ዘመነ ክረምት – ክፍል ሁለት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሐምሌ ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች፤ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰላምታ እንደምን ሰነበታችሁ? በርኅራኄው እየጠበቀ፣ በቸርነቱ እየመገበ እስከ ዛሬ ድረስ ያቆየን ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን! እንደምታስታዉሱት ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ባስተላለፍነው ክፍል አንድ ዝግጅታችን ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ያለው የዘመነ ክረምት ክፍል ስለ ክረምት መግባት፣ ስለ ዘርዕ እና ደመና የሚነገርበት ወቅት እንደ ኾነ በማስገንዝብ ወቅቱን (በዓተ ክረምትን) የሚመለከት አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበን ነበር፡፡ ስለ ዘር እና ደመና የሚያትተውን ቀጣይ ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል፤  

ዘርዕ

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹እለ ይዘርዑ በአንብዕ ወበሐሤት የዐርሩ ሶበሰ የሐውሩ ወፈሩ እንዘ ይበክዩ ወጾሩ ዘርዖሙ ወሶበ የአትዉ መጽኡ እንዘ ይትፌሥሑ ወጾሩ ከላስስቲሆሙ፤ በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይሰበስባሉ፡፡ በሔዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው መጡ፤›› በማለት እንደ ተናገረው (መዝ. ፻፳፭፥፭-፮)፣ ይህ ወቅት አርሶ አደሩ በእርሻና ዘር በመዝራት የሚደክምበት፣ የምርት ጊዜውንም በተስፋ የሚጠባበቅበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ የአርሶ አደሩ ድካምና ተስፋም የሰውን ልጅ የሕይወት ጉዞና ውጣ ውረድ እንደዚሁም በክርስቲያናዊ ምግባር የሚወርሰውን ሰማያዊ መንግሥት ያመለክታል፡፡

ምድር ከሰማይ ዝናምን፣ ከምድርም ዘርን በምታገኝበት ወቅት ዘሩን አብቅላ ለፍሬ እንዲበቃ ታደርጋለች፡፡ በምድር የምንመሰል የሰው ልጆችም ከእግዚአብሔር ባገኘነው ጸጋ ተጠቅመን፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት እና ከመምህራነ ቤተ ክርስቲያን የምናገኘውን ቃለ እግዚአብሔር በተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባን ከምድር እንማራለን፡፡ ይህን ካደረግን ዋጋችን እጅግ የበዛ ይኾናል፤ ከዚህም አልፎ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንበቃለን፡፡ የተዘራብንን ዘር ለማብቀል ማለትም ቃሉን በተግባር ለማዋል ካልተጋን ግን በምድርም በሰማይም ይፈረድብናል፡፡ ‹‹ምድርም በእርስዋ የሚወርደውን ዝናብ ከጠጣች፣ ያን ጊዜ ስለ እርሱ ያረሱላትን መልካም ቡቃያ ታበቅላለች፡፡ እሾኽን እና ኵርንችትን ብታበቅል ግን የተጣለች ናት፡፡ ለመርገምም የቀረበች ናት ፍጻሜዋም ለመቃጠል ይኾናል፤›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ገለጸው (ዕብ. ፮፥፯-፰)፡፡

ደመና

እግዚአብሔር አምላካችን የውቅያኖስ እና የሐኖስ ድንበር ይኾን ዘንድ በውኃ መካከል ጠፈርን ፈጥሮ ከጠፈር በታች (በዚህ ዓለም) ያለው ውኃ በአንድ ቦታ እንዲወሰን አድርጎታል፡፡ ከዚያም ከምድር እስከ ብሩህ ሰማይ ድረስ የነበረውን ውኃ ከሦስት ከፍሎ ሢሶውን አርግቶ ጠፈር ብሎ ሰይሞታል፡፡ ከጠፈር በላይ ያለውን ሢሶው የውኃ ክፍል ሐኖስ ብሎታል፡፡ ሢሶውንም ይህንን ዓለም ከሰባት ከፍሎ ሰባተኛውን ዕጣ አጐድጕዶ በዚያ ወስኖ ስሙን ውቅያኖስ ብሎ ጠርቶታል፡፡ የብሱን ክፍል ደግሞ ምድር ብሎ ሰይሞታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከደረቅ ምድር ደረቅ ጢስን፤ ከርጥብ ባሕር ርጥብ ጢስን አስወጥቶ እንደ ጉበት በለመለመች ምድር ላይ ደመናን አስገኝቷል (ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት፣ መዝ. ፻፴፬፥፯)፡፡

