ዘወረደ

እንኳን አደረሳችሁ!

በቃሉ እሱባለው

የካቲት ፲፬፳፻፲  .

በቀደመው ክፍል ስለ ዐቢይ ጾም እና ስለ ጾም ጠቃሚ ሐሳቦችን እንደ መነሻ አድርገን ተመልክተናል። በዚሁ ክፍል ደግሞ የዐቢይ ጾም ሳምንት መጀመሪያ የሆነውን ዘወረደን አንሥተን ለእኛ የሚገቡ ጉዳዮችን እንዳስሳለን።

ዐቢይ ጾም በተለያዩ ስያሜዎች ይጠራል። ከእነዚህም ውስጥ የሁዳዴ ጾም የሚለው አንዱ ነው፡፡ ሁዳድ ማለት “የመንግሥት መሬት፣ የመንግሥት ርስት” ማለት ነው። የመንግሥት ሁዳድ በሚታረስበት ጊዜ፣ አዝመራው በሚሰበሰብበት ጊዜ፣ ልጅ ዐዋቂ ሳይባል የሀገሩ ዜጋ ሁሉ ለሥራ ታጥቆ እንደሚነሣ፣ ይህንንም የጌታ ጾም (ሁዳድ) የክርስቶስ ዜጎች የሆኑ ምእመናን ሁሉ ይጾሙታልና የሁዳዴ ጾም ተባለ። (ዐምደ ሃይማኖት፥ ብርሃኑ ጎበና፣ ገጽ ፻፶፰) ዐቢይ ጾም ተብሎም ይጠራል፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጾም ጌታ አርብዓ መዓልት እና አርብዓ ሌሊት ገዳመ ቆሮንቶስ ወርዶ ጾሞታልና። (ማቴ.፬፥፩-እስከመጨረሻው) ጾመ አርብዓ፣ የካሣ ጾም ተብሎም ይጠራል፡፡ ስለ በደላችን ክርስቶስ በእኛ ተገብቶ ጾሞታልና፤ የመሸጋገሪያ ጾም እየተባለም ይጠራል፤ ዐቢይ ጾም ወደ ፋሲካ መሸጋገሪያ ጾም ነው፡፡

ይህም ከዐቢይ ጾም በኋላ የምናገኘውን የፋሲካ በዓል የምናገኝበት እና መሸጋገርያ የሚሆነን ነው። ፋሲካ ቃሉ የጽርዕ ሲሆን በአይሁድም ዘንድ የመሸጋገሪያ በዓል ተደርጎ ይከበራል። እኛም ወደ ፋሲካችን ክርስቶስ፣ ወደ ቅድስት ትንሣኤውም የምሸጋገርበት ጾም ነው። (ምንጭ ሐመር መጽሔት፥ መጋቢት ፳፻፲፮፣ ገጽ ፱)፤ ጾመ አስተምህሮ ይባላል፡፡ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጾሙ ፍቅርን፣ ትሕትናን፣ ትዕግሥትን የፈተናን ማለፊያ መንገድ አስተምሮበታልና፡። የድል ጾም ተብሎም ይጠራል፡፡ ፈታኝ ዲያብሎስ በገዳመ ቆሮንቶስ በሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ ድል ሆኖበታልና፡፡ (ማቴ ፬ን ሙሉ ይመልከቱ)፣ የመዘጋጃ ጾም ለትንሣኤ የምንዘጋጅበት ጾም ነውና ወዘተ እየተባለ በብዙ መጠሪያ ይጠራል።

ይህን ዐቢይ ጾም ደግሞ ሐዋርያትን በስብከቱ፣ ሊቃውንቱን በትርጓሜው፣ መላእክትን በጥዑም ዜማው የሚመስላቸው የቤተ ክርስቲያናችን እንዚራ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው በየሳምንቱ ከፋፍሎ፣ ዜማ ደርሶ አስቀምጦታል። በዚህ በመጀመሪያው ሳምንት ያለውን ፰  ቀን ዜማ ደርሶ፣ በምዕራፍ ከፍሎ ‘ዘወረደ’ ብሎ  ይጠራዋል። ቤተ ክርስቲያንም የቅዱስ ያሬድን ትምህርት ተቀብላ ሥርዓት ሠርታለታለች።

