የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር እንደሚካሔድ ተገለጸ
ጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ማኅበረ ቅዱሳን ሐዊረ ሕይወት /የሕይወት ጉዞ/ የተሠኘውንና ምእመናንን በማሳተፍ በተመረጡ ቅዱሳት መካናት የሚያካሒደውን መርሐ ግብር ታኅሣሥ 6 ቀን 2006 ዓ.ም. በደብረ ዘይት ደብረ መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እንዳዘጋጀ የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ገለጸ፡፡
አቶ ግርማ ተሾመ የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ዋና ጸሐፊና የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዝግጅቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ በመርሐ ግብሩ ላይ ከ5000 በላይ ምእመናን ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና የቲኬት ሽያጩንም በማሰራጨት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ምእመናን ቲኬቱን በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል ጽ/ቤት፤ በማኅበሩ የንዋያተ ቅዱሳት ማከፋፈያና መሸጫ ሱቆች እንደሚያገኙ የተናገሩት አቶ ግርማ የቲኬት ሽያጩም ኅዳር 25 ቀን 2006 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ አሳውቀዋል፡፡
በእለቱም ሰባኪያንና ዘማሪያን የሚገኙ ሲሆን ከምእመናን ለሚቀርቡ በመንፈሳዊ ሕይወት ዙሪያ ያተኮሩ ጥያቄዎች በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምላሽ ይሰጥባቸዋል፡፡
የትራንስፖርት ክፍያን ከግምት ውስጥ በማስገባትና ከዚህ በፊት ከተካሔዱት የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብራት ተሞክሮዎች በመነሳት የተሻለ አገልግሎት ለምእመናን ለመሥጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ግርማ የምሣ መስተንግዶን ጨምሮ የቲኬት ዋጋው 195.00 /አንድ መቶ ዘጠና አምስት ብር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የቲኬት ሽያጩ ከተጠናቀቀ በኋላ ምእመናን ቱኬቱን ለመግዛት ጥያቄ በማቅረብ በአገልግሎት ላይ ከፍተኛ ጫና እየተፈጠረ እንደሚገኝ ካለፉት ተሞክሮዎች ኮሚቴው የተረዳ በመሆኑ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ምእመናን ቲኬቱን እንዲገዙ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡
የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ጊዜያት መከናወኑ ይታወሳል፡፡