ዘመነ ዕርገት
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
‹ዕርገት› በግእዝ ቋንቋ ማረግ፣ ከታች ወደ ላይ መውጣት ማለት ሲኾን የጌታችን ትንሣኤ በተከበረ በዐርባኛው ቀን የሚውለው ዐቢይ በዓልም ‹ዕርገት› ይባላል (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፯፻፷)፡፡ በዓለ ዕርገት ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለዐርባ ቀናት በግልጽም በስውርም ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለቅዱሳት አንስት መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትርጓሜ መጻሕፍትን፣ ምሥጢራትን፣ ሕግጋትንና ቀኖናተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያስተምር ቆይቶ ወደ ቀደመ ዙፋኑ ወደ ሰማይ በክብር በምስጋና ማረጉን በደስታ የምንዘክርበት ዐቢይ በዓል ነው፡፡ በዓለ ዕርገት በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡ በዓሉ የሚውልበት ዕለት ሐሙስን ባይለቅም ቀኑ ግን የአጽዋማትና በዓላት ማውጫ ቀመርን ተከትሎ ከፍ እና ዝቅ ይላል፡፡
በዚህ መሠረት የዘንድሮው በዓለ ዕርገት ግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ይውላል ማለት ነው፡፡ ከጌታችን የዕርገት በዓል ጀምሮ (ከበዓለ ትንሣኤ ዐርባኛው ቀን) እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ ዋዜማ (ዐርባ ዘጠነኛው ቀን) ድረስ ያለው ወቅትም ‹ዘመነ ዕርገት› ተብሎ ይጠራል፡፡ በዘመነ ዕርገት ውስጥ በሚገኘው እሑድ (ሰንበት) ሌሊት ሊቃውንቱ የሚያደርሱት መዝሙርም ‹‹በሰንበት ዐርገ ሐመረ›› የሚል ሲኾን ይኸውም ጌታችን በሰንበት ወደ ታንኳ በመውጣት ባሕርንና ነፋሳትን እንደ ገሠፀ፤ ሐዋርያቱንም ‹‹ጥርጥር ወደ ልቡናችሁ አይግባ፤ አትጠራጠሩ›› እያለ በሃይማኖት ስለ መጽናት እንዳስተማራቸው፤ እንደዚሁም ወንጌልን ይሰብኩ፣ ያስተምሩ ዘንድ በመላው ዓለም እንደሚልካቸው፤ በሰማያዊ መንግሥቱ ይኖሩ ዘንድም ዳግመኛ መጥቶ እንደሚወስዳቸው የሚያስገነዝብ መልእክት አለው (ሉቃ.፰፥፳፪-፳፬፤ ዮሐ.፲፬፥፪፤ ፳፥፳፩)፡፡
በበዓለ ዕርገት ሊቃውንቱ ሌሊት በማኅሌት፣ በዝማሬ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ያድራሉ፡፡ ሥርዓተ ማኅሌቱ እንዳበቃ የሚሰበከው የነግህ ምስባክም፡- ‹‹ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ሰማይ ዘመንገለ ጽባሕ ናሁ ይሁብ ቃሎ ቃለ ኃይል›› የሚለው የዳዊት መዝሙር ሲኾን፣ ቀጥተኛ ትርጕሙ፡- ‹‹በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ (ላረገ) ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ የኀይል የኾነውን ቃሉን እነሆ ይሰጣል፤›› ማለት ነው (መዝ.፷፯፥፴፫)፡፡ ምሥጢራዊ ትርጕሙ ደግሞ ‹‹ነፍሳትን ይዞ ከሲኦል ወደ ገነት ለወጣ፤ አንድም በደብረ ዘይት በኩል ላረገ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርቡ›› የሚል መልእክት አለው፡፡ እንደዚሁም ጌታችን በዐረገ በዐሥረኛው ቀን ‹የኀይል ቃል› የተባለ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት እንደ ላከላቸው፤ በተጨማሪም ጌታችን በሕያዋን እና በሙታን (በጻድቃን እና በኃጥአን) ላይ ለመፍረድ ዳግም እንደሚመጣ፤ እኛም ይህንን የጌታችንን የማዳን ሥራ እያደነቅን ለእርሱ ምስጋና፣ ዝማሬ ማቅረብ እንደሚገባን ያስረዳናል – ምስባኩ፡፡
