ዘመነ ክረምት – ክፍል አራት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በክፍል ሦስት ዝግጅታችን ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፱ ቀን ድረስ ያለው ሁለተኛው ክፍለ ክረምት መብረቅ፣ ነጐድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል እንደሚባል በማስታወስ ከወቅቱ ጋር ተያያዥነት ያለው ትምህርት አቅርበን ነበር፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ቀጣዩን ክፍል ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!

፫. ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ

ከነሐሴ ፲ እስከ ፳፯ ቀን (ከማኅበር እስከ አብርሃም) ድረስ ያለው ሦስተኛው የዘመነ ክረምት ክፍለ ጊዜ (ንዑስ ክፍል) ‹ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ› ይባላል፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ ብቻ ሳይኾን የሰማይ አዕዋፍ፣ የምድር አራዊትና እንስሳት ሳይቀሩ እግዚአብሔርን አምነው በተስፋ መኖራቸው የሚዘከርበት፤ በተጨማሪም በዝናም አማካይነት በዙርያቸው ያለው የውኃ መጠን ከፍ ሲልላቸው ደሴቶች ዅሉ በልምላሜ ማሸብረቃቸው የሚነገርበት ክፍለ ክረምት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ዅሉ በእነዚህ ምሥጢራት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥለን ስለ ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያትና ዓይነ ኲሉ በቅደም ተከተል ማብራሪያ ለመስጠት እንሞክራለን፤

ዕጕለ ቋዓት

‹ዕጕል፣ ዕጓል› ማለት ‹ልጅ›፤ ‹ቋዕ› ደግሞ ‹ቍራ› ማለት ነው፡፡ ‹ቋዕ› የሚለው ቃል በብዙ ቍጥር ሲገለጽም ‹ቋዓት› ይኾናል፡፡ በዚህ መሠረት ‹ዕጕለ ቋዓት› የሚለው የግእዝ ቃላት ጥምረትም (ሐረግ) ‹የቍራ ልጆች (ግልገሎች፣ ጫጩቶች)› የሚል ትርጕም አለው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን የቍራ ጫጩቶች አስተዳደግ ከምእመናን ሕይወት ጋር ተነጻጽሮ ይነገራል፡፡ ይህም እንዲህ ነው፤ የቍራ ጫጩት ከእንቍላሉ ፍሕም መስሎ ይወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ እናትና አባቱ ባዕድ ነገር የተወለደ መስሏቸው ትተውት ይሸሻሉ፡፡ እርሱም በራበው ጊዜ ምግብ ፍለጋ አፉን ይከፍታል፡፡ በዚህ ሰዓት ርጥበት የሚፈልጉ ተሐዋስያን ወደ አፉ ይገባሉ፡፡ ከዚያም አፉን በመግጠም ይመገባቸዋል፡፡ እንደዚሁም ተሐዋስያን በአጠገቡ ሲያልፉ በእስትንፋሱ (በትንፋሹ) እየሳበ ይመገባቸዋል፡፡ የቍራ ጫጩት እስከ ፵ ቀን ድረስ እንደዚህ እያደረገ ከቆየ በኋላ ቀስ በቀስ ፀጕር ያበቅላል፤ ከዚህ በኋላ በመልክ እነርሱን እየመሰለ ስለሚመጣ እናት አባቱ ተመልሰው ይከባከቡታል፡፡ ይህ የቍራ ዕድገትና ለውጥም እግዚአብሔር ፍጡራኑን የማይረሳ አምላክ እንደ ኾነ፣ ፍጥረቱንም በጥበቡ እየመገበ እንደሚያኖራቸው ያስገነዝበናል፡፡