ከላይ እንደ ተጠቀሰው ደመና፣ ዝናምን የሚሸከም የማይጨበጥ፣ የማይዳሰስ ጢስ መሰል ፍጥረት ነው፡፡ በትነት አማካይነት፣ በደመና ተሸካሚነት ከውቅያኖሶች እና ከወንዞች እየተቀዳ ወደ ሰማይ ተወስዶ እንደ ገና ተመልሶ ወደ ምድር የሚጥለው ውኃ ዝናም ይባላል፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ጥበብ በደመና ወንፊትነት ተጣርቶ ለፍጡራን በሚመችና በሚጠቅም መጠን በሥርዓት ይወርዳል፡፡ ‹‹ያጸንዖ በፍኖተ በድው ከመ ይዝንም ብሔረ ኀበ አልቦ ሰብእ ወኢይነብሮ ዕጓለ እመሕያው፤ ዝናሙን ሰው በሌለበት በምድረ በዳ ያዘንመዋል፤›› እንዳለ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በቅዳሴው፡፡ ይህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔር በረዶውን በምድረ በዳ አፍስሶ የጠራውን ውኃ ሰው ወዳለበት እንዲዘንም ማድረጉን የሚያስረዳ መልእክት የያዘ ሲኾን፣ ምሥጢሩም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንበለ ዘርዐ ብእሲ (ያለ ወንድ ዘር) በልዩ ጥበቡ ተፀንሶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱንና በለበሰው ሥጋ በምድር ተመላልሶ ወንጌልን ማስተማሩን፤ እንደዚሁም ‹‹ሑሩ ወመሀሩ፤ ሒዱና አስተምሩ›› ብሎ ቅዱሳን ሐዋርያትን በመላው ዓለም ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማሠማራቱን ያመለክታል (ትርጓሜ ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ፣ ፪፥፭-፮)፡፡

‹‹ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር ዘያበቍል ሣዕረ ውስተ አድባር ወሐመልማለ ለቅኔ እጓለ እመሕያው፤ ሰማዩን በደመና የሚሸፍን፣ ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ፣ ሣርን በተራሮች ላይ፣ ልምላሜውንም ለሰው ልጆች አገልግሎት የሚያበቅል … እርሱ ነው፤›› (መዝ. ፻፵፮፥፰) በማለት ቅዱስ ዳዊት እንደ ዘመረው እግዚአብሔር አምላክ ውኃ ከውቅያኖሶች ተቀድቶ፣ በደመና ተቋጥሮ፣ ወደ ሰማይ ሔዶ፣ እንደ ገና ተመልሶ ወደ ምድር እንዲዘንም እያደረገ ዓለምን በልዩ ጥበቡ ይመግባል፡፡ ይህን አምላካዊ ጥበብ በማድነቅ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት አምላክነ በተነ ጊሜ ረቂቅ ዘያአቍሮ ለማይ ያዐርጎ እምቀላይ ወያወርዶ እምኑኀ ሰማይ፤ ረቂቅ በኾነ የጉም ተን ውኃውን የሚቋጥረው፤ ከወንዝ ወደ ላይ የሚያወጣው፤ ከሩቅ ሰማይም የሚያወርደው እግዚአብሔር ቅዱስ፣ ልዩ፣ ምስጉን አሸናፊ አምላክ ነው፤›› በማለት ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ልዑል እግዚአብሔርን ያመሰግናል (መጽሐፈ ሰዓታት ዘሌሊት)፡፡

የደመና አገልግሎቱ ዝናምን ከውቅያኖስ በመሸከም ወደ ምድር እያጣራ ማውረድ ነው፡፡ ኾኖም በሰማይ የሚዘዋወርና በነፋስ የሚበታተን ዝናም አልባ ደመናም አለ፡፡ በመልካም ግብር፣ በትሩፋት ጸንተው የሚኖሩ ምእመናን ዝናም ባለው ደመና ሲመሰሉ፣ ያለ ክርስቲያናዊ ምግባር በስመ ክርስትና ብቻ የምንኖር ምእመናን ደግሞ ዝናም በሌለው ደመና እንመሰላለን፡፡ ሐዋርያው ይሁዳ ‹‹… በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች …›› በማለት የተናገረውም የእንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን ሕይወት ይመለከታል (ይሁዳ ፩፥፲፪)፡፡ አንድም ዝናም ያለው ደመና የእመቤታችን የቅድስት ደንግል ማርያም ምሳሌ ነው፡፡ እርሷ ንጹሑን የሕይወት ውኃ (ዝናም) መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገኝታልናለችና፡፡ ‹‹አንቲ ዘበአማን ደመና እንተ አስተርአይኪ ለነ ማየ ዝናም፤ የዝናም ውኃን ያስገኘሽልን እውነተኛ ደመና አንቺ ነሽ፤›› እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም (ውዳሴ ዘረቡዕ)፡፡ እኛም ውኃ ሳይኖረው በነፋስ እንደሚበታተን ዝናም አልባ ደመና ሳይኾን፣ ዝናም እንደሚሸከም ደመና በምግባረ ሠናይ ጸንተን ልንኖር ይገባል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም የእግዚአብሔርን ቃል ሕይወታችን በማድረግ ራሳችንን ከማዳን ባሻገር ለሌሎችም አርአያና ምሳሌ ልንኾን ያስፈልጋል፡፡

