የሐዋርያት ጾም
ዲያቆን ዮሐንስ ተመስገን
ግንቦት ፳፭፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ሰባቱ ኪዳናትና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እያስተማረ አልፎ አልፎም እየተገለጠላቸው ፵ ቀን ቆይቶ ‹‹አንትሙሰ ንበሩ ሀገር ኢየሩሳሌም እስከትለብሱ ኃይለ እምአርያም፤ እናንተ ግን ከሰማይ ኃይል እስክታገኙ በኢየሩሳሌም ቆዩ›› ብሏቸው ዐረገ፡፡ (ሉቃ.፳፬፥፶)። በዐሥረኛው ቀንም እንደተናገረው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ወደ ሚላኩበት አጽናንቶም ቢሉ አጽንቶ ሊልካቸው መጣላቸው። ጌታ ‹‹ሑሩ ወመሐሩ፤ ሂዱና አስተምሩ›› ብሎናል፤ ‹‹መንፈስ ቅዱስ አድሮብናል›› ብለው ወጥተው አልተበተኑም፤ (ሐዋ.፪፥፬) በኅብረት፣ በሱባኤ የአገልግሎታቸውን ሥምረት ያጸኑ ዘንድ የጋራ ጾም ያዙ እንጂ።
ጾም የነፍስን ቁስል ይፈውሳል፤ ጾም የተሰወረውን ይገልጣል፤ ጾም ፍርኃትን ያጠፋል፤ ጾም ያጸናል፤ ጾም በርከት ያስገኛል፤ ጸም ለኃጢአት ሥርየት ይሰጣል፤ ‹‹በጾም ወበጽሎት ይሰረይ ኃጢአት፤ ኃጢአት በጾምና በጸሎት ይስተሠርያል›› እንዲል፡፡ (ጾመ ድጓ ዘወረደ) ስለዚህም ድውይ ነፍስ እንዲፈወስላቸው፣ የተሰወረ እንዲገለጥላቸው፣ የፈራ ሥጋቸው በአላውያን ነገሥታት ፊት በጥብዓት እንዲመሰክርላቸው፣ ሊመጣ ያለው የሐዋርያነት አገልግሎታቸ ሁሉ የበረከት እንዲሆንላቸው የጾምን ጥቅም መምህራቸው አስተምሯቸዋልና፡። (ማቴ.፮፥፲፮) በአንድነት ሁነው በርደተ መንፈስ ቅዱስ ማግሥት ጾምን ለራሳቸው ዐወጁ። ጾሙም በስማቸው መሰየሙ ለዚህ ነው።
ጾሙን በጰራቅሊጦስ ማግሥት ጀምረው የጥያቄያቸውን መልስ እስኪያገኙ እስከ ሐምሌ አምስት ቆይተዋል። የጌታ ፈቃዱ ሆኖም በሐዋርያነት አገልግሎታቸው የሚታወቁት የሰማዕትነት ኅልፈታቸው ጾሙን ፈተው ለአገልግሎት በተሠማሩበት ዕለት ሁኗል (ስንክሳር ዘሐምሌ አምስት)። በረከታቸው ይደርብን!
ለአገልግሎት እንዲሁ አይወጣም፤ የጌታን መንገድ እንዲያቀና የተጠራ ሁሉ እንዲሁ አይሰማራም፤ ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ የተገባ ነው እንጂ። በአበው ሕይወት የምናየውም ይህን ነው። ሙሴ በሲና ተራራ፣ ኤልያስ በቀርሜሎስ ኮረብታ አምላካችንን በጾም ይጠይቁት እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ምስክራችን ነው። ከፈጣሪያቸው አንዳች ነገር ሲፈልጉ ፈጣሪያቸውን በጾምና ጸሎት ይጠይቁ ነበር። ሐዋርያትም የተውልን ይህን ነው። እስራኤል ዘነፍስ የምንባል እኛም ጥያቄያችን እንዲመለስ በጾምና ጸሎት መጠየቅ ይገባናል።
ከጾም ጋር አብረው የሚፈጸሙት ብዙ ናቸው። ጸሎት አለው፤ ቅዳሴ አለው፤ ሰዓታት አለው፤አደራረስ አለው፤ ጾም ሲገባ የነፍስ ምግቧ ብዙ ነውና ከብዙ ምግቦቿ እናሳትፋት። በዚህ ዓመት ግንቦት ፳፰ መግቢያው ነው። በንስሓና በተመስጦ ሁኖ ጾሙን መቀበልን መዘንጋት የለብንም።
አምላካችን እግዚአብሔር ጾማችንን ይቀበልልን፤ አሜን!