ዘመነ ዕርገት – ካለፈው የቀጠለ
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትም በዕለተ ዕርገት (ሐሙስ) ከተነበቡት ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፡፡ ለማስታወስ ያህልም ከጳውሎስ መልእክት ሮሜ ፲፥፩ እስከ ፍጻሜው፤ ከሌሎች መልእክታት ፩ኛ ጴጥሮስ ፫፥፲፭ እስከ ፍጻሜው ድረስ ይነበባሉ፡፡ የሐዋርያት ሥራ፣ ምስባኩና ቅዳሴው ከሐሙስ ዕለቱ (ከዕርገት) ጋር አንድ ዓይነት ሲኾን ወንጌሉም ሐሙስ ጠዋት (በነግህ) የተነበበው ሉቃስ ፳፥፵፭ እስከ ፍጻሜው ድረስ ያለው ኃይለ ቃል ነው፡፡
በዘመነ ዕርገት ከሚቀርቡ ዝማሬያት መካከል ‹‹ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና›› የሚለው አንደኛው ሲኾን፣ ይህም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ የነሣ (የተዋሐደ)፤ ለእስራኤላውያን በሲና በረኀ መና ያወረደ፤ ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነ፤ ሰንበትን ለሰው ልጆች ዕረፍት የሠራ፤ የክርስትና ሃይማኖትን ያቀና (የመሠረተ)፤ ከሰማይ የወረደው የሕይወት እንጀራ፤ በባሕርዩ ምስጋና የሚገባው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደመና ተጭኖ ወደ ሰማይ ማረጉን የሚያስረዳ ሰፊ ምሥጢር አለው፡፡
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዐርባ ስድስተኛውን የመዝሙረ ዳዊት ክፍል በተረጐመበት አንቀጹ ‹‹‹ድል መንሳት ባለበት የነጋሪት ድምፅ እግዚአብሔር ዐረገ› አለ እንጂ ‹መላእክት አሳረጉት› አላለም፡፡ በፊቱ መንገድ የሚመራው አልፈለገም፡፡ በዚያው ጎዳና እርሱ ዐረገ እንጂ፤›› በማለት ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላካዊ ሥልጣኑ ወደ ሰማይ ማረጉን ተናግሯል፡፡ በተመሳሳይ ምሥጢር የጌታችንን ዕርገት ከነቢዩ ኤልያስ ዕርገት ጋር በማነጻጸር ነቢዩ ኤልያስ በመላእክት ርዳታ ወደ ሰማይ መወሰዱን፤ መድኀኒታችን ክርስቶስ ግን የመላእክት ፈጣሪ ነውና በእነርሱ ርዳታ ሳይኾን በገዛ ሥልጣኑ ማረጉን ሊቁ ያስረዳል (፪ኛነገ.፪፥፩-፲፫፤ ሐዋ.፩፥፱-፲፪)፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በተጨማሪም ‹‹ሕማም የሚስማማው ግዙፍ ሥጋን ተዋሕዶ ሳለ ከስቅለቱ አስቀድሞ በባሕር ላይ ከሔደ፣ ዛሬ ነፋስን ከፍሎ ሲያርግ ቢታይ ማንም ማን አይጠራጠር፡፡ ሥጋው አልተለወጠምና፤›› ሲል ጌታችን ከሞቱና ከትንሣኤው አስቀድሞ በውኀ ላይ እንደ ተራመደ ዅሉ፣ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላም በለበሰው ሥጋ በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ማረጉን አስረድቷል (ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ፤ ክፍል ፲፫፣ ምዕ.፷፯፥፲፪-፲፭)፡፡
መጽሐፈ ስንክሳርም በዓለ ዕርገት የክብር ባለቤት ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ በነሣው ሥጋ ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ወዳለው የአንድነት አኗኗሩ ወደ ሰማይ ያረገበት ዕለት መኾኑን ጠቅሶ፣ ‹‹ያን ጊዜ በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ ወጣ፤ በነፋሳትም ክንፎች ላይ ኾኖ ወጣ፤›› (መዝ.፲፯፥፲) የሚለው የዳዊት ትንቢት በዚህች ቀን መፈጸሙን ያትታል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ሌሊት በራእይ አየሁ፤ እነሆም እንደ ሰው ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና መጣ፡፡ በዘመናትም ወደ ሸመገለው ደረሰ፡፡ ወደ ፊቱም አቀረቡት፡፡ ወገኖችና አሕዛብ፣ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ኹሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር፣ መንግሥትም ተሰጠው፡፡ ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት፤ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፤›› የሚለው የነቢዩ ዳንኤል ትንቢት በጌታችን ዕርገት መፈጸሙን ይናገራል (ዳን.፯፥፲፫-፲፬፤ መጽሐፈ ስንክሳር፣ ግንቦት ፰ ቀን)፡፡