ዘወረደ ማለት “ከላይ የመጣ፣ የወረደ” ማለት ነው።  ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን “ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኩሉ ዘየሐዩ፤ አዳምን ለማዳን ከሰማይ የወረደውን አምላክ አይሁድ ሰቀሉት፤ የሰማይ ሥልጣን ያለው የሁሉ ጌታ እንደሆነም ምንም አላወቁም”  እያለች በሰንበት ዋዜማ ዜማውን መሐትው (መግቢያ) አድርጋ የሳምንቱን ዜማ በማስተጋባት የጌታችንን ከሰማይ መውረድ ታመሠጥርበታለች፤ ታመሰግንበታለች። (ጾመ ድጓ፥ ዘዘወረደ ዋዜማ)

ይህን ሳምንት በልዕልና በዘለዓለማዊ ቅድስና እና በማትመረመር ጥበብ ራሱን ሰውሮ የሚኖር አምላክ በገሃድ  ለሰው ልጅ የተገለጠበትን፣ ዘለዓለማዊ አምላክ ሰውን ከተደበቀበት  ለመፈለግ ብሎ ”ኦ አዳም አይቴ ሀሎከ- አዳም ሆይ ወዴት ነህ” እያለ በማያልቅ የፍቅር ድምፅ ፍለጋ ወደ ዱር (ወደ ዓለም) የገባበትን ሳምንት የምንዘክርበት ነው። አምላካችን እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ምን ያህል በበዛ ፍቅሩ እንደሚፈልገው፣ ከፍ ላለ ዓላማውም እንዳጨው ያሳየበት፣ ከሁሉም ደግሞ በሕሊና ሊታሰብ የማይችለውን የሰማይ አኗኗሩን ትቶ በሚታይ የአዳም ሥጋ የተገለጠበት፣ መጋረጃው እሳት፣ ዙፋኑ እሳት፣ ልብሱ እሳት የሆነው አምላክ በሚበሰብስ ሥጋ የተገለጠበት፣ በጨርቅ፣ ያንን የሚያስደነግጥ መለኮታዊ ክብሩን ስለ ሰው ልጅ መዳን ተጨንቆ በሕፃን አምሳል ተገልጦ በበረት የተገኘበትን ሳምንት እናስብበታለን። ቅዱስ አትናቴዎስ  የእግዚአብሔር ልጅ ለሰው ልጅ ድኅነት ሲል መወለዱን እንዲህ በማለት ይገልጠዋል፡፡ “ለዚሁ ዓላማ (ለሰው ልጅ ድኅነት) የማይበሰብስ፣ የማይሞት አካል ያለው የእግዚአብሔር ልጅ ወደዚህ ዓለም ገባ” (On the Incarnation: Saint Athanasius page 6)

ዘወረደ ከዚህ ትርጉም ባለፈ የአዳም ሳምንት ተብሎ ይጠራል። አዳምን ከጠፋበት ሊፈልግ፣ ከወደቀበት ሊያነሣ፣ ከገባበት ሊያወጣ የትንቢቱ ጊዜ በደረሰ ሰዓት ከብላቴናይቱ ድንግል ተወልዶ ተስፋ አዳም ተፈጽሞበታልና። “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤” እንዲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (ገላ.፬:፬)።

ሠለስቱ ምዕት በጸሎተ ሃይማኖት “ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እምሰማያት፤ ተሰብአ ወተሰገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል፤ ስለ እኛ ስለ ሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም  ፍጹም ሰው ሆነ” (ጸሎተ ሃይማኖት) እንዲሉ በሥጋ የአዳምን ዘር ለማዳን ሰው ሆኖ ለአዳም የገባውን ኪዳን ፈጸመ። የሥጋ ዘመዳችንም ሆነ። (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ)

