‹‹ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ፤ የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል›› (መዝሙረ ዳዊት ፻፲፩፥፮)
የምድራዊ ሕይወት ውጣ ውረድን አልፎ፣ የእሾህና አሜኬላዋን ሥቃይ ተቋቁሞ፣ ቀናውን የጽድቅ ጎዳና ተጉዞ፣ ሩጫውን በገድል ጨርሶ፣ በመልካም ፍሬ ዘለዓለማዊ ዕረፍትን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፡፡ ቅዱሱ መጽሐፍ ‹‹ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ፤ የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል›› ይለናል፡፡ (መዝሙረ ዳዊት ፻፲፩፥፮)
ታዲያ ይህ ቃል ለሙታን መታሰቢያ ማድረግ እንዳለብን ምስክር ነው፤ ቅዱሳት መጽሐፍት የአምላካችን ትእዛዝ ሲያስተላልፉልን በበጎ ፈቃድ ተቀብለን መተግበር እንድንችል እንዲሁም “እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድድ ሰው ምስጉን ነው” በተባለ በከበረ ቃል በረከትን እንድናገኝ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡
በግልም ሆነ በማኅበር የቅዱሳንን ዝክር ማዘከር የተገባ በመሆኑ ገድላቸውን በማሰብ መታሰቢያቸውን ማድረግ ይገባናል፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ለቅዱሳን በሰጠው ክብርና በስማቸው በሚደረገው መታሰቢያ ለእኛ ልጆቹ ምሕረትን፣ ይቅርታን፣ ቸርነትን ያደርግልናልና፡፡
የቅዱሳን ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!
