“ዝክረ ቅዱስ ቂርቆስ” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው መንፈሳዊ መርሐ ግብር ተጠናቀቀ፡፡


ሐምሌ 17 ቀን 2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

1በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ያዘጋጀው መርሐ ግብር ከሐምሌ 12 እስከ ሐምሌ 15 ቀን ተካሄደ፡፡ ዝግጅቱ በሁለት ዐበይት ክፍሎች ተከፍሎ የተካሄደ ሲሆን፡- ይህም ከመክፈቻው ሐምሌ 12-14 በዐውደ ርዕይ፣ እንዲሁም ሐምሌ 15 ቀን 12 ሰንበት ትምህርት ቤቶች የተሳተፉበት መንፈሳዊ መርሐ ግብር የቀረበበት መሆኑ ታውቋል፡፡

 

ለ3 ቀናት የቆየውን ዐውደ ርዕይ በጸሎት የከፈቱት የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን  አስተዳዳሪ መልአከ ገነት አባ ኀይለ ማርያም መንገሻ  ዐውደ ርዕዩን በጸሎት ከከፈቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት በዕድሜ ሕፃናት የሆኑት ልጆች ባዘጋጁት መርሐ ግብር ከፍተኛ ደስታና ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸው፡- “የዛሬ አበባ የነገ ፍሬ የሆኑ ሕፃናት ልጆቻችንን በደንብ ልንንከባከባቸው ይገባናል፡፡ ይህንንም ካደረግን በመጪው ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን የሚረከብ ትውልድ በብዛት ብቻ ሳይሆን በጥራትም እናፈራለን፤ ይህም ታላቅ ተስፋችን ነው፡፡” ብለዋል፡፡ መልአከ ገነት አባ ኀይለ ማርያም በማጠቃለያ መልእክታቸው “የአድባራት አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የምንገኝ መሪጌቶችና አገልጋዮች በሙሉ ለሰንበት ትምህርት ቤት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለብን፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የነገዋን ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ፈተና ውስጥ እንደሚገባ ልንረዳ ይገባናል” ብለዋል፡፡

 

5“ሰንበት ትምህርት ቤታችን ከዚህ ቀደም የተለያዩ ዐውደ ርዕዮችን ያዘጋጀ ሲሆን ሕፃናትን በተመለከተ ግን ይህ ዐውደ ርዕይ የመጀመሪያው ነው፡፡ ሕፃናትን የተመለከተ ዐውደ ርዕይ እንድናቀርብ የተፈለገበት ዋነኛው ምክንያት ተገቢውን ትኩረት ለሕፃናት እንዲሰጥ ለመቀስቀስ ነው፡፡” በማለት ዐውደ ርዕዩ በሕፃናት ዙሪያ እንዲከናወን ምክንያት ስለሆነው ሁኔታ ያስረዳው ወጣት ዮሐንስ መረቀኝ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ምክትል ሰብሳቢ ነው፡፡

 

“በቀደምት ኢትዮጵያውያን ወላጆቻችን ዘንድ እንደ ልምድ ተይዞ የነበረው ልጆችን በሕፃንነት እድሜአቸው ወደ አብነት ትምህርት ቤት የመላክ ሁኔታ አሁን አሁን እየተቀየረ÷ በዘመናዊ ትምህርት ብቻ እንዲማሩ ማድረግ  ‘ባሕል’ እየሆነ የመጣበት ጊዜ ላይ በደረስንበት በዚህ ወቅት ሕፃናት ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ጸሎቱንና የመሳሰለውን እንዲማሩና እንዲያውቁ የማስቻል ሓላፊነት ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ወላጆች ልንወጣ ይገባናል፡፡በዐውደ ርዕዩ ላይ የተካተቱት ልዩ ልዩ ክፍሎች ሕፃናት በቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ተስፋ ለማመላከት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው” በማለት ወጣት ዮሐንስ አስረድቷል፡፡

 

25 የሚደርሱ ሕፃናት በገላጭነት የተሳተፉበት ዐውደ ርዕዩ በ8 ልዩ ልዩ ክፍሎች ተከፋፍሎ የተዘጋጀ ሲሆን በዋነኝነት ሕጻናት ሊቃውንት፣ ሕጻናት ሰማዕታት፣ ሕጻናት በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ሕጻናትና ሥራዎቻቸው ፣ ሕጻናትና ጥፋታቸው፣ እንዲሁም ለወላጆች የሚሉና መሰል ሌሎች ክፍሎች የተካተቱበት ነበር፡፡

 

በመዝጊያ መርሐ ግብሩ ላይ በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ሰንበት ትምህርት ቤት አማካኝነት “ቁጥሮች ለሕፃናት” እንዲሁም 12ቱም ሰንበት ትምህርት ቤቶች በጋራ የተሳተፉበት “ድምፀ ሕፃናት” በሚል ርዕስ የተዘጋጁ የኅትመት ውጤቶች ተመርቀው ለአንባብያን ቀርበዋል፡፡