ሌላኛው ይህ ሳምንት ጾመ ሕርቃል በመባል ይታወቃል። ይህም በ፮፻፲፬ ዓ.ም የፋርስ ንጉሥ ኪርዮስ ኢየሩሳሌምን ወርሮ፣ አብያተ ክርስቲያናትን ዘርፎ እና መዝብሮ ክርስቲያኖችን ማርኮ ንግሥት ዕሌኒ ካሠራችው ቤተ መቅደስ የክርስቶስን መስቀል ዲያቆናትን አሸክሞ በምርኮ ወሰደ። ከምርኮ ያመለጡ ክርስቲያኖች ወደ ሮሙ ንጉሥ ከ፲፬ ዓመት በኋላ በ፮፻፳፰ ዓ.ም ለንጉሥ ሕርቃል ጩኹታቸውን ያሰማሉ፤ እርሱም በፋርሱ ንጉሥ በኪርዮስ ላይ ድል አግኝቶ መስቀሉን መለሰላቸው። በሕገ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ሰው የገደለ ዘመኑን ሁሉ ይጹም›› የሚል በሐዋርያት ስለተደነገገ የንጉሡን ዕድሜ ተከፋፍለው አንድ ሳምንት ደርሶባቸው ስለ ንጉሡ ጾመወለታል፤ በዚህም የእርሱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ይህ ሳምንት  ጾመ ሕርቃል በመባል ይጠራል ። እኛም ይህንን ዋቢ አድርገን እንጾማለን። (ምንጭ፡- ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት ፲)

ዘወረደ ከአርብዓው ዕለት የሚካተት ባይሆንም ቤተ ክርስቲያን ትእዛዝ አድርጋ ከአርብዓው ዕለታት ጋር ደምራ እንድንጾም ሕግ ሠርታለታች። እኛም እንደ ፈቃድ ሳይሆን እንደ ትእዛዝ ተቀብለን እንጾማለን።

እንዴት እንጹም?

ጾማችን ጸመ ሐዋርያትን እንዲመስል፣ ለጥያቄያችን መልስ እንድናገኝ፣ የልባችን መሻት እንዲፈጸም ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾሞ ያስተማረንን በሕይወታችን ሁሉ በመፈጸም የሥጋ ፈቲው ከሚያመጡ ግብራት በተዐቅቦ፣ ሕዋሳትን በመግራት እና መልካም ምግባራትን ወዳጅ በማድረግ መጾም ይገባናል። ከጌታችን መወለድ ብዙ የምንማራቸው ነገሮች አሉ። ከልዕልናው ልዑልነቱ ሳይገድበው በትሕትና፣ በደላችንን ሳያይ የምሕረት ጠሉን በላያችን ላይ እያርከፈከፈ፣ እየራቅነው እርሱ በፍቅር እየተከተለን፤ በጥልቁ ስንወድቅ ከጥልቁ ሊያወጣን፣ የአባትነት እጆቹን እየዘረጋልን “አዳም ሆይ ወዴት ነህ?” (ዘፍ ፫:፱) እያለ መልካሙ እረኛ እኛን ፍለጋ እንደመጣ እኛም የፍቅር ጎርፍ በሕይወታችን እየፈሰሰ፣ የርኅራኄ እና የቸርነት ሥራን በሚጠሉን ላይ እያደረግን፣ የወዳጅነት እጃችን በጥልቅ መከራ እና በብዙ ችግር ለወደቁት አብዝቶ ያለመታከት በመዘርጋት ያመንነውን አምላክ በግብርም እርሱን በመከተል የሐሴት ማዕበል የሰዎች ልብ ውስጥ እንዲጸና በማድረግ እንጾማለን።

