ዝክረ ግማደ መስቀሉ!
መምህር ቢትወደድ ወርቁ
መጋቢት ፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
በብሉይ ኪዳን ከባድ ወንጀሎችን የሚፈጽሙ ሰዎች የሚበየንባቸው የመጨረሻው ፍርድ በእንጨት መስቀል ነበር፡፡ ነቢዩ “እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ” በማለት እንደተናገረው፤(ዘዳ.፳፩፥፳፪-፳፫) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ” ብሎ እንደሰበከው ንጹሐ ባሕርይ ኢየሱስ ክርስቶስ ካሣ ቤዛ ሊሆነን ስለ እኛ ከኃጢአተኞች ጋር ተቆጥሮ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ (፩ኛጴጥ.፪፥፳፬) አይሁድ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሙታንን በማሥነሳቱ ድውያንን በመፈወሱ ለምፃሞችን በማንፃቱና ሌሎች ተአምራትንም በማድረጉ ምክንያት ተመቅኝተው ጉድጓድ አስቆፍረው ቀበሩት፡፡ በዚያም ስፍራ ሰዎች ቆሻሻ እንዲደፉበት አድርገው ለሦስት መቶ ዓመታት ያክል ተቀብሮ እንዲቀር አደረጉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበት ቦታው ወደ ተራራነት ተቀየረ፡፡ ምንም እንኳን መስቀሉን ለማውጣት ባይችሉም በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ያውቁት ነበር፡፡ በሰባ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስለጠፋች በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ፡፡ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱ መስቀሉ ከ፫፻ ዓመታት በላይ ተዳፍኖ /ተቀብሮ/ ኖረ፡፡
በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (በ፫፻፳፯ ዓ.ም) የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ቅድት እሌኒ መስቀሉን ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ ቅድት ዕሌኒ መስከረም ዐሥራ ስድስት ቀን በታሪክ አዋቂው አረጋዊው ኪራኮስ አማካኝነት ዕጣን እንዲጤስ አድረጋ በዕጣኑም ጢስ አመልካችነት መስቀሉን ከተቀበረበት ቦታ ለማውጣት በመስከረም ፲፯ ቀን ቍፋሮ አስጀምራለች፡፡ ንግሥት እሌኒ ከመስከረም ፲፯ ቀን አስጀምራ እስከ መጋቢት ፲ ቀን ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ቆሻሻውንም ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ፡፡ የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል፡፡ መስቀሉ የተገኘው መጋቢት ፲ ቀን ፫፻፳፮ ዓ.ም. ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ መስቀሉ ከተቀበረበት ተራራ ተቈፍሮ የወጣበት መጋቢት ፲ ቀንም በቤተ ክርስቲያን በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ በተጨማሪም መስከረም ፲፯ ቀን ንግሥት ዕሌኒ ቅዳሴ ቤቱን ያከበረችበትን የመታሰቢያ በዓል ታቦት አውጥተው ዑደት በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ያከብሩታል፡፡ ከሦስቱ መስቀሎች መካከል ጌታችን የተሰቀለበት መስቀል የተለየው ተአምራት በማድረጉና ብዙ ድውያንን በመፈወሱ ነው፡፡
ዛሬም ወዳለንበት ተግባራዊ ኑሮ ስንመጣ በእያንዳንዱ ክርስቲያን ልቡና በሃይማኖት በበጎ ምግባር፣ በትሩፋትና በመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ሊያበራ የሚገባው መስቀል ሕማማተ ክርስቶስ እንዲሁም ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ያስተማረን ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ምሕረት፣ ሰላም፣ ትሕትናና ስለሌሎች ራስን አሳልፎ መስጠት በኃጢአት በክፋት በዘረኝነት በስግብግብነት በተንኮልና በመሳሰሉት እኩያት ምግባራት ተሸፍኖዋል፡፡ የጌታችን መስቀል ከተቆፈረበት ሲወጣ ጨለማውን እንዳስወገደ ሙታንንም እንዳስነሣ በሕይወታችንም መልካም የምንላቸው ነገሮች ጎልተው እንዲታዩ የክፋት ቆሻሻን በንስሓ ልናስወግድ ይገባናል፡፡
አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርሚያስ አንደበት “ኢየሩሳሌም ሆይ ትድኝ ዘንድ ልብሽን ከክፉ ነገር እጠቢ” በማለት እንዳስተማረ፡፡ (ኤር.፬፥፲፬) ቂምና በቀል፣ ጠብ መዝራትና ሰውን ከሰው ጋር ማጋጨት፣ ሰዎችን መናቅና ማቃለል እንዲሁም የተለየ ዓላማ አንግቦ ስም ማጥፋት፣ ቅንአትና ቁጣ፣ ስካርና አለመጠን መብላት መጠጣት፣ ዝሙትና መዳራት፣ ጣዖት አምልኮና ምዋርት፣ ጥልና ስሜታዊ ንትርክ፣ አድመኝነትና መለያየት እነዚህ በሙሉ መስቀለ ክርስቶስ በልቡናችን እንዳያበራ የመስቀሉን ነገር የሚቀብሩ ነፍስንም ሥጋንም የሚያረክሱ ቆሻሾች ናቸው፡፡ የመስቀሉም እንቅፋቶች ናቸውና ሐዋርያው “የመስቀሉ እንቅፋቶች” መሆናቸውን ገልጾ ያስተማረው፡፡ (ገላ.፭፥፲፩-፳፮)
በመስቀል ተገደለ የተባለ ጠብን እየዘሩ ስለ መስቀል መናገርም ሆነ በመስቀሉ ላይ ተሰቅሎ ሰላምን ያወጀልንን በመስቀሉም ላይ ባፈሰሰው የከበረ ደሙ ከራሱ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያስታረቀንን ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ማምለክ አይቻልም፡፡ መጽሐፍ “የጌታን ስም የሚጠራ ከዓመፅ ይራቅ” ይላልና፡፡ (ኤፌ.፪፥፲፮፣ ቆላ.፩፥፳፣ ፪ኛጢሞ.፪፥፲፱) ሐዋርያት “ከጌታችን ከኢየሱስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ!” በማለት አስተምረውናል፡፡ (ገላ.፮፥፲፯) ታዲያ የሐዋርያት ተከታይ ነኝ፤ እነርሱም ያመለኩትን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶሰን አመልክዋለሁ የሚል ክርስቲያን የክርስቶስን መስቀል ቸል ብሎና ዘንግቶ በዘርማንዘሩ፣ በጎጡ፣ በገንዘቡ፣ በሥልጣኑ፣ በጉልበቱ፣ በትምህርት ደረጃው እየተመካ እኔ ክርስቶዊ ነኝ ሊል እንዴት ይችላል? በእንዲህ ዓይነት ክፉ የሥጋ ትምክህትስ የተያዘ ሰው በሕይወቱና በኑሮው መስቀሉን አልቀበረውምን?
ሐዋርያት መስቀልና ስለ ክርስቶስ መከራ መቀበልን አያይዘው እንዳስተማሩ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በመሆኑም ሐዋርያው “ነገር ግን ደግሞ መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን” በማለት አስተማረ፡፡ (ሮሜ ፭፥፫-፬) “እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል” ተብሎ እንደተጻፈ ጌታችን በመስቀል ትዕግሥትን “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደእኛ የተፈተነ ነው እንጂ ከድካማችን የማይራራ ሊቀ ካህን የለንም” እንደተባለም በመስቀል ላይ መፈተንን፤ (ዕብ.፲፪፥፪) እንዲሁም “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንደትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና” ተብሎ እንደተነገረንም መከራ መቀበልን አስተምሮናልና ትዕግሥት፣ ፈተናና መከራን ከመስቀለ ክርስቶስ ነጥሎ ማየት አይቻልም፡፡ (፩ኛጴጥ.፪፥፳፩)
ሐዋርያው “በመከራችን ደግሞ እንመካለን” ሲልም በመከራ መስቀሉ እንመካልን ማለቱ እንደሆነ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ክርስቲያን ሆኖ ስለ ክርስትና የሚመጣውን መከራ መሰቀቅ ፈተናም ሲመጣ “እርሱን እያመለክሁ ለምን እፈተናለሁ? መከራስ ለምን ይደርስብኛል? ማለትም መስቀልን መቅበር ነው፡፡ በዚህ ዘመን ክፋታችንን ጠቅጥቀን ጥለን ወደ ደግነት፣ ዝሙትና ርኩሰትን ንቀን ወደ ንጽሕና፣ ቂም በቀልን ትተን ወደ እርቅና ስምምነት፣ ዳንኪራና አስረሽ ምቺውን እርግፍ አድርገን በመተው ወደ ተመስጦና ዝማሬ፣ ጠብ መዝራትን ትተን ሰዎችን ወደ ማስታረቅና ማስማማት የምንመጣ ከሆነ ቆሻሻውን በእምነት አስወግዳ፣ ተራራውን ንዳ መስቀሉን ከገለጠችው ከንግሥቲቱ እሌኒ ጋር አንድ ሆነናል ማለት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት የእናቱ የእመቤታችን ቅድስት ድንግላ ማርያም አማላጅነት አይለየን!!