ቅዱስ ዳዊት ይህን የቍራ የዕድገት ደረጃና የእግዚአብሔርን መግቦት በተናገረበት መዝሙሩ ‹‹ወሐመልማለ ለቅኔ ዕጓለ እመሕያው ዘይሁቦሙ ሲሳዮሙ ለእንስሳ ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውዕዎ፤ ለሰው ልጆች ጥቅም ለምለሙን የሚያበቅል፤ ለእንስሳትና ለሚለምኑት የቍራ ጫጩቶች ምግባቸውን የሚሰጣቸው እርሱ ነው›› ሲል ይዘምራል (መዝ. ፻፵፮፥፱)፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በትርጓሜያቸው እንደ ገለጹት ይህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔር አምላክ ለእርሱ ለሚገዙ የሰው ልጆች እኽሉን፣ ተክሉን የሚያበቅልላቸው፤ ለእንስሳቱና ለአዕዋፍ ምግባቸውን የሚሰጣቸው እርሱ እንደ ኾነ ያስረዳል፡፡ ‹‹… ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውዕዎ፤ … ለሚለምኑት ለቍራ ጫጩቶች›› የሚለው ሐረግም አዕዋፍ፣ ምግብ እንዲያዘጋጅላቸው እግዚአብሔርን እንደሚለምኑትና እርሱም ልመናቸውን እንደሚቀበላቸው ያስገነዝበናል፡፡ በመዝሙረ ዳዊት አንድምታ ትርጓሜ እንደ ተጠቀሰው ‹‹ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውዕዎ›› የሚለው ሐረግ ‹‹… እለ ኢይጼውዕዎ›› ተብሎ ሊነገር ይችላል፤ ይህም የቍራ ጫጩቶች አፍ አውጥተው ባይነግሩትም እንኳን እርሱ ፍላጎታቸውን ዐውቆ የዕለት ምግባቸውን እንደሚያዘጋጅላቸው የሚያመለክት ምሥጢር አለው፡፡ ምሥጢሩን ወደ እኛ ሕይወት ስናመጣውም እግዚአብሔር አምላክ ስሙን የሚጠሩትንም የማይጠሩትንም፤ ‹‹የዕለት እንጀራችንን ስጠን›› እያሉ የሚማጸኑትንም የማይጸልዩትንም በዝናም አብቅሎ፣ በፀሐይ አብስሎ ሳያደላ ዅሉንም በቸርነቱ እንደሚመግባቸው ያስተምረናል፡፡ ‹‹… እርሱ ለክፎዎችና ለደጎች ፀሐይን ያወጣልና፤ ለጻድቃንና ለኃጥአንም ዝናምን ያዘንማልና፤›› እንዳለ ጌታችን በወንጌል (ማቴ. ፭፥፵፭)፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቍራዎችንና የሌሎችንም አዕዋፍ አኗኗር ምሳሌ በማድረግ ስለ ምድራዊ ኑሮ ሳይጨነቁ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ መኖር እንደሚገባን በቅዱስ ወንጌል አስተምሮናል፡፡ እንዲህ ሲል፤ ‹‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፡፡ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና፡፡ ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱምም፡፡ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፡፡ እናንተ ከወፎች ትበልጡ የለምን? … አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም፤ አይፈትሉምም … ዛሬ ያለውን፣ ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የኾነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከኾነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ! እናንተንማ ይልቁን እንዴት? … የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፤ አታወላውሉም፡፡ ይህንስ ዅሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፡፡ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል፡፡ ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ፤ ይህም ዅሉ ይጨመርላችኋል፤›› (ሉቃ. ፲፪፥፳፪-፴፩)፡፡

