ዘመነ ጽጌ
መስከረም ፳፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በዝግጅት ክፍሉ
በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ በአገራችን በኢትዮጵያ የወቅቶች ሥርዓተ ዑደት መሠረት ከመስከረም ፳፮ ቀን ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ፺ ቀናትን የሚያጠቃልለው ጊዜ ‹‹ዘመነ መጸው›› ይባላል፡፡ ‹‹መጸው›› ማለት ወርኀ ነፋስ ማለት ሲኾን ይኸውም ‹‹መጸወ ባጀ፤ መጽለወ ጠወለገ›› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ዘመነ መጸው ከዘመነ ክረምት ቀጥሎ የሚብት (የሚገባ) የልምላሜ፣ አበባ፣ የፍሬ ወቅት ነው፡፡ በውስጡም አምስት ንዑሳን ክፍሎችን የሚያካትት ሲኾን እነዚህም፡- ዘመነ ጽጌ፣ ዘመነ አስተምህሮ፣ ዘመነ ስብከት፣ ዘመነ ብርሃን እና ዘመነ ኖላዊ ናቸው /ያሬድና ዜማው፣ ገጽ ፵፰-፵፱/፡፡
ከአምስቱ የዘመነ መጸው ክፍሎች መካከል የመጀመሪያው ክፍለ መጸው ዘመነ ጽጌ ተብሎ የሚጠራ ሲኾን ይህም ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ቀን ድረስ ያሉትን ፵ ቀናት ያጠቃልላል፡፡ ‹ጽጌ› ቃሉ ‹ጸገየ አበበ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም አባባ ማለት ነው፡፡ ‹ዘመነ ጽጌ› ደግሞ ‹የአበባ ወቅት፣ የአበባ ጊዜ፣ የአበባ ዘመን› ማለት ነው፡፡ ይህ ወቅት ዕፀዋት በአበባ የሚያጌጡበት፣ ምድር በአበቦች ኅብረ ቀለማት የምታሸበርቅበት፣ ወንዞች ንጹሕ የሚኾኑበት፣ ጥሩ አየር የሚነፍስበት፣ አዕዋፍ በዝማሬ የሚደሰቱበት፣ እኛም የሰው ልጆች ‹‹አሠርጎካ ለምድር በሥነ ጽጌያት፤ አቤቱ ምድርን በአበቦች ውበት አስጌጥሃት›› እያልን የዘመናት አስገኚና ባለቤት የኾነውን ልዑል እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት፤ ከዚህም ባሻገር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከገሊላ ወደ ግብጽ ምድር መሰደዷን የምናስብበት ወቅት ነው፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም በተወለደ ጊዜ የዘመኑ ንጉሥ ሄሮድስ ሥልጣኔን ይቀማኛል በሚል ቅናት ተነሣሥቶ ጌታችንን ለማስገደል አሰበ፡፡ ያንጊዜም ጌታችን በተአምራት መዳን ሲቻለው የትዕግሥት፣ የትሕትና አምላክ ነውና በለበሰው ሥጋ በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ በመልአኩ ተራዳኢነት፣ በአረጋዊው ዮሴፍ ጠባቂነትና በሰሎሜ ድጋፍ ከገሊላ ወደ ግብጽ ተሰዶ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቆይቷል፡፡ ሄሮድስም ጌታን የጋኘሁ መስሎት በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙ ሀለት ዓመት ከዚያ በታች የኾኑ አንድ መቶ ዐርባ አራት ሺሕ ሕፃናትን በግፍ አስፈጅቷል፡፡
በተአምረ ማርያምና በማኅሌተ ጽጌ ተጽፎ እንደሚገኘው ጌታችን በግብጽ ምድር በስደት ሳለ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም እናቱን እመቤታችንን የዘለፏትን ትዕማንና ኮቲባ የሚባሉ ሴቶችን ከሰውነት ወደ ውሻነት መቀየሩ፤ ውሃ በጠማቸው ጊዜ ውሃ እያፈለቀ ማጠጣቱና ይህንን ውሃ ክፉዎች እንዳይጠጡት መራራ ማድረጉ፤ ለችግረኞችና ለበሽተኞች ግን ጣፋጭ መጠጥና ፈዋሽ ጠበል ማድረጉ፤ ‹‹የሄሮድስ ጭፍሮች ደርሰው ልጅሽን ሊገድሉብሽ ነው›› ብሎ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ እመቤታችንን በማስደንገጡ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ድንጋይ ኾኖ እንዲቆይ ማድረጉ፤ መንገድ ላይ የተራዳቸው ሽፍታ ሰይፉ በተሰበረች ጊዜ እንደ ቀድሞው ደኅና እንድትኾን ማድረጉ፤ እንደዚሁም የግብጽ ጣዖታትን ቀጥቅጦ ማጥፋቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የጌታችንና የእመቤታችን የስደት ወቅት በወርኀ ግንቦት ነው፤ ነገር ግን ዘመነ ጽጌ የአበባና የፍሬ ወቅት በመኾኑ እመቤታችንን በአበባ፣ ጌታችንን ደግሞ በፍሬ እየመሰሉ ለማመስገንና ለማወደስ በሚያስችል ምሥጢር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የስደቱ ጊዜ በዘመነ ጽጌ እንዲዘከር አድርገዋል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዘለዓለሙ የማይደርቀውን የሕይወት ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን ንጽሕት የማትጠወልግ አበባ ናትና፡፡ ይህ የእመቤታችን አበባነትና የጌታችን ፍሬነትም እንደ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫና አባ ጽጌ ድንግል ባሉ ሊቃውንት ድርሰቶች በሰፊው ተገልጧል፡፡
በዘመነ ጽጌ በማኅሌትና በቅዳሴ ጊዜ የሚቀርቡ መዝሙራትና የሚሰጡ ትምህርቶችም ይህንኑ ምሥጢር የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት በሚገኙ ሰንበታትም ሊቃውንቱ ሌሊቱን ሙሉ ስለ እመቤታችን አበባነትና ስለ ጌታችን ፍሬነት የሚያትት ትምህርት የያዙትን ማኅሌተ ጽጌና፣ ሰቆቃወ ድንግልን ከቅዱስ ያሬድ ዚቅ ጋር በማስማማት ሲዘምሩ፣ ሲያሸበሽቡ ያድራሉ፡፡ ቅዳሴውም በአባ ሕርያቆስ የተደረሰውና ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ሥላሴንና ነገረ ማርያምን የሚተነትነው ቅዳሴ ማርያም ነው፡፡ ምንባባቱም ከዚሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ናቸው፡፡
በአጠቃላይ እመቤታችን በስደቷ የደረሰባትን መከራ በማስታዎስ ዘመነ ጽጌን በፈቃዳቸው የሚጾሙ ካህናትና ምእመናን ብዙዎች ናቸው፡፡ ኾኖም ግን የጽጌ ጾም የፈቃድ ጾም እንጂ ከሰባቱ አጽዋማት ጋር የሚመደብ ስላልኾነ ጽጌን የማይጾሙ አባቶች ካህናትንና ምእመናንን ልንነቅፋቸው አይገባም፡፡ አምላካችን በአበባ የሚመሰለው ሰውነታችን የጽድቅ ፍሬን ሳያፈራ በሞት እንዳንወሰድ መልካም ፈቃዱ ይኹንልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።