ዘለዓለማዊ ሰላም
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሚያዚያ ፳፪፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ፍጹም ጤና፣ ዕረፍት፣ ዕርቅ፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ደኅንነት፣ ተድላ፣ ደስታ፣ ሰላምታ፣ የቡራኬ የምርቃት ቃል ሰው ሲገናኝ የሚለዋወጠው የመልካም ምኞት መግለጪያ የሆነው ሰላም ለሁሉ ነገር መሠረት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፰፻፷፮) ምንጩ ደግሞ እውነተኛ ዘለዓለማዊ ሰላምን የሚሰጥ የሰላም አምላክ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ የሰላም አለቃ ነውና ‹‹…የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ…›› እንዲል፡፡ (ኢሳ.፱፥፮) እውነተኛ ሰላም የሚገኘው ከእርሱ ዘንድ መሆኑን እንዲህ በማለት ነግሮናል፤ ‹‹…ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም…፡፡›› (ዮሐ.፲፬፥፳፯)
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን አማናዊ የሰላም ባለቤት ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲህ ያገልጹታል፤ ሰው ቢሰጥ ያንዱን ለአንዱ ወስዶ ነው፤ ሰው ሰላምን አመጣው ቢል አንዱን ያስደስታል፤ ሌላውን ያሳዝናል፤ ለዚያውም ኃላፊውን ነው፤ እርሱ ግን የሚሰጠው ሰላም የማያልፈውን ነው፤ እርሱ ግን የሚሰጠው ማንንም የማያስከፋ ሁሉን የሚያስደስት ነው፡፡ እርሱ ቢሰጥ መመረር፣ መጸጸት የሌለበትን ዘለዓለማዊ ሰላም ነው፡፡ ዓለም የምትሰጠን ሰላም ጊዜያዊ አድሎ ያለበት ለጸብ ለፍጅት የሚዳርገውን ነው፤! አምላካችን ግን የሚሰጠን ፍጹምና ዘለዓለማዊውን ሰላም ነው፡፡
ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ አስፈላጊና ዋነኛው ነገር ነው፤ ሰላም ከሌለ ደስታ፣ እድገት፣ ፍቅር፣ ጤና አይኖርም፤ ሰላም ከሌለ መረጋጋት አይኖርም፤ ሰላም ከሌለ ነገን አርቀን መመልከት፣ ማቀድና መመኘት አይቻልም፤ ሰላም ከሌለ አምልኮን መፈጸም፣ ውለታን አስታውሶ በዓልን ማድረግ አይቻልም፤ ሰላም ከሌለ ተኩሎ መዳር፣ ወልዶ መሳም፣ አሳድጎ ለቁም ነገር ማድረስ አይቻልም፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት የዋኀት ራስን መግዛት ነው›› በማለት ከመንፈስ ፍሬዎች መካከል አንዱ ሰላም እንደሆነ ነግሮናል፡፡ (ገላ.፭፥፳፪)
ሰላም ለሰው ልጆች አስፈላጊ በመሆኑ ነው! ጌታችን በሲኦል ለነበሩት ነፍሳት ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› በማለት ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት ሰላም አጥተው ነጻነት ተነፍገው፣ ከክብር ተዋርደው ለነበሩ ለአዳምና ለልጆቹ የምሥራቹን ያበሠራቸው፤ ባርነቱ ቀርቶ፣ ጨለማው ተወግዶ ልጅነትን አግኝተው፣ ክብር ተጎናጽፈው ያጧትን ገነት ወርሰው፣ በደስታ ተረጋግተው መኖር የቻሉት ሰላማቸው ታውጆ ነው፤ ያጡትን ለማግኘት፣ ተድላ ደስታን ለመጎናጸፍ ሰላም አስፈላጊ ነው፡፡
ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰላም አለቃ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስን በወለደች ጊዜ በቤተ ልሔም ለነበሩ እረኞች የምሥራቹን ሲያበሥራቸው፣ አብረውት በቤተ ልሔም የተገኙት ቅዱሳን መላእክት ስለአዳምና ልጆቹ መዳን በተደረገው ድንቅ ውለታ ተደንቀው ባቀረቡት ምስጋና ሰላም መሆኑን ገልጸዋል፤ ‹‹…ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር ለሰው በጎ ፈቃድ…›› በማለት ለሰው ልጆች በተገኘው ሰላም ተደስተው የሰላምን አምላክ አመስግነዋል፡፡ (ሉቃ.፪፥፲፬)
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ሞታችንን ገድሎ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አብሥሮ፣ ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ ጊዜ በፍርሃትና በጭንቀት ተከበው በዝግ ቤት ለነበሩት ደቀመዛሙርቱ በተገለጠላቸው ጊዜ ከአንደበቱ የወጣው ፍርሃትን አርቆ ጽናትን፣ ጭንቀትን አስወግዶ ደስታን ያላበሰበት የማጽናኛው ቃሉ ሰላም ነበር፡፡ ‹‹…ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት አይሁድን ስለፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ በመካከላቸው ቆመ፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው…፡፡›› (ዮሐ.፳፥፲፱)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹…ወደ ምትገቡበትም ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ›› በማለት እንዳስተማራቸው (ሉቃ.፲፥፭) ፈለጉን ተከትለው የምሥራቹን ወንጌል ሲሰብኩ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን…›› በማለት ሰላምን ላጡ ሰላምን ይሰብኩ ነበር፤ ‹‹… በሮሜ ላላችሁት ሁሉ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን…›› እንዲል፡፡ (ሮሜ ፩፥፯)
ሰላምን የሚሰጥ የሰላም ባቤት እግዚአብሔር ነው፤ ፍጹም የሆነውን ሰላም ለማግኘት በፈቃዱ መኖር፣ ሕጉን ማክበር ያስፈልገናል፤ የሰው ልጅ ሰላሙን የሚያጣው ለሁከት፣ ለጭንቀት የሚጋለጠው ሰላምን ከሚሰጥ እግዚአብሔር እቅፍ ሲርቅ ትእዛዝ ሲጥስ፣ ሕግን ሲያፈርስ ነው፤ አምላካችን እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ባስተላለፈልን መልእክት እንዲህ ይለናል፤ ‹‹…እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ፣ በምትሄድበትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር…፡፡›› (ኢሳ.፵፰፥፲፯) ሰላማችን እንዲበዛ ከሁከት፣ ከጭንቀት ለመራቅ ትእዛዙን እንስማ፡፡
ሰላም ከቤተ እግዚአብሔር ይገኛል፤ ሰላማችን እንዲበዛ ከቤቱ አንራቅ፤ የሰላም ወደብ እንባ ማበሻ፣ የከበደንን የበደል ሸክም ማቅለያ፣ የተጨነቀው ልባችንን ማረጋጊያ ከሆነች ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን መራቅ ለሰላም እጦት ለጭንቀትና ተስፋን ወደ መቁረጥ ያደርሳል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በጻፈልን በጌታችን በመድኃኒታችን ቅዱስ ወንጌል ላይ ያለው የጠፋው ልጅ ታሪክ ለዚህ አብነት ይሆነናል፤ ተድላ ደስታ ከሞላበት ከአባቱ ቤት በወጣ ጊዜ ሰላሙ ከእርሱ ራቀ ደስታው ጠፋ ለጭንቀት ተዳረገ፤ ተጸጽቶ ወደ አባቱ ቤት በመጣ ጊዜ ሰላሙ ተመለሰ ተድላ ደስታ ተደረገለት፤ ሰላማችን እንዲመለስ በእኛ መዳን ቅዱሳን መላእክቱ እንዲደሰቱ ከእግዚአብሔር ቤት አንራቅ፣ የሕይወት ቃሉን እንስማ፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የሰላም ሰው እንዲሆኑ እውነተኛ ሰላምን እናገኝ ዘንድ በትምህርቷ ሁል ጊዜም ሰላምን ትሰብካላች፤ ስለ ሰላም ትጸልያለች፤ የሰላም ጥሪዋን አድምጠን ሰላማዊ ሰዎች እንሁን፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላው መልእክቱ ‹‹…በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ …›› በማለት በአባታዊ ምክሩ ነግሮናል፡፡ (ሮሜ ፲፪፥፲፰)
ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር እውነተኛውን ሰላም ለማግኘት ከክፋት እንራቅ፤ ‹‹ለክፉዎች ሰላም የላቸውም…›› እንዲል፡፡ (ኢሳ.፵፰፥፳፪) ቅዱስ ቃሉ ሰላማችን እንዲበዛ ከክፋት እንመለስ፤ ሰላምን ስንፈልግ የሰላም ሰው ለመሆን እንዘጋጅ፤ ቢቻለን ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንኑር፤ የሰላም ፍላጎታችንን በዝማሬ ብቻ ከመግለጽና ከመናፈቅ በተግባር የሰላም ሰዎች እንሁን፡፡
ለትልቁ አገራችን ሰላም መጥፋት መፍትሔን አጠገባችን ከተጣላነው ሰው ጋር ይቅር በመባባል እንጀምር፤ እውነተኛውን ሰላም ለማግኘት ከሰላም አለቃ መድኅን ዓለም ክርስቶስ ያራቀንን ክፉ ሥራችንን በንስሐ ከሕይወታችን እናርቀው፤ ያኔ ታዲያ እውነተኛውን ሰላም አግኝተን በምድር በረከቱን በሰማይ የክብር ሕይወትን አግኝተን መኖር ይቻለናል፤ እውነተኛውን ሰላም ያገኘን ጊዜ ከምድር መዓቱን አርቆ ከሰማይ ምሕረቱን ያጎናጽፈናል፤ እውነተኛ ሰላም ያገኘን ጊዜ ኃጢአታችን እንደ ጉድፍ ለቆየን ጸሎታችን ሥሙር ይሆንልናል፤ እውነተኛ ሰላም ያገኘን ጊዜ ነገራችን ጥሞ ሐሳባችን ገጥሞ ተሳስበንና ተፋቅረን መኖር ይቻለናል፡፡
የሰላም አምላክ ሰላሙን ፍቅሩን ያድለን፤ ከላይ ምሕረቱን ይላክልን፤ ከታች መዓቱን ያርቅልን! ቸር ይግጠመን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!