በነግህ (ከቅዳሴ በፊት የሚነበበው) ወንጌል ደግሞ ሉቃስ ፳፬፥፵፭ እስከ መጨረሻው ድረስ ያለው ኃይለ ቃል ነው፡፡ ቃሉም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት እንደሚወርድ፣ የሰውን ልጅ ለማዳን ሲል መከራ እንደሚቀበል፣ እንደሚሞት፣ ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ፣ ወደ ሰማይ እንደሚያርግና ዳግም እንደሚመጣ በነቢያት የተነገረው ትንቢት መፈጸሙን፤ ለዚህም ቅዱሳን ሐዋርያት ምስክሮች መኾናቸውን ማለትም በመላው ዓለም እየዞሩ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ እንዲሰብኩና በሰማዕትነት እንዲያልፉ፤ እንደዚሁም ሰማያዊ ሀብትንና ዕውቀትን እስኪያገኙ ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ መታዘዛቸውን ያስረዳል፡፡ ይህ ምሥጢር ለጊዜው የሐዋርያትን ተልእኮ የሚመለከት ይኹን እንጂ ለፍጻሜው ግን ዅላችንም ቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩትን ቃል አብነት አድርገን የእግዚአብሔርን ሰው መኾንና የማዳኑን ሥራ አምነን፣ ሌሎችንም በማሳመን በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር እንደሚገባን፤ እግዚአብሔር አምላካችን ኃይሉን፣ ጸጋውን፣ ረድኤቱን እንዲያሳድርብንም ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን መለየት እንደሌለብን የሚያስገነዝብ መልእክት አለው፡፡
በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ዕብራውያን ፩፥፩ እስከ ፍጻሜው ድረስ፤ ከሌሎች መልእክታት ደግሞ ፩ኛ ጴጥሮስ ፫፥፲፰ እስከ ፍጻሜው፤ የሐዋርያት ሥራ ፩፥፩-፲፪ ሲኾኑ፣ ምስባኩም ‹‹ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ›› የሚለው ነው፡፡ ትርጕሙም ‹‹በዕልልታና በመለከት ድምፅ ላረገ ለአምላካችን፣ ለጌታችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና አቅርቡ›› ማለት ነው (መዝ.፵፮፥፭-፮)፡፡ ወንጌሉ ደግሞ፣ ማርቆስ ፲፮፥፲፬ እስከ ፍጻሜ ድረስ ሲኾን ቃሉም በነግህ ከተነበበው የወንጌል ክፍል ቃል ተመሳሳይነት አለው፡፡ ቅዳሴውም ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ሲኾን ይህ ቅዳሴ ከሦስቱ አካላት አንዱ የኾነውን የእግዚአብሔር ወልድን (የኢየሱስ ክርስቶስን) ዘለዓለማዊነት የሚያስረዳ፤ ሥጋዌዉን፣ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤዉን፣ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱንም የሚናገር በመኾኑ በዘመነ ትንሣኤ፣ በዘመነ ዕርገትና በበዓለ ኀምሳ ሰሙን ይቀደሳል፡፡
ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በቅዳሴዉ መጀመሪያ ላይ ሀልዎተ እግዚአብሔርንና ምሥጢረ ሥላሴን መሠረት በማድረግ ለእግዚአብሔር ምስጋና ካቀረበ በኋላ፣ ቍጥር ፴፩ ላይ ‹‹… ወበ፵ ዕለት አመ የዐርግ ሰማየ አዘዞሙ እንዘ ይብል ጽንሑ ተስፋሁ ለአብ፤ … ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በዐርባኛው ቀን በብርሃን፣ በሥልጣን፣ በይባቤ ወደ ሰማይ በሚያርግበት ጊዜ ‹አብ የሚሰድላችሁ መንፈስ ቅዱስን እስክትቀበሉ ድረስ ከዚህ ቆዩ ብሎ አዘዛቸው›፤›› በማለት ቅዱስ ወንጌልን መሠረት ባደረገ ኃይለ ቃል ጌታችን ወደ ሰማይ ስለ ማረጉና ለሐዋርያት አምላካዊ ትእዛዝ ስለ መስጠቱ ይናገራል (ሉቃ.፳፬፥፵፱)፡፡
ይቆየን