ስለ ደመና ሲነገር ዝናምም አብሮ ይነሣል፡፡ ዝናም ያለ ደመና አይጥልምና፡፡ ዝናም የቃለ እግዚአብሔር ምሳሌ ነው፤ ዝናም ለዘር መብቀል፣ ማበብና ማፍራት ምክንያት እንደ ኾነ ዅሉ በቃለ እግዚአብሔርም በድንቁርና በረኃ የደረቀ ሰውነት ይለመልማል፤ መንፈሳዊ ሕይወትን የተራበችና የተጠማች ነፍስም ትጠግባለች፤ ትረካለችና፡፡ ‹‹ሲሲታ ለነፍስ ቃለ እግዚአብሔር፤ የነፍስ ምግቧ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤›› እንዲል፡፡ በሌላ በኩል በዚህ ዓለም የሚያጋጥም ልዩ ልዩ ፈተናም በዝናም ይመሰላል፡፡ ጌታችን በወንጌል እንደ ነገረን ቃሉን ሰምቶ በሥራ ላይ የሚያውል ክርስቲያን ቤቱን በዓለት ላይ የመሠረተ ልባም ሰውን ይመስላል፡፡ ቤቱ በጐርፍ ቢገፋ አይናወጥምና፡፡ ቃሉን የማይተገብር ክርስቲያን ግን ያለ መሠረት በአሸዋ ላይ ቤቱን የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል፡፡ ቤቱ በዝናብ፣ በጐርፍና በነፋስ ተገፍቶ የከፋ አወዳደቅ ይወድቃልና፡፡ ይህም ሃይማኖቱን በበጎ ልቡና የያዘ ክርስቲያን ከልዩ ልዩ አቅጣጫ በሚደርስበት መከራ ሳይፈራና በሰዎች ምክር ሳይታለል፤ በኢዮብ እንደ ደረሰው ዓይነት ከባድ ፈተና ቢመጣት እንኳን ሳያማርር በምክረ ካህን፣ በፈቃደ ካህን እየታገዘ አጋንንትን ድል እያደረገ በሃይማኖቱ ጸንቶ እንደሚኖር፤ በአንጻሩ ሃይማኖቱን በበጎ ሕሊና ያልያዘ ክርስቲያን ግን ፈተና ባጋጠመው ጊዜ በቀላሉ እንደሚክድና ለአጋንንትም እጁን እንደሚሰጥ የሚያስረዳ ምሥጢር አለው (ትርጓሜ ወንጌል፣ ማቴ. ፯፥፳፬-፳፯)፡፡

ዝናም ሲጥል የወንዞች ሙላትና ማዕበል ቤት እንዲያፈርስ፤ ንብረት እንዲያወድም በክርስቲያናዊ ሕይወት በሚያጋጥም ፈተናም በእምነት መዛል፣ በመከራ መያዝ፣ መቸገር፣ መውጣትና መውረድ ያጋጥማል፡፡ ዝናም ለጊዜው እንዲያስበርድና ልብስን እንዲያበሰብስ ፈተናም እስኪያልፍ ድረስ ያሰንፋል፤ ያስጨንቃል፤ ያዝላል፡፡ ነገር ግን ዝናም፣ ጐርፍና ማዕበል ጊዜያቸው ሲደርስ ጸጥ እንደሚሉ ዅሉ፣ ምድራዊ ፈተናም ከታገሡት የሚያልፍ የሕይወት ክሥተት ነው፡፡ ስለዚህ ዅላችንም እምነታችንን በጠንካራ መሠረት ላይ በመገንባት በውኃ ሙላትና በማዕበል ከሚመሰል ውድቀት ራሳችንን እንጠብቅ፡፡ ዝናም ሲመጣ የውኆችን ሙላትና ጐርፉን ሳንፈራ ወደ ፊት የምናገኘውን ምርት ተስፋ እንደምናደርግ፣ በሃይማኖታችን ልዩ ልዩ ፈተና ሲያጋጥመንም ከእግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘውን ሰማያዊ ዋጋ በማሰብ ዅሉንም በትዕግሥት እናሳልፍ፡፡

ይቆየን