ከላይ እንደ ተመለከትነው በዘመነ ዕርገት በማኅሌት፣ በቅዳሴ፣ በመሥዋዕት ጊዜ በቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ ትምህርታት፣ የሚቀርቡ መዝሙራትና የሚነበቡ መጻሕፍት የእግዚአብሔርን ሰው መኾን፣ ተአምራቱን፣ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ነፍሳትን ከሲኦል ማውጣቱን፣ ትንሣኤውን፣ ለሐዋርያትና ለቅዱሳት አንስት መግለጡን፣ በተለይ ደግሞ ዕርገቱን፣ ዳግም ምጽአቱንና ምእመናን በእርሱ አምነው የሚያገኙትን ድኅነት፣ ጸጋና በረከት፣ እንደዚሁም የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር የሚያስረዳ ይዘት አላቸው፡፡
ከዚሁ ዅሉ ጋርም ምርኮን (የነፍሳትን ወደ ገነት መማረክ) የሚያትቱ ትምህርቶች የሚሰጡትም በዚህ በዘመነ ዕርገት ወቅት ሲኾን፣ ይኸውም በሰይጣን ባርነት ተይዘው ይኖሩ የነበሩ ነፍሳት በኢየሱስ ክርስቶስ አምላካዊ ሥልጣን ነጻ መውጣታቸውን ያመለክታል፡፡ ‹‹ምርኮን ማረከህ፤ ወደ ሰማይም ወጣህ፡፡ ስጦታህንም ለሰዎች ሰጠህ፡፡ ያድሩ ዘንድ ይክዱ ነበርና፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት (መዝ.፷፯፥፲፰)፡፡ ይህም ጌታችን ነፍሳትን ከሲኦል ወደ ገነት እንደ መለሰ እና ለምእመናን የሥላሴ ልጅነትን እንደ ሰጠ የሚያስረዳ ሲኾን፣ ‹‹ያድሩ ዘንድ ይክዱ ነበር›› ሲልም በክህደት ይኖሩ የነበሩ ዅሉ ጌታችን በሰጠው ልጅነት ተጠርተው፣ አምነውና በሃይማኖት ጸንተው መኖራቸውን ያጠይቃል፡፡
በአጠቃላይ ዘመነ ዕርገት ወደ ላይ የመውጣት፣ የማረግ፣ ከፍ ከፍ የማለትና የማደግ ወቅት ነው፡፡ ይኸውም በአካል ማረግን (ከፍ ከፍ ማለትን) ወይም ወደ ሰማይ መውጣትን ብቻ ሳይኾን፣ በአስተሳሰብና በምግባር መለወጥን፣ በአእምሮ መጐልመስንም ያመለክታል፡፡ ከዅሉም በላይ መድኀኒታችን ክርስቶስ ወደ ሰማይ እንደ ዐረገ እና ዳግም ለፍርድ ተመልሶ እንደሚመጣ በስፋት የሚነገርበት ወቅት ነው – ዘመነ ዕርገት፡፡ ‹‹እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ! ወደ ሰማይ እየአያችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ፣ ወደ ሰማይ ሲሔድ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሐዋ.፩፥፲፩)፡፡ እኛም ሞት የማያሸንፈው አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች እንደ መኾናችን በሞት ከመወሰዳችን በፊት (በምድር ሳለን) ለሰማያዊው መንግሥት የሚያበቃ መልካም ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ እናም ሕሊናችን በጽድቅ ሥራ እንዲያርግ (ከፍ ከፍ እንዲል) ዘወትር በሃይማኖታችን እንጽና፤ በክርስቲያናዊ ምግባር እንበርታ፤ በትሩፋት ሥራ እንትጋ፡፡
በሞቱ ሕይወታችንን ለመለሰልን፤ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን፣ በዕርገቱ ክብራችንን ለገለጠልን፤ ዜና ብሥራቱን፣ ፅንሰቱን፣ ልደቱን፣ ዕድገቱን፣ ስደቱን፣ ተአምራቱን፣ ሕማሙን፣ ሞቱንና ትንሣኤውን በሰማንበት ዕዝነ ልቡናችን፣ ባየንበት ዓይነ ሕሊናችን ዕርገቱንም እንድንሰማና እንድናይ ዕድሜ ለንስሐ ሰጥቶ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ለጠበቀን ልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይደረሰው፡፡ ዳግም ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜም ‹‹እናንተ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ›› የሚለውን የሕይወት ቃል እንዲያሰማን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ምንጮች፡–
- መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፤ አዲስ አበባ፣ ፳፻ ዓ.ም፡፡
- መዝሙረ ዳዊት ንባቡና ትርጓሜው፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ፤ አዲስ አበባ፣ ፲፱፻፹፪ ዓ.ም፡፡
- ማኅቶተ ዘመን፣ መ/ር በሙሉ አስፋው፣ ገጽ ፻፺፩–፻፺፬፤ አዲስ አበባ፣ ፳፻፩ ዓ.ም፡፡
- ዝማሬ ወመዋሥዕት፣ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፤ አዲስ አበባ፣ ፲፱፻፹፱ ዓ.ም፡፡