ የየሰንበት ት/ቤቶች እና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት፤ የኢፊድሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በአጠቃላይ በመቶ ሺሕ የሚቈጠር ሕዝብ በሥርዓቱ ታድሟል፡፡
በዕለቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፡፡
በቃለ ምዕዳናቸውም የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ጥሪያቸውን አክብረው ወደኢትዮጵያ በመምጣት በዓሉን በጋራ በማክበራቸው መደሰታቸውን ገልጸው፣ ‹‹የመስቀል በዓል በየዓመቱ በደማቅ ሥርዓት የሚከበረው መስቀሉ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን የፈጸመበት በመኾኑ ነው›› በማለት በዓሉ የሚከበርበትን ምክንያት አስገንዝበዋል፡፡
አያይዘውም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሰላምን፣ አንድነትን፣ ፍቅርን እንደሰጠን ዂሉ፣ እኛ ኢትዮጵያውያንም አገራዊ አንድነታችንንና ወንድማማችነታችንን በመጠበቅ በመካከላችን ፍቅርንና ሰላምን ማስፈን፤ ዕድገታችንንም ማስቀጠል እንደሚገባን ቅዱስነታቸው አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ከዚሁ ዂሉ ጋርም በቅርቡ በኦሮምያ እና ሱማሌ የኢትዮጵያ ክልሎች በተነሣው ግጭት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩ ወገኖች ዕረፍትን፤ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን፤ ጉዳት ለደረሰባቸውና ሕክምና ላይ ለሚገኙት ደግሞ ፈውስን እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተመኝተዋል፡፡
በዕለቱ መንግሥትን ወክለው መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ደሪባ ኩማ በበኩላቸው ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው ማለት አንዳቸው በአንዳቸው አስተዳደር ጣልቃ አይገቡም ማለት እንጂ ለአገር ሰላም በሚጠቅሙ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ አይመክሩም ማለት እንዳልኾነ አስታውሰዋል፡፡
የመስቀል በዓል አከባበር ሥርዓት በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በቅርስነት መመዝገቡ ለቱሪዝም ዕድገት ከሚኖረው አገራዊ ፋይዳ ባሻገር የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም ጸሎተ ቡራኬ ተደርጎ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ እና በዶክተር ሙላቱ ተሾመ የመስቀል ደመራው ከተለኮሰ በኋላ የበዓሉ አከባበር ሥርዓት በሰላም ተፈጽሟል፡፡