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን?” በማለት የጾማችን መልክ ምን መምሰል እንዳለበት የሚገሥጸን ለዚህ ነው። (ኢሳ.፶፰:፮)

የእኛን ጾምም ምን መምሰል እንዳለበት በርቱዓ ሃይማኖት በእንተ ጾም ድርሳን ላይ ያስቀመጠውን የጾም ትምህርት ለዛሬ መውጫ አድርገን በማቅረብ እንጨርሳለን። “እግዚአብሔር የሚወደውን እና እግዚአብሔር የሚጠላውን ጾም እንነግራችሁ ዘንድ ስሙ።   አፍህ በከንቱ እንዳይጸልይ አድምጥ። ነቢዩ ኢሳይያስ “የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለም” አለ እግዚአብሔር በማለት አሰምቶ ተናገረ። አንገቱን እንደ ዘንግ ቢያቀጥን፣ በርኖስ (ማቅ) ለብሶ በአመድ ላይ ቢተኛ ይህ ጾም በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ጾም አይደለም አለ። “ድሆችን እያስጨነቁ፣ እያስለቀሱ፣ የሌላውን ገንዘብ እየወሰዱ፣ እየተደባደቡ፣ ዝሙት እየፈጸሙ፣ እየገደሉ፤ ቂም፣ በቀልን፣ ሽንገላን በልቡናቸው እያስቀመጡ ቢጾሙ እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለም።” እነዚህን እያደረገ በሰውነቱ ላይ ቢሠቃይ እንኳን ይህ ጾም አያስደስተኝም። በኃጢአት ላይ ኃጢአት ይጨመርበታል እንጂ።  ነገር ግን የተቸገሩትን ሁሉ አድን፤ የመረጥሁት ጾም ይህ ነው። ከመሥዋዕት ምጽዋትን እመርጣለሁ። እርሷ የጾም ልጅ ናትና፤ ምጽዋትም ከእርስዋ ተወልዳለችና። የተራበ ሁሉ ለተራበ ያዝናልና። የጠገበ ሰው ግን የተራቡት ሲመለከት ይንቃቸዋል። ስለ ጽድቅ የሚራቡትን በኃጢአት ለተራቡት ያዝናሉ።” (ርቱዓ ሃይማኖት፣ ገጽ ፹፭-፹፮)

የእኛንም ጾም የበደል እስራት የሚፈታ፣ የደከሙትን የሚያጠነክር፣ የጠፉትን የሚፈልግ ጾም ያድርግልን። ለሚመጣው የዘለዓለም ሕይወትም በቀኙ ከሚያቆማቸው የሚደምር፣ በሥጋችንም ዕረፍትን የሚሰጥ፣ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያሰጥ፣ የሰላም ድምፅ የሚያሰማ ጾም ይሁንልን፨

ቅዳሴ: ቅዳሴ እግዚእ

“ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እምሰማያት፤ ተሰብአ ወተሰገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል፤ ስለ እኛ ስለ ሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም  ፍጹም ሰው ሆነ፡፡” ወንጌል (ዮሐ.፫፥፲-፩፬)

ምስባክ ዘነግህ-:- “ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እምሰማያት፤ ተሰብአ ወተሰገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል፤ ስለ እኛ ስለ ሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም  ፍጹም ሰው ሆነ፡፡”

ምስባክ ዘቅዳሴ:- “ተቀነዩ ለእግዚአብሔር፤ ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ፤ አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር፤ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፤ በረዓድም ደስ ይበላችሁ፤ ጌታ እንዳይቆጣ ተግሣጹንም ተቀበሉ፡፡” (መዝ.፪፥፲፩)

መልእክታት:-

ሠራኢ ዲያቆን: ዕብ.፲፫፥፲፯

ንፍቅ ዲያቆን  ያዕ. ፬፥፮- ፍጻሜው

ንፍቅ ካህን  የሐዋ. ፳፭፥፲፫-ፍጻሜ

ስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን!