ዘመነ መስቀል
ካለፈው የቀጠለ
ዲያቆን ዘካርያስ ነገደ
መስከረም ፲፭፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ቅዱስ ያሬድ በመስከረም ወር ከ፲፯ኛው እስከ ፳፭ኛው ቀን ድረስ ያለውን ጊዜ ዘመነ መስቀል በማለት ሰይሞታል፡፡
መስቀል በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ለዕርቅ የተተከለ ትእምርተ ፍቅር ነው፡፡ በመስቀል የነፍስና የሥጋ መርገም የተሻረበት በመሆኑ ሰው ሁሉ ለችግሩ መጽናኛ ማግኘትና ነፍሱን ማትረፍ የሚችለው መስቀልን በጽናት ተስፋ አድርጎ ሲቆም ነው፡፡ (ዮሐ.፲፱፥፳፭)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ሞት ድረስ ለሰዎች በመታዘዙ የብዙዎችን ጥፋት ተሸክሞ ለጽድቅ እንዲያበቃ የመከራ ተቀባይ አገልጋይ ድርሻን የፈጸመበት መስቀል የታዛዥነት ምልክት ነው፡፡
ጌታችን ከትንሣኤው በኋላ ድውያንን መፈወስ፣ ሙታንን ማስነሣት የጀመረው በቅዱስ መስቀሉ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ የዳኑትና ድንቅ ተአምሩን የተመለከቱ ሁሉ ሕይወትና ቤዛ የመሆን ጸጋ የተሰጠው መሆኑን እያመኑ “መስቀል ኀይልነ መስቀል ቤዛነ መስቀል መድኀኒተ ነፍስነ” እያሉ የጸጋና የአክብሮት ስግደት የሚሰግዱለት ሆነዋል፡፡ (የዘወትር ጸሎት)
አይሁድ ግን መስቀል በፊታቸው ልዩ ልዩ ተአምራትን ሲፈጽም ሲመለከቱ ማመን ተሳናቸው፤ ስለዚህም ቅዱስ መስቀሉን መሬት ቆፍረው ቀበሩት፤ የቤት ጥራጊ ቆሻሻ ይጣልበት ዘንድ ዐዋጅ ነገሩ፡፡ ቆሻሻው ተራራ እስኪያህል ድረስ የቆሻሻ ማከማቻ አደረጉት፡፡ በዚህ ሁኔታ ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ከኖረ በኋላ መስቀሉ ያለበትን የሚያውቀው ሰው ጠፋ፡፡
ነገር ግን በ፫፻፳፮ ዓ.ም. የሮም ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ በማፈላለግ ኪርያኮስ በተባለ የአይሁድ ሽማግሌ ጥቆማ መሠረት ደመራ አስደምራ፣ ዕጣኑን ጨምራ፣ ደመራውን ብታቀጣጥለው የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ወጥቶና ተመልሶ መስቀሉ ከተቀበረበት ተራራ ላይ ጢሱ ሰገደ፤ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታም አመለከተ፡፡
ቅድስት ዕሌኒም የዕጣኑን ቅታር ተመልክታ ቅዱስ መስቀል ከዚህ አለ ብሎ ሲጠቁመን ነው በማለት አምና ከመስከረም ፲፯ ቀን ጀምሮ በማስቆፈር መጋቢት ፲ ቀን ቅዱስ መስቀሉን ለማውጣት ችላለች፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ መስከረም፣ ፲፮ ቀን)
መልካም በዓል!
ይቆየን!