ከዚህ ላይ ‹‹… ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ …›› የሚለው ኃይለ ቃል እንደ እንስሳት ሳትሠሩ እግዚአብሔር ምግብ እንዲሰጣችሁ ለምኑት ማለት እንዳልኾነ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ኃይለ ቃሉን ለማብራራት ያህል የሰው ልጆች ከእንስሳት ከምንለይባቸው ባሕርያት አንደኛው ሠርተን መብላት መቻላችን ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም የታታሪነትንና የሠርቶ ማደርን ጥቅም እንጂ ሳይሠሩ ተቀምጦ መብላትን አላስተማሩንም፡፡ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሰው ልጅ እጁ ከሥራ መለየት እንደማይገባው ተገልጿል፡፡ ለምሳሌ አባታችን አዳም ከሳተ በኋላ በምድር ጥሮ፣ ግሮ እንዲኖር ተፈርዶበታል፡፡ ይህንም ‹‹… የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ፡፡ ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ›› ከሚለው ኃይለ ቃል ለመረዳት እንችላለን (ዘፍ. ፫፥፲፰-፲፱)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እግዚአብሔር አማላክ አዳምን ከዔደን ገነት ያስወጣው የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ መኾኑም ተጠቅሷል (ዘፍ. ፫፥፳፫)፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ ሠራቶ አዳሪ ፍጥረት መኾኑን የሚያመላክት ምሥጢር ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም ‹‹አንተ ታካች! እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? ጥቂት ትተኛለህ፤ ጥቂት ታንቀላፋለህ፡፡ ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ታጥፋለህ፡፡ እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፣ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል›› በማለት የሰው ልጅ እንቅልፍን (ስንፍናን) ካበዛና ካልሠራ ክፉ ድህነት እንደሚመጣበት ተናግሯል (ምሳ. ፮፥፱-፲)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ‹‹ከእናንተ ሊሠራ የማይወድ አይብላ›› በማለት ሥራ የማይወድ ሰው ምግብ መሻት እንደሌለበት አስረድቷል (፪ኛ ተሰ. ፫፥፲)፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ስንፍናን የሚያወግዝ፣ ሥራን ደግሞ የሚያበረታታ ኾኖ ሳለ ‹‹ለምንድን ነው መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ …› ሲል ያስተማረው?›› የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ያህል ቃሉ አትጨነቁ ማለቱ ‹‹ለሥጋዊ ጉዳይ ቅድሚያ አትስጡ፤ እየሠራችሁ እግዚአብሔርን በጸሎት ጠይቁ›› ሲለን ነው፡፡ የሰው ልጅ ሠራተኛ ፍጥረት ቢኾንም ዝናም አልጥልለት ሲል፤ የዘራበት መሬት ሳያበቅል ሲቀር፤ የወር ደመወዙ ሲዘገይ፤ እኽል የሚሸምትበት ገንዘብ ሲያጣ፤ ወዘተ. በመሳሰሉት ፈተናዎች ውስጥ በኾነ ጊዜ ምን ልበላ ነው? ልጠጣ ነው? ልጆቼ እንዴት ሊኾኑብኝ ነው? ዛሬን እንዴት ላልፍ ነው? በሚሉትና በመሳሰሉት የጭንቀትና የተስፋ መቍረጥ ስሜቶች ሳይያዝ የዕለት ጕርሱን፣ የዓመት ልብሱን ይሰጠው ዘንድ የጠፋውን ዝናም ማምጣት፤ የደረቀውን ዘር ማለምለም፤ ባዶ የኾነውን ቤት መሙላት የሚቻለውን እግዚአብሔርን (እርሱን) በእምነት ኾኖ በጸሎት ይጠይቀው ለማለት መድኀኒታችን ክርስቶስ ‹‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ›› ብሎናል፡፡ ሐሳቡ ሲጠቃለል የሰው ልጅ ይርበኛል፣ ይጠማኛል ማለቱን ትቶ በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩን በማሰብ ዓቅሙ በሚችለው ዅሉ እንዲሠራ፤ የጐደለውን እንዲሞላለት ደግሞ ጸሎቱን ወደ ፈጣሪው እንዲያቀርብ ሲያስረዳ ጌታችን ‹‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት፣ ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ›› በማለት አስተምሯል፡፡

ይህም የሰው ልጅ ለሚበላው፣ ለሚጠጣው መጨነቅ እንደማይገባውና እየሠራ ሙሉ ተስፋውን በእግዚአብሔር ላይ ማድረግ እንዳለበት፤ ከዅሉም በላይ ለምድራዊው ኑሮው ድሎት ሳይኾን ሰማያዊውን መንግሥት ለመውረስ መትጋት እንደሚጠበቅበት ያስገነዝባል፡፡ ስለዚህም አምላካችን እንዳስተማረን ስለምንበላውና ስለምንጠጣው ሳይኾን ስለ በጎ ምግባርና ስለ ዘለዓለማዊው መንግሥት መጨነቅ ይገባናል ማለት ነው፡፡ ራሳችንን ለመንግሥተ እግዚአብሔር በሚያበቃ የጽድቅ ሥራ ካስገዛን ለሥጋችን የሚያስፈልገን ምድራዊ ዋጋም አብሮ ይሰጠናልና፡፡ ‹‹ወዘእንበለ ንስአሎ ይሁብ ፍትወተነ ዘእምፈቃዱ፤ ሳንለምነው ልባችን የተመኘውን በፈቃዱ የሚሰጠን እርሱ ነው›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መጽሐፈ ኪዳን)፡፡ ‹‹ይሰጠዎ ወይሰምዖ ጸሎቶ ለኵሉ ለዘሰአሎ እግዚአ ለሰንበት አምላከ ምሕረት ያርኁ ክረምተ በበዓመት ይሰምዑ ቃሎ ደመናት፤›› በማለት ቅዱስ ያሬድ በዘመነ ክረምት መዝሙሩ ያቀረበው ምስጋናም ይህንኑ እውነት የሚያንጸባርቅ ኃይለ ቃል ነው፡፡ ትርጕሙም፡- ‹‹እግዚአብሔር አምላክ የለመነዉን ፍጥረት ዅሉ ጸሎት ተቀብሎ ምላሽ ይሰጣል፡፡ የሰንበት (የፍጥረታት) ጌታ እርሱ የምሕረት (የይቅርታ) አምላክ ነው፡፡ የምሕረት አምላክ በመኾኑም በየዓመቱ (በየጊዜው፣ በየዘመኑ) ወርኃ ክረምትን (ወቅቶችን) ያፈራርቃል፡፡ ደመናትም (ፍጥረታትም) ቃሉን ይሰማሉ (ትእዛዙን ይፈጽማሉ)፤›› ማለት ነው፡፡

ይቆየን