ዘካርያስ

ካለፈው የቀጠለ

ዲያቆን ዘካርያስ ነገደ
መስከረም ፮፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

የመስከረም ወር የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አባት ዕረፍት የሚታሰብበት ወር ነው፡፡ መስከረም ፰ ቀን ደግሞ የበራክዩ ልጅ ካህንና ነቢይ የነበረ ዘካርያስ በሄሮድስ እጅ በሰማዕትነት ያረፈበት ነው፡፡

ካህኑ ዘካርያስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በሦስት ዓመቷ በቤተ መቅደስ ትኖር ዘንድ የተቀበላት፣ በዐሥራ አምስት ዓመቷ ለአረጋዊው ለዮሴፍ በአደራ የሰጣት፣ የልጁን የዮሐንስን መፀነስ ከመልአኩ ከቅዱስ ገብርኤል አንደበት የብሥራት ቃል የሰማ፣ እርሱም ሆነ፤ ሚስቱ ኤልሳቤጥ በእርጅና ዘመናቸው ልጅን ያገኙ መሆናቸውን ከታሪካቸው እንረዳለን፡፡

በስተመጨረሻም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል የአይሁድ ንጉሥ የተወለደው ወዴት ነው እያሉ በመጡ ጊዜ ይህን የሰማ ሄሮድስ መንግሥቴን የሚነጥቅብኝ ከወዴት መጣ? ብሎ ፈራ፡፡ ስለዚህ በገሊላና በአውራጃዋ የነበሩትን ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆናቸውን ሕፃናት በሰይፍ አስመተራቸው፡፡

ነገር ግን ብዙ ሺህ ሕፃናት ካስገደለ በኋላ የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ መሆኑን በማሰቡ ሕፃኑን ያመጣ ዘንድ ዘካርያስን ግድ አለው፤ ሆኖም በእርሱ ዘንድ ባለመኖሩ (እናቱ ኤልሳቤጥ ይዛው በመሸሽዋ) ዘካርያስም ልጁ ያለበትን ባለመግለጡ ሄሮድስ ወታደሮቹን አዝዞ በመስከረም ፰ ቀን በመሠዊያው መካከል ገደሉት፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋለ ሥጋዌው ትምህርቱ ለዘካርያስ መገደል ምክንያት አይሁድ ናቸውና “በቤተ መቅደስ መካከል የገደላችሁት የዘካርያስ ደም በላያችሁ ይደርሳል” ብሏቸዋል፡፡ (ማቴ.፳፫፥፴፭)

ዘመነ ፍሬ

በቅዱስ ያሬድ አስተምህሮ ከመስከረም ፱ እስከ ፲፭ ያሉት ቀናት ዘመነ ፍሬ ይባላሉ፡፡ ይህም አክሊለ በረከቱን፣ ጠለ ረድኤቱን ሰጥቶ የሚመግብ እግዚአብሔር መሆኑን ተገንዝበን በስጦታው አንጻር ሰጪውን ለማመስገን ነው፤ ይህንንም በዝማሬው ሲገልጥ “ያርኁ ለነ ክረምተ፣ ይገብር ለነ ምሕረተ፣ እስመ በእንተ ሰብእ ሠርዐ ለነ ሰንበተ ለዕረፍተ ከመ ኅቡረ ይትፈሣሕ ዘይዘርዕ ወየአርር፡፡ ክረምትን ይከፍትልን ዘንድ፣ ምሕረትን ያደርግልን ዘንድ፣ ስለ ሰው ሰንበትን ለዕረፍት ፈጠረልን፤ የሚዘራውም የሚያጭደውም በአንድነት ይደሰት ዘንድ” በማለት ዘምሯል፡፡ (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)

በምድር ላይ የሚገኙ አዝርዕት፣ አትክልት እና ዕፀዋት እኩሉ በእግራቸው፣ እኩሉ በጎናቸው፣ እኩሉ በራሳቸው ያፈራሉ፤ በራሳቸው የሚያፈሩት ዕፀዋት ራሳቸው ጥረው ግረው ባገኙት የሚጠቀሙትን፣ በጎናቸው የሚያፈሩት ደግሞ በልጆቻቸውና በሚስቶቻቸው የሚጠቀሙትን፣ በእግራቸው የሚያፈሩት ደግሞ በሠራተኞቻቸው ለሚጠቀሙ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኵል በእግራቸው የሚያፈሩ የባለሠላሳ፣ በጎናቸው የሚያፈሩ የባለስድሳ እና በራሳቸው የሚያፈሩት ደግሞ የባለ መቶ ፍሬ ክብር የሚገባቸው መሆኑን ያሳያሉ፡፡

ዘመነ ፍሬ ቡቃያና ወላዳ እሸትና ዝርዝር ሆኖ የቆየው አዝመራ ወደ ተነሣበት ዓላማና ወደ መጨረሻው ውል ዕድል የሚመላለስበት ወቅት ነው፡፡ ሆኖም ግን ጊዜያዊ ሁኔታው ይህን ይምሰል እንጂ ወርቃማው ገጽታ ግን ለነፍስ የሚገባት ንስሐ ማድረግ የሚጠቁም ይዘት ያለው ነው፡፡ “እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” እንዲል፡፡ (ማቴ.፫፥፰)

